FEATUREDፖለቲካ/ፍልስፍና

«መንግሥት የባላደራነት ተፈጥሮ አለው» ጆን ሎክ (1632-1704)

ፑሪታን (Puritan) በእንግሊዝዋ ንግሥት፣ በቀዳማዊት ኤልሳቤጥ ዘመን የቤተክርስቲያኗ ተሃድሶ ሙሉ አይደለም የሚሉና የአምልኮ ሥርዓቶችን ቀላል በሆነ መንገድ ለማስኬድ የሚሹ የፕሮቴስታንቶች ቡድን መጠሪያ ነው። በፖለቲካ ፍልስፍና ጠንካራ መሠረት ከጣሉት ሰዎች አንዱ መሆኑ የሚነገርለት ጆን ሎክ ከፑሪታን ቤተሰብ ነው የተወለደው፤ እ.አ.አ በ1632 ሶመረስት፣ ኢንግላንድ ውስጥ። አባቱ፣ በእርስ በርስ ጦርነቱ ወቅት ፈረሰኛ ጦር አሰባስቦ በፓርላመንታሪያኖቹ (Parliamentarians) ወገን ሆኖ ተዋግቷል። ሎክ በ1652 ነበር በክራይስት ቸርች ትምህርቱን ለመከታተል ወደ ኦክስፎርድ ያቀናው። ቀዳሚ የፖለቲካ ሥራው፣ “Essays on the Law of Nature” የተፃፈው በ1660 ነው።

በ60ቹ የሕክምና ትምህርት ፍላጐት ያደረበት ጆን ሎክ፣ እንደሙያ ባይሰራበትም በ1675 በሕክምና ዲግሪ ይዟል። በወቅቱ (በ1660) አዲስ ከተመሠረተውና “ሮያል ሶሳይቲ” ከተባለው የምሁራን ክበብ አባላት ጋር መገናኘት የጀመረ ሲሆን፣ በ1668 እርሱም የክበቡ አባል መሆን ችሏል። በ1667 የአንቶኒ አሽሊ ኩፐር የሕክምና አማካሪም ሆኖ ነበር፤ እንዲሁም ሻፍትስቡሪ በ1672 ሎርድ ቻንስለር ወይም የፍትሕ አካሉ የበላይ ሆኖ ሲሾም፣ ጆን ሎክ ፀሐፊው ሆነ።

ሆኖም ጆን ሎክ፣ ከሻፍትስቡሪ የተገንጣይ ፖለቲካ እና ከክበቡ ጋር ባለው ቁርኝት፣ ንጉሥ ጀምስ 2ኛ በ1685 ዙፋኑን ሲረከብ አዋጪው መንገድ ወደ ሆላንድ መሰደድ እንደሆነ በማሰብ ሀገሩን ለቀቀ። በስደት እያለ በእንግሊዝ መንግሥት ሰላዮች አማካኝነት ከፍተኛ አደጋ እየተንዣበበበትም ቢሆን፣ “Essay Concerning Human Understanding” የተሰኘውን ሥራ ለመጨረስ ችሏል። በኋላም በ1689 ዙፋኑ በኦሬንጁ ዊሊያም (William of Orange) እጅ መግባቱን ተከትሎ፣ ሎክ ወደ ኢንግላንድ በመመለስ “Essay” የተባለውን ሥራ አሳትሟል። በተመሳሳይ ዓመትም በመንግሥት ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚያውጠነጥን ጥናታዊ ሥራ፣ “Two Treatises of Government” እና መቻቻልን በሚመለከት የመጀመሪያውን ፅሁፍ፣ “Letters Concerning Toleration” ሊያሳትም በቅቷል። እንዲሁም ሥርዓተ ትምህርትን በሚመለከት በ1693 “Thoughts on Education” እና የክርስትና እምነት ላይ በ1695 “On the Reasonableness of Christianity” ለንባብ በቅተውለታል።

ጆን ሎክ እንደ ፈላስፋነቱ፣ በአብዛኛው ማለት ይቻላል፣ እውቀትን ማዕከል ባደረገው የፍልስፍና ዘርፍ (epistemology) የሚታወቅ ይሁን እንጂ፣ ለፖለቲካ እሳቤ ታላቅና የረጅም ዘመን ዕድሜ ያለው አስተዋጽኦ አበርክቷል። ይህ የሎክ አስተዋጽኦ በዋናነት በሁለቱ የመንግሥታዊ ባሕሪይ ጥናቶቹ፣ “Two Treatises of Government” ላይ የተካተተ ነው፤ በተለይም በሁለተኛው ላይ። ለብዙ ዓመታት እነዚህ ሥራዎቹ የተፃፉት የ1688 የእንግሊዝ አብዮትን (the Glorious Revolution) ምክንያታዊነት ለማረጋገጥ እንደሆነ ተደርጎ ይወሰድ ነበር። ሆኖም ለፕሮፌሰር ፒተር ላዝሌት ምርምሮች ምስጋና ይሁንና፣ ሁለቱ ሥራዎቹ የተዋቀሩት በ1689 ከመታተማቸው ከአስር ዓመታት በፊት መሆኑ ታምኗል። ሎክ ለህትመት ሳያበቃቸው ለዚህን ያህል ጊዜ ይዞ ማቆየቱ ከጥንቃቄ የተነሳ እንደሆነ ይገመታል። ምክንያቱም፣ በተፃፉበት ጊዜ ቢታተሙ ኖሮ በሀገር ክህደት ሊያስወነጅሉት ይችሉ እንደነበር ጥርጥር የለውም።

