Ankuar

Politics, culture and society in Ethiopia

FEATUREDአንኳሮች

ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድርጅት የሚከፈለው 50 ብር ምንድነው?

ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድርጅት የሚከፈለው 50 ብር ምንድነው?

By Gizaw Legesse
(ጥቅምት 17 ቀን 2002 ዓ.ም አውራምባ ታይምስ ቁጥር 87 ዕትም)

የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት (ኢሬቴድ) በተለይ ባሳለፍነው ዓመት አካባቢ ከፍተኛ ቅስቀሳ ላይ ነበር። «ቴሌቪዥናችሁን አስመዝግቡ፤ ዓመታዊውን ክፍያ ፈጽሙ።» በከፍተኛ የቅስቀሳ ስትራቴጂም በጥቂት ወራት ውስጥ ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች ብቻ 50 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡ ተነገረ። 50 ብር መጣም ቀረ እምብዛም የማያስጨንቀው ሰው ይኖራል። በዚያው ልክም የምንዱባን አገር ነንና የ50 ብር ጉዳይ የሚያሳስበንም ሞልተናል። ይሁንና ግን የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ከገንዘብ መጠኑ ጋር ንክኪ የለውም፤ የኢትዮጵያ ህዳሴ መበሰርንም አይቃወምም። ይልቁንስ ድርጅቱ በየዓመቱ የሚሰበስበው 50 ብር (በነፍስ ወከፍ) መሠረቱ ምንድነው? እና በተያያዥ አዋጆችስ አግባብነት አለው ወይ? የሚለውን ይመለከታል፡፡

ሁሉም ማለት ቢቻልም፣ አብዛኛው ሕዝብ እንደሚያስበው ይህ ክፍያ ከግብር ጋር ተያያዥነት ይኖረው ይሆን? ወይንስ ለሚሰጠን አገልገሎት የሚጠበቅብን የአገልግሉት ክፍያ ነው? በየዓመቱ መክፈላችን ከፈቃድ እደሳ ጋር የሚያገናኘው መንገድ እንዳለስ? አነዚህን ጥያቀዎች ለመመለስ ሚዛናዊነትን ለማሟላት የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ድረስ መሄድ ሳያስፈልገን ከድርጅቱ በላይ የሆነውን፣ ድርጅቱን ያቋቋመውን አዋጅና ተያያዥ ሕጎች መሠረት በማድረግ ብቻ የሚከተለውን ዳሰሳ ልናቀርብ ተገደናል።

የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን አገልግሎት ድርጅት ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመው በደርግ ዘመነ መንግስት በትእዛዝ ቁጥር 50/1960 አማካኝነት በ1960 ዓ.ም ነው። ከዚያም የድርጅቱን ሥልጣን ለመወሰን «የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን አገልገሎት ድርጅት አዋጅ ቁጥር 15/1967» የተሰኘውን ሕግ የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደሩ ምክር ቤት በጥር ወር 1967 ዓ.ም አፀደቀ። ቀጥሎም በተመሳሳይ ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ተመሳሳዩን አዋጅ ለማስፈፀም በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር በነበሩት ሜጀር ያቆብ ገብረ አግዚአብሔር ፊርማ «የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን አገልግሎት ድርጅት ደንብ ቁጥር 20/1967» ወጣ።

የደርግ ዘመነ መንግስት አበቃ። እናም የሸግግር መንግስቱ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትን በአዲስ መልክ በማዋቀር የድርጅቱን የሥራ አድገትና ቅልጥፍና በተሻለ መንገድ እንዲራመድ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በማመኑ ከሃያ ዓመታት በኋላ በሕገመንግስት ጉባኤ የመሸጋገሪያ ውሳኔ መሠረትና በወቅቱ የሽግግር መንግስቱ ፕሬዝዳንት በነበሩት በአቶ መለስ ዜናዊ ፊርማ በ1987 ዓ.ም አዲስ አዋጅ ታወጀ። ይህ አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው አዋጅ «የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 114/1987» ይሰኛል። ኋላ ላይ የምንመለስበት ቢሆንም፣ የዚህ አዋጅ አንቀጽ 114 ተፈፃሚነት ስለሚኖራቸው ሕጎች ሲያወሳ አስቀድመን የጠቀስናቸው የደርግ ዘመነ መንግስት ሕጎች፣ ማለትም አዋጅ ቁጥር 15/1967 እና ደንብ ቁጥር 20/1967 እንደ አግባቡ በድርጅቱ ላይ ተፈፃሚነታቸው መቀጠሉ ልብ ይባል፤ የተሰመረበት ቃልም እንደዚያው። ከዚህ በኋላ ይህንን ማቋቋሚያ አዋጅ ለማሻሻል በ1989 ሌላ ሕግ የወጣ ቢሆንም ከርዕሰ ጉዳያችን ጋር ተያያዥነትን አንደሌለው በማረጋገጣችን ለዛሬ ተነሺነት አይኖረውም።

