ፖለቲካ/ፍልስፍና

“መንግሥት የኃጥያት ውጤት ነው” – ቅዱስ ኦገስቲን (354-430)

“መንግሥት የኃጥያት ውጤት ነው” – ቅዱስ ኦገስቲን (354-430)

ኦገስቲን የተወለደው አልጄሪያ ውስጥ ነው፤ ቀድሞ ታኽገስቴ አሁን ደግሞ ሱክ አኽራስ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ፡፡ እናቱ ክርስቲያን ብትሆንም ወደ እምነቱ እንዲጠጋ ለምታደርጋቸው ጥረቶች ምላሽ የሚሰጥ አልነበረም፡፡ ወጣት ሳለ የሲስሮ እና የፕሎቲነስ አድናቂ የነበረ ሲሆን “ማንቼይዝም” ለተባለው (Manichaeism – የክርስትና እና የባዕድ እምነቶች አለባዊያንን ያካተተ) የሃይማኖት ሥርዓት እና ለስኬፕቲሲዝም (የጠርጣራነት ፍልስፍና) ትኩረት ነበረው፡፡ የእርሱ የበሰለ ምሁራዊ አቋም “Christian Neoplatonism” ወይም የፕሌቶንና ሌሎች የግሪክ እሳቤዎችን ከሩቅ ምስራቅ እምነቶች ጋር ያዋሀደ ክርስትና ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ348 ብቁ ተናጋሪነትንና ፀሐፊነትን በሚላን ከተማ ለሰዎች በሚያስተምርበት ወቅት፣ በዚያው ከተማ ታዋቂ በነበሩ ክርስቲያኖች ተፅዕኖ ስር ዋለ፡፡ ከዚያም፣ “Confessions” በተሰኘው ሥራው በዝርዝር እንደተናዘዘው፣ ከረዥም የሕሊና ትግል በኋላ በ387 በዕለተ ስቅለት በቅዱስ አምብሮሴ አማካኝነት ተጠመቀ፡፡ በ391 ክህነት ተሰጥቶት ቄስ ሆነ፤ በ396 ቀድሞ ሒፖ፣አሁን ደግሞ አናባ ተብላ በምትጠራው የአልጄሪያ ከተማ ጵጵስናን ተቀበሎ፣ የሒፖ ጳጳስ ተባለ፡፡ እስከ እልፈተ ህይወቱም ከዚህች ከተማ አልተንቀሳቀሰም፡፡

የኦገስቲን የሥነ-ጽሁፍ ውጤቶች አሸን የነበሩ ቢሆንም በመደበኛ እይታ ግን የፖለቲካ “ፅንሰ-ሐሳብ አፍላቂ” ወይም “theorist” አይደለም፡፡ እርሱ የሚጠቀስባቸው ፖለቲካዊ አስተምህሮዎች የክርስትና ጳጳስ እና ልሂቅ በሆነበት ዘመን ከተነሱ ውዝግቦች እንደ ተቀጽላ ውጤት ሆነው የፈለቁ ነበሩ፡፡ “The City of God” የተሰኘው ትልቁ ሥራው ያለቀለት የፖለቲካ ፍልስፍና ክምችት ነው የሚለው አመለካከት የተሳሳተ ነው፡፡ የእርሱ የፖለቲካ እሳቤ ከ30 ዓመታት በላይ ጊዜ ውስጥ ከተዘጋጁ የተለያዩ ሥነ-ጽሁፎች (ማለትም ከደብዳቤዎች፣ ሃይማኖታዊ ስብከቶች፣ መንፈሳዊ ትንታኔዎች፣ ክርክራዊ ጽሁፎችና ከጥናታዊ ሥራዎች) ውስጥ ተለቃቅሞ ሊሰባሰ ግድ ነው፡፡

የመጀመሪያው ኃጥያት (Original Sin)

