“ንጉሡ ለሃይማኖት አባቶች መንፈሳዊ ምክር ተገዢ መሆን አለበት” – ቅዱስ ቶማስ አኩዊናስ (1225-74)
ቅዱስ ቶማስ አኩዊናስ የተወለደው በጣሊያን አኩዊኖ አቅራቢያ፣ በሮካሲካ ቤተ-ነገሥት (Castle) ውስጥ፣ ከባለፀጋና ከመኩዋንንት ቤተሰብ ነበር፡፡ ትምህርት የጀመረውም አጎቱ የበላይ ኃላፊ በነበሩበት ቤኔዲክታዊ (ቅዱስ ቤኔዲክት በመሠረተው ሥርዓት በሚመራው) የሞንቴ ካሲኖ ገዳም ውስጥ ነው፡፡ ዕድሜው ሃያ እንደደረሰ፣ ከቤተሰቦቹ ተቃውሞ እየገጠመው ቢሆንም፣ በቅዱስ ዶሚኒክ የተፀነሰውን የሮማ ካቶሊክ ዶሚኒካን ሥርዓት ተቀላቀለ፤ እንዲሁም ከጀርመናዊው የሃይማኖት አስምህሮ ልሂቅ፣ ከአልቤርተስ ማግነስ እውቀትን ለመቅሰም ወደ ፓሪስ ዩኒቨርስቲ አቀና፡፡ በ1256 የማስተርስ ዲግሪውን ከያዘ በኋላ፣ ቀጣዮቹን 18 ዓመታት በፓሪስ፣ ኔፕልስ፣ ኦሪቪየቶ፣ ቪቲርቤ፣ እንዲሁም በሮም እያስተማረና እየተማረባቸው አሳለፋቸው፡፡
“Summa Contra Genetiles” የተሰኘ፣ ወደ ሙስሊሞች እና አይሁዶች ለሚያቀኑ ሚሲዮናዊያን የተሰናዳ ሥራውን ያጠናቀቀው በ1264 ነበር፡፡ ግዙፍ ቦታ የሚሰጠውን “Summa Theologiae” በ1266 ጀምሮት በ1273 ጤናው እስከከዳው ጊዜ ድረስ ለፍቶበታል፡፡ ወደ ሁለተኛው የሊዮንስ ጉባኤ ለመሳተስ እያመራ ባለበት ሰዓት ነው ህይወቱ ያለፈችው፡፡
አብዛኛዎቹ የእርሱ ፖለቲካዊ አስተምህሮቶች በዚህ “Summa Theologiae” በተሰኘ ሥራው ላይ የሥነ-መለኮት እና የሞራል ትንታኔዎቹን ታክከው የፈለቁ ናቸው፡፡ ራሱን ችሎ የተገኘው “De regimine principum” ነው፤ ሆኖም ይህ ሥራው በ1267 ገደማ ሳይጨርሰው አቋርጦት በኋላም በደቀመዝመሩ በቶሎሜዮ አማካኝነት በተጠናቀቀና ይበልጥ ሰፊ በሆነ ሥራው ውስጥ የሚገኝ አንድ ክፍል ነበር፡፡
የአርስቶትል እሳቤዎች እና የአመለካከት ንድፎች በቅዱስ ቶማስ ፍልስፍና ላይ ምን ያህል ተፅዕኖ ያሳደሩ መሆናቸው በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ ኒዮፕላቶኒዝም (የፕሌቶንና ሌሎች የግሪክ እሳቤዎችን ከሩቅ ምስራቅ እምነቶች ጋር ያዋሀደ የክርስትና አስተምህሮ) በቅዱስ ኦገስቲን ጽሁፎች አማካኝነት ተላልፎ በስፋት መታየት ይቻል እንጂ፣ የአርስቶትል ሥነ-ምግባራዊ እና ፖለቲካዊ ጽሁፎች ከጥንቱ ዘመን አንስቶ እስከ 11ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ድረስ በምዕራቡ ዓለም በጭራሽ የማይታወቁ ነበሩ። እነዚህን ሥራዎች የማጥናቱ ድርሻ ለብዙ ዓመታት በአረብ ተንታኞች፣ በይበልጥም በአቬሮይስ (1126-98) የተያዘ ነበር፡፡ እናም በድጋሚ በምዕራቡ ዘንድ ለጥናት የቀረቡት አብዛኞቹ በፓሪስ ዩኒቨርሲቲ ይሰሩ በነበሩ ጥቂት ተመራማሪዎች እና ተርጓሚዎች አማካኝነት ነው፤ ቅዱስ ቶማስም፣ በአልቤርተስ ማግነስ አስጠኝነት የአርስቶትልን ሥራዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቃቸው እዚያ ነው፡፡