የመንግሥት ባሕሪይ

በሁለቱ የመንግሥት ባሕሪይ ጥናታዊ ፅሁፎቹ ላይ ስናተኩር፣ የመጀመሪያው ፅሁፍ፣ መሳፍንታዊው (Royalist) ፀሐፊ ሰር ሮበርት ፊልመር “Patriarcha” በተሰኘ መፅሐፉ ላይ ላዳበረው የንጉሦች መለኮታዊ መብት ፅንሰ-ሐሳብ ዓይነት ምላሽ የሚሰጥ ነው። የሎክ ዓላማ፣ ንጉሣዊ ሥልጣን በተፈጥሮው አባታዊ (patriarchal) የሆነና ስለዚህም በሚተገበርባቸው ሕዝቦች ሊሰጥም ሆነ ሊነጠቅ የማይችል ነው የሚለውን የፊልመር ሐሳብ ማክሸፍ ነው።

ፊልመር፣ በብሉይ ኪዳን የተፃፈውን መሠረት በማድረግ፣ አዳም እና ትውልዶቹ ዓለምን እንዲገዙ መለኮታዊ ሹመት እንደተሰጣቸውና ከዚያ በኋላ የመጡ የሁሉም ንጉሦች ሥልጣን ከዚህ እውነታ እንደተመዘዘ መከራከሪያውን አስቀምጦ ነበር። ሎክ፣ ይህን መከራከሪያ ሐሳብ በቀላሉ ይደመስሰዋል። በምትኩም፣ ማንም ሰው የሌላ ሰው ተፈጥሯዊ ገዢ ይሆን ዘንድ በእግዚአብሔር አልታሰበም የሚለውን መርሆ አዳበረ። (በዚህ አጋጣሚ ፊልመር እንደ የፖለቲካ ፈላስፋ፣ ሎክ ከሚሰጠው ቦታ በላይ ችሎታ እንደነበረው መጠቆም ሊኖርብን ይችላል። ፊልመር ደረጃው ብዙም ቦታ ከማይሰጣቸው ሰዎች ዘንድ ተመድቦ መቅረቱ እንደመጥፎ ዕድል የሚቆጠር ሲሆን፣ ለዚህም ሎክ በመጀመሪያው የመንግሥት ባሕሪይ ጥናታዊ ሥራው አማካኝነት ያደረሰበት ጥቃት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።)

ሎክ የራሱን እሳቤዎች ያቀረበው ከመጀመሪያው ይልቅ በሁለተኛው ጥናታዊ ሥራው ነው። ትክክለኛ ርዕሱም “An Essay Concerning the True Original, Extent and End of Civil Government” የሚለው ነው (የሕዝባዊ መንግሥትን ትክክለኛ ምንጭ፣ የትግበራውን መጠንና ፍፃሜውን ያመላክታል)። ይህ ሥራው መነሻውን የሚያደርግበት ነጥብ የመጀሪያው ጥናታዊ ሥራ አንግቦት ከነበረው ዓላማ ነው፤ ይህም ማንም ሰው በተፈጥሮም ሆነ በመለኮታዊ ፈቃድ የማንም ሰው ተገዢ አይደለም የሚለው ነው። ሁሉም ሰው እኩል ሆኖ ነው የተወለደው፤ እያንዳንዱ ግለሰብ ቀድሞውኑ እንደነበረው ሁሉ የራሱ ሰውነት (ማንነት) ሉዓላዊ ገዢ ነው። ግር በሚያሰኝ፣ ነገር ግን ሆን ተብሎ በተደረገ ቋንቋ (አገላለጽ)፣ ጆን ሎክ እያንዳንዱ ሰው በሰውነቱ «ንብረት» ያለው መሆኑን ይናገራል። ይህንን መነሻ በማድረግ፣ ማንም ሰው በራሱ ፈቃድ (ስምምነት) ካልሆነ በቀር የሌላ ሰው፣ አልያም የማንኛውም ሕግ ተገዢ ሊሆን አይችልም የሚለው ይከተላል።

ጆን ሎክ በሁለተኛው ጥናታዊ ሥራው ምዕራፍ አራት ላይ እንዲህ ይላል፡-

“በህብረተሰብ ውስጥ የሰው ልጅ ነፃነት በጋራ ብልፅግናው (commonwealth) ውስጥ በስምምነት በተመሠረተው እንጂ በማንኛውም ሕግ የማውጣት ሥልጣን ቁጥጥር ስር አይደለም፤ እንዲሁም ሕግ አውጪው በተሰጠው ኃላፊነት ወይም እምነት አማካኝነት እንጂ በማንኛውም በሌላ አካል ፈቃድ ቁጥጥር ስር የሆነ ወይም በማንኛውም ሕግ የተገደበ አይደለም።”

ታዲያ በዚህ ዘመን የሚገኙትን መንግሥታት ሁኔታ ወይም በየትኛውም መጠን የተቀባይነት ደረጃቸውን የምንመለከተው እንዴት ነው?

