«የሥልጣን ክፍፍል (Separation of Power) የሁሉም ሕዝቦች ነፃነት ዋስትና ነው» ሞንተስኪው (1689-1755)
ሞንተስኪው ላ ቤርዴ፣ ፈረንሳይ ውስጥ ነው የተወለደው። ከ1700 እስከ 1705 ድረስ በጁውሊ ኮሌጅ ከተማረ በኋላ በቦርዴክስ ዩኒቨርሲቲ ሕግ አጥንቷል። የጽሁፍ ሥራዎቹን በተመለከተ ዝናውን መገንባት የጀመረው በ1721 “LettresPersanes” ወይም “የፐርሺያ ደብዳቤዎች” የተሰኘው ሥራው ከታተመ በኋላ ነው። ይህ ሥራው ግራ በተጋቡ ሁለት የፐርሺያ ተጓዦች የተፃፉ ደብዳቤዎች ተደርጐ በተዘጋጀ መልኩ በፈረንሳያውያን ህይወት፣ ባሕል እና የፖለቲካ ተቋማት ላይ የሚያውጠነጥን ሽሙጣዊ (Satire) ጽሁፍ ነው። ሞንተስኪው ከ1728 እስከ 1731 ያሉትን ጊዜያት በአውሮፓ ውስጥ በመጓጓዝ አሳልፏል። በኢንግላንድም ለአጭር ጊዜ የኖረ ሲሆን፣ የእንግሊዞችን ህይወትና ፖለቲካ መመልከቱ ጥልቅ ስሜት አሳድሮበታል።
በ1734 ሞንተስኪው “The Causes of the Greatness and Decline of the Romans” (የሮማዊያን ታላቅነት እና ውድቀት መንስኤዎች) የተሰኘ መፅሐፉን አሳትሟል። የዚህ ሥራው ከፊል ዓላማም የጥንታዊቷ ሮም ታሪክ የሮማዊያንን አኗኗር እና ድርጊቶች የቀረፁት ውጫዊ ሁኔታዎች ውጤት የመሆኑን ጉዳይ አፅንኦት ለመስጠት ነው። ይህ ለውጫዊ ሁኔታዎች የተሰጠው አፅንኦት፣ ሞንተስኪው ይበልጥ በሚታወስበት “The Spirit of the Laws (1748)” በተሰኘ ሥራው ውስጥ ከሰፈሩ ወሳኝ ጭብጦች ውስጥ የአንድኛው ጠቋሚ ወይም አመላካች ነው።
“The Spirit of the Laws” የተሰኘው ሥራውን ማንበብ እጅግ አስቸጋሪ ነው። በጣም ረጅም ከመሆኑ ባሻገር በግልፅ የሚታይ የቅርፅ እና የተያያዥነት ችግር ይስተዋልበታል። ያልተለመደ የሥነ-ጽሁፍ አቀራረቡ በተወሰነ መጠን ብቻ ቢሆንም ሆን ተብሎ የተደረገ ነው። ሞንተስኪው ግልጥ ባላለ መልኩ የፃፈው፣ በከፊል ነገሮችን በቀላሉ የሚመለከቱ አንባቢያን ምናልባትም የሚያሳስቡ ሊሆኑ በሚችሉት አስተምህሮዎቹ እንዳይጐዱ ለመከላከል፣ በከፊል እርሱ ባስቀመጣቸው ትርጉሞች ላይ አንባቢዎች የራሳቸውን ምርምር እንዲያደርጉ ለመፈተን፣ እንዲሁም በከፊል ደግሞ ቅድመ-ምርመራን (Censorship) ለማስወገድ ነው። (ቅድመ-ምርመራ ለሚባለው ነገር ከፍተኛ ስጋት ነበረው፤ ሦስቱም ዋና ዋና ሥራዎቹ በመጀመሪያ የታተሙት ከሀገር ውጭና ማንነቱ ሳይገለፅ ነበር።) እናም በዚህ ያልተለመደ በሆነ አፃፃፉ ምክንያት “The Spirit of the Laws” የተሰኘ ሥራውን ያለእንከን ለመዳሰስ ቀላል አይሆንም። በዚህ ጽሁፍም ይህ ልብ ሊባል ይገባዋል።