የሚያስገርም ባይሆንም፣ የአርስቶትልን መልሶ «ህይወት መዝራት» ቤተክርስቲያን በጥሩ ዓይን አልተመለከተችውም፡፡ ሃይማኖት የለሽ ወይም በዓለም ከሚታወቁት ሃይማኖቶች ውጭ የሆነ እምነት ያለው (pagan) ከመሆኑ ባሻገር፣ አረብ ልሂቃን አርስቶትልን በጥልቀት ሲያጠኑት የመቆየታቸው እውነታ በራሱ በወቅቱ ቤተ ክርስቲያን በጥላቻ እንድታየው ምክንያት ነበር፡፡ በ1277 የፓሪሱ ጳጳስ ቴንፒየር፣ በአርስቶትሊያን አስተምህሮዎች ላይ ይፋዊ ውግዘቱን ሲያውጅ ነገሮች የባሰ ደረጃ ላይ ደርሰው ነበር። በእርሱ ዘመን አርስቶትሊያኒዝም ላይ የነበረው ተቃውሞ በልጦ ቢገኝም (ምናልባትም ይህ በመሆኑ ምክንያት)፣ ቅዱስ ቶማስ ገና ከመነሻው የአርስቶትል ትምህርቶች ከክርስትና እምነት ጋር ሊታረቁ እንደሚችሉ ያምን ነበር፡፡ አርስቶትል፣ መለኮታዊ ራዕይን ሳይጠቀም እስከቻለው ድረስ ምሁራዊ ምርምሩን አካሂዷል። ድምዳሜዎቹ ከስህተት በፀዱና በራዕይ በተገለጠ እውነት በታገዙ ጊዜ፣ የሚገኘው የምክንያት እና የራዕይ ጥምረት በእሳቤ የታነፀ ምሉዕ ሥርዓትን ይፈጥራል፡፡ ይህም የቅዱስ ቶማስ እምነት ነበር:: እናም “Summatheologiae” መፅሐፉ ላይ በተስተዋለው መልኩ፣ ዝርዝር በሆነ ፍልስፍናዊ ጥንታኔ አማካኝነት እንዲህ ያለውን ጥምረት ማግኘት የዕድሜ ልክ ሥራው ሆነ፡፡
ስለዚህም፣ እንደምንጠብቀው ሁሉ፣ የእርሱ ፖለቲካዊ እሳቤ የፕሌቶ ወይም የኦገስቲን ከሆኑ የቀድሞ ዘመን አስተምህሮዎች በመሠረታዊ መልኩ የተለዩ ናቸው። ኦገስቲን ወደፊት በሚመጣው ዓለም ላይ ዓይኑን በመትከል፣ ይኼኛውን ዓለም በኃጥያት የተሞላና ሥርዓት ያጣ፣ እንዲሁም ፖለቲካው ከባድ እና አስገዳጅ ብቻ ሆኖ አግኝቶታል። ለኦገስቲን፣ ግለሰቡ ወይ ከምድር ጋር፣ አልያም ከገነት ጋር የወገነ ነው። የአንዱ ወዳጅ መሆን፣ በሌላኛው የተጠላ መሆን ማለት ነው። ቅዱስ ቶማስ በአንፃሩ፣ በአርስቶትል በተጠቆመው ምክንያታዊ፣ ለሰው ልጆች ተስማሚና ሥርዓት ባበጀ ዓለም ላይ ቅር የሚያሰኘው ምንም ነገር አላገኘም። በምድር ላይ የሚገኙ መልካም ነገሮችን የራስ በማድረግ እና በገነት ያሉትን ዘላለማዊዎች በማሳካት መካከል ያሉት ልዩነቶች ሊታረቁ የማይችሉበት ሁኔታ አይታየውም፤ ይህም የፊተኛው ወደ ኋለኛው ለመጓዝ የሚደረግ፣ እንዲሁም ኋለኛው ለፊተኛው ሲባል ቸል የሚባል ካልሆነ በቀር ነው።
የሰው ልጅ አንድ እውነተኛና የመጨረሻ ግብ አለው – ከእግዚአብሔር ጋር በገነት ፍፁም ደስታን ማጣጣም። (ስለዚህ ግብ አርስቶትል የሚያውቀው ነገር የለም።) ነገር ግን ምድራዊ ደስታም የሚቻልና የሚያረካ ነው። የምድር ህይወት፣ ቅዱስ ኦገስቲን እንደሚጠቁመው፣ የስቃይ ጉረኖ አይደለም፤ እንዲሁም የተገደበ እና በሁለተኛነት ደረጃ ያለ ቢሆንም፣ በምድራዊ ህይወት ምቾት ማግኘት እራሱን የቻለ ግብ ነው። እንዲህ ያለውን ምቾት ማሳካት ደግሞ የመንግሥትን መኖር ይጠይቃል፤ ሆኖም የሰው ልጅን አውዳሚነት በኃይል እና ፍርሃትን በማስረፅ የሚቆጣጠረው ዓይነት የኦገስቲንያን መንግሥት አይደለም። አብሮ እና ተባብሮ ሯሪ ለሆነው የሰው ልጅ፣ እጅግ የተመቻቸ አስተዳደር ነው። ማንም ሰው ለህይወቱ የሚያስፈልጉትን ሁሉ በራሱ ማግኘት አይቻለውም፤ የሥራ ክፍፍል ጠቀሜታዎችን ለማረጋገጥ መተባበር ያስፈልገናል። ግቦቻችንን ለማሳካት የሚያስችሉ ከአንድ በላይ መንገዶች ሊኖሩ ይችላሉ፣ እናም የተሻለ በሆነው በብልሃት ልንመራ ያስፈልገናል። እነዚህ ሁሉ ከኃጥያት ጋር ምንም የማይገናኙ ናቸው። እንዲሁ በቀላሉ የሰብዓዊ ተፈጥሮ እውነታዎች ናቸው። ብልጠት በተሞላበት አመራር የጋራ ወደሆነ መልካም ነገር ለመመራት፣ የአንድ ማኅበረሰብነ ለጋራ ዓላማ በአንድነት የማበር አስፈላጊነትን የሚያረጋግጡ እውነታዎች ናቸው።