ቶማስ ሆብስ እንዳደረገው ሁሉ፣ ጆን ሎክም የፖለቲካ ፅንሰ-ሐሳቡን ለመገንባት ያስችለው ዘንድ መንግሥት የሌለበት የህብረተሰብ እሳቤን (state of nature) ይጠቀማል። በሆብስ እንዳየነውም፣ በተወሰነ መልኩ አሻሚ የሆነ የቋንቋ አጠቃቀም ቢስተዋልበትም፣ ይህ የመንግሥት-አልባ ህብረተሰብ እሳቤ ታሪካዊ መሠረት ያለው አይደለም። አንድ ምክንያታዊ ወይም የሚያስተውል ሕዝብ ያለ መንግሥት እየኖረ ካለና፣ እንዲሁም ይህን መንግሥት የሚባለውን ለመመስረት በፈለገ ጊዜ ሊፈጥር የሚችለውን መንግሥት ከግምት በማስገባት ትክክለኛውን የመንግሥት አወቃቀር የመግለፅና ከሁሉም በላይ ደግሞ የፖለቲካዊ ግዴታ ፅንሰ-ሐሳብን የመቅረጽ ሙከራ ነው።

የሰው ፍጡራን ለተፈጥሮ ሕግ ብቻ ተገዢ የሆኑበት፣ ማኅበራዊ እንጂ ፖለቲካዊ ያልሆነ «ኦሪጅናል» ሁኔታን በምናባችን መሳል ይኖርብናል። እዚህ ላይ የተፈጥሮ ሕግ የተባለው፣ ከእግዚአብሔር የተሰጠና በሰው ልጆች አዕምሮ አማካኝነት የተገለጠ፣ እንዲሁም «ሁሉም እኩልና በራሳቸው መቆም የሚችሉ ወይም ነፃ የሆኑ መሆናቸው፣ ማንም ሰው በሌላ ሰው ህይወት፣ ነፃነት ወይም ይዞታዎች ላይ ጉዳት ማድረስ እንደማይገባው ሁሉንም የሰው ፍጡራን የሚያስተምር» ሕግ ነው። (ይህ የተፈጥር ሕግ ከመነሻው በውልደት የምናገኘው እሳቤ ወይም ‘innate idea’ ዓይነት መምሰሉና ሎክ ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ በማያሻማ መልኩ አለመሆኑን መካዱ ጠንካራ ችግር ሆኖ ተስተውሏል፤ ሆኖም ምንም መፍትሔ ያላቀረበበት ችግር ነው።) እናም ከዚህ በመነሳት ግለሰቦች ከዚህ ምሉዕ ሊባል የሚችል ነፃነት ከሰፈነበት ሁኔታ ወደ ፖለቲካዊ ህብረተሰብ ለምን እና እንዴት ሊሸጋገሩ እንደሚችሉ፣ እንዲሁም ይህን በማድረጋቸው ሊከሰቱ የሚችሉትን ሞራዊ እና ተግባራዊ ውጤቶች እንመለከታለን።

ጆን ሎክ የተፈጥሮ ሕግ የመኖር፣ የነፃነት እና ንብረት የመያዝ (የማፍራት) መብቶችን ለሰው ልጆች እንደሚያጎናፅፍ ያስቀምጣል፤ ነገር ግን ትኩረቱን የሳበውና በይበልጥም አድፍጦ የሰራበት ንብረት የመያዝ ተፈጥሯዊ መብት ላይ ነው። አግዚአብሔር ምድርንና ፍሬዎቿን በጋራ ይዞታነት ለሰው ልጆች ሰጠ። ሥራ የግል ንብረት ምንጭ እና ማረጋገጫ ሲሆን ለግል ንብረትም እሴት ይጨምራል። የግል ንብረት የሚፈጠረው (ሎክ የግል ንብረት ሲል የመሬት ባለቤትነት ማለቱ ነው) ግለሰቦች እግዚአብሔር በሰጠው ላይ «ጉልበታቸውን ሲቀላቅሉበት» ነው።

በሌላ አገላለጽ፣ ሥራ በመስራት በሰውነታቸው ወይም ሰው በመሆናቸው በነበራቸው ኦሪጅናል ንብረት ላይ ጉልበታቸውን ይቀላቅሉበታል። ንብረታቸውም የእነሱነታቸው ክፍል ይሆናል። ይህ ንብረትን የራስ የማድረግ ሂደት፣ ማንም የማንንም ሰው መብት እስካልጣሰ ድረስ በተፈጥሮ ሕግ መሠረት ተቀባይነት ወይም ሕጋዊነት አለው። ይህም ማለት፣ ማንም ሰው ለራሱ ከሚያስፈልገው መጠን በላይ አይወስድም፤ እንዲሁም ሌላ ሰው ሊጠቀምባቸው ይችል የነበሩ አንጡራ ሀብቶች እንዲባክኑ ማድረግ አይችልም። ስለዚህም የግል ንብረት የመያዝ መብት ያልተገደበ አይደለም። ንብረትን ማንም ሰው ጥቅም ላይ ሊያውለው ከሚችለውና ከበቂው በላይ፣ እንዲሁም ለሌሎች ሊተወው የሚገባውን መወሰድ አይችልም።

