«ልዑል ከሆንክ ከቻልክ በሕዝቦችህ ተፈቀር፣ ካልሆነ ግን እንዳትናቅ ጣር» ኒኮሎ ማኪያቬሊ (1469-1527)
በጣሊያን፣ ፍሎረንስ ውስጥ ጥንታዊ መሠረት ካለው፣ ነገር ግን ኪሳራ ላይ ከወደቀ ቤተሰብ ነው የተወለደው – ኒኮሎ ማኪያቬሊ፡፡ በፍሎረንስ ሪፐብሊክ ውስጥ ማገልገል የጀመረው በ1494 ሲሆን በፈረንሳይ፣ በሆሊ ሲ እና በጀርመን ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዎችን ፈጽሟል፡፡ በ1521 የፍሎረንስ ሪፐብሊክ ሲያከትምለት ለአጭር ጊዜ ቢሆንም የእስራት እና የግርፋት እጣ ገጥሞት ነበር፡፡ በኋላም የግል ህይወቱን መርጦ በ1513 “ThePrince”፣ በ1516 ገደማ “TheDiscourses”፣ እንዲሁ በ1520 አከባቢ “TheArtofWar” የተሰኙ ሥራዎቹን ይፋ በማድረግ በፖለቲካዊ ትንታኔ፣ በወታደራዊ ፅንሰ-ሐሳብ እና በታሪክ ጥናት ላይ እራሱን አጠመደ፡፡ “ThePrince” (ወይም ልዑሉ) የተሰኘውን ጽሁፉን የማዘጋጀቱ ከፊል ዓላማ፣ የፅሁፉ መታሰቢያነቱ የተበረከተለትን የሜዲቺ ቤተሰብ የሆነውን ሎሬንዞን ለማማለል ነበር፤ ይሁንና እስከ 1525 ድረስ ለመንግሥታዊ አገልግሎት ጥሪ አልተደረገለትም ነበር፡፡ ብዙ አልቆየም፤ የሜዲቺ ቤተሰቦች ሥርዓት በ1527 ሲገረሰስ እንደገና ከመንግሥት ቢሮ ተገለለ፡፡ በህይወቱ የመጨረሻ ዓመታት “HistoryofFlorence” የተሰኘ ሥራውን አጠናቋል፤ እንዲሁ ዘመን በመቁጠር ላይ የሚያተኩር ሳይሆን፣ አስገራሚ በሆነ መልኩ ውስብስብ ምክንያታዊ ግንኙነቶችን ያቀረበበት፣ በፍሎረንስ ታሪካዊ ክስተቶች ላይ የሚሽከረከር ሥራው ነው፡፡
ማኪያቬሊ፣ የመካከለኛው ዘመን የፖለቲካ እሳቤ መገለጫ የነበሩት ሃይማኖታዊ እና ክርስቲያናዊ ጉዳዮች አይጥሙትም፡፡ የተባለውን የመፈጸምና የመገዛት ክርስቲያናዊ መርሆዎችን በቁርጠኝነት የሚከተል የዋህ ሕዝብ ጭካኔ በሞላው የዓለም ፖለቲካ ውስጥ ሊጐለብት እንደማይችል በማመኑ እርሱና ክርስትና ጠላት ናቸው፡፡ ለውጫዊ ወረራና ለውስጣዊ አመጽ አቅሙን ያጠናከረ መንግሥት የመመስረትና ጥንካሬውንም የማራዘም ፍላጐት ያነገበ ሪፐብሊክአዊ እና አርበኛ ነው፡፡ ይህ ፍላጐቱ እራሱን በሁለት መንገዶች ይገልፃል፡፡ “ThePrince” ላይ የማኪያቬሊ ትኩረት አንድ ሰው በተገዢዎቹ ላይ እንዴት መንጐማለል እንደሚችል ማሳየት ነው፤ “TheDiscourses” ላይ ደግሞ አንድ የሪፐብሊክ ሥርዓት የዜጐቹን መሠረታዊ የራስ-ወዳድነት ጥንካሬዎች ሕዝባዊ ጠቀሜታ ወዳላቸው መንገዶች በመቀየስ እንዴት ዘላቂ እና የበለፀገ መሆን የመቻሉን ጥያቄ ይመልሳል፡፡
የማኪያቬሊ ስልት፣ በተለይ ጥንታዊና ዘመን አይሽሬ ክስተቶችን እንደምሳሌ በማጣቀስ ላይ የሚመረኮዝ ሆኖ፣ ታሪክ ተኮር እና ንፅፅራዊ ነው፡፡ ዓላማው ክስተቶች በሚከሰቱባቸው ሁኔታዎች አማካኝነት እንዴት የተወሰኑ (በሁኔታዎቹ ላይ የተመሠረቱ) እንደሆኑ ማሳየት፣ ምክንያቶቻቸውን መጠቆም፣ እንዲሁም ለሰው ልጅ ግንኙነቶች እና ባሕሪይ መሠረት የሆኑ ጥቅል መርሆዎችን ግልፅ ማድረግ ነው፡፡ በተጨማሪም የማኪያቬሊ መሠረታዊ ተስፋ ጠንካራ ልዑል አንድ ቀን ጣሊያንን አንድ ያደርጋታል፣ ከዚያም ሪፐብሊካዊ የመንግሥት ሥርዓት ይፈልቃል የሚለ ዓይነት ነው፡፡
የሰው ልጅ ተፈጥሮ
ማኪያቬሊ፣ በአጠቃላይ ፅሁፎቹ ወጥ የሆነ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ፅንሰ-ሐሳብን ይከተላል፡፡ ጉልህ ቦታ የሚሰጠው የዚህ ፅንሰ-ሐሳብ ክፍል የሰው ልጅ ተፈጥሮ ለውጥ-የለሽ ወይም የማይቀያየር ነው የሚለው ነው፡፡ ይህም ነው፣ ስለ ፖለቲካ ጥቅላዊ ድምዳሜዎችን እንድንወስድ የሚያስችለን፡፡ ምንም እንኳን ባሕሪያቸው ሁልጊዜ የአኗኗር ሁኔታቸውን ተመርኩዞ በተወሰነ መልኩ ሊቀየር ቢችልም፣ የሰው ፍጡራን ተመሳሳይ መሠረታዊ ጠባያትን ያሳያሉ፤ እንዲሁም እነዚህ ጠባያት በተለምዶ የሚደነቁት (ጥሩ ቦታ የሚሰጣቸው) ዓይነት አይደሉም፡፡ ማኪያቬሊ “ThePrince”ላይ ይህን ይላል፡-