“De regimine principum”ላይ፣ ያለንበት ሁኔታ የሚጠይቀው የአመራር ዓይነት ከሁሉ በተሻለ መልኩ የሚቀርበው ንጉሣዊ ሥርዓት መሆኑን ያስቀምጣል፡፡ የንጉሥ ሥርዓት፣ በአንድ ሰው የሚመራ መንግሥት እንደመሆኑ፣ እጅግ ተፈጥሯዊ የመንግሥት ዓይነት ነው። ትክክለኛ ተምሳሌቱ የእግዚአብሔር የሆነው አጽናፈ-ሰማይ (Universe) መንግሥት ነው፤ እናም በየትም ቦታ በተፈጥሮ ውስጥ ተንፀባርቆ እንመለከተዋለን፡፡ ከሁሉም በላቀ መልኩ ብቁ የመንግሥት ዓይነት ነው፤ ምክንያቱም የንጉሥ ሥልጣን ያልተከፋፈለና እርምጃ የመወሰድ ነፃነቱም ያተገደበ ነው፡፡
የመንግሥት ሥርዓቶችን በተመለከተ “De regimine principum” ላይ የሰፈሩ ማብራሪያዎች ሙሉ አይደሉም፡፡ “Summatheologiae”ላይ የንጉሥ ሥርዓትን በድጋሚ ይጠቁመዋል፤ ሆኖም እዚህ ላይ በዴሞክራሲ እና በኦሊጋርኪ አላባዊያን የረገበ ወይም የተገደበ የንጉሥ ሥርዓት ሆኖ ነው፡፡ በርግጥ ይህ አርስቶትል “Politics” ላይ ያነሳውን የቅይጥ መንግሥት ሐሳብ የተዋሰ ሆኖ፣ ከአርስቶትሊያን ገለፃ ዘንድ የሚመደብ ነው፡፡ ቅዱስ ቶማስ፣ ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች ከማስደሰቱ እውነታ አንፃር እንዲህ ያለው መንግሥት መረጋጋትን ያሰፍናል በማለት አርስቶትልን ይከተላል፡፡
ነገር ግን ንጉሡ የእርሱ ተግባር ውጫዊ ሁኔታዎችን ብቻ መግዛት አለመሆኑን ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡ በንጉሥነት ዘመኑ ለተገዢዎቹ የሞራል ልዕልና እና ድህነት (ጽድቅ) ምቹ የሆነ የአኗኗር ሁናቴን መፍጠር የእርሱ ተልዕኮ ነው፡፡ የሚያደርገው ነገር ሁሉ (ለተገዢዎቹ) ቁሳዊ ምቹነት ሊኖረው የሚገባው እንደማሸጋገሪያ ግብ ብቻ ነው፡፡ የእርሱ ትክክለኛ ክፍያው ቁሳዊ ጥቅም አልያም አላፊ የሆነው ሰብዓዊ ክብር አይደለም፡፡ ይልቁንም ዘላለማዊው የገነት በረከት ነው፡፡ ይሁንና ግን ቅዱስ ቶማስ ስለ «ቤተ-ክርስትያን እና መንግሥት» ቁልጭ ያለ ፅንሰ-ሐሳብን አለማጎልበቱ አስገራሚ ሐቅ ነው፤ ወይም በየትኛውም መልኩ ስለሚለው ነገር ግልጽ ያልሆነና ቁርጠኝነት የጎደለው ነው፡፡ በጥቅሉ እንዳስቀመጠው፣ ከፍተኛ ደረጃ (ሥልጣን) ያለው ሊቀ-ጳጳስ የክርስቶስ ምድራዊ ተወካይ ነው፤ ንጉሡ ከሃይማኖት አባት ለሚሰጠው መንፈሳዊ አቅጣጫ (ምክር) ተገዢ መሆን አለበት፤ በተወሰኑ በግልጽ ባልተጠቀሱ ጉዳዮች ላይ ለቤተ-ክርስቲያን ምድራዊ ትዕዛዝ ተገዢ ነው፤ እናም ይህ መንፈሳዊ እና ምድራዊ ሥልጣን በሊቀ-ጳጳሱ ተጣምሮ ይገኛል። ሆኖም የእነዚህን አባባሎች ዝርዝር አስተዋጽኦዎች አላስቀመጠም፤ ምክንያቱን ማወቅ ባንችልም፣ እርሱ በግሉ በፖለቲካ ውዝግቦች ውስጥ ባለመሳተፉ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል እንገምታለን፡፡