የ50 ብሯ ጉዳይ ከነዚህ አዋጆች አታልፍምና አንድንከፍላት መጠየቃችን ለግብር ይሁን ለሚሰጠን አገልግሉት፣ አልያም ለፈቃድ ማደሻ የሚለውን ወደማወቁ እናምራ።

ግብር

እሩቅ ከመሄዳችን በፊት የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትን በአዲስ መልክ ባዋቀረው የ1987 አዋጅም ሆነ የ1967 አዋጅ አና ደንብ ውስጥ «ግብር» የሚለው ቃል እንዳልተጠቀሰ እናስታውስዎ። ሆኖም ለድርጅቱ የሚከፈለውን ገንዘብ ግብር ከመሰብሰብ ጋር ለሚያያይዙት ሰዎች ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ አንድ ግለሰብ ንብረት (ቴሌቪዥን) ስላለው ብቻ ግብር አንደማይጠየቅ ማስገንዘብ ግድ ነው።

አንድ መንግስት ዋናው የበጀት ምንጩ ከህዝብ የሚሰበሰበው ግብር ነው (ወይም ሊሆን ይገባል)። ማንኛውም ዜጋ በመቀጠርም ሆነ በመነገድ ከሚየገኘው ገቢ ለመንግስት ግብር ሊከፍል ይገባዋል። አንዲሁም ንብረቱን በማከራየትም ሆነ በሌላ መንገድ ለሚያገኘው ገቢ ግብር መክፈል ሲጠበቅበት ንብረቱን በመጠቀሙ ግን የሚከፍለው ሳንቲም አይኖርም። ለምሳሌ ቤታችን ያለውን፣ በገንዘባችን የገዛነውን ወንበርና ጠረጴዛ በመጠቀማችን ክፍያ የሚጠይቀን አይኖርም፤ ወንበርና ጠረጴዛው ባለቤትነቱ የሌላ ሰው ሆኖ በኪራይ የምንጠቀምበት ካልሆነ በቀር። ቴሌቪዥንም ከሌሎች ንብረቶች የሚለይበት ጽኑ ምክንያት ባለመኖሩና ባለቤትነቱ የግለሰቡ በመሆኑ ግለሰቡ ቴሌቪዥኑን አከራይቶ ወይም ሽጦ ገቢ (ትርፍ) እስካላገኘበት ድረስ ግብር አይጠየቅም።

ጉዳዩን በሌላ መልኩ ስንቃኘው፣ በፌደራሉ የመንግስት አወቃቀር (ኢሬቴድ በፌደራል መንግስቱ ስር በመሆኑ) ግብር የመሰብሰብ ስልጣን ለየትኛው የመንግስት መሥሪያ ቤት የተሰጠ ነው? የፌደራል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሥራው ምንድነው? ይህ በአንዲህ እንዳለ፣ ወደ ኢፌዴሪ ሕገመንግስት በማምራት የፌዴራል መንግስቱንና የክልል መስተዳደሮችን የግብር አሰባሰብ ሥልጣን ስንመለከት ንብረትን በመጠቀም ግብር የሚከፈልበት ሁኔታ ባይጠቀስም በንብረት አማካኝነት ከሚመነጭ ገቢ ግብር የመሰብሰብ ሥልጣን እንኳን ለክልል መስተዳደሮች የተሰጠ ነው። (አንቀጽ 96 እና 97 (6) ይመልከቱ።)