ህዋ (Universe)፣ እኛ ሕጐች ብለን የምንጠራቸውን የአወቃቀር ዓይነቶች እንደ የተፈጥሮው አንድ ክፍል አድርጐ እንደሚያቀርባቸው ሞንተስኪው ይገነዘባል። ከዚህ አንፃርም ሕጐች ከነገሮች ምንነት (ተፈጥሮ) የሚመነጩ አስፈላጊ ግንኙነቶች ወይም መስተጋብሮች ናቸው። ፈጣሪ እንኳን ፈጠራዊ ተግባሮችን በሚያስችሉ ‘ሕጐች’ – አስፈላጊ (መሠረታዊ) ሁኔታዎች – የተከበበ ነው። እነዚያ ከሰው ልጅ ባሕሪይ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የህዋ ሕግ ክፍሎች «የተፈጥሮ ሕጐች» ይባላሉ። የተፈጥሮ ሕጐች ከለላን በመስጠት ረገድ ከሰው ልጅ መሠረታዊ የመኖር ህልውና ስኬታማነት ጋር ይዛመዳሉ፤ ነገር ግን ደመ-ነፍሳዊ ዓይነት ብቻ አይደሉም። ምን ማድረግ የሚገባንን ይጠቁሙናል፤ እንዲሁም የእነሱ ጥቆማ በሰው ልጅ ሕሊና (የማሰብ ብቃት) አማካኝነት የሚገኝ ወይም የሚደረስበት ነው።
ይሁንና ግን – ሞንተስኪው ይቀጥላል – ሰዎች ብቸኛ የሆኑና በፍርሃት የተከበቡ ናቸው፣ እናም የማሰብ ብቃታቸው የዳበረው በጣም በዝቅተኛ መጠን ብቻ ነው። ሕሊናን ለማሰራትና የማሰብ ብቃትን ለማጥራት የሆነ ግፊት ወይም ቀስቃሽ (Stimulus) አስፈላጊ ነው። ማኅበራዊነት የሚጎለብተው ከሌሎች ከመሰሎቻቸው ጋር ከሚኖሩት ህይወት እርካታዎችንና ጥቅሞችን ማግኘት ወይም መታዘብ በሚጀምሩ ጊዜ ነው። ሆኖም ሰዎች አንዱ ሌላውን የመበዝበዝ ተፈጥሯዊ አዝማሚያቸውን በሚመለከቱ ጊዜ፣ የማኅበራዊነት መጐልበት ግጭትና አለመግባባትን ይወልዳል። ልክ እንደ ቶማስ ሆብስ ሁሉ፣ ለሞተስኪውም መንግሥት የሌለበት የሰው ልጆች አኗኗር (State of Nature) የስቃይ እና የብጥብጥ ይሆናል። ከዚያም እስከዚያን ጊዜ ድረስ ባለበት ቆሞ የነበረው የሰው ልጅ የማሰብ ብቃት፣ ሰላምና ፀጥታን ማስፈን የሚያስችሉትን ሰብዓዊ ሕጐች (Positive Laws) መፍጠርና ማስፈፀም አስፈላጊ ስለመሆኑ እንዲህ ባለው ብጥብጥ ቀስቃሽ ሁኔታ አማካኝነት እንዲማር (እንዲገነዘብ) ያደርገዋል። እጅግ መሠረታዊ በሆነ የማብራራት ደረጃ፣ መንግሥት ለመመስረት (ለመፈጠር) የሚበቃበት መንገድ ይህ ነው። የሞንተስኪው የመከራከሪያ ሐሳብ የሩሶ እና የሆብስ ሀሳብ ሲደባለቅ ዓይነት ነው፤ እንዲሁም ሕግ ላይ ያለው ምልከታ በቅዱስ ቶማስ አኩዊናስ ላይ የተመሠረተ ዓይነት ነው።
ስለዚህም እንደጥቅል ሁኔታ ስንመለከተው፣ መንግሥት የተፈጠረው አብሮነትን በተላበሰ የሰው ልጅ እና በፍላጐቶቹ አማካኝነት ነው፤ ነገር ግን አንድ መንግሥት እራሱን የሚገልፅባቸው እያንዳንዱ ሁኔታዎች የተለያዩ ናቸው። ይህ ልዩነት የመነጨው ሰብዓዊ ፍላጐቶች የሚገለፁትና የሚሟሉት የተለያዩ ሁኔታዎችን መሠረት በማድረግ በተለያዩ ሕዝቦች እና በተለያዩ መንገዶች ከመሆኑ እውነታ ነው። መንግሥት እና ሕግ የሚኖራቸው ቅርፅ እና ይዘት በእያንዳንዱ ሀገር ባለው አጠቃላይ መንፈስ ላይ የሚመረኮዝ ሲሆን፣ ይህ መንፈስ እራሱ ደግሞ በተለያዩ መንስኤዎች ወይም ምክንያቶች ይወሰናል፤ ለምሳሌም – የአየር ጠባይ፣ የቆዳ ስፋት፣ ታሪክ፣ የካርታ አቀማመጥ፣ ሃይማኖት፣ እና