“ስለሰዎች በጥቅሉ እንዲህ ብሎ መደምደም ይቻላል፡- ምስጋና የለሽ፣ የማይታመኑ፣ ውሸታሞች እና አጭበርባሪዎች ናቸው፤ ምሽግ ውስጥ የሚያቀረቅሩና ትርፍ ለማግኘት የሚስቆነቆኑ፤ በደንብ ስትንከባከቧቸው የናንተ ናቸው… አደጋ ላይ ስትወድቁ ግን ፊታቸውን ያዞሩባችኋል።”
ማኪያቬሊ “TheDiscourses”ላይም ይቀጥላል፡-
“ሰዎች ሁሉ መጥፎና አጋጣሚውን ባገኙ ቁጥር የጨካኝነት ተፈጥሯቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ የሆኑ ናቸው፡፡ የተጠናወታቸው ተግባረ-ጥፋትነት ለጊዜው ባይታይ (ቢደበቅ)፣ በሆነ ባልታወቀ ምክንያት መሆን አለበት፤ እናም እራሱን የሚያሳይበት አጋጣሚ አጥቶ ነው ብለን መገመት ይኖርበናል፤ ነገር ግን የሁሉም ዓይነት እውነት አባት መሆኑ የተነገረለት «ጊዜ» አደባባይ ሊያወጣው አይሳነውም፡፡”
የሰው ልጅ ተጠናውቶ–ጥፋት (evil disposition) መነሻው ጽኑ መሠረት ያለው ራስ-ወዳድነት እንደሆነ ማኪያቬሊ ያምናል፡፡ ይህ ራስ-ወዳድነት በቀዳሚነት እራሱን የሚገልጠው ጥልቅ በሆነ ራስን የመጠበቅ እና የደህንነት ፍላጐት ውስጥ ነው፡፡ ከዚያም ደህንነት በተረጋገጠ ጊዜ ለግል ሥልጣን እና ተቀፅላው ለሆነው ዝና የሚደረግ የአንድ አቅጣጫ ትጋት ይሆናል፡፡ በተጨማሪ ሥልጣን ማለት ነፃነት ነው፤ ሰዎች ለሥልጣን ዋጋ እንዲሰጡ ካደረጓቸው ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ ይህ አንዱ ነው፡፡ ሌሎችን መግዛት የማይሹት እንኳን ቢሆኑ፣ ቢያንስ ቢያንስ ሙሉ ለሙሉ በሌሎች ቁጥጥር ስር እንዳይወድቁ እራሳቸውን ለመከላከል የሚያስችል ሥልጣን እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ፡፡ ዓለም በጨቋኞች እና ላለመጨቆን በሚታገሉት መካከል የተከፋፈለች ናትና፡፡
ይህ ሥልጣንን የመሻት ሁኔታ በሰው ልጅ ባሕሪይ ላይ ጉልህ ሚና በመጫወቱ ምክንያት ነው፣ ፖለቲካዊ ህይወት ምንጊዜም ቢሆን የትንቅንቅ ጠባይ እንዲኖረው ያደረገው፡፡ ፖለቲካ፣ ፕሌቶ እና አርስቶትል ይቻላል ስለሚሉት የመተባበር እና አንዱ ባንዱ ላይ የመደጋገፍ ዓይነት አይደለም፣ ሊሆንም አይችለም፡፡ በርግጥ ሰዎች መተባበርን (አብሮ መሥራትን) ይችላሉ፤ ነገር ግን ይህን የሚያደርጉት ትብብሩ እነሱን የሚያብስ (የሚጠቅም) እስከሆነና መሆኑ እስከቀጠለ ድረስ ብቻ ነው፡፡ የፖለቲካ ግብ ሕብር የሰፈነበት የጋራ መልካምን ማምጣት ነው የሚለው ተለምዷዊ አስተያት ቅጥፈት ነው፡፡ ፖለቲካ ትግልን የግድ ያካትታል፡፡ ማኪያቬሊ እንደሚለው፣ በንጉሣዊ ሥርዓት ውስጥ ያለው ትግል፣ አንድ ሰው የተቀሩትን ሁሉንም ለመቆጣጠር በሚል የሚደረግ ትግል ነው፡፡
የልዑሉ የግል እርካታ ማግኘት ለአጠቃላይ ሕዝቡም መልካም ሊሆን መቻሉ እውነት ነው፡፡ የጨካኙ የጣሊያን ልዑል፣ የሲዛሬ ቦርጂያ ወሳኝ ብቃቶች ናቸው ጣሊያንን ለማዋሃድ በትክክል የሚያስፈልጉት፡፡ ነገር ግን የልዑሉ ቀዳሚ ዓላማ ሥልጣኑን ማስጠበቅ እና ሥልጣኑን በነፃነት ማጣጣም ነው፡፡ ገና ሥልጣኑን የጨበጠና በዚህም መንበሩ ተደግፎ የቆመው በባሕል፣ በሕዝቡ ቸልተኝነት ወይም ሕዝቡ ለእርሱ ቤተሰብ ባለው አክብሮት ያልሆነ ልዑልን ስንመለከት ከላይ የተገለፀው ትግል ይበልጥ ግልጽ ሆኖ ሊታይ ይችላል፡፡ ‹አዲሱ› ልዑል ቦታውን የሚያመቻቸውና ዘላቂ የሚያደርገው በራሱ ጥንካሬና ብቃት ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ እናም “ThePrince”የተሰኘው ሥራው ልዑሉ ይህንን እንዴት ማድረግ እንደሚችል የሚተነትን ነው፡፡