የኦገስቲንን የፖለቲካ እሳቤዎችን በተቀናጀ መልኩ ለማቅረብ የመጀመሪያው ኃጥያት (Original Sin)፣ የእግዚአብሔር ፀጋ (Grace) እና አስቀድሞ የተፃፈ እጣ-ፈንታ (predestination) ከተሰኙት አስተምህሮዎቹ መነሳት ይገባል፡፡ አዳም እና ሔዋን ከነፃ ፈቃድ (Free Will) ጋር ነበር የተፈጠሩት፡፡ የተከለከለውን ፍሬ ሲበሉ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ላለማክበር በመምረጣቸው ምክንያት ኃጥያት ሰሩ፡፡ ይህንንም በማድረጋቸው የፍትህን ተፈጥሯዊ ሥርዓት አናጉት፤ ፍቅረ-አግዚአብሔርን በፍቅረ-ራስ ተኩ፡፡ ለዚህም ከገነት በመባረርና በሞት እና በስቃይ ፍርድ ተቀጡ፡፡ ሆኖም የእነሱ ኃጥያት በሁሉም ውላጆቻቸው ላይ ከፍተኛ ውጤቶችን ያስከተለ ነበር፡፡ እያንዳንዱ ተከትሎ የመጣ የሰው ዘር አባል ከተመሳሳይ የጭቃ አካል የተሰራ ነው፤ እናም በዚያ አካል የተቀላቀሉ ኃጥያቶች በእኛም ውስጥ አሉ፡፡ እያንዳንዳችን በመጀመሪያው ኃጥያት ጥፋተኞች ሆነን ነው የተወለድነው፡፡

እንዲሁም ከመጀመሪያቹ ቤተሰቦቻችን እንከናማ ፈቃድ ወርሰናል፡፡ መነሻው ከስቁንቁንነት፣ ከመኩራራት እና ከራስ ፍቅር ባልሆነ በማንኛውም መንገድ አንድን ድርጊት ለመፈፀም አቅም የሌለን ሆነን ተወልደናል። ከነፃ ፈቃዳችን ወይም ከነፃ ምርጫችን የተረፈን ነገር ቢኖር ተንሰራፍተው ከሚገኙት አያሌ ኃጥያቶች ውስጥ አንዱን ለመፈፀም በነፃነት የምንመርጥበት ነው፡፡ በቀላሉ በዚህ መልክ ሲቃኝ፣ ወደዚህ ዓለም የመጣነው ዘላለማዊው ሲዖል የሚገባን ሆነን ነው፡፡ ኦገስቲን፣ ይህ ዓይነቱ የሰው ልጅ ሁናቴ ሊያካትት ስለሚችላቸው ነገሮች ለማተኮር አልሞከረም፡፡ የእርሱ ዋስትናው (ማረጋገጫው) ቅዱሳን መጽሐፍት ወይም በየትኛውም መጠን የእርሱ የቅዱሳን መጽሐፍት አተረጓጐም ነው፤ እናም እንደርሱ ሐሳብ የመጽሐፍቱ ምስክርነት የማያጠያይቅ ነው፡፡

ሁለቱ የኦገስቲን ከተሞች

እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ (Omniscient) በመሆኑ፣ ገና ከመነሻው አዳም ኃጥያትን እንደሚሰራ ያውቅ ነበር፤ እናም በምህረቱ ከሰው ዘር አባላት ውስጥ ጥቂቱንና ጥቂቱን ብቻ ከውድቀት ለማዳን መፍትሔ አበጀ፡፡ ይህንንም በእውነተኛ መንገድ በፍቅረ-ራስ ምትክ ፍቅረ-እግዚአብሔርን እንዲያስቀድሙ፣ ብሎም ድርጊታቸው ሁሉ ከስግብግብነት፣ ከመኩራራት እና ከጊዜያዊ መሻት እንዳይመነጭ የሚያስችላቸውን ፀጋ በማጐናፀፍ አደረገው፡፡ ይህ ፀጋ እንዲሁ ሊገኝና በይገባኛል ሊጠየቅ የሚችል አይደለም፡፡ እጣ-ፈንታቸው ቀድሞውኑ ለተፃፈላቸው ሰዎች ምክንያት በማይሻ ምርጫው የተቸረ የእግዚአብሔር ነፃ ስጦታ ነው፡፡ እነዚህ እጣ-ፈነታቸው የተወሰነ፣ የተቀቡ ሰዎች የእግዚአብሔር ከተማ (Civitas Dei) አባላት ናቸው፡፡ የተቀሩት የሰው ዘሮች የምድራዊው ከተማ (Civitas Terrena) አባላት ናቸው፡፡ እነርሱ ያልተመረጡት፣ መርሆ የለሾች፣ የምህረት ተስፋ ሳይኖራቸው ዘላለማዊ ጋሃነም የተፈረደባቸው ናቸው። እግዚአብሔር ሌሎችን ትቶ የተወሰኑትን፣ ወይም ሁሉንም ከመምረጥ ይልቅ የተወሰኑትን፣ አልያም ብዙዎችን አስቀርቶ ጥቂቶችን ብቻ ስለምን እንደመረጠ አናውቅም፤ ነገርግን በእርሱ ፍርድ ላይ ጥያቄ ለማንሳት አልተፈቀደልንም፡፡ እግዚአብሔር አብላጫ ቁጥር ያላቸው የሰው ዘሮች ላይ ዘላለማዊውን ጋሃነም የመፍረዱ እውነታ የእርሱን ፍትህ ያሳያል፤ ጥቂቶችን የማትረፉ (የማዳኑ) እውነታ የእርሱን ምህረት ያመላክታል፡፡