እንዲሁ አጽንኦት ለመስጠት ፈልገን አንጂ ከላይ የጠቀስነው በቂ ነበር – በሦስቱም ሕጐች ስለግብር አልተነሳም፤ ሊነሳም  አይችልም። ስለዚህ ለኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን የሚከፈለው 50 ብር ግብር አለመሆኑንና ከነጭራሹ ከግብር ጋር የተያያዘ አለመሆኑን ህብረተሰቡ አንዲገነዘብ እንፈልጋለን።

አገልግሎት

የ1987 የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ማቋቋሚያ አዋጅ የድርጅቱን ሥልጣን እና ተግባር በሚዘረዝርበት አንቀጽ 3 (10) ድርጅቱ «ለሚሰጠው አገልግሉት ዋጋ ያስከፍላል፤ እንደአስፈላጊነቱ በከፊል ወይም በሙሉ ከክፍያ ነፃ ያደርጋል» ሲል ይደነግጋል፡፡ ከዚህም የሚሰበሰበው የአገልግሎት ክፍያ ከድርጅቱ የበጀት ምንጮች አንዱ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

አዋጁ «የአገልግሎት ክፍያ» ማለቱ ድርጅቱ ለሚያሰራጫቸው ፕሮግራሞች ሊከፈለው የሚገባ ክፍያን ከሆነ ከብዙ ነባራዊ እውነታዎች ጋር የሚጋጭ ይሆናል። የመጀመሪያውና በሁላችንም ዓይምሮ ውስጥ የሚከሰተው ጥያቄ «ድርጅቱ

የሚያሰራጫቸው ፕሮግራሞች ነፃ አይደሉም እንዴ?» የሚለው ነው። ለዚህ ጥያቄ መነሻው የድርጅቱ ፕሮግራሞች «በሳተላይት ዲሽ» ነፃ ፕሮግራሞች ተብለው ያለክፍያ ከሚታዩት ውስጥ መመደባቸው ነው። በርግጥ በቴሌቪዥን አንቴና ተጠቅሞ ፕሮግራሞቹን የሚከታተል ሰው የፕሮግራሞቹን በነፃ መተላለፍ አይገነዘብ ይሆናል፤ ባለመገንዘቡ ግን ክፈል ሊባል አይገባውም። አልያም ደግሞ በሳተላይት ዲሽ ለሚመለከቱ ነፃ፣ በቴሌቪዥን አንቴና ለሚመለከቱ በክፍያ ልንል ነው።

የድርጅቱ ፕሮግራሞች ነፃ ስለመሆናቸውና ህዝቡ የሚከፍለው 50 ብር የአገልግሎት ክፍያ አለመሆኑን ለማሳየት በሳተላይት ዲሽ ነፃ ተብለው መሰራጨታቸው ማረጋገጫ ወይም ማሳመኛ አይሆንም ከተባለ ደግሞ ወደሚቀጥለው እንቀጥል። ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ ሌላ አገልግሎት ሰጪ የመንግስት ተቋምን እንደምሳሌ እናንሳ – የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን።

ቴሌ የስልክ መስመሮችን በመዘርጋት ከዘመድ አዝማዶቻችን ጋር እንድንገናኝ ያደረገበትን አገልግሎት ይሰጠናል። ይሄን ያህል አገልግያችኋለሁ ሲለን ይሄን ያህል እንከፍለዋለን። ቴሌ አገልግሎት እንዲሰጠን፣ እኛም የአገልግሎት ክፍያውን በአግባቡ እንድንፈጽም የሚያደርገን ወይም የሚያስገድደን አንድ ነገር በመካከላችን አለ — ውል (contract)፡፡ ውል በተዋዋዮቹ መካከል አንደ ሕግ ይሰራልና የሚጠበቅብንን ካልከፈልን ወይም የሚጠበቅበትን ካላገለገለን እኛና ቴሌ ፍርድ ቤት እንቆማለን፤ ተፈቃቅደን የተዋዋልነው በመሆኑም በውላችን መሠረት እንዳኛለን። ታዲያ አኛና የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት አገልግሎት ለመስጠትና ለመቀበል የተዋዋልነው ውል አለን? የተዋዋለ ካለ በውሉ መሠረት የአገልግሉት ይክፈል። ያልተዋዋለ ሰው ግን አሁን በዓመት 50 ብር አየከፈለ የሚገኘው የአገልግሎት ክፍያ አይደለም።

እሺ፣ ቴሌስ የደወልንበትን ቦታና ደቂቃ አስልቶ ይህን ያህል ክፈሉ ይለናል፣ 24 ሰዓት የኢሬቴድ ፕሮግራሞችን የኮመኮመው እና «አል ጃዚራን» ወይም በዲቪዲ አማካኝነት የሆሊውድ ፊልሞችን መመልከት የመረጠው በምን ሂሳብ ነው እኩል 50 ብር የሚጠየቁት? ክፍያው አገልግሎት ነው ከተባለ በተገለገልነው መጠን መክፈል አይገባንም ነበር?