ማኪያቬሊ፣ ልዑሉ በዋነኛነት በታቀደ የኃይል እና የማጭበርበር አጠቃቀም ላይ መመርኮዝ እንዳለበት ይጠቁማል። ምክንያቱም የሰው ልጅ የራሱ የራስ ወዳድነት ስሜቶች ባሪያ ስለመሆኑ ቅድመ-ግምት መውሰድ የሚገባን ሲሆን፣ ሕዝቦችን ምክንያታዊ የሆነ ፈቃዳቸውን በማግኘት ወይም ጥሩ የሆነ የሞራል ምሳሌን በማሳየት መግዛት (ማስተዳደር) ይቻላል ብሎ ማሰብ ፋይዳ-ቢስ እና ለአደጋ የሚጥል ነው። ምርጫ ባለበት ቦታ ሁሉ፣ ሰዎች ለሞራላዊ አስተውሎ መስፈርቶች ሳይሆን ለስሜታቸው ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣሉ። ስለዚህም የሌሎችን ስሜቶች አውቆ ጥቅም ላይ በማዋል ነው፣ እንዲያደርጉ የተፈለገውን የሚያደርጉ እንዲሆኑ ማድረግ የሚቻለው። በፖለቲካ ዓለም ውስጥ ምክንያትን ወይም አስተውሎን (reason) በአግባቡ መጠቀም የሚባል ነገር የለም። ሰብዓዊ ባሕሪይን የሚቆጣጠሩ አራት ስሜቶች እንዳሉ ማኪያቬሊ ይጠቁማል። እነዚህም ፍቅር፣ ጥላቻ፣ ፍርሃት እና ንቀት ናቸው። ፍቅር እና ጥላቻ እርስ በርሳቸው የሚጠፋፉ ወይም በአንድነት ሊቆሙ የማይችሉ ናቸው፤ በተመሣሣይ ሰዓት አንድን ሰው ማፍቀርም፣ መጥላትም የማይቻል መሆኑ ግልፅ ነው። በተመሣሣይም፣ አንድን ሰው መፍራት እና አለማክበር አይቻልም፤ እናም ፍርሃት እና ንቀት አይጣጣሙም። ሆኖም ፍቅር እና ፍርሃት ተጣጣሚ ወይም በአንድነት የሚቆሙ ናቸው፤ ጥላቻ እና ንቀት፣ ጥላቻ እና ፍርሃት፣ ፍቅር እና ንቀትም እንዲሁ ተመጋጋቢ ናቸው። በማያሻማ መልኩ ልዑሉ እንዲሰፍኑ የሚሻቸው ስሜቶችም ተመጋጋቢዎቹ ፍቅር እና ፍርሃት ናቸው። ሕዝቦች በገዢያቸው ላይ ጥላቻ እና ንቀት ካሳደሩ እነሱን መቆጣጠር የማይቻል ሲሆን፣ እንዲያውም በገዢው ላይ ለመነሳት ሰበብ የሚፈልጉ ይሆናሉ። ስለዚህም ፍቅር እና ፍርሃት እንዲሰርፁና ንቀት እና ጥላቻ እንዲወገዱ ያስፈልጋል።
ለአንድ ገዢ ሥልጣኑን ለማስጠበቅ በሚያደርገው ጉዞ ሊገጥመው የሚችለው እጅግ አስከፊው ነገር በሕዝቦቹ መናቅ እንደሆነ ማኪያቬሊ ይጠቁማል። እናም ምንም እንኳን ፍቅር እና ፍርሃት ከሁሉም የተሻለው ጥምረት ቢሆንም፣ ከፍቅር እና ንቀት ይልቅ ጥላቻ እና ፍርሃት ተመራጭ ነው። ፍርሃት ያለበት የትኛውም ጥምረት ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም ተገዢዎችን በሚያድርባቸው ፍርሃት አማካኝነት መቆጣጠር ይቻላል ማለት ነውና። በሌላ በኩል፣ ሌላኛው ተጣማሪ ፍቅር ቢሆንም እንኳን፣ ንቀት ያለበት የትኛውም ጥምረት መቀረፍ ይኖርበታል፤ ምክንያቱም የገዢውን የማስገደድ ሥልጣን የሚነጥቅ ይሆናልና፤ ምክንያቱም ፍርሃት እና ንቀት በአንድነት የሚቆሙ አይደሉምና። መፈቀር የግድ አስፈላጊ አይደለም፤ ነገር ግን መፈራት የግድ አስፈላጊ ነው፤ እንዲሁም አለመናቅ ደግሞ በጣም አስፈላጊ ነው።
ይህ ማለትም ቀጥ በቀጥ ሲገለፅ፣ የልዑሉ ሥልጣን መሠረት የተጣለው በኃይል ላይ እና ይህን ኃይሉን ያለርህራሄ የመጠቀም ፈቃደኝነቱ ላይ ነው። ይህም ልዑሉ እንዲኖረው የሚያስፈልጉት ብቸኛ ጥበባት ወታደራዊ ጥበባት ናቸው የሚለውን የማኪያቬሊ ማስረገጫ የሚመለከት ነው። የማኪያቬሊ ሬኔይሳንስ ዘመን ፀሐፊዎች ልዑሉ የጎለበተ እና ሰብዓዊነት ያደረበት መሆን አለበት የሚለውን ሐሳብ እንደመፈክር ወስደውት ቆይተዋል፤ ለጥበባት፣ ለሩህሩህነት፣ ለብልህነት እና ለመሳሰሉት ቦታ የሚሰጥ መሆን አለበት። ሆኖም ለማኪያቬሊ ለልዑሉ ተገቢ የሆነ ጥናት የጦርነት ጥበብ ነው። ለዚህም ምክንያቱ፣ ለማኪያቬሊ፣ ፖለቲካ ራሱ ድምፅ-አልባ ጦርነት ነው። በገዢው እና በተገዢዎቹ መካከል ያሉት ግንኙነቶች፣ በመጠን ደረጃ ባይሆንም እንኳን በይዘት፣ በሉዓላዊ መንግስታት