የመሳሰሉት። አካላዊ፣ አካባቢያዊ እና ባሕላዊ መንስኤዎች የአንድን ሕብረተሰብ ፀባይ መወሰናቸውን በተመለከተ ሞንተስኪው አፅንኦት መስጠቱ የፖለቲካ ሥነ-ሕብረተሰብን (Political Sociology) በመፃፍ ረገድ ቀደምት ሙከራ ነው። ይሁንና ግን የተለያዩ ሁኔታዎች የተለያዩ የመንግሥት ሥርዓቶችን ሊፈጥሩ ስለመቻላቸው ሞንተስኪዊ ያነሳው ሐሳብ አርስቶትል በቀዳሚነት ያቀረበውን ትንታኔ ተከትሎ ከመሄድ የዘለለ አይደለም።
ሞንተስኪው፣ በአካባቢያዊ ተፅዕኖዎች ሊቀየሩ የሚችሉ ቢሆኑም ሦስት ዋና ዋና የመንግሥት ዓይነቶችን ይዘረዝራል፡- ዴስፖቲዝም (despotism)፣ ሪፐብሊክ (republic) እና ሞናርኪ (monarchy)። በእያንዳንዱ የመንግሥት ዓይነት ላይ እርሱ «ተፈጥሮ» እና «መርህ» በማለት የሚጠራቸው ንጥረ ነገሮች አሉ። የመንግሥት «ተፈጥሮ» ሉዓላዊው ሥልጣን በተሰየመበት ይወሰናል፤ የመንግሥት «መርህ» (ያለ መርህ መንግሥት ስኬታማ ሆኖ መስራት አይቻለውም) ተስማሚ የሆነ አወቃቀር ወይም በተገዢዎቹ ዘንድ ያለ አመለካከት ነው።
ይህንን መሠረት በማድረግም፣ ዴስፖቲዝም በመንግሥትነት «ተፈጥሮው» በአንድ ሰው የሚመራ አግባብ-የለሽና ፍፁማዊ ሥልጣን የሰፈነበት መንግሥት ነው። ሕግ የሚባል ነገር የሌለበት የተለየ መንግሥት ነው። የዴስፖቲዝም «መርህ» የተገዢዎች ፍርሃት ወይም አንገት መድፋት ነው። በሌላ በኩል የሪፐብሊክ መንግሥት የአሪስቶክራሲ እና የዴሞክራሲ ድብልቅ ወይም ቅይጥ ሲሆን ከዜጐቹ ከፍተኛ የሞራል መመዘኛ ወይም የሕዝባዊ መንፈስ ጠንካራ ስሜትን ይጠይቃል፤ ይህም ዜጐቹ ግላዊ ጥቅምን ከሕዝባዊ ጥቅም በታች እንዲያደርጉት ያበረታታቸዋል። ሞንተስኪው ሪፐብሊክን ያደንቃል፤ ነገር ግን ከራስ በላይ ሕዝባዊ ጥቅምን የማስቀደም መመዘኛዎች ብዙውን ጊዜ የሚሟሉት የዜጐችን ግለሰባዊነት ችላ የሚያስብሉ ግትር ምግባሮችን ተቋማዊ በማድረግ መሆኑን ይጠቁማል። እርሱ እንደሚለው፣ ከፍተኛ የሞራል መመዘኛዎች የተዘረጉበት ሪፐብሊክ ልክ እንደገዳም ህይወት ነው።
ሞንተስኪው በሦስተኝነት ያስቀመጠው የመንግሥት ዓይነት ሞናርኪ (ዘውዳዊ ሥርዓት) ነው። ሞናርኪ፣ በአንድ ሰው የሚመራ ግን ደግሞ ፓርላማዎች፣ የከተማ መስተዳድሮች፣ መኳንንቶች እና የሃይማኖት አባቶች በመሳሰሉት «አማካይ ኃይሎች» በሚሰነዘር የተቃርኖ መልስ ምት የሚቃና መንግሥት ነው። በሞንተስኪው ሐሳብ፣ በክብር እና በዝና እሴቶች ላይ መሠረት ያደርጋል፤ ይህም በዋናነት በማኅበረሰቡ ዘንድ የከፍተኛ ደረጃ ወይም የተከባሪነት ጠንካራ ስሜትን፣ በተለይም ለወታደራዊ ጀብዱ የሚሰጥ ቦታን ማለቱ ይመስላል። አሁንም በድጋሚ ሞንተስኪው፣ በአርስቶትል የመንግሥታዊ ሥርዓቶች እና ዓይነታቸው አገላለጽ ላይ መመርኮዙ ግልፅ ነው።