የመካከለኛው ዘመን የኦገስቲን አድናቂዎች (ደጋፊዎች)፣ የእግዚአብሔር ከተማ የተባለው ተቋማዊዋን ቤተ-ክርስቲያን ወክሎ እንደተገለፀ ምሳሌ፣ እንዲሁም ምድራዊ ከተማን ደግሞ የነገሥታት እና የገዥዎች ሥልጣን ተምሳሌት እንደሆነ አድረገው ይወስዱታል፡፡ ሆኖም ኦገስቲን ይህንን ማለቱ እንዳልሆነ መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ከተማ ተለይቶ በተወሰነ ቦታ ወይም ጊዜ ላይ ያለ አይደለም፡፡ በምድር ላይ እየኖሩ የሚገኙ አስቀድሞ የተመረጡትን የሚያካትት ነው፤ ነገር ግን ከእነርሱ በተጨማሪ በምድር ሞተው በገነት የሚገኙ የምርጦቹ ነፍሶች፣ እንዲሁም የሳጥናኤልን ማመፅ ተከትሎ ለእግዚአብሔር በታማኝነት የቆሙትን መላዕክት ጭምር ያካትታል፡፡ እግዚአብሔርን የሚያፈቅሩ ሁሉ ያሉበት አጠቃላይ ማህበረሰብ (Communio Sanctorum) ነው፡፡ በተመሳሳይም፣ የኦገስቲን ምድራዊ ከተማ ‹ትዕዛዝ እስከ አለማክበር በደረሰ የራስ ፍቅር› ሕብረት የፈጠሩት ሁሉ ያሉበት ማህበረሰብ ነው፡፡ በዚህ፣ በህይወት ያሉት ኃጥያተኞች፣ በምድር ሞተው በሲዖል የሚሰቃዩ ኃጥያተኛ ነፍሶች፣ እንዲሁም የዲያቢሎስ ተከታዮች ወይም የተወገዙ መላዕክት ይገኛሉ፡፡

እግዚአብሔር ባስቀመጠው እጣ-ፈንታ መሠረት ሁሉም ሰው የአንዱ ወይም የሌላው ከተማ አባል ነው፡፡ በምድር ላይ በርግጥ ሁለቱ ከተሞች ለጊዜው አብረው ተቀላቅለው ይገኛሉ፡፡ አባላቶቻቸው ተመሳሳይ ሀብቶችን ሲጋሩ፣ ተመሳሳይ ውጣ ውረዶችንና ስቃዮችንም ይጋፈጣሉ፡፡ በማንኛውም ውጫዊ ምልክት ማን የየትኛው ወገን እንደሆነ ሊናገር የሚቻለው የለም፤ እንዲሁም ቤተ-ክርስቲያንን ጨምሮ ሁሉም ምድራዊ ማህበረሰቦች የሁለቱንም አባላት በውስጣቸው ይዘዋል፡፡ ስለዚህም ክርስቶስ መዳንን ያገኙትን ከተወገዙት እስከሚለይበትና እያንዳንዱ ቡድንም «መጨረሻ የለሹን መጨረሻ» እስከሚቀበልበት የመጨረሻው ፍርድ እስከሚመጣ ድረስ ሁለቱ ከተሞች እንደተቀላቀሉ ይቆያሉ፡፡

ፖለቲካዊ እሳቤውስ?