መካከል ካለው ግንኙነት ጋር ተመሣሣይ መሆናቸውን ያምናል። ሀገራት ሁልጊዜም እንደደመና በተንዣበበ ወይም ደግሞ በተግባር ባለ ጦርነት ውስጥ እንደሆኑት ሁሉ፣ ተገዢዎችም ከገዢያቸው ጋር ዘላቂነት ባለው ጦርነት ውስጥ ናቸው። ስለዚህም የልዑሉ ትክክለኛ ፖሊሲ እርሱን ለመገታተር በቂ ኃይል ያለው ሰው አለመኖሩን ማረገጋገጥ ነው፤ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት ሰዎች ካሉ፣ ሥልጣን የመያዝ አጉል ፍላጎት ያለጥርጥር ለእርሱ ፈታና ይሆኑ ዘንድ እንደሚገፋፋቸው መገመት ይገባዋል።
በሌላ በኩል፣ በሀገራት መካከል ጦርነት ለተወሰነ ጊዜ ሊራዘም እንጂ መቼም ቢሆን ሊወገድ እንደማይችላ ማኪያቬሊ ያስባል፤ ይህንንም ያልተገነዘበ ልዑል ወደ ጥፋት እያመራ ነው። የልዑሉን ኃይል የመፈተን አቅም ያላቸው አጎራባች ኃይላት ካሉ፣ ጦርነት አይቀሬ ነው፤ ምክንያቱም ከወዲያኛው ወገን የአደጋ ስጋት እስካልተቀረፈ ድረስ፣ ሁለቱም ወገኖች ደህንነት ተሰምቷቸው አርፈው አይቀመጡም። እናም ዕድሉን ካገኘ ማጥቃት፣ ካልሆነ ደግሞ የሌላውን የማጥቃት ዕድል በዲፕሎማሲ ማክሸፍ ሁሌም ቢሆን የተሻለ ነው። ኋላ ራስ ላይ ጉዳት ለማምጣት ጦርነትን ማቆየት ወይም ለወደፊት ማራዘም አይገባም። ከሁሉም በላይ ልዑሉ ሌሎችን መጉዳት ግድ ከሆነበት፣ ለዘለቄታው ኃይላቸውን በሚያሳጣቸው ወይም ከነጭራሹ በሚያወድማቸው መንገድ ማጥቃት አለበት። ይህን ካላደረገ፣ የመበቀል ፍላጎታቸው ተፈጥሯዊ ህልማቸውን ያጠነክረውና እርሱን መቀመቅ ለመክተት በሚያደርጉት ጥረት የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም።
በዚህም የተነሳ የማኪያቬሊ የሞራላዊነት እና የፖለቲካ ምልከታ፣ ከተለመደው ጥሩ መሪ የግድ ጥሩ ሰውም ነው ከሚለው አቋም እጅግ የተለየ ነው። ጥሩ መሪ በራሱ አኗኗር እና በራሱ ተግባራት ላይ የሞራል ልዕልናን (virtue) ያሳያል፣ ለተገዢዎቹ መልካም ምሳሌ ይሆናል፣ የራሱን ብቻ ሳይሆን የጋራ የሆነውን ጥሩ ነገር ለማረጋገጥ ይጥራል፣ ከቤተ ክርስቲያን የሚሰጠውን ምክር ይሰማል ከሚለው ጋር ይለያያል። “ThePrince” ላይ ላየነው ማኪያቬሊ፣ ፖለቲካ ሥልጣን ወይም ኃይል ስለማግኘት እና የራስ አድርጎ ስለማስቀረት ነው። ‘virtue’ ለሚለው ቃል ክህሎታዊ መሰል ትርጓሜ ሰጥቶታል። ለማኪያቬሊ ‘virtue’ ማለት ሞራላዊነት ወይም የሞራል ልዕልና አይደለም፤ ይልቁኑ አንድ የሆነ የክህሎት ወይም የችሎታ ዓይነት እና እርሱን ጥቅም ላይ የማዋል ፈቃደኝነት በአንድ ላይ ተዳምረው እንደማለት ነው። (ምልከታዎቹን ለመተንተን ሲባል በጣሊያንኛ “virtù” የሚለውን ቃላ እንዳለ ለማስቀረት በተለምዶ ጥቅም ላይ ይውላል እንጂ አግባቡ ሌላ ነው።)
ይህን ሐሳብ ማኪያቬሊ “ThePrince” ላይ በገለፃቸው “virtù” እና “fortuna” መካከል ያለውን ተዛምዶ በመመርመር ማስተጋባት እንችላለን። ሁላችንም በተወሰነ መጠን በተለዋዋጯ የዕድል አምላክ (Fortuna) ቁጥጥር ስር መሆናችንን ይጠቁማል፤ እንዲሁም ተሞክሮ እንደሚያስተምረን፣ በተለምዶ በምናውቃቸው የሞራል ልዕልናዎች (virtues) እና በጥሩ ወይም በመጥፎ ዕድል ክስተቶች መካከል ሁሌ ግንኙነት የለም። ታምኝ እና ጎበዝ ነጋዴ መርከቦቹ ሁሉ በማዕበል ሊሰምጡ ይችላሉ፤ እናም የእርሱ ታማኝነት አያግዘውም። ትጉህ እና ፈሪሐ-እግዚአብሔር ያለው ገበሬ ሰብሉ በሙላ በዶፍ ዝናብ ሊወድምበት ይችላል። ህይወት በተመቻቸ ቦይ አትፈስም፤ የማይገመቱ እና የማይጠበቁ ነገሮች ይከሰታሉ፤ የምንኖረው አንድ ሰው በሚገባው እና በሚያገኘው መካከል አስፈላጊ ተዛምዶ በሌለበትና ሞራላዊ ወጥነት በማይታይበት ዓለም ነው። እናም ይህ ተገማችነት ማጣት እና ሞራላዊ ወጥነት አለመኖር ከሌላ ቦታ ይልቅ በይበልጥ የሚታየው በፖለቲካዊ መድረክ ነው። የተለዋዋጩን እና መረጋጋት የማይታይበትን ዓለም ፖለቲካ የተቆጣጠሩት በከፍተኛ መጠን በዕድል ቁጥጥር ስር ናቸው። በርግጠኝነት ለእነሱ በመከዳት እና በመሸለም መካከል ትስስር የለም። ከዛሬ ነገ ምን እንደሚፈጠር፣ ታማኝነት እንዴት እንደሚቀየር፣ የኃይል ምዛኑ እንዴት እንደሚለወጥ፣ እና ሌላ ሌላውንም አያውቁትም።