ፖለቲካ – ለቅዱስ ቶማስ አኩዊናስ – ለሕዝቦች የተመቸ፣ እንዲሁም ቀና እርምጃዎችን እና ሕዝባዊ ደስታን ግቡ ያደረገ በመሆኑ ምክንያት፣ ጨቋኝ መንግሥትን (tyranny) ከኦገስቲን በተለየ መልኩ ይመለከተዋል፡፡ ሆኖም ይህን በተመለከተ የእርሱ አመለካከት የኦገስቲን የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ጨረሶ አላስወገዳቸውም፡፡ ነገር ግን ጨቋኝ መንግሥትን በመለኮታዊ መንገድ እንደታሰበ ቅጣት አድርጎ መውሰድን አልመረጠም፤ ለጨቋኝ መንግሥት ተገዢ ያለመሆን መብት ዘላቂነቱ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በግልጽ ለሚጣረሱት ተግባራቱ ብቻ አለመሆኑንም ያስገነዝባል፡፡ ነገሥታት ሊኖሩ የቻሉት ጥፋተኝነትን ከመግታትና እምነትን ከመፈተን ባሻገር እንዲሠሩ ነው፤ የመኖራቸው ምክንያት የጋራ መልካምን ወይም ሕዝባዊ ጥቅምን እንዲያረጋግጡ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ በተቃራኒው ንጉሡ ለራሱ በግል ጥቅሙ ላይ ካተኮረ – ወይም በአርስቶትል “Politics”መጽሐፍ ክፍል ሦስት ላይ በቀረበው መልኩ ጨቋኝ (tyrant) ከሆነ – በእግዚአብሔር የተሾመበትን ዓላማ ክዷል፤ እናም ሕዝቦቹ ያከብሩት ዘንድ ምንም ግዴታ የለባቸውም፡፡
እዚህ ላይ ሕዝቦቹ ምን ዓይነት እርምጃ የመውሰድ መብት እንዳላቸው ቅዱስ ቶማስ ሙሉ ለሙሉ ግልጽ አይደለም፤ ምናልባት ቢያንስ በከፊል እርሱ እራሱ ጥያቄው ቁልጭ ያለ መልስ ሊኖረው እንደማይችል በማሰቡ ምክንያት ይሆናል፡፡ አንዳንድ ፀሐፊዎች ቶማስ በጉዳዩ ላይ ወጥነትና ወኔ እንደሚጐድለው ያስባሉ። “Scripta super libros sententiarum” በተሰኘ ሥራው የጁሊየስ ቄሳርን መገደል በግልጽ ደግፎ ሲናገር፣ ጨቋኝነቱ ለከት-የለሽ በሆነና ሌላ አማራጭ የእርምጃ መንገድ በጠፋ ጊዜ፣ ጨቋኙን መግደል (tyrannicide) አንዱ የሕዝቦቹ መብት እንደሆነ አድርጐ የጠቆመ ይመስላል፡፡ “De regimine principum” ላይ በጨቋኞች ላይ እርምጃ ሊወሰድ የሚችልበትን ምልከታም ይጠቅሳል፤ ነገር ግን ይህን ማድረግ የሚችሉት በሆነ መንገድ እርምጃውን የመውሰድ ሥልጣኑ ያላቸው ብቻ ናቸው፡- ምክንያቱም መደበኛ «የአንጋሽነት» ሚና ስላላቸው፣ አልያም የተጨቋኙን ማህበረሰብ ፍላጐት ስለሚያስጠብቁ፡፡ ጨቋኝ የመንግሥት ሥርዓቶች፣ ንጉሡን እንዲሁ በማይወደው ሰው የግል ውሳኔ ላይወገዱ ይችላሉ፡፡
ቅዱስ ቶማስ ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ፣ “De regimine principum” እና “Summa theologiae” ላይ አንፃራዊ በሆነ መልኩ ለዘብ ያለ ጨቋኝ ሥርዓትን ችሎ (ታግሶ) መቀመጥ እንደሚገባ፣ እንዲሁም እርምጃው መወሰድ ያለበት ይህንን ማድረግ የሚያስከትለው ጉዳት እና አሉባልታ በእርምጃው ከሚረጋገጡት ጥቅሞች የማይበልጥ በሆነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ የአሁኑን ዓረፍተ ነገር ሌላ ቦታ ላይ ስለ ጦርነት እና ሁከት ከሚለው ጋር አጣምረን ልንመለከተው እንችላለን። ይኸውም፣ ወረራን ለመከላከል ወይም ከጭቆና ለመውጣት የሚደረጉ ጦርነቶች፣ እንዲሁም ራስን ለመከላከል የሚደረግ ጭካኔያዊ ያልሆነ የኃይል እርምጃ ከሞራል አንፃር ተቀባይነት አላቸው፤ ነገር ግን ለመከላከል ከታሰበው ጉዳት በላይ ላለማድረስ ምንጊዜም መጠንቀቅ ይገባል። በርግጥ የቅዱስ ቶማስ አቋም ወጥነት የሌለው አይደለም፤ ጉዳዩንም አያድበሰብሰውም፡፡ ጥቆማዎቹ በአንድነት ሲደመሩ፣ ሕዝቡ በጨቋኝ መንግሥቱ ላይ ከፍተኛ እርምጃ ቢወስድ ተቀባይነት ያለው (ምክንያታዊ) ሊሆን ቢችልም፣ መቅረት የሚችልበት መንገድ ካለ ግን እርምጃው መወሰድ እንደሌለበት የሚጠቁም የጠንቃቃ ወግ-አጥባቂነት አቋምን ያንፀባርቃሉ፡፡
ከቅዱስ ቶማስ ፖለቲካዊ ጽሑፎች ውስጥ ይበልጥ የሚታወቀው የሕግ ዓይነቶችን በአራት ዘርፍ መድቦ ያስቀመጠበት “Summa theologiae” የተሰኘ ሥራው ክፍል ነው፡፡ ሕግን አራት መልክ ሲሰጠው ዘላለማዊ ሕግ (Eternal Law)፣ የተፈጥሮ ሕግ (Natural Law)፣ ሰብዓዊ ሕግ (Human Law)፣ እና መለኮታዊ ሕግ (Divine Law) በማለት ነው፡፡
ቅዱስ ቶማስ፣ ሕግን እንደምክንያታዊ ንድፍ (አወቃቀር) አድርጐ ይወስደዋል፡፡ በበላይ እና በበታች ወይም በአዛዥ እና በታዛዥ መካከል ያለ ማንኛውም ግንኙነት፣ የበታቹ ምን ማድረግ እና መሆን እንዳለበት በበላዩ ሕሊና ውስጥ የተቀረጸ ምስልን ያካተተ ነው፤ ይህም አንድ የዕደ-ጥበብ ባለሙያ ምንም ዓይነት ሥራ ከመጀመሩ በፊት ስለሚሰራው የዕደ-ጥበቡ ውጤት በሕሊናው የሚኖረው ሐሳብ እንደማለት ነው፡፡ በገዢ እና ተገዢ መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ፣ ተገዢዎቹ ሊያደርጉ ስለሚገባቸው ነገር በገዢው ሕሊና ውስጥ የሚኖር ሐሳብ ሕግ ብለን የምንጠራው ነው፡፡ ሕግ፣ በሚረቀቅና ይፋ በሚደረግ (በሚታወጅ) ጊዜ የተገዢዎቹን ድርጊቶች የሚመራ (የሚቆጣጠር) «ድንጋጌ እና እርምጃ (ቅጣት)» ነው፤ ተገዢዎቹ ሊያደርጉ (ሊተገብሩ) የሚገባቸውን ሲያደረጉ፣ ጠረጴዛው በአናፂው ሕሊና ውስጥ ካለው የጠረጴዛ ሐሳብ ጋር «ቁርኝት» (participate) እንደሚያደርግበት ተመሳሳይ መንገድ፣ እነሱም ከሕጉ ጋር «ቁርኝት» ያደርጋሉ፡፡
እግዚአብሔር የሁሉም ነገር የበላይ ገዢ (አስተዳዳሪ) በመሆኑ ምክንያት፣ በእርሱ ሕሊና የሚገኘው የአጽናፈ-ሰማይ (ህዋ) (Universe) መንግሥት አወቃቀር እጅግ ጥቅል እና ሁል-አቀፍ በሆነ መልኩ «ሕግ» ነው። ግዙፉን አጽናፈ-ሰማይ ከብጥብጣዊ እና ከምክንያት-የለሽነት ይልቅ፣ ሥርዓታማ እና ተገማችነት ያለው ያደረገው ይህ «ሕግ» ነው፡፡ ይህን ምክንያታዊ አወቃቀር ነው፣ ቅዱስ ቶማስ «ዘላለማዊ ሕግ» በማለት የሚጠራው፤ በዚህ በተፈጠረው ህዋ ውስጥ የሚገኝ ሁሉም ነገር ለዚህ ሕግ ተገዢ ነው፡፡