አንዳንድ ጊዜ ያለውል በግዴታ (ወይም በውዴታ ግዴታ) የምንቀበላቸውና የምንሰጣቸው አገልግሎቶች አሉ። ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ሲባል የብሔራዊ አገልግሉት (ውትድርና) መስጠት ሊጠበቅብን ሲችል በሌላ መልኩ ደግሞ ወረርሽኝም ሆነ ሌላ በሽታን ለመከላከል የክትባት አገልግሉት ሊሰጠን ይችላል። የያዝነው ርዕሰ ጉዳይ ግን ከሁለቱም ወገን አይመደብም።

ሌላ ምሳሌ፣ ለዘመኑ ምስጋና ይግባውና «ቲቪ ካርድ» – በኮምፒዩተር ቴሌቪዥን መመልከት የሚያስችል፤ አንዲሁም ተንቀሳቃሽ ስልክ ሆኖ ቲቪ ቻናል ያለው ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ የድርጅቱን ፕሮግራሞች የሚከታተል ሰው የአገልግሎት አለመጠየቁ 50 ብሯ የአገልግሉት አለመሆኗን ያስረዳል።

ይህ «የአገልግሎት ክፍያ» ሲል ያስቀመጠው የ87 አዋጅ ክፍያው 50 ብር ስለመሆኑ፣ በምን ስሌት አንደሚቀመርም ሆነ በስንት ጊዜ እንደሚከፈል የገለፀው ነገር የለም። ታዲያ እቺ 50 ብር ከየት መጣች ቢባል ከ1967 የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን አገልግሉት ድርጅት ደንብ ቁጥር 20/1967 መሆኑን እንመለከታለን፡፡ እዚህ ላይ ከወደላይ ያሰመርንባትንና ኋላ እንመለስባታለን ያልናትን «እንደ አግባቡ» የተሰኘችውን የ87 አዋጅ አንቀጽ 14 ቃል ልናነሳት ነው፤ ወደኋላም እንደ አግባቡ እንጠቀማታልን።

የ1967 ሕጎች ተፈፃሚነታቸው «እንደ አግባቡ» ነው ስንል በ87 አዋጅ ላይ ከተቀመጡ ድንጋጌዎች ጋር የሚስማሙና በአዲሶቹ ድንጋጌዎች ንፍቀክበብ ውስጥ የሚገኙ፣ እንዲሁም ለአዲሶቹ ድንጋጌዎች አተገባበር አስፈላጊነታቸው ጉልህ የሆነ አንቀፆቻቸው አልተሻሩም፣ አሁንም በሥራ ላይ ናቸው ማለታችን ነው። ስለዚህ «የአገልግሎት ክፍያ» የሚለውን የ87 አዋጅ ድንጋጌ መነሻ በማድረግ በ67 ሕጎች ውስጥ እንደ አግባቡ ተፈፃሚ የሚሆኑ አንቀፆችን እንፈልግ፤ በዚያውም የ50 ብርን ምንጭ እንመልከት።

በደርግ ዘመነ መንግስት ድርጅቱ በአዋጅ ቁጥር 15/1967 አንቀጽ 3 (4) ላይ «ለሚሰጠው ፈቃድና በቴሌቪዥንና በራዲዮ ፕሮግራም ውስጥ ለሚሸጠው ጊዜ የአገልግሎት ዋጋ ለመወሰንና ለመሰብሰብ» ሥልጣን ተሰጥቶት ነበር:: በሚቀጥለው ርዕስ የምንመለከተው የፈቃድ ጉዳይ አንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ አዋጅ መሠረት ድርጅቱ በቴሌቪዥን የመጠቀም ፈቃድ እንዲሰጥ ሥልጣን ስለተሰጠው ከአየር ጊዜ ሽያጭ በተጨማሪ ፈቃድን አስመልክቶ ክፍያ አንደሚሰበስብ ይህ ድንጋጌ ያስረዳል። ይህ አንቀጽ ስለ ሁለት ክፍያዎች ብቻ ስለማውራቱ ልብ ይሏል።