ታዲያ ስለፖለቲካ ምን ተባለ? ፕሌቶ እና አርስቶትል፣ የፖለቲካ ህይወት ለሰው ልጅ ተፈጥሯዊ እንደሆነ አስቀምጠዋል፡፡ የራስ-ገዝ ከተማ (polis) ህይወት ምክንያታዊ፣ ውይይት እና ድርድር ያለበት፣ እንዲሁም መተባበር የሰፈነበት ሆኖ ለሰው ልጅ ተፈጥሮ ተስማሚ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ሆኖም ኦገስቲን በመሠረታዊ ደረጃ ከዚህ መርህ ይነጠላል፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር በእንስሳት ዘንድ የበላይነትን ሰጥቶታል፤ የእርሱ ዘር በሆኑ በሌሎች ላይ ግን የመግዛት ሥልጣንን አልሰጠውም፡፡ የሰው ልጆች በሕብረት እና በእኩልነት በተፈጥሮ ሕግ ጥላ ስር ሆነው “አንተ ላይ ቢደረግ የማትወደውን በሌሎች ላይ አታድርግ” የሚለውን መርህ ሰንቀው በአብሮነት ይኖሩ ዘንድ ነበር የታሰበው፡፡ ሆኖም የኃጥያት ወደዚህ ዓለም መግባት አስደናቂ ሕብረተሰባዊ አብሮነትን ማምጣት በማይቻልበት መልኩ የሰውን ልጅ ተፈጥሮ በርዞታል፡፡ የተሰናከለው ሰው መለያ የሆኑት ስቁንቁንነት እና እራስ አፍቃሪነት፣ ኦገስቲን “libido dominandi” በማለት በሚጠራው የመግዛት እና የመቆጣጠር ጥልቅ ፍላጐት አማካኝነት እራሳቸውን ያገልጣሉ፡፡ ይህ ሰብዓዊ መሻት ነው ለመንግሥት መኖር ምክንያት የሆነው፡፡ መንግሥት ማለት የሰው ልጅ የመግዛት አምሮት ተቋማዊነትን ሲላበስ ማለት ነው፡፡

ይሁንና ግን መንግሥት አንታዊ ተግባራትም አሉት፡፡ የእርሱ የመቆጣጠር እና የመገደብ ተፅዕኖ ባይኖር ኖሮ፣ ሰዎች አንዱ የሌላው የበላይ በመሆንና የምድርን ሀብት በመቆጣጠር ትግላቸው እርስ በርሳቸው ተላልቀው ሊጠፉ ይችሉ ነበር፡፡ የሰውን ልጅ ተጠፋፊነት ገድቦ በመያዝ ይህንን እስከተከላከለ ድረስ፣ መንግሥት በኃጥያት ምክንያት ለሚመጡ ውጤቶች መመከቻ፣ እንዲሁም ከውጤቶቹ አንዱ ነው፡፡ መንግሥት በማያሻማ መልኩ ዓላማዎቹን በአብዛኛው በሽብር እና በስቃይ ያሳካል፡፡ እንደ ኦገስቲን አመለካከት፣ ሰብዓዊ ሥልጣን ወይም ኃይል በሰቃዩ እና በገራፊው እጅ ነው፡፡ እንዲሁም የሕግ እና የፍትህ ሥርዓቶቹ ሁሉ በስህተት የታጠሩ ናቸው፡፡ ብዙውን ጊዜ ንፁሃን ይፈረድባቸዋል፤ ጥፋተኞች ነፃ ይለቀቃሉ፡፡ ያም ሆኖ ግን መንግሥት አሁንም በድጋሚ መለኮታዊ ዓለማ አለው፡፡ ጨካኝነት እና ኢ-ፍትሃዊነት ከእርሱ ጋር ተዳምረው አጥፊዎችን ለሰሩት ኃጥያት ለመቅጣት፣ እንዲሁም ትክክል ወይም ልክ አድራጊዎችን በምድራዊ ህይወታቸው ለመፈተንና ለማጣራት ያገለግላሉ፡፡ እንደቀድሞው ሁሉ፣ እግዚአብሔር መልካምን ለይቶ ለማውጣት ሲል ጥፋትን ይጠቀማል፡፡፡