በአንፃሩ ላልረጋው እና ለጊዜያዊው የተግባራዊ ጉዳዮች ዓለም፣ በጥቅሉ ሰብዓዊ ፍጡራን ግትር እና የማይለዋወጥ ባሕሪይ አላቸው። የሰው ልጅ ፀባይ እና ባሕሪይ፣ በዚህም ሁኔታዎችን የሚያካሂድበት መንገድ በመደበኛ መልኩ የማይለዋወጥ እና ተከታታይ ነው ማለት እንደሚቻል ማኪያቬሊ ተመልክቷል። በርግጥም ዘ-ልማዳዊ የሞራል ትምህርት የምንለው ሂደት እንዲህ ያለውን የማይለዋወጥ እና ተከታታይ ባሕሪይ እንዲያጎለብት ያደርገዋል (ከልጅነቱ አንዳንዴ ብቻ ወይም ለእርሱ ዓላማ ሲመቸው ብቻ ሞራላዊ እንዲሆን ተደርጎ አላደገማ)። ታዲያ ዕድል የምትጥለን ሁኔታ እንዲህ ላለ ተለዋዋጭነት የተጋለጠ በሆነበት ዓለም የማይለዋወጥ የአካሄድ ስልት መያዛችን ጥቅሙ ምኑ ላይ ነው? እራስህን የምታገኝበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ ሁልጊዜ በተመሳሳይ መንገድ መራመድ ወይም ተመሣሣይ እርምጃ መውሰድ የአደጋ መገለጫ መሆኑን ማኪያቬሊ ያስረግጣል። ይህም በይበልጥ በተለዋዋጭ እና በጭካኔያዊ የፖለቲካ ዓለም ውስጥ ለመኖር የምትሞክር ልዑል፣ በተለይም አዲስ ልዑል ከሆንክ እውነት ነው።
እናም በጥቅሉ ለማኪያቬሊ “virtù” ማለት የዕድልን ግፊቶች ለመጋፈጥና አስፈላጊ በሆነ መንገድ ሁሉ ለመቅረፍ የሚያስችል የአንድ ግለሰብ ብቃት ወይም ችሎታ ነው። ፖለቲካዊ ስህተትን ለማስቀረት በሚደረግ ትንቅንቅ ውስጥ፣ ዕድል ልክ እንደ ነዝናዛ እና አቃጣይ ሴት እንደሆነች ይነግረናል። እናም አንድ ሰው ሊያስተካክላት ይገባዋል፤ አንዲት ነዝናዛ እና አቃጣይ ሴትን እንደሚያስተካክለው፤ ሰጥ ለጥ እስክትል በመምታት (ይህ የተባለበትን ዘመን ልብ ይሏል)። ልዑሉ ከዕድል ጋር በሚጋፈጥ ጊዜ በግትር የሞራል ባሕሪይ መወሰን አያዋጣውም። ከነገሮች የሚላመድ መሆን ይገባዋል። በውስጡ ያሉትን አንበሳነት እና ቀበሮነት ሁለቱንም የመጠቀም አቅም እና ዝግጁነት ሊኖረው ይገባል፤ ሰውም አውሬም የመሆን አቅም ሊኖረው ይገባል። ምህረት ማድረግ ውጤት ሲኖረው መሐሪ ይሁን፤ ሆኖም አስፈላጊ ሲሆን ደግሞ ምህረት-የለሽ፣ ጨቃኝ እና አንቀጥቃጭ ይሁን። አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሀቀኛ እና እውነተኛ ይሁን፤ ነገር ግን አስገዳጅ ሁኔታ ሲገጥመው የሚዋሽ እና ቃሉን የሚያጥፍ ይሁን። ልዑሉ ሁኔታዎች የሚጠይቁትን ነገር ሁሉ ማድረግ ይገባዋል፤ እናም እነዚያ ሁኔታዎች ዘ-ልማዳዊ የሞራል እሴቶችን እና ክርስቲያናዊ ምግባሮችን እንዲገፋ ወይም እንዲጣረስ ካስገደዱትም የራሱ ጉዳይ፣ ያደርገዋል። የሥልጣን ማጣት አጋጣሚዎችን በሚጨምሩ መንገዶች መጓዝ፣ ወይም ሥልጣንን ይዞ የመቆየት አጋጣሚዎችን የሚጨምሩ መንገዶችን አለመከተል እራስን እንደመጣል ነው።
አብዛኞቹ የማኪያቬሊ ዘመን ሰዎች፣ እንዲሁም አብዛኞቹ በኋላ የመጡ ተቺዎቹ እርሱ የጥፋት አስተመሪ ነው የሚል አቋም ነበራቸው፡፡ በአሥራ-ሰባተኛው ክ/ዘመን መጀመሪያ፣ የማኪያቬሊ ስም ለጨቋኝ ሥርዓት (tyranny) እና ለከሀዲ ስያሜዎች ተለዋጭ አቻ ስም ሆኖ ነበር፡፡ ሆኖም ማኪያቬሊ እርኩሰትን ወይም ጥፋትን እንደማያስተምርና የእርሱም ልዑል እርኩስ እንዳይደለ ለመመልከት አያስቸግርም፡፡ ከመደበኛው የሞራላዊነት ምልከታ አንፃር፣ ማኪያቬሊ የፖለቲካ ተዋናዮች አስከፊ ነገሮችን እንዲፈፅሙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደሚያስገድዷቸው ለማመን እጅግ የተዘጋጀ ነው። ምናልባት ይህ አሳዛኝ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ተከትሎ የአካሄድ ስልቱን መለዋወጥ የማይችል ልዑል ረዘም ላለ ጊዜ በልዑልነቱ ያለመቀጠሉ እውነታ እንዳለ ነው። ይህ የህይወት እውነታ ነው፤ እናም ይህ በመሆኑ እጅን ማሽሞንሞን ፋይዳ ቢስ ነው ሲል ማኪያቬሊ ያስባል።