ይህ ቅድመ ሁኔታ ንብረት የመያዝን ተፈጥሯዊ ገደብ ያስቀምጣል፤ በተጨማሪም የእያንዳንዱ ሰው ፍላጐትና የመጠቀም አቅም በተወሰነ መልኩ ተመሳሳይ እንደመሆኑ፣ ማንኛውም ሰው ለእኔ ይገባኛል የሚለው የንብረት መጠን የሚታየው ወይም የሚሰላው በመርህ ደረጃ በተቀራራቢ እኩልነት (approximate equality) መመዘኛ ነው። ይሁንና ግን ይህ እኩልነት ገንዘብ የመገበያያ ዘዴ ሆኖ በተፈጠረ ጊዜ በተግባር ተገርስሷል። ገንዘብ፣ ማንኛውም ግለሰብ እርሱ ሊጠቀመው ከሚችለው በላይ የሆነ መሬት ባለቤት እንዲሆንና ከመሬቱም ትርፍ እንዲያገኝ፣ ብሎም የተወሰኑ ግለሰቦች አኗኗር (ህይወት) በምድር ፍሬዎች ላይ በቀጥታ የሚመረኮዝ ሳይሆን በሚያፈሱት ጉልበት በሚከፈላቸው የጥሬ ገንዘብ ክፍያ ላይ እንዲሆን መንገድ ይከፍታል። አሁንም በድጋሚ ይህ ዓይነቱ አሰራር የተፈጥሮ ሕግን አይጣረስም፤ እነዚያ ጉልበታቸውን የሚሸጡት ሰዎች ይህንን የሚያደርጉት በፈቃደኝነት በገቡት ውል መሠረት እስከሆነ ድረስ። በግለሰብ ደረጃ ሊያዝ የሚችለው መሬት ወሰን የለሽ ወይም የማያልቅ ባለመሆኑም፣ እንዲህ ያለው ስምምነት ላይ የተደረሰበት የግብይት ሥርዓት መከሰቱ የማይቀር ነው።

በፅንሰ-ሐሳብ ደረጃ፣ እነዚህ ሁሉ ኢካኖሚያዊ ሂደቶች በደመ-ነፍስ ወይም ሳይታቀዱ፣ ያለ መንግሥታዊ ጣልቃ-ገብነት ወይም ቁጥጥር ሊመጡ የሚችሉ ናቸው። መንግሥት የሌላቸው ሰብዓዊ ፍጡራን እርስ በርሳቸው ለሚኖራቸው ግንኙነት ምን ዓይነት እርምጃዎችን ይወስዳሉ የሚለውን በተመለከተ፣ የቶማስ ሆብስን ፀለምተኛ ምልከታ አይቀበልም። (በቶማስ ሆብስ የፖለቲካ እሳቤ መንግሥት የሌለበት ህብረተሰብ በሰው ልጅ የራስ ወዳድነት ባሕሪይ ምክንያት ለእርስ በርስ ግጭት እንደሚዳረግና ቀውስ እንደሚፈጠር ተገልጿል።) ከሆብስ በተቃራኒው፣ መንግሥት አልባውን ህብረተሰብ (state of nature) የሥልጣኔ በረከቶች እውን እንደማይሆኑበት መቻቻል-የለሽ ሁኔታ አድርጐ አይወክለውም። ሰዎች በፍርሃት ተነድተው ለአምባገነን መንግሥት በመገዛት ሊያመልጡት የሚሹት የጦርነት ዓለምም አይደለም። ሎክ በሚያስቀምጠው መንግሥት-አልባ ህብርተሰብ ውስጥ ሊኖር የሚችለው እንከን ወይም ጉዳት «ምቾት-የለሽ» ከመሆን የዘለለ (የባሰ) አይደለም።

“ማኅበራዊ ውል”

በርግጥ፣ በተለይ የንብረት ክፍፍል አለመመጣጠን ወይም እኩል አለመሆን እየጨመረ ሲመጣ፣ አለመግባባቶች ሊፈጠሩ መቻላቸው የማይቀር ነው፤ እንዲሁም በመንግሥት-አልባው ህብረተሰብ እንዲህ ያሉ ልዩነቶችን ለመፍታታ ስምምነት ላይ የተደረሰበት እና አስተማማኝ የሆነ መንገድ አይኖርም። እናም ሰዎች ለራሳቸው ጉዳይ እራሳቸው ዳኞች ሆነው አግባብ ባለፈ መልኩ ለመብቶቻቸው ዘብ የቆሙ ይሆናሉ፤ መብቶቻቸውንም በሚጥሱባቸው ላይ ከመጠን ያለፈ ቅጣት ወደመጣል ያመራሉ። እነዚህን ምቹ ያልሆኑ (አስቸጋሪ) ሁኔታች በመገንዘብም፣ ግለሰቦች አንዱ የሌላውን መብቶች ለማስጠበቅ ዓላማ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ይስማማሉ። በአጭሩ፣ “ማኅበራዊ ውል” ወይም «Social Contract» ይኖራል።