የ50 ብር ነገር ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ የተነሳው ግን ይህንን የአዋጁን አንቀጽ ለማስፈፀም በተደነገገው የደንብ ቁጥር 20/1967 አንቀጽ 5 (3) ላይ ነው። ይሁንና ይህ ድንጋጌ 50 ብሩ ፈቃድ የመስጠት አገልግሎትን የተመለከተ እንጂ የፕሮግራም ስርጭትን እንዳልሆነ ይነግረናል:- «ማንኛውም የቴሌቪዥን ባለቤት ወይም ባለይዞታ ፈቃድ ሲሰጠው ሃምሳ (50) ብር የአገልገሎት ዋጋ በየዓመቱ ለመዝጋቢው ባለስልጣን ይከፍላል።» እናም በዚህ ጉዳይ ላይ የ67 ሕጎችን ተፈፃሚ ልናደርጋቸው አይቻለንም። በዚህ ምክንያት ለድርጅቱ እየከፈልን የምንገኘው የአገልግሎት ሊሆን አይችልም፡፡

ስለዚህም የድረጅቱ የፕሮግራም ስርጭት ነፃ በመሆኑ፣ ከድርጅቱ ጋር አገልግሎትን በተመለከተ የተዋዋልነው ውል ባለመኖሩ፣ አንዲሁም በ67 ሕጎች መሠረት ቢሆን እንኳን 50 ብሩ የሚከፈለው ፈቃድን አስመልክቶ በመሆኑ በየዓመቱ እንድንከፍል የሚጠበቅብን ገንዘብ የአገልግሉት አይደለም። ታዲያ አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው የ87 አዋጅ «የአገልግሎት ክፍያ» ሲል ፈቃድ የመስጠት አገልግሎት ይሆን?

ፈቃድ

የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን አገልግሎት ድርጅት በ1960 በትዕዛዝ ከተቋቋመ በኋላ በ1967 ሥልጣኑን ለመወሰን አዋጅ ቁጥር 15/1967 እንደወጣለት ከላይ ተመልክተናል። እናም በዚህ አዋጅ አንቀጽ 3 (1) መሠረት የቴሌቪዥን ባለቤትነትን ወይም ባለይዞታነትን የመመዝገብና ፈቃድ የመስጠት ሥልጣን ተሰጥቶት ነበር። ከሁሉም በላይ ደግሞ ይህንን አዋጅ ለማስፈፀም የወጣው ደንብ ቁጥር 20/1967 በአንቀጽ 7 ላይ «ማንኛውም ሰው በዚህ ደንብ መሠረት ፈቃድ ካልያዘ በቀር በቴሌቪዥን መጠቀም አይችልም» ይላል። /መስመር ተጨምሯል/

ነገር ግን የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በ1987 በአዲስ መልክ ሲቋቋም በአስራ ሁለት ንዑስ አንቀፆች የተዘረዘሩ ሥልጣንና ተግባራት በአዋጅ የተሰጡት ሲሆን ፈቃድ የመስጠት ሥልጣን አልተካተተም። አሁን በሥራ ላይ በሚገኘው በ87 አዋጅ የድርጅቱን ሥልጣንና ተግባር የሚዘረዝረው አንቀጽ ከጅማሬው «ድርጅቱ የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባሮች ይኖሩታል» ሲል ሥልጣንና ተግባሮቹ የተዘረዘሩት ብቻ ወይም “Exhaustive” መሆናቸውን ያመላክተናል። ከነዚህ ውጪ ሥልጣንም ተግባርም የለውም።