ስለዚህም ለኦገስቲን፣ መንግሥት በሦስት መልኮች ይገለፃል፡፡ የኃጥያት ውጤት ነው፤ በኃጥያት ምክንያት የሚመጣ ጉዳትን መገደቢያ መንገድ ነው፤ እንዲሁም አደብ የማስገዢያ ሥርዓት ነው፡፡

እውነተኛው ፍትህ

ኦገስቲን፣ የትኛውም ምድራዊ መንግሥት እውነተኛ ፍትህ (vera iustitia) ሊኖረው እንደማይችል መከራከሪያውን ያቀርባል። ፍትህ፣ በቀደመ ትረጓሜው፣ ለእያንዳንዱ የሚገባቹውን ከመስጠት ይመነጫል፡፡ ሆኖም የሁሉም ምርድራዊ መንግሥታት ሕዝቦች፣ ክርስቲያን በሚባሉት ውስጥ ያሉት ጭምር፣ የምድራዊ ከተማዋ አባል የሆኑና በዚህም ለእውነተኛው አምላክ የሚገባውን አምልኮ የማይሰጡ አብላጫ ቁጥር ያላቸውን ግለሰቦች ይይዛሉ፡፡ ስለዚህ የተወሰኑ ግለሰብ አባላቱ ፍትሃዊ ቢሆኑም እንኳ፣ የትኛውም መንግሥት በቡድን ወይም በጥቅል ፍትሃዊ ሊሆን አይችልም፡፡

መንግሥት የሞራል ማህበረሰብ አይደለም፡፡ ለውስጣዊ ህይወታችን ምንም ዓይነት ጠቀሜታ የለውም፡፡ ምድራዊ ፍትህ፣ የእውነተኛው ፍትህ ደብዛዛ ቅጂ ብቻ ነው፡፡ ምድራዊ ፍትህ፣ ድህነት ያገኙት እና ያልተመረጡት የሆነ ዓይነት የጋራ ህይወት መኖር ይችሉ ዘንድ ብጥብጥን ከመገደብና ከውጫዊ ሥርዓቱ ጋር መጣጣምን ተፈፃሚ ከማድረግ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ በአንፃሩ እውነተኛው ፍትህ ደግሞ ብጥብጥ የሚባል ነገር ከነጭራሹ የሌለበት ሁናቴ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፍቅር ቤተሰባዊ አንድነት ፈጥረው የሚኖሩበት ሁናቴ ነው፡፡ ነገር ግን እውነተኛው ፍትህ የሚገለጠው በታሪኩ ማብቂያ፣ ቅይጥ ማህበራቱ በሚለዩበት ጊዜ የእግዚአብሔር ከተማ ወደፍፁማዊው የሐሴት ውርሷ ስትዘልቅ ብቻ ነው፡፡