ሞንተስኪው፣ ነባራዊ ግብ በማይሰጣቸው የፖለቲካ ሥርዓቶች ትንታኔዎች ላይ እንዳተኮረ ቢያምንም፣ በተግባር ግን ትንታኔዎቹን በእርሱ ዘመን ከነበረው የፈረንሳይ የፖለቲካ ችግሮች ትዝብቱ መነጠል አልተቻለውም። ፈረንሳይ የሞናሪኪ ሥርዓት ሊኖራት እንደሚገባ ያስባል፤ በሪቸሊዩ እና በሉዊ 14ኛ የማዕከላዋነትን አዝማሚያ ዘመን ስር በነበረችበት ወቅት ወደ ዴስፖቲዝም መጥታ እንደነበር ያስባል።
ታዲያ ከነፃነት ጋር ይበልጥ የሚጣጣመው የመንግሥት ሥርዓት ዓይነት የትኛው ነው፤ ማለትም፣ ግለሰቦች ያለማንም ጣልቃ-ገብ ህይወታቸውን እንዲመሩና ንብረታቸውንም በሰላም እንዲጠቀሙበት ይበልጥ የሚያስችላቸው ሕገመንግሥታዊ አወቃቀር የትኛው ነው? እናም የዚህ ጥያቄ ምላሽ ሞናርኪ ወይም ዘውዳዊ ሥርዓት እንደሆነ ሞንተስኪው ያስባል፤ በተለይም በኢንግላንድ የታዘበው ዓይነት ዘውዳዊ መንግሥት።
ስለ እንግሊዝ መንግሥታዊ ሥርዓት ያቀረበው ታዋቂ ማብራሪያ “The Spirit of the Laws” በተሰኘው መጽሐፍ ክፍል 11 ላይ የሰፈረ ነው። የጥንቶቹ የፊውዳል ሞናርኪዎች በውስጣቸው መረጋጋትን የሚያሰፍኑት በንጉሡ፣ በመኳንንቱ እና በሃይማኖት መሪዎቹ መካከል በተከፋፈለ የኃይል ሚዛን ነበር። በእርሱ ዘመኗ ኢንግላንድ ይህ የኃይል ሚዛን በመደበኛው «የሥልጣኖች ክፍፍል» ወይም «Separation of Powers» በሚባለው መርህ እራሱን ይገልፃል። ሕግ የማውጣት፣ የመተርጐም እና የማስፈፀም ተግባራት በተለያዩ እጆች ስር ናቸው፤ እንዲሁም እነዚህ ተግባራት ተፈፃሚ የሚሆኑባቸው የተለያዩ መንገዶች አንዱ ሌላውን በሚቆጣጠርበት (checks and Balances) መልኩ ይከናወናሉ። ስለዚህም ሥልጣን በአንድ አካል ስር ብቻ ሊጠራቀም አይችልም፣ ዴስፖቲዝም ሊፈጠር አይችልም፣ እንዲሁም የሁሉም ሕዝብ ነፃነት ስለመጠበቁ ዋስትና ተሰጥቷል።
ሞንተስኪው፣ እንግሊዞች ለንግድ የሰጡት ትኩረትም የተሻለ ደረጃ ላይ የማድረስ ተፅዕኖ እንዳለው ያስባል። ንግድ ከብልፅግና ቁሳዊ ጥቅሞቹ ባሻገር አመለካከትንም ያሰፋል፤ ጉዳት የሚያስከትሉ ሃይማኖታዊ እና ብሔራዊ ልዩነቶችን የመፍታት እድል አለው፤ በሰላማዊ የንግድ ልውውጦች የመሳተፍ ጥልቅ ፍላጐት ሰብዓዊ ፍጡራን ከወታደራዊ ብዝበዛዎች ሱስ እንዲፀዱ ያደርጋል፤ ንብረት በአግባቡ የመያዝ፣ የትጋት፣ የአመዛዛኝነት፣ የፅናት እና የሥርዓት ሞራላዊ እሴቶችን ያሰርፃል። በርግጥ በአንድ ሀገር የሚደረግ የሌላ ሀገር ባሕሎችን እና አሰራሮችን የመኮረጅ ማንኛውም ተግባር የታሪክ እና የባሕል ልዩነቶችን ከግምት ያስገባ መሆን አንዳለበት ቢገነዘብም፣ ሕግ የማስፈጸም፣ የማውጣትና የመተርጐም ሥልጣኖች በንጉሡ እጅ ላይ ተጠራቅመው በሚገኙበት በፈረንሳይ ሀገር የተንሰራፋው የፖለቲካ ችግር የእንግሊዝ መንግሥትን ዋና ዋና መገለጫዎች ወደሀገር ውስጥ በማስገባት በመርህ ደረጃ ሊወገድ እንደሚችል ምንተስኪው ያምን ነበር።