ብዙ ሰዎች ፀባያቸው ወይም ትምህርታቸው አስቀድሞ እንዲሆኑ ካደረጋቸው ማንነት መለወጥ አይችሉም፤ ወይም ደግሞ በአንድ መንገድ ተጉዘው ስኬታማ ከሆኑ፣ በሌላ መንገድ መሄድን እንዲለምዱ እራሳቸውን ማስገደድ አይቻላቸውም። አንድ ሰው የህይወቱን ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ተከትሎ የአካሄድ ስልቱን ወይም ፀባዩን መለወጥ ቢችል ዕድሉ መቼም ቢሆን አትለወጥም ነበር። እንደ ማኪያቬሊ ሐሳብ፣ ስኬታማ ልዑል ማለት ይህንን በትክክሉ ማድረግ የሚችል ሰው ነው። የዕድልን ውጤቶች የሚመክትበት ችሎታው ገደብ-የለሽ በሆነ መልኩ ተጣጣፊ፣ ነፋሱ በነፈሰበት ነፋሽ የመሆን ችሎታ ነው። የሚያደርገው ሁሉ የተደረገው ሁኔታዎች ስላስገደዱት ነው፤ እንዲሁ ባሕሪይው ወይም የሞራል መርሆዎች ስለመሩት አይደለም የሚያደርገው። ስለዚህም ልዑሉን እጅግ በቀላሉ ሞራል-አልባ (amoral) እንደሆነ አድርገን መግለፅ እንችላለን። ጥሩም ሆነ መጥፎ አይደለም፤ እርኩስም ሆነ ተቃራኒው አይደለም። የሞራል-አልባነት ባሕሪይ አለው። በአንድ በተወሰነ መንገድ እንዲራመድ የሚያደርገው ግትር ማንነት ወይም የሕሊና ልማድ የለውም። ግትር ማንነት ካላቸው ብዙ ሰዎች በተቃራኒው፣ ሙሉ ለሙሉ የሞራል ልዕልና ያለው የመሆን ወይም ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ጨካኝ የመሆን ችሎታ ያለው ሲሆን፣ ሁለቱንም እንዴት መሆን እንደሚችል ያውቅበታል። ዘ-ልማዳዊዎቹ የሞራል እሴቶች እንዲሁ የእርሱ ባሕሪይ አካሎች አይደሉም። አብዝቶም ሆነ አሳንሶ የሚያቀነቅናቸው ፍፁሞች አይደሉም፤ እንዲሁ ሲፈልግ በፈቃዱ የሚያነሳቸውና የሚጥላቸው የእርምጃ ስልቶች ናቸው።
የማኪያቬሊ ሪፐብሊክ
ማኪያቬሊ ስለሰው ልጅ ተፈጥሮ እና ባሕሪይ ያለው አመለካከት፣ ምንም እንኳን ሥልጣን በቀላሉ ሊጸና የሚችለው በአዲስ ልዑል ጊዜ ቢሆንም፣ ጤናማና ይበልጥ ስኬታማ የመንግሥት ዓይነት ከዘውዳዊ (monarchy) ይልቅ ሪፐብሊክ ነው ወደሚል ድምዳሜ አምርቶታል፡፡ ይህ “TheDiscourses” የተሰኘው ሥራው ዋና ጭብት ነው፤ “ThePrince” ከተሰኘው እጅግ የተለየ፣ ነገር ግን በተመሳሳይ መላምት ላይ የሚንሳፈፍ ሥራው ነው፡፡ በዘውዳዊ ሥርዓት አንድ ሰው ላዕላይ ወይም ጠቅላይ ሥልጣን አለው፡፡ አንድ ሰው በእርሱ ተገዢ ከሆኑት ሁሉ የሚፈልቀውን ግንፈላ ለመገደብ በቦታው ተቀምጧል – ለህልውናው ካሰበም ሊገድብ ግድ ነው፡፡
በሪፐብሊኩ ውስጥ እያንዳንዱ ግለሰብ ልዑል ነው፤ እያንዳንዱ ግለሰብ ለደህንነቱ፣ ለነፃነቱ እና ለንብረቱ ከለላነት የራሱን “virtù” የማጎልበት እና ተፈፃሚ የማድረግ ችሎታ ያለው ሲሆን፣ በዚህም የሁሉም የሆነ ምቾት እና ደህንነት የሚያመጣ የጋራ ወይም ሕዝባዊ “virtù” ይፈጥራል። ማኪያቬሊ እንደሚለው፣ በዘውዳዊ ሥርዓት አንድ ሰው ብቻ ነፃ ነው፤ በሪፐብሊክ ግን ሁሉም ነፃ ናቸው፡፡ ይህ የጋራ “virtù” ከውድጅት ወይም ከመተሳሰብ የሚመነጭ አይደለም። ሰዎች የሚተባበሩት የጋራ ጥበብ እና ጥረት በጥቅሉ ግለሰባዊ ከሆነው ከማንኛውም እንደሚሻል በማወቃቸው ምክንያት ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው በተመሳሳይ ሰዓት ሰዎች ዋጋ ለሚሰጧቸው – ዝና፣ ክብር፣ ሀብት – ነገሮች ከሌሎች ጋር የሚፎካከር ቢሆንም፣ የራሱን ጥቅም የሚያስጠብቅለት እስከሆነ ድረስ ከሌሎች ጋር ይተባበራል፡፡ ሪፐብሊክ፣ የመተባበር ጥቅምን እና ከሌሎች ጋር አብሮ ጥሮ ግልፅ በሆነ መድረክ ራስን በማሳየት “virtù” የተባለውን ክህሎት የማጎልበት አማራጭን ያጐናፅፋል፡፡