እናም የክርስቲያን መንግሥታት እንኳን እውነተኛውን ፍትህ (vera iustitia) አይወክሉም። ይሁንና ግን በሁለት ምክንያቶች ክርስቲያን ካልሆኑት ይልቅ የተሻለ የፍትህ አምሳያነትን ማስፈን ይችላሉ። የመጀመሪያው፣ ክርስቲያን ገዢዎች ለሕዝቦቻቸው ጥሩ ተምሳሌትነትን በሚያሳዩበት መንገድ መኖር ይችላሉ፣ አለባቸውም። ሁለተኛው፣ ክርስቲያን ገዢዎች ከጠላቶቿ ለመከላከልና ሥራዋን ለማስፋፋት የሥልጣናቸውን መዘውር ለቤተ-ክርስቲያን ለማቀበል ዝግጁ መሆን አለባቸው። ሆኖም ኦገስቲን እንዲህ ያሉ ገዢዎች በመደበኛነት የቤተ-ክርስቲያን የበታች ወይም ለትዛዛቷ ተገዢ ናቸው አለማለቱ ወይም ይህንንም አለማመላከቱ ግልፅ ሊሆን ያስፈልጋል። በቀላሉ ዋናው ነጥቡ፣ ሁሉም ሰው ማንም ይሁን ማን፣ በየትኛውም የአቅም ደረጃ ቢሆን እግዚአብሔርን ማገልገል ይገባዋል። ክርስቲያን ልዑሎች የቤተ-ክርስቲያኒቱን ሥራዎች ለማገዝ ቢሮዋቸው የሚችለውን አጋጣሚ ሁሉ መጠቀም አለባቸው፤ ጫማ ጠገጋኞች፣ አናፂዎች ወይም ወታደሮች እንደሚያደርጉት ሁሉ። በአሥራ-አንደኛው ክፍለዘመን ይህ ዓይነቱ አመክኒዮ ቤተ-ክርስቲያን ወይም ጳጳሱ ንጉሠ ገሥቶችን ማዘዝ እና ማንሳት ትችላለች ወይም ይችላል ወደሚል አቋም እያደገ መጥቶ ነበር። ኦገስቲን ግን በርግጠኝነት ይህን የመሰለ ሐሳብ በአእምሮው አልነበረም።

የኦገስቲን የክርስቲያን ልዑሎች ግዴቴዎች ግንዛቤ፣ በተለይም ሃይማኖታዊ ጭቆናን በተመለከተ፣ በይበልጥ እየዳበረ የመጣው በሰሜን አፍሪካ ከተገንጣይ የዶናቲስት ቤተ-ክርስቲያን ጋር በነበረ ግጭት ወቅት ነው። እርሱም እራሱ ከ391 እስከ 417 ዓ.ም በዚህ ግጭት ውስጥ ተሳታፊ ነበር። ሃይማኖታዊ ልዩነቶች በምክንያት እና በመነጋገር (በመከራከር) መፈታት አለባቸው የሚል ቀዳሚ ሐሳብ ነበረው። ከ400 ዓ.ም በኋላ፣ ቤተ-ክርስቲያን ከሃይማኖት ውጭ የሆኑት የመንግስት ኃላፊዎችን ከሥርዓቷ ባፈነገጡ (heretics) እና በተገነጠሉት (schismatics) ላይ ሕጎች እንዲያወጡ እና እንዲያስፈፅሙ ጥሪ ማቅረቧ አይፈረድባትም የሚል ጠንካራ እምነት እያሳደረ መጣ። ይህም የሚሆነው በአንድ በኩል በርግጥም በካቶሊኮች እና በንብረታቸው ላይ የሚሰነዘር የጥቃት እርምጃዎችን ለመከላከል ሲሆን፤ ነገር ግን የቤተ-ክርስቲያኗን አንድነት እና አስተምህሮአዊ ጥንካሬን ለማስጠበቅም ጭምር ነው። ከ406 ዓ.ም በኋላ በዚህ በሁለተኛው ነጥብ ላይ አፅንኦት መስጠቱ ይበልጥ እየታየ መጥቷል። በዚያ ዓመት የኃይል ወይም የማስገደድ ፖሊሲን ሊደግፍ እንደሚችል “Epistulae” በተሰኘ ሥራው ላይ አሳይቷል።