ጆን ሎክ እንዲህ ያለው «ማኅበራዊ ውል» የእያንዳንዱን ተዋዋይ ፈቃደኝነት ወይም ስምምነት ይጠይቃል ይላል። ማኅበረሰቡ አንድ ጊዜ ከተመሠረተ የራሱ ሕግ አውጪ እና ሌሎች ተቋማትን ወደመፍጠር ያመራል፤ ምንም እንኳን ጆን ሎክ ይህን ለማድረግ የአብላጫው መስማማት በቂ ነው ብሎ ቢያስብም። እነዚህ ተቋማት በተሰበሰበ ግብር መደጐም ያስፈልጋቸዋል። ነገር ግን ግብር አሰባሰቡ በንብረት ባለቤቶች ስምምነት ላይ መሠረት ያደረገ ሊሆን ይገባዋል፤ ባለንብረቶቹ ስምምነታቸውን የሚሰጡት በግለሰብ ደረጃ ወይም የተሰወኑትን በወከሉበት ጉባኤ ሊሆን ይችላል። ይህ የግብር አሰባሰብ መስፈርት ያስፈለገበት ምክንያት ከመነሻው መንግሥት የመመስረቱ ዓላማ ንብረት የመያዝና ሌሎች መብቶችን ለማስከበር እስከሆነ ድረስ፣ መንግሥት የንብረቱ ባለቤቶች ስምምነታቸውን ሳይሰጡ ንብረታቸውን እንዳያሳጣቸው ወይም ወደሌሎች እንዳያከፋፍልባቸው በሚል ነው። የሎክ ገለፃ ሙሉ ለሙሉ ግልጥ ያለ ነው ባይባል እንኳን፣ «ማኅበራዊ ውል» ሦስት ደረጃዎች ያሉት ይመስላል፡- በተዋዋዮቹ አማካኝነት የአንድ ማኅበረሰብ መመስረት፤ የመንግሥታዊ ተቋማት መቋቋም፤ እና ግብር እንዲጣል መፍቀድ።

ሕግ አስፈፃሚ የመንግሥት ተቋማት ለሕግ የበላይነት ተገዢ ይሆናሉ። መለኮታዊ ሥልጣንን ከሚቃወም ሰው የሚጠበቅ እንደመሆኑ፣ ይህ ነጥብ ለጆን ሎክ በጣም አስፈላጊ ነው። የመንግሥት እንቅስቃሴ የሚመራው በትዕዛዝ ወይም በልዩ ሥልጣን ሳይሆን ተወስነው በተቀመጡና በሚታወቁ የሕግ እና የሥነ-ሥርዓት መመዘኛዎች ሊሆን ይገባል። ይሁንና ሎክ በተወሰነ መጠን ትዕዛዛዊ ሥልጣንን ይፈቅዳል፤ ነገር ግን ይህ ሥልጣን ተግባራዊ የሚሆነው ልዩ ሁኔታዎች በሚፈጠሩ ጊዜና በግልጽ ለሚታይ ሕዝባዊ ጥቅም ሲባል ብቻ ነው። በተጨማሪም ሎክ የተለያዩ የመንግሥት ተግባራት በተለያዩ እጆች ስር ቢሆኑ የተሻለ እንደሚሆን ያስባል፤ እንዲሁም ሕግ አስፈፀሚው አካል የሕግ አውጪው የበታች መሆን እንዳለበትም ይጠቁማል። ሆኖም «Separation of Power» ወይም በመንግሥት አካላት መካከል ያለ «የሥልጣን ክፍፍል» የሚባለውን መርህ በዝርዝር አላብራራም፤ መርሆውንም በተደጋጋሚ ሲጠቀምበት አይታይም። ስለዚህም አንዳንድ ፀሐፊዎች እንደሚሉት የዚህ አስተምህሮ ጠንሳሽ ነው መባሉ በተወሰነ መልኩ የተጋነነ ይመስላል።