የሰው ልጅ የህዋ ሥርዓት አካል እንደመሆኑ መጠን፣ ከሰብዓዊ ባሕሪያቱ ጋር ብቻ በተለየ መልኩ ግንኙነት ያለው የዘላለማዊ ሕግ ክፍል መኖሩ ግድ ይላል፡፡ ይህም “የተፈጥሮ ሕግ” ወይም ተፈጥሯዊ ሕግ (lex naturalis) ነው፡፡ እሳቤው እጅግ የጥንት ቢሆንም፣ ቅዱስ ቶማስ ከዚህ ቀደም ባልተገለፀበት ሙልኩ በፍልስፍናዊ ዝርዝር ያስቀምጠዋል፡፡ ሁሉም እንስሳት “ተፈጥሯዊ” ሕግ አላቸው የሚል ጥቅል ግንዛቤ አለ፡- ነገሮችን የሚረዱ ፍጥረታት ሁሉ እራሳቸውን ከአደጋ የመጠበቅ እና ዘራቸውን የመተካት ደመነፍሳዊ የሆነ ምሪት አላቸው የሚል ግንዛቤ።
ነገር ግን የሰው ልጆች ተገዢ የሚሆኑበት ተፈጥሯዊ ሕግ እራስን የማቆየት እና የማብዛት ውስጣዊ ምሪት (instinct) ብቻ አይደለም፡፡ የመመሪያነት ባሕሪይም ያለው ጭምር ነው፤ ምን ማድረግ እንዳለብን ይነግረናል፡፡ መልካምን እንድንሰራና ጥፋትን እንድናስወግድ ይነግረናል፤ ከጐረቤቶቻችን ጋር በሰላም እንድንኖር ይነግረናል፡፡ በተፈጥሯችን መመሪያዎቹ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ግልፅ የሆኑልን ፍጥረቶች ከመሆናችን አንፃር፣ ለእኛ «ተፈጥሯዊ» ነው፡፡ ልንማራቸው ወይም በሕግ መልክ ፀድቀው ሊቀርቡልን አያስፈልግም፤ ሃይማኖት-የለሾችን ጨምሮ፣ በሁሉም ሰብዓዊ ፍጡራን ሕሊና ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡
ታዲያ ይህ ሆኖ ሳለ ሰብዓዊ ሕግ (Human/Positive Law) ሊያስፈልግ የቻለው ለምንድነው? ለዚህም ምክንያቱ፣ የተፈጥሮ ሕግ ድንጋጌዎች ለእኛ ግልጽ ቢሆኑም እንኳ፣ ብቁ በሆነ መልኩ በዝርዝር ሁኔታዎች ላይ እኛን ለመምራት እጅግ ጥቅል ናቸው፡፡ መጥፎውን አስወግደን መልካሙን መሥራት እንደሚገባን እናውቃለን፤ ነገር ግን በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ መልካም ወይም መጥፎ ምን እንደሆነ በትክክል አናውቅም፤ እንዲሁም ጥፋት የሠሩ ሰዎችን ምን እንደምናደርጋቸው ጭምር አናውቅም፡- ምን ዓይነት ቅጣቶች ሊኖሩ ይገባል፤ ቅጣቶቹ የሚጣሉትስ በማን ነው? ሰብዓዊ ሕጐች፣ ከተፈጥሯዊ ሕግ ጥቅል መርሆዎች በተግባራዊ አመክኒዮ የተጨለፉ ዝርዝር ድንጋጌች ናቸው፡፡ በሳይንሳዊ ወይም መላምታዊ አመክኒዮ ከቀዳሚ መርሆዎች እየጨመቅን አንድ ደምዳሜ ላይ ከምንደርስበት መንገድ ጋር ተመሳሳይነት አለው – ከተፈጥሮ ሕግ የሚጨለፉበት መንገድ፡፡
ሁሉም ሰብዓዊ ሕግ የሕግነት ጠባዩን የያዘው ከተፈጥሯዊው ሕግ የመነጨ ከመሆኑ እውነታ ነው፡፡ ሰብዓዊ ሕጐች ከተለዋዋጭ ጊዜያት ወይም ከልዩ ሁኔታዎች ጋር ለመስማማት ሊለወጡ ወይም ሊቀየሩ ይችላሉ። ነገር ግን የተፈጥሮ ሕግ ጥቅል መርሆዎች ሊለወጡ አይችሉም፤ ምንጊዜም ሊከበሩ ይገባቸዋል፡፡ በተመሳሳይ አባባል፣ ከተፈጥሯዊው ሕግ ያልመነጩ “ሕጎች” – ማለትም ተገዢዎቻቸውን የሚጫኑ (የሚጨቁኑ) ወይም የእነሱን መልካም ማረጋገጥ የሚሳናቸው ሕጐች – ጭራሹኑ ሕጐች አይደሉም፤ እናም እኛ ለእነሱ ተገዢ የመሆን ግዴታ የለብንም። ቅዱስ ቶማስ እንደሚለው፣ ከሕግነት ይልቅ የኃይል (የጉልበት) ጠባይ አላቸው፡፡