ሃይማኖታዊ ጭቆናዎች ተቀባይነት ያላቸው ስለመሆናቸው ምክንያቶቹ በሙሉ በ408 እና በ417 ዓ.ም በተፃፉት ረዣዥም ደብዳቤዎቹ ይገኛሉ። በርግጥ ትክክለኛ ልባዊ ለውጦች በኃይል ሊመጡ ይችላሉ የሚል እምነት የለውም። ነገር ግን፣ የራሱንም ሆነ የሙያ ባልደረቦቹን ተሞክሮ መሠረት በማድረግ እንደሚነግረን፣ ጠንከር ያሉ የኃይል እርምጃዎች እና የእነዚህ እርምጃዎች ፍራቻ ተጠቂዎቹ እምነታቸውን ለራሳቸው እንደገና እንዲመረምሩ ማስደረግ ስለመቻላቸው ወደማሰቡ መጥቶ ነበር። ጭቆና፣ በዚህ በሁለተኛው ገፅታው፣ ለተጨቋኙ ጠቀሜታ ሊያመጣ ይችላል። እነዚያ በኃይል ተገደው እውነትን ወደሚያስተምሩቱ እንዲመጡ የተደረጉት ሁሉ፣ እውነትን ሊመለከቷት ይችላሉ፤ በካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን የሚደረገግ የማስገደድ ጫና ከአፈንገጋጭ ጫና ፍርሃት ሊገላግል ይችላል፤ የኃይል ጫና የሱስ እና የስንፍና ቀንበርን ሊሰብር ይችላል። ከቤተ-ክርስቲያን ውጭ በሆኑት ላይ ኃይልን በመጠቀም ጫና ማድረስ፣ በትክክለኛው ዓላማ የተፈፀመ የፍቅር ድርጊት ነው የሚል አቋም ኦገስቲን ይዟል። የትኛውም ፍቅር ከክርስቶስ ፍቅር አይበልጥም፤ ሆኖም ቅዱስ ጳውሎስን ለአገልግሎት ሊጠራው በፈለገ ጊዜ፣ በቅድሚያ የዓይን ብርሃኑን ነስቶት ነበር። በታላቁ እራት የክርስቶስ ምሳሌ ላይ ባሪያዎቹ እንግዶችን እንዲያድኑ ሲላኩ፣ ጌታቸው የሰጣቸው ትዕዛዝ ወሳኝነት አለው፦ “ቤቴ እንዲሞላ ወደ መንገድና ወደ ቅጥር ውጣና ይገቡ ዘንድ ግድ በላቸው.”

የሕዝቦች ፖለቲካዊ ግዴታ

በርግጥ ኦገስቲን የፖለቲካ ግዴታ (ኃላፊነት) ፅንሰ-ሐሳብን አያመላክትም፡፡ እንዲያው በጥቅሉ፣ ይህ ጥያቄ ለእርሱ እንደጭብጥ አይደለም፡፡ አብዛኛው ሕዝብ ከመንግሥት ጋር ያለው ዝምድና በቀላሉ ሊገለጽ የሚችለው ከራስ ፍላጐት አንፃር እንደሆነ ያምናል፡፡ ብዙዎቹ ዜጐች ለመንግሥት ተገዢ የሚሆኑት ከግዴታነት ስሜት ሳይሆን፣ ይልቁንም ይህንን ባያደረጉ ሊከሰት የሚችለውን በመፍራት፣ አልያም ሀገራቸውን (መንግሥታቸውን) በደንብ ለሚያገለግሉ ሰዎች የሚቀርቡ ሽልማቶችን (ክፍያችን) – ሀብት፣ ሥልጣን፣ ዝና – በእጃቸው ለማስገባት ነው፡፡ እነርሱን በተመለከተ የግዴታ ጉዳይ በጭራሽ አይነሳም፡፡

በሌላ በኩል ክርስቲያኖች ለመንግሥት ተገዢ የመሆንና ህብረተሰባዊ ተቋማትን የማክበር ንፁህ ግዴታን ሊቀበሉ ይገባል፤ ነገር ግን ይህ ግዴታ በቀጥታ ከፖለቲካ ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ ለመንግሥት ተገዢ የመሆን ግዴታ ያለብን መንግሥት በእኛ ላይ ያን ያህል የሞራል ጥያቄ ስላለው ሳይሆን፣ ተገዢ እንድንሆን የእግዚአብሔር ፈቃድ በመሆኑ ምክንያት ነው፡፡ መንግሥት የኃጥያት ውጤት ነው፤ ነገር ግን ሊኖር የቻለው እና የሚያደርገው ተግባር እግዚአብሔር ለዓለም ያዘጋጀውን እቅድ መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ቢያንስ መጠነኛ ሰላም እና ሥርዓት (መረጋጋት) ለማምጣት የተሽመደመዱ ቢሆኑም እንኳን ተቋማትን ይጠቀማል፡፡ ክርስቲያኖች ይህንን ያውቃሉ፤ ድርጊታቸውም ይህንን የተከተለ ይሆናል፡፡ የትኛውም ምድራዊ ገዢ በክርስትና እምነት ከግምት ስለሚገቡት ዜጋ የመሆን መመዘኛዎች ላይ ጥያቄ ሊያነሳ የሚችልበት ምንም ምክንያት የለውም፡፡