ይሁንና ግን የ1967 ሕጎች አንደ አግባቡ ተፈፃሚ ስለመሆናቸው በዚሁ አዋጅ ላይ መደንገጉ ክፍተትን የሚያመቻች ስለሚመስል በነዚህ ሕጎች ተሰጥቶት የነበረው ፈቃድ የመስጠት ሥልጣን አሁንም እንደሚቀጥል ተደርጉ በስህተት ሊወሰድ ይችላል። ሆኖም ከላይ ለማብራራት እንደሞከርነውም፣ የ67 ሕጎች የድርጅቱን ሥልጣንና ተግባር በተመለከተ ተፈጻሚነታቸው እንደ አግባቡ ወይም በ87 አዋጅ ከተዘረዘሩት ሥልጣንና ተግባሮች በተያያዘ ብቻ ነው። ይህንን ካስገነዘብን፣ ድርጅቱ በቴሌቪዥን ስለመጠቀም ፈቃድ የመስጠትም ሆነ የፈቃድ ማደሻ ገንዘብ የመቀበል ሥልጣኑ ከ1987 ዓ.ም በኋላ ቀርቷል። ማለትም 50 ብሩ ከፈቃድ አደሳ ጋር አይገናኝም። ሆኖም «የ1967 ሕጎች ተፈፃማነት አላቸው» ቢባል እንኳን ድንጋጌዎቹ የሕግነት መርህን ያልተከተሉ መሆናቸውን፣ በዚህም ምክንያት የተሻሩ መሆናቸውን ማስገንዘብ ተገቢ ነው።

በቴሌቪዥን ለመጠቀም ፈቃድ ማግኘት ከሚጠይቀው የደንብ ቁጥር 20/1967 ድንጋጌ እንጀምር። «ማንኛውም ሰው በዚህ ደንብ መሠረት ፈቃድ ካልያዘ በቀር በቴሌቪዥን መጠቀም አይችልም» ይላል። እዚህ ላይ ድንጋጌው በቴሌቪዥን መጠቀምን ወይም የቴሌቪዥን ባለቤት መሆንን አልከለከለም፤ ነገር ግን በቴሌቪዥን ለመጠቀም ፈቃድ ማግኘትን ይጠይቃል። ከድንጋጌው መንፈስና ሕጉ ከወጣበት ዘመን አንፃር «መጠቀም» የሚለው ቃል ምንን ያመለክታል? በዚያን ወቅት ቪሲዲ፣ ዲቪዲ፣ ሳተላይት ዲሽ የመሳሰሉት የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመታደም ባለመታደላችን ሳይሆን አይቀርም ቴሌቪዥን ያለው

ሰው ቴሌቪዥኑን የሚጠቀምበት በኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን አገልግሉት ድርጅት የሚሰራጨውን ፕሮግራም ለመመልከት ብቻ አንደሆነ አድርጐ ቅድመ ግምት (presumption) ይወስዳል፤ ይህ ቅድመ ግምት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ውድቅ ሊሆን ቢችልም። እናም ያን ጊዜ ድርጅቱ ፈቃድ የመስጠት ሥልጣን የተሰጠው የደርግ ሥርዓት ሆነና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞቹን በመከታተል ረገድ ብቻ እንጂ በአሁኑ ዘመን ያሉትን የቴሌቪዥን ጥቅሞች እንደማይመለከት መረዳት ይቻላል።

የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በሬዲዮ አማካኝነት ለሚሰራጨው ፕሮግራሙ ፈቃድ እና ክፍያ ለምን አልጠየቀም? ለዚህ ትክክለኛው ምላሽ ህዝቡ ቀድሞውኑ በሬዲዮ የድርጅቱ ያልሆኑ ፕሮግራሞችን ይከታተል ስለነበር ነው። የወቅቱ ሕግ ለሬዲዮ አጠቃቀምም ፈቃድ ቢጠይቅ ኖሮ የድርጅቱ ላልሆኑ ፕሮግራሞችም ድርጅቱን ፈላጭ እና ቆራጭ ማድረግ ስለሆነበት ነው።

ታዲያ በዚህ በሰለጠነና ህዳሴውን በምናበስርበት ዘመን የቴሌቪዥን ጥቅሙ የድርጅቱን ፕሮግራሞች ማሰራጨት ብቻ ይመስል ስለምን ፈቃድ እንድንይዝ እንጠየቃለን? ቀድሞውኑ ይህንን የሚለው ሕግ ለረጅም ዘመን የማስተዳደር ብቃትን ባለመላበሱ የሕግነት መርህን ከመቃረኑ በላይ አዳዲስ ሁኔታዎች በሚከሰቱበት ጊዜ እርሱ ተሽሮ ሌላ አስተዳዳሪ ሕግ ሊተካለት ይገባ ነበር። በአኛ አመለካከት በ1987 ድርጅቱን በአዲስ መልክ ያቋቋመው አዋጅ በቴሌቪዥን ስለመጠቀም ፈቃድ የጠቀሰው ነገር ያለመኖሩ ዋነኛው ምክንያት ያ ይመስለናል።