ሪፐብሊኮች ከዘውዳዊ ሥርዓቶች በበለጠ የተረጋጉ ይሆናል፤ ይበልጥ እራሳቸውን መከላከል የሚችሉና ግዛታቸውን በጦርነት በማስፋፋት ረገድ ይበልጥ ስኬታማ ይሆናሉ፡፡ ይህም በተወሰነ መልኩ ለራስ መቆምን በማዝቀጣቸው ወይም በመመከታቸው ምክንያት ሳይሆን፣ ይልቁንም ለጉዳዩ ይበልጥ የሰፋ ነፃነት በመስጠታቸውና በዚህም ጀግና፣ መጨቆንን የማይሻ፣ በራሱ የሚተማመን ግለሰብን በመፍጠራቸው ምክንያት እንጂ፡፡
ለሪፐብሊኩ ዘለቄታ
የሰው ልጅ ተፈጥሮ ምንም ሆነ ምን፣ ሪፐብሊኩ ላይ የተጋረጠው ችግር ወደ ጨቋኝ ሥርዓት (tyranny) አለመለወጡን ማረጋገጡ ወይም የመውደቂያውን ጊዜ በተቻለ መጠን ማራዘሙ ላይ ነው፡፡ ሪፐብሊኮች የተረጋጉ እንደሆኑ መቀጠል የሚችሉት፣ ማንም ቢሆን ሌሎቹን ሁሉ በቀላሉ ለመቆጣጠር የሚያስችለውን መጠን ያለፈ ሥልጣን እንዲኖረው ሳይፈቀድለት ሰዎች እርስ በርሳቸው ፈጠራ በተሞላበት መንገድ እንዲፎካከሩ ባስቻሉ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ በላይኛው መደብ የህብረተሰብ ክፍል ወይም የንግድ መስመሩን በተቆጣጠሩት እና በአጠቃላዩ ሕዝብ መካከል ግጭት መኖሩ አይቀሬ ነው። የላይኛው መደብ ብዙሃኑን ይጫነዋል፤ ብዙሃኑ ደግሞ ከዚህ ጫና ነፃ ለመውጣት ይመኛል። እንዲህ ያለው ግጭት የማይቀርና ለመፈንዳት ሰበብ የሚፈልግ ነው። በሮም ሪፐብሊክ በተራው ሕዝብ እና በመሳፍንቱ መካከል የነበረው ትንቅንቅ ማኪያቬሊ እንደምሳሌነት የተመለከተው ነው። ተፃራሪ ፍላጎቶች ጥሩ ሕጎች የሚፈጠሩበትን ኃይል ያመነጫሉ፤ ይህም እንዲህ ያለ ግጭት በአግባቡ በተዋቀሩ የፖለቲካ ተቋማት አማካኝነት ከተገደበ ነው።
ማኪያቬሊ፣ በተግባር ያሉ የመንግሥት ዓይነቶች እንደየሕዝባቸው ሁኔታ እንደሚለያዩ ተረድቷል፤ ነገር ግን እሱ እንደሚያስበው፣ ከሁሉም የተሻለው የመንግሥት ዓይነት፣ አርስቶትል እንደሚደግፈው ዓይነት፣ ቅይጥ ሕገ-መንግሥት ያለው ሪፐብሊክ ነው፡፡ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ትርጉም ያለው ድርሻ ሲኖረው ሁሉም በክብራቸው፣ በንብረታቸው እና በሰውነታቸው የዋስትና ስሜት እንዲኖራቸው ያስችላል፡፡ ሕጐቹ ግልፅ እና በሕዝብ የሚታወቁ ሊሆኑ ይገባል፡- ዜጐቹ ሳይቀጡ በከፍተኛ የእርግጠኛነት መጠን መሥራት የሚችሉትንና የማይችሉትን ሊያውቁ ይገባል፡፡ ጥቅል ኢኮኖሚያዊ ብልፅግና መበረታታት ያለበት ሲሆን፣ ከመጠን ያለፈ የግለሰብ ሀብት እና ቅንጦት በሕጐች መገደብ ይኖርበታል፡፡ ለዜጐች ጥቅሞች ጉልህ እውቅና ሊሰጥ ይገባል፤ እንዲሁም ክብር እና ዝና ለሚሹ ሁሉ በመንግሥታዊ አገልግሎቶች ላይ እንዲሳተፉ መፈቀድ አለበት፡፡
ሕዝባዊ ሞራልን ለመገንባት እና ለመጠበቅ መንግሥታዊ ሃይማኖት መኖር አለበት፡፡ ሆኖም ይህ ሃይማኖት ደካማነትንና ተገዢነትን የሚያበረታታው ክርስትና መሆን የለበትም፡፡
ሪፐብሊኩን ለመጠበቅም ሆነ በወረራ ጦርነቶች ይዞታውን ለማስፋፋት በዜጐች የተዋቀረ ሠራዊት ሊኖር ይገባል፡፡ ሠራዊቱ ለትምህርታዊ እና ለወታደራዊ ዓላማ ይተጋል፡- በዜጐች ዘንድ ለባለሥልጣን ክብር መስጠትን፣ አርበኝነትን እና ወታደራዊ ሥነ-ምግባርን ያሰርፃል፡፡ በተጨማሪም ግለሰባዊ ህልሞች (ምኞቶች) ተፈጥሯዊ እና ጤናማ ተፈፃሚነት የሚያገኙበትን መንገድ ያመቻቻል፡፡ በሪፐብሊኩ ውስጥ ያለ ህይወት እጅግ የተመቸ መሆንም የለበትም፡፡ በችግር እና በአደጋ ጊዜ ህብረተሰባዊ ጥምረት እና ጥንካሬ ቀድሞውኑ ተረጋግጠዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ጊዜያት በሕዝቡ ያለውን መልካምነት በማውጣት በአብሮነት እንዲሠራ ብርታት ይሆኑታል፡፡