ጆን ሎክ፣ የማኅበራዊ ውል ተዋዋዮቹን ስምምነት ፖለቲካዊ ግዴታዎችን የማስቀመጫ መሠረታዊ መንገድ ማድረጉ ጥያቄ የሚያስነሳበት ይሆናል። የእርሱ መከራከሪያ ዋና ነጥብ ማንም ሰው በተፈጥሮው ለመንግሥት ተገዢ ባለመሆኑ ምክንያት፣ የአንድ መንግሥት ሕጋዊነት ወይም ተቀባይነት ማግኘት በእያንዳንዱ ግለሰብ «ለመገዛት» ፈቀደኛ መሆን ላይ ይመረኮዛል የሚለው ነው። ይሁንና ግን፣ እንዲህ ያለው ፈቃደኝነት በምን ዓይነት መንገድ ነው በተግባር ሊከናወን የሚችለው? ፈቃደኝነት ወይም ስምምነት የሚሰጠው እንዴት እና መቼ ነው? ይህ ሁሉም ዓይነት ሥልጣንን በፈቃድ (Consent) የማስተላለፍ ፅንሰ-ሐሳቦች ላይ መከሰቱ የማይቀር ስንክሳር ነው። አብዛኛው ሕዝብ በአንድ አካል ለመገዛት በቀጥታ ወይም በራሱ ፍላጐት ፈቃዱን ስለመስጠቱ በግልፅ የሚታወቅበት መንገድ ያለመኖሩ እውነታ፣ ሎክ ማስገንዘብ ለሚፈልገው ዓይነት መከራከሪያ አስቸጋሪ መሰናክል ነው። ሆኖም ይህንን ችግር ለመፍታት፣ ጆን ሎክ በይፋ ያልተገለፀ ፈቃድን ወይም መስማማትን (Tacit Consent) ይጠቅሳል።

እንደሱ አባባል፣ ቀጥተኛ ወይም በይፋ የተገለፀ ስምምነት የግድ አስፈላጊ አይደለም። በመንግሥት ጥበቃ ስር ሆኖ ንብረቱን የሚጠቀም ወይም በንብረቱ የሚያዝ (ማዘዝ የሚችል)፣ አልያም ደግሞ በመንግሥት የሚደረጉ ጥበቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን (ይህም ማለት «ሌላው ቢቀር በአውራ ጐዳናው ላይ በነፃነት መጓዝ» ማለት ቢሆንም) እንኳን – በነፃ የሚጠቀም ማንኛውም ሰው በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ ወይም በይፋ ባልገለፀው መንገድ ለመንግሥት ሥልጣን ፈቃዱን እንደሰጠ ይቆጠራል። በአጭሩ ሲቀመጥ፣ በዚያ ቦታ ተገኝተን በመኖራችን ብቻ ስምምነታችንን ሰጥተናል። የዚህ ዓይነት ስምምነት ደካማ ጐን በዴቪድ ሂዩም ሲነቀስ እንመለከታለን።

ጆን ሎክ እና አመፅ

የጆን ሎክ የፖለቲካ ፅንሰ-ሐሳብ ከሁሉም በላይ የአመፅ (resistance) ፅንሰ-ሐሳብ ነው። ሰዎች መንግሥትን የመሠረቱት፣ በመንግሥት-አልባው ዓለም (State of Nature) የማይቻል በነበረው የመተማመን እና የእኩልነት መንፈስ ተፈጥሯዊ መብቶቻቸውን ለማስጠበቅና የተፈጥሮን ሕግ ለማረጋገጥ ነው። ይሁንና ግን መንግሥት የተፈጥሮ ሕግን አይተካም፣ እንዲሁም የተፈጥሮ ሕግ ያጎናፀፋቸውን መብቶች መጣስ ወይም ችላ ማለት አይችልም። መንግሥት የታማኝነት ወይም የባላደራነት ተፈጥሮ አለው። ስለመብቶቻችን መጠበቅ እምነት ወይም አደራ እንጥልበታለን፤ ነገር ግን እነዚያን መብቶች ለእርሱ አሳልፈን አንሰጠውም። ስለዚህም ተፈጥሯዊ መብቶችን የሚጥስ መንግሥት እምነቱን እንዳፈረሰ ወይም አደራውን እንደበላ ነው፤ እናም ሕዝቦቹ እርሱን በመቃወም – አስፈላጊ ከሆነ በኃይልም – መብቶቻቸውን እና ነፃነቶቻቸውን የማስከበር መብት አላቸው። ጥሰቱ ከፍተኛ መጠን ያለው በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ሕዝቡ አብዮት የማስነሳት መብት አለው፤ ይህም ማለት መጀመሪያ ለመንግሥት ተሰጥቶ የነበረውን ሥልጣን መልሶ መንጠቅ ማለት ነው።

አብዮት፣ የጨቋኝ መንግሥት ሰለባ ሆነናል የሚሉ ሕዝቦች ፍርድ ይሰጣቸው ዘንድ ወደ ገነት የሚጠይቁት የይግባኝ ዓይነት እንደሆነ ሎክ ያስባል። አብዮቱ ስኬታማ ከሆነ – መለኮታዊው ፍርድ ለሕዝቡ ከተፈረደ – ሉዓላዊነት ሰዎችን ከመንግሥት-አልባው ዓለም ባወጣቸው የቀደመ ስምምነት (በማኅበራዊ ውል) ወደተመሠረተው ማኅበረሰብ ይቀለበሳል፤ ከዚያም የፖለቲካ ተቋማትን የመፍጠሩ ሂደት በድጋሚ ይጀመራል።

“በዚህ እና መሰል ምክንያቶች መንግሥት ከተወገደ ሕዝቦች በውስጡ ባሉት ሰዎችም ሆነ በዓይነቱ ወይም በሁለቱም የሚለይ አዲስ የሕግ አውጪ አካል ለደህንነታቸው እና ለጥቅማቸው ተስማሚ በሆነ መልኩ የማቋቋም ነፃነት አላቸው።”