ኦገስቲን በፖለቲካዊ እና በጨቋኝ አገዛዝ መካከል ያለውን ተለምዷዊ ልዩነት ይቀበላል፤ ነገር ግን እንደሕዝብ (እንደተገዢዎች) በእኛ ላይ ግዴታ በመጫን አንፃር የተለየ ጉልህነት አይሰጠውም፡፡ ገዢያችን ምንም ያህል የጥፋት ኃይል ወይም ጨቋኝ ቢሆን የአመጽ ተግባር ወይም ድርጊት-አዘል ተቃውሞ ምክንያታዊ ሊሆን አይችልም፡፡ ከፈቃደ-እግዚአብሔር በቀጥታ የሚጣረስ ነገር የጠየቀን (ያስገደደን) እንደሆን ተገቢው ምላሽ የሚሆነው ድርጊት-የለሽ ተቃውሞ ነው፡፡ ትህትና በተሞላበት መልኩ የታዘዝነውን ከመፈፀም ተቆጥበን፣ ይህንን ተከትሎ የሚመጣብንን ስቃይ (እንግልት) በፈቃደኝነት መቀበል አለብን፤ ኦገስቲን ከዚህ የዘለለ ነገር አልጠቆመም፡፡

ሁሉም የፖለቲካ ሥልጣን – የጥፋት አድራጊ ገዥዎች ሥልጣንም ጭምር – ከእግዚአብሔር ስለመምጣቱ በግልፅ ያስቀምጣል፡፡ ተገዢዎች (ሕዝቦች) እነርሱ ያላወጡትን ማውረድ አይችሉም፡፡ በተጨማሪም ኦገስቲን፣ መጥፎ ገዥዎች የእኛ ፍትሃዊ ቅጣቶች ስለመሆናቸው በግልፅ ይናገራል፡፡ አንድ ገዥ ቢበድለን ወይም ቢጨቁነን የእኛ ትክክለኛ ገዢ መሆኑን አያስቀረውም፡፡ ሀሰተኛ አማልክትን እንድናመልክ ቢያዘን ታዛዥ ከመሆን የምንቆጠበው ለእርሱ ሥልጣን እውቅና ባለመስጠታችን ምከንያት ሳይሆን፣ ገዥውን ጨምሮ ሁላችንም ከእርሱ የላቀ ሥልጣን ስለመኖሩ እውቅና የመስጠት ግዴታ ስላለብን ነው፡፡ ታዛዥ መሆንንም ሆነ አለመሆንን በተመለከተ የክርስቲያኖች የፖለቲካ አመለካከት ለእግዚአብሔር ባላቸው ታማኝነት እንጂ በሌላ በምንም መርሆ አይመራም፡፡ መታዘዝ እና አለመታዘዝ፣ ሁለቱም የሚመነጩት ፖለቲካዊ ሳይሆን ሃይማኖታዊ ከሆነ ግዴታ ነው፡፡

ለበለጠ ንባብ

ቀዳሚ ምንጮች፡-

The City of God Against the Pagans, ed. R.W. Dyson (Cambridge: Cambridge University Press, 1998).

Political Writings, ed. E.M. Atkins and R.J. Dodaro (Cambridge: Cambridge University Press, 2001).

ተቀፅላ ምንጮች፡-

Brown, P.: Augustine of Hippo: A Biography (London: Faber & Faber, 1967).

Deane, H.A.: The Social and Political Ideas of St Augustine of Hippo (New York: Columbia University Press, 1963).

Dyson, R.W.: The Pilgrim City (Woodbridge: Boydell Press, 2001).

Markus, R.A.: Saeculum: History and Society in the Theology of St Augustine (Cambridge: Cambridge University Press, 1970).

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.