በአጭሩ ማኪያቬሊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴን የተለያየ ዓይነት እና መጠን ያለው ሥልጣን በመያዝና የያዙትንም ላለማጣትና የበለጠ ለማጠናከር የሚሞክሩ የግለሰቦች እንቅስቃሴ እንደሆነ አድርጐ ይወስደዋል፡፡ “The Prince” እና “The Discourses” ሥራዎቹ ጉልህ የሚባል ልዩነት የላቸውም፤ እርስ በርስ የሚቃረኑም አይደሉም፡፡ ሁለቱም የሰው ልጅ ተፈጥሮ ግለሰባዊ፣ ተፎካካሪና አስፈላጊ ሲሆንም ጨካኝ እና ሥርዓት አልበኛ የመሆኑን ምልከታ ይጋራሉ፡፡ “The Prince” ልዑሉ ከሰብዓዊ ተፈጥሮ የሚመነጩ ኃይሎችን ለራሱ በሚጠቅመው መልኩ እንዴት እንደሚቆጣጠር የሚያሳይ ነው፤ “The Discourses” ደግሞ እነዚህ ኃይሎች አንድነትን እና ሕዝባዊ ደህንነትን በሚያረገጋግጥ መልኩ ጥቅም ላይ የሚውሉበትን መንገድ የሚጠቁም ነው፡፡ ሆኖም በሁለቱም ላይ የሚገኙት ኃይሎች ተመሣሣይ ናቸው፡፡
ብዙውን ጊዜ ማኪያቬሊ መንግሥታት ለሚወስዷቸው እርምጃዎች ምክንያት ሊኖራቸው ይገባል (raison d’état) ለሚለው እሳቤ ጠንካራ ትኩረት በመስጠት ረገድ የመጀመሪያው የፖለቲካ ፅንሰ-ሐሳብ አፍላቂ እንደሆነ ይነገራል። ይህ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ይህ ብቻ አይደለም። ማኪያቬሊ፣ ለመንግሥት እርምጃዎች የሚታይ ምክንያት በሌለበት ሁኔታ እንኳን፣ “virtù” ብሎ ለሚጠራቸው የተግባር ብቃቶች ጥምረት አድናቆት አለው። የዚህም ምክንያቱ ሥልጣን ከሚያስከትላቸው ውጤቶች በላይ እራሱ ሥልጣን የተባለው ነገር ይበልጥ ይመስጠዋልና ነው።
ለማኪያቬሊ፣ ሥልጣን ተግባራዊ የሚሆንባቸው የመጨረሻ ውጤቶች የቀዳሚነት ሳይሆን የሁለተኛነት ደረጃ ያላቸው ስለመሆኑ ልብ ማለት አይቀርም፡፡ ማኪያቬሊ በሁሉም መደበኛ መመዘኛዎች ጨካኝ እና ጨቋኝ የነበረውን የጣሊያን ወታደራዊ መሪ ሴዛሬ ቦርጂያ፣ የሞራል ጠባዩን ሳይሆን ውጤታማነቱን ያደንቅለታል፡፡ በጊዜው ከነበሩትም ሆነ ከቀደሙት ከአብዛኛዎቹ በተቃራኒው፣ ፖለቲካ ከሞራል አኳያ ገለልተኛ የሆነ ጥበብ ስለመሆኑ ማኪያቬሊ አጠንክሮ ያምናል፡፡ ከማንም በላይ ይህንን ፖለቲካዊ ክስተቶች እና ግንኙነቶች ሊተነተኑ የሚገባበትን ጉልህ ምልከታ የማበርከቱ እውነታ ነው፣ የእርሱ ልፋት በፖለቲካ እሳቤ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ቦታ ሊሰጠው ያስቻለው፡፡
ለበለጠ ንባብ
ቀዳሚ ምንጮች፡
The Discourses, ed. L.J. Walker and B. Crick (Harmondsworth: Penguin, 1970).
The Prince, ed. Q. Skinner and R. Price (Cambridge: Cambridge University
Press, 1988).
ተቀፅላ ምንጮች፡
Pocock, J.G.A.: The Machiavellian Moment (Princeton, NJ: Princeton University Press, 1975).
Skinner, Q.R.D.: The Foundations of Modern Political Thought, vol. 1: The Renaissance (Cambridge: Cambridge University Press, 1978).
Machiavelli (Oxford: Oxford University Press, 1981). Viroli, M.: Machiavelli (Oxford: Oxford University Press, 1998).