እናም እዚህ ላይ ከጨቋኝ የመንግሥት ሥርዓት (tyranny) ጋር በተያያዘ ቀደም ብለን የተመለከትነው ተመሳሳይ ሁኔታ ይነሳል፡፡ አለማክበራችን የሚያስከትለው ውጤት፣ ባለማክበር ከምናረጋግጠው ከማንኛውም ጥሩ ነገር የከፋ በሚሆንበት ጊዜ ኢ-ፍትሃዊ ወይም ጨቋኝ (tyrannical) ሕጐችንም ቢሆን ልናከብራቸው ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም ጥያቄ የሚያስነሱ “ሕጐች” በትክክልም ሕጐች ባለመሆናቸውና ማስገደድ ስለማይችሉ እነሱን የማክበር ግዴታ የለብንም፡፡ (ይህ ነጥብ በላቲን ቋንቋ ሲገለፅ ይበልጥ ግልጽ ነው፤ “lex” ወይም “ሕግ” ከስርወ-ቃል አንፃር “ligare” ወይም “ለማስገደድ” ከሚለው ቃል ጋር የተዛመደ እንደመሆኑ፡፡)
አራተኛው እና የመጨረሻው የሕግ ዓይነት “መለኮታዊ ሕግ” ነው፡፡ መለኮታዊ ሕግ፣ ይበልጥ ጥቅል ከሆኑት ተፈጥሯዊ መርሆዎች በምክንያታዊ የማጣቀሻ ሂደት የመጣ ባለመሆኑና ተቀባዮቹ የማይመረምሩት (ለምን ሆነ የማይሉት) በመሆኑ ምክንያት ከሰብዓዊ ሕግ ጋር ይለያያል፡፡ የዘላለማዊ ሕግ አንድ አካል ነው፤ ነገር ግን በቅዱሳን መፅሐፍት ትምህርቶች እና በቤተ-ክርስቲያን አማካኝነት ልናገኘው እንድንችል የተደረገ የራዕይ ሕግ (Law of Revelation) ነው፡፡
ምክንያታዊ ፍጡራን ከተፈጥሮ እና ከሰብዓዊ ሕጐች በተጨማሪ በራዕይ የተገለጠ ሕግ ስለምን ያስፈልጋቸዋል? ለዚህም ምላሹ፣ ሰብዓዊ ሕግ የሚያተኩረው በውጫዊ ሁኔታዎች ክንውን ላይ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል ዘላለማዊ ድህነት (ፅድቅ) ውስጣዊ የሞራል ልዕልና እንዲኖረንም ሆነ ውጫዊ ተገዢነት (ሕግ አክባሪነት) እንዲኖረን ይጠይቀናል። መለኮታዊ ሕግ ውስጣዊ ህይወታችንን ይቆጣጠራል፤ ማንም ሊመለከት የማይችላቸውን ተግባራት ይቆጣጠራል፤ እንደወንጀለኞች ሳይሆን፣ እንደ ኃጥያተኞች ቅጣቶችን በእኛ ላይ ይጥላል፤ ከሕዝባዊ ይልቅ ሃይማኖታዊ በሆኑ ግዴታዎች ይመራናል፡፡
ስለዚህም በጥቅሉ ሲታይ፣ የቅዱስ ቶማስ የሕግ ፅንሰ-ሐሳብ “ቮለንተሪስት” (ለምንም ነገር መሠረቱ ፈቃድ /will/ ነው የሚል አስተምህሮ) ሳይሆን፣ “ኢንቴሌክችዋሊስት” (ምክንያታዊነት (rationalisim) ላይ መሠረት ያደረገ አስታምህሮ) ዓይነት ነው፡፡ ሕግ ከሞራል አንፃር ወሳኝ የሆኑ ባሕሪያቱን ያገኘው ጠቅልሎ ከያዘው ምክንያታዊ ይዘት እንጂ፣ ከሕግ አውጪው ፈቃድ ወይም ሥልጣን እንዳልሆነ ቅዱስ ቶማስ ያስባል፤ ከተፈጥሮ ሕግ የሚለያዩ የሕግ አውጪው አዋጆች እንዲሁ በቀላሉ የሕግነት ባሕሪይ የላቸውም፡፡ እወጃ እና ትዕዛዝ መስጠት ሕግን እውን የማድረግ ወሳኝ ክፍሎች ሲሆኑ፣ መጥፎ ሕጐችም እንኳን ቢሆኑ ሕጐች ናቸው የሚል መደበኛ ወይም ቴክኒካዊ ግንዛቤ አለ፤ ነገር ግን ተፈጥሮን የሚፃረርን ነገር የሚይውጅ ወይም ትዕዛዝ የሚሰጥ ማንም ሰው በትክክለኛው መንገድ ሕግን አይፈጥርም፡፡ ከሁሉም በላይ፣ ሕግ የሚኖረው ዋጋ እና ተቀባይነት ዘላለማዊ እና ከማይቀያየሩ የሞራል መርሆዎች ጋር መጣጣሙ ላይ መሠረት ያደርጋል፡፡