የሞንተስኪውን የፖለቲካ ግምገማ በአጭሩ ማስፈር ቀላል አይደለም። “The Spirit of the Laws” መጽሐፉ፣ የፈረንሳይ አብርሆት (French Enlightenment) ፖለቲካዊ እሳቤ ዘመን-አይሽሬ ሥራ ተደርጐ ሊወሰድ የሚችል ነው፤ ነገር ግን “ኦሪጂናል” ወይም አዲስ ሊባል የሚችል ሐሳብ አይታይበትም፤ በእንግሊዝ የመንግሥት ሥርዓት ላይ ያደረገው ትንታኔም በ18ኛ ክፍለ ዘመን አጋማሽ የነበረው የእንግሊዝ ሥርዓት ምን ዓይነት ስለመሆኑ በጣም በትክክለኛ የሚገለፅ ምልከታ አልነበረም። ጥናቱን ያደረገው ከምንም ተነስቶ እንደሆነ ቢገልፅም፣ እርሱ የሚያነሳው አብዛኛው ነገር በጆን ሎክ፣ በሐሪንግተን እና በቦሊንግብሮክ እሳቤች ላይ የተመረኮዘ ይመስላል። ታዋቂው «የሥልጣኖች ክፍፍል» ወይም «Separation of Powers» የተሰኘው አስተምህሮም ቢሆን በፕሌቶ፣ በአስርቶትል እና በፖሊቢየስ ከተነሳው ቅይጥ የመንግስት ሥርዓት እሳቤ የተለየ አይደለም። የሞንተስኪው እውቀት ሰፊ እንጂ ጥልቅ አይደለም፤ ትንታኔዎቹ ብዙውን ጊዜ ቅድመ-ድምዳሜ የሚስተዋልባቸውና ሁል-አቀፍ ያልሆኑ ናቸው፤ “The Spirit of the Laws” ሥራው አፃፃፍ በአግባቡ አለመዋቀሩ ሆን ተብሎ መደረጉን ሳይሆን የሥነ-ጽሁፍ ክህሎት ማጣትን የሚጠቁም ወደመሆኑ ያመዝናል።
ይሁንና ከላይ የተገለፁት አሉታዊ አስተያየቶች ቢኖሩም እንኳን፣ የሥራዎቹን መጠን እና ትጋቱን አለማድነቅ አይቻልም። ከዚህም በላይ የአንድ ሀገር የካርታ አቀማመጥ፣ አካባቢያዊ ሁኔታ እና ሌሎች ውጫዊ ነገሮች በፖለቲካ ተቋማት ላይ ሊያሳድሩ የሚችሉትን ተፅዕኖ ለመመርመር የሞከረ የመጀመሪያው የዘመኑ ፈላስፋ ነው። በአሜሪካ ሕገመንግሥት አርቃቂዎች ዘንድ የተሰጠው ክብርና አድናቆት ለእርሱ እውቅና ሚና ተጫውቷል። ሞንተስኪው እጅግ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሮ ቆይቷል፣ ይህም በፖለቲካ ፍልስፍና ታሪክ ትልቅ ቦታ እንዲይዝ አስችሎታል።
ለበለጠ ንባብ
ቀዳሚ ምንጮች፡
The Political Theory of Montesquieu, ed. M. Richter(Cambridge: Cambridge University Press, 1977).
The Spirit of the Laws, ed. A.M. Cohler, B.C. Miller and H.S. Stone (Cambridge: Cambridge University Press, 1989).
ተቀፅላ ምንጮች፡
Durkheim, E.: Montesquieu and Rousseau: Forerunners of Sociology, ed. R. Mannheim (Ann Arbor, MI: University of Michigan Press, 1960).
Pangle, T.L.: Montesquieu’s Philosophy of Liberalism (Chicago, IL: University of Chicago Press, 1973).
Shackleton, R.: Montesquieu: A Critical Biography (Oxford: Oxford University Press, 1961).