አንድ ሕዝብ ሥልጣንን ከመንግሥት ላይ በተመቸው ጊዜ በቀላሉ መግፈፍ መቻሉ፣ መንግሥት ባለመኖሩ ምክንያት የሚከሰት የሥርዓት-አልበኝነት ሁኔታ (Anarchy) መገለጫ አይደለምን? ለዚህ ተቃውሞ፣ ጆን ሎክ ሁለት ምላሾች አሉት። በመጀመሪያ ደረጃ፣ መንግሥታት በዜጎቻቸው ላይ ለሚያደርሱት ለእያንዳንዱ እፍኝ ለማይሞላ በደል መገልበጥ አለባቸው የሚል አመለካከት የለውም። ጨቋኝ መንግሥታት (Tyrants)፣ በድርጊታቸው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ተጐጂ ካልሆነ በቀር አይታመፅባቸውም። ሁለተኛ፣ ጨቋኝ የሆነ መንግሥት እራሱን በራሱ የሚጥልበት ወይም የሚያስወግድበት ሁኔታ አለ፤ ቀድሞውኑ ህልውናውን የሚያረጋግጡለትን ብቸኛ ተግባራት ወይም ኃላፊነቶች ባለመፈፀሙ።

«ሕግ አውጪዎች የሕዝቡን ንብረት ለመቀማት ወይም ለማውደም፣ አልያም በማንአለብኝነት ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ሕዝቡን ወደ ባሪያነት ለማውረድ በሚተጉበት ጊዜ፣ እራሳቸውን ከሕዝቡ ጋር ጦርነት ከፍተው ያገኙታል ሕዝቡም ማንኛውንም ተጨማሪ ትዕዛዝ ከማክበር እራሱን ነፃ በማውጣት እግዚአብሔር ኃይል እና ብጥብጥ ለሚጠሉ ሰዎች ወዳዘጋጀው የጋራ መጠለያ ያቀናሉ፡አመፅ (Resistance)።»

ጆን ሎክ ስለሃይማኖት

ጆን ሎክ በሃይማኖታዊ መቻቻል ጥያቄ ላይም ትኩረት አድርጓል፤ በርግጥም በመላ ሕይወቱ አነጋጋሪ የነበረ ጥያቄ ነው። መቻቻል ላይ የሚያውጠነጥን ሥራውን (Essay on Toleration) ገና በ1667 አቅርቧል፤ በኋላም ሦስት ደብዳቤያዊ ፅሁፎቹን አሳትሟል (በ1689፣ በ1690፣ በ1692፤ ከሞተ በኋላ አራተኛ ደብዳቤው ታትሟል)።

ሎክ፣ የሃይማኖት ነፃነትን በተመለከተ ሦስት ጭብጦችን ያስቀምጣል። አንደኛ፣ ጠላትነት እና የሃይማኖት አለመቻቻል ከወንጌል መንፈስ ጋር የሚጋጩ ወይም የሚቃረኑ ናቸው። ሁለተኛ፣ የመንግሥት ሥራ ወይ ኃላፊነት ሕዝቡን እና ውጫዊውን ሥርዓት ብቻ መጠበቅ ነው። እርሱ እንደሚለው፣ የሕግ ሚና የሕዝቦችን አመለካከቶች (አስተያየቶች) መቆጣጠር ሳይሆን ለጋራ ብልፅግናው (Commonwealth) ደህንነት እና ምቹ ሁኔታን ማቅረብ ነው። ሃይማኖታዊ ተግባራት እና እምነት የግል ጉዳዮች ናቸው፡- ሃይኖታዊ ትግበራ (አምልኮ)፣ የሚተገብረውን ግለሰብ እንጂ ማንንም የሚነካ አይደለም። ስለዚህም የመንግሥት ኃላፊዎች በማንኛውም የሃይማኖት ጉዳይ ማንንም ሰው ከኅሊናው በተቃራኒ ይሰራ ዘንድ የመጠየቅ መብት የላቸውም።

ሦስተኛ፣ ሃይማኖታዊ እምነት (faith) በየትኛውም መልኩ አምኖ የመቀበል (belief) ጉዳይ ነው፤ አምኖ መቀበል (belief) ደግሞ ከፈቃድ የሚመነጭ ድርጊት አይደለም (እዚህ ላይ ይህን አድርግ ሲባል እሺ ብሎ ፈቃዱን የሚሰጥበት ድርጊት አይደለም ለማለት ነው)። ስለዚህ የመንግሥት ኃላፊዎች ማስገደድ የሚችሉት ፈቃድን ብቻ እንደመሆኑ፣ ሃይማኖታዊ አምኖ መቀበልን (belief) በግዴታ ተግባራዊ ለማድግ መሞከር ምክንያት-የለሽ እና ውጤት-አልባ ነው። ይህ ሦስተኛው የሎክ መከራከሪያ፣ የመንግሥትን ሥልጣን የያዙ ወገኖች ተግባራዊ ለማድረግ የሚሞክሩት የሃይማኖት ተከታይነትን እንጂ ሃይማኖታዊ እምነትን ባለመሆኑ ነጥቡን የሳተ ይመስላል፤ ይሁንና ግን የሎክ መከራከሪያች በአጠቃላይ በብዙ መንገዶች የጄ.ኤስ. ሚል እሳቤዎችን የሚያስታውሱ የሊበራል እሳቤዎች ናቸው።