ገና ከመነሻው የሮማ ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ከፊል-ይፋዊ ፈላስፋ የመሆኑ እውነታ፣ ቅዱስ ቶማስን ከትችት ጠብቆታል፡፡ በተወሰነ መልኩ እንደፈላስፋ ከሚገባው በላይ ቦታ ተሰጥቶት ቆይቷል፡፡ የእርሱን ሥነ-ጽሁፋዊ ስልት ለመረዳት ከባድ ነው፡፡ በማብራራት ሂደት ላይ ሳለ ትኩረቱ በጐንዮሽ ጉዳዮች ይሰረቃል፡፡ መከራከሪያዎቹ አላስፈላጊ የሆኑ ዝርዝሮችና አንዳንድ ጊዜም አነስተኛ ልዩነቶች ብቻ የዳመናቸው ወደመሆን ያዘምማሉ። ለሃይማኖታዊ እና ለሞራላዊ እምነቶች ጥብቅ ሥርዓት አስቀድሞ ቁርጠኝነቱን ያሳያል፤ “ፍስፍናዊ” መከራከሪያዎቹም እነዚያን እምነቶች በመደገፍ እና በማረጋገጥ መልኩ የታቀዱ (የተቃኙ) ናቸው፡፡ ይህን ካልን ዘንዳ፣ ትጉህነቱንና ጥንቁቅነቱን፣ እንዲሁም የፍልስፍናዊ አስተሳሰቡን የጥልቅነት መጠን ሳናደንቅ ማለፍ አይቻለንም፡፡ በተለይም ፖለቲካዊ ፍልስፍናን በተመለከተ ሦስት ነጥቦችን ልናነሳ እንችላለን፡፡
በመጀመሪያ፣ የአርስቶትልን የፖለቲካ እና የሥነ-ምግባር እሳቤ ለላቲን ቀመሱ ምዕራብ ዓለም ወደ ትምህርታዊ መርሀ-ግብር ውስጥ ዳግም እንዲተዋወቅ በማድረጉ ረገድ (ብቻውን ሊባል ባይቻል እንኳን) ቅዱስ ቶማስ ተጠሪነቱን ይወስዳል፡፡ ይህ በራሱ ጉልህ ቦታ የሚሰጠው እውነታ ነው። በሁለተኛ ደረጃና እንዲሁም የአርስቶትል መልሶ ህይወት መዝራት ቀጥተኛ ውጤት በመሆን፣ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴን እና ተሳትፎን ከቤተ-ክርስቲያን ጋር ሳያያይዛቸው እንደጠቃሚ እንቅስቃሴዎች በስፋት በመገምገሙ ረገድም ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ ከዚህ አኳያ «ዘመናዊ» መደበኛ የፖለቲካ ፅንሰ-ሐሳብ እንዲኖር እገዛ አድርጓል ማለትም እንችላለን፡፡ ሦስተኛ፣ ምንም እንኳን እሱ ራሱ “ቤተ-ክርስቲያን እና መንግሥት” በሚለው ጉዳይ ላይ ሰፊ ምልከታ ከመስጠት ቢቆጠብም፣ እርሱን ተከትለው የመጡት በአውሮፓውያን የፖለቲካ ጽሁፎች ውስጥ የነበረውን መሠረተ-ጥንት የኢ-ሃይማኖታዊ (secular) እና የመንፈሳዊ ጭብጦች ትስስር (ቁልፍልፍ) መፍታት የጀመሩበትን ምሁራዊ መሣሪያ አስቀምጧል፡፡ እነዚህ እውነታዎች ቅዱስ ቶማስ በፖለቲካ እሳቤ ታሪክ ከመጀመሪያው ረድፍ እንዲመደብ ያስችሉታል፡፡
ለበለጠ ንባብ
ቀዳሚ ምንጮች፡
St Thomas Aquinas: Political Writings, ed. R.W. Dyson (Cambridge: Cambridge
University Press, 2002).
ተቀፅላ ምንጮች፡
Coleman, J.: A History of Political Thought, vol. 2 (Oxford: Blackwell, 2000).
Finnis, J.: Aquinas: Moral, Political and Legal Theory (Oxford: Oxford University Press, 1998).
McInerny, R.: Ethica Thomistica: The Moral Philosophy of Thomas Aquinas (Washington, D.C.: Catholic University of America, 1982).
O’Connor, D.J.: Aquinas and Natural Law (London: Macmillan, 1967).
Weisheipl, J.: Friar Thomas d’Aquino: His Life, Thought and Works (Oxford: Blackwell, 1974).