በመሠረቱ «ፈቃድ» ምንድነው፣ ለምንስ ያስፈልጋል? አንዳንድ ነገሮችን የሚሰራ ወይም የሚጠቀም ሰው ለሦስተኛ ሰው የሚሰጠውን ግልጋሎት ለመቆጣጠር (ጤና ጥበቃ የሚሰጠው ዓይነት ፈቃድ)፤ ሕጋዊነትን ለመቆጣጠርና ተገቢውን ግብር ለመሰብሰብ (የንግድ ፈቃድ)፣ እንዲሁም ለአጠቃቀሙ እውቅና ለመስጠትና ፀጥታ ለማስፈን (ጦር መሳሪያ የመያዝ ፈቃድ) ከመንግስት ፈቃድ ማግኘት ይጠበቅበት ይሆናል። አንድ ግለሰብ በወንበሩ ለመጠቀም ግን ፈቃድ መጠየቅ አያስፈልገውም፤ በቴሌቪዥን መጠቀምም ከዚህ አይለይም። ግለሰቡ ቴሌቪዥን 24 ሰዓት ሙሉ መጠቀሙ ከሰፊው በንብረት የመጠቀም መብት አንዱ ተግባራዊ መሆኑ ነው። ይህንን ስንመለከት በርግጥ የ1967 ሕጎች መሻር ይገባቸው ነበር ያስብለናል። ከዚህም በላይ ድርጅቱ ፈቃድ የሌለውን ቴሌቪዥን ባገኘ ጊዜ ባለቤቱ በሦስት ወር ውስጥ የሚከፈለውን ካልከፈለ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በሐራጅ የመሸጥ መብት የሚያጎናፅፈውን የ67 ሕግ ስንቃኝ ለመሻሩ እርግጠኞች እንሆናለን።

በዚህ በኑሮ ውድነት ከጥራጥሬ እስከ ፍራፍሬ፣ ከቤት እቃ እስከ ቢሮ እቃ፣ ከመለዋወጫ እስከ ነዳጅ የሁሉም ነገሮች ዋጋ በአጥፍና በሦስት አጥፍ ጨምሮ አቺ 50 ብር ግን ለ35 ዓመታት ንቅንቅ አለማለቷ ምክንያቱ ምን ይሆን? ምክንያቱ አንድና አንድ ነው – የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት እንኳንስ ዋጋ የሚጨምርበት ቀርቶ 50 ብሯን የሚያስከፍልበት የሕግ መሠረት አልነበረውም።

ሆነም ቀረ አሁን በሚሰራው የ፲987 አዋጅ መሠረት ድርጅቱ ፈቃድ የመስጠትም ሆነ 50 ብር የመቀበል ሥልጣን አልተሰጠውም፤ የ1967 ሕጎችም ተፈፃሚነት አግባብ የሌለው ነው። ታዲያ በየዓመቱ የሚከፈለው ወይም እንዲከፈል የሚጠበቀው 50 ብር ግብር ካልሆነ፣ የአገልግሉት ካልሆነ፣ አልያም የፈቃድ እድሳት ካልሆነ የምንድነው? እኛ «መልስ የለውም» ብለነዋል። ከመግቢያችን ላይ እንደገለፅነው 50 ብር በዝቶ ወይም አንሶ አይደለም፤ የሕግ አግባብ ፈልገን አጣንለት እንጂ። ጉዳዩን እኛ በዚህ መልኩ ተመልክተነዋል፤ ይህ ድምዳሜም የእኛ ብቻ ነው። ነገር ግን የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ነገሩን አጢነውት ምላሽ ቢሰጡበት ምኞታችን ሲሆን ህዝቡ ለሚከፍለው ገንዘብ ምክንያቱ ሊነገረው ይገባል ስንል እንደመድማለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.