“The Reasonableness of Christianity” ሥራው እንደሚያመለክተው፣ ሎክ ክርስትናን ውስብስብ እና የገነነ መዋቅር ያለው አስተምህሮ አድርጎ አይረዳውም። የክርስትና እምነት ዝቅተኛዎቹ መሠረታዊ መመዘኛዎች በእግዚአብሔር ከማመን እና ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ከማመን የበለጡ አይደሉም። ስለዚህም በተገንጣይ ሃይማኖቶች መካከልም ሆነ ከአንገሊካን ሃይማኖት ጋር የሚያለያያቸውን ሥነ-መለኮታዊ ልዩነት ችላ ለማለት አልከበደውም። ያም ሆኖ እንደሱ ሐሳብ፣ ሃይማኖታዊ መቻቻል ሲባል የሮማ ካቶሊኮችን እና ኢ-አማኞችን (atheists) አይጨምርም። ለዚህም ምክንያቱም ከሃይማኖታዊ ነጥብ ሳይሆን፣ የሮማ ካቶሊኮች ለውጭ ኃይል ጥሩ አመለካከት የሌላቸው በመሆኑ፤ እንዲሁም ኢ-አማኞች፣ የሞራል ኃላፊነቶች መሠረት በሆነው በእግዚአብሔር ስለማያምኑ ኃላፊነቶችን በማክበር ረገድ እምነት የሚጣልባቸው ባለመሆናቸው ነው።

ጆን ሎክ – ምናልባትም ከቶማስ ሆብስ ጋር በጥምረት – ከሁሉም የእንግሊዝ የፖለቲካ ፅንሰ-ሐሳብ አፍላቂዎች በላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳደረ ነው። ፖለቲካዊ ጽሁፎቹ፣ እንደ ሁሉም የፖለቲካ ጽሁፎች በአንድ በተወሰነ ጊዜ እና ቦታ ለተፈጠሩ ጉዳዮች እና ክስተቶች የተሰጡ ምላሾች ሲሆኑ፣ የእነዚያን ጉዳዮች እና ክስተቶች ልዩ እይታን ያንፀባርቃሉ። ከ1603-1714 ኢንግላንድን የገዙ ንጉሦች (Stuart Kings) ያሰረፁትን ርዕዮተ-ዓለም በጽኑ የሚቃወም ነው። አከራካሪ ቢሆንም፣ እርሱ የሚከራከርላቸው ሁል-አቀፍነታቸው በግልፅ የሚታይ መርሆዎች እና እሴቶች የመጤው ካፒታሊስት መደብ ፍላጎትና ዓላማች ከመሆን አይዘሉም። ይህ ምልከታም ሲ.ቢ. ማክፈርሰን በታዋቂው «The Political Theory of Possessive Individualism» መፅሐፉ አሳማኝ በሆነ መልኩ ያስቀመጠው ነው።

ያም ሆነ ይህ፣ የሎክ የፖለቲካ እሳቤ ጊዜ የማይሽረው ጠቀሜታን ያዘለ ስለመሆኑ በአያሌ የሊበራል ትውልዶች ሲተዋወቅ የኖረ ነው። እሳቤዎቹ በአሜሪካ ሕገ-መንግሥት እና በፈረንሳይ አብዮተኞች ላይ ያሳደሩት ተፅዕኖ ግልፅ ሆኖ ሳለ፣ በሃያኛው ክፍለ ዘመንም ሊበራል የፖለቲካ ጠበብቶች – ሮበርት ኖዚክ ቀዳሚው ተጠቃሽ ነው – ንብረትን በሚመለከተው ፅንሰ-ሐሳቡ ተፅዕኖ ስር መሆናቸውን ቀጥለውበት ነበር።

ለበለጠ ንባብ

ቀዳሚ ምንጮች

A Letter Concerning Toleration, ed. R. Klibansky and J.W. Gough (Oxford: Clarendon Press, 1968).

Two Treatises of Government, ed. P. Laslett (Cambridge: Cambridge University Press, 1988).

Essays on the Law of Nature, ed. W.M. von Leyden (Oxford: Clarendon Press, 2002).

ተቀፅላ ምንጮች

Cranston, M.: John Locke: a Biography (London: Longman, 1957).

Dunn, J.: The Political Thought of John Locke (Cambridge: Cambridge University Press, 1969).

Gough, J.W.: John Locke’s Political Philosophy (Oxford: Clarendon Press, 1973). Hampsher-Monk, I.: A History of Modern Political Thought (Oxford: Blackwell, 1992).

Macpherson, C.B.: The Political Theory of Possessive Individualism (Oxford: Oxford University Press, 1962).

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.