FEATUREDPoliticsአንኳሮችፖለቲካ/ፍልስፍና

“መንግሥት በራሱ ሕዝቦች ሊወገድ የሚችል መሆን ይገባዋል!” ቶማስ ፔይን (1737-1809)

ብዙውን ጊዜ “ቶም” በመባል የሚታወቀው ቶማስ ፔይን፣ ኢንግላንድ ውስጥ ቴትፎርድ በምትባል የገበያ ከተማ ነው የተወለደው። በአካባቢው ባለ የሰዋሰው ትምህርት ቤት ተምሯል። የኤግዛይስ ታክስ ኦፊሰር ሆኖ በመጀመሪያ በሊንከንሻየር፣ በኋላም በሱሴክስ ከመቀጠሩ በፊት መምህርነት ጀምሮ ነበር። በግብር ሰብሳቢነት በሚሰራበት ወቅት በአካባቢው የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ መሳተፍ የጀመረው ፔይን፣ አንድ የክርክር ክበብም መስርቶ ነበር። ለተሻለ ክፍያ እና ለተሻሉ የሥራ ሁኔታዎ­ች ቅስቀሳ ማካሄድ መጀመሩ (ለመጀመሪያ ጊዜ ለህትመት ያበቃው የኤግዛይስ ኦፊሰሮች የሥራ ሁኔታን በተመለከተ “The Case of the Officers of Excise” በሚል ርዕስ ያዘጋጀው ፋምፍሌት ነበር) ከሥራው እንዲፈናቀል ምክንያት ሆነው።

ከዚህ በኋላ ነው ከቤንጃሚን ፍራንክሊን ጋር በለንደን የተገናኙት፤ በቤንጃሚን ፍራንክሊን የተበረታታው ፔይን ወደ አሜሪካ አቀና። በአሜሪካ በቅኝ ግዛቶቹ እና በእንግሊዝ መካከል የነበረው ግንኙነት በመፋፋሚያው ጫፍ ላይ ነበር ፊላደልፊያ የገባው፤ ከዚያም አክራሪ ጋዜጠኝነትን ጀመረ። የባሪያ ሥርዓት እንዲወገድ የሚሞግት ፅሁፉን ጨምሮ፣ የተለያዩ አርቲክሎችን ፔንሲልቫኒያ መፅሔት ላይ አውጥቷል። ፀረ-ዘውዳዊ ሥርዓት የሆነው የቶማስ ፔይን፣ “Common Sense” የተሰኘው ወሳኙ ሥራው (በ1776 የተሰራጨ ፋምፍሌት) በከፍተኛ ሁኔታ ነፃ መውጣትን የሚደግፍ ወይም የሚቀሰቅ ስነበር፣ በወቅቱ በስፋት የተነበበ ሲሆን 150,000 ኮፒዎች እንደተሸጡ ይነገራል። በዚያኑ ዓመት የአሜሪካን ነፃ መውጣት ያስከተለ የመነጋገሪያ መድረክ ለመፈጠሩ በማያጠራጥር መልኩ አስተዋፅኦ አበርክቷል።

ከአሜሪካ ነፃነት በኋላ፣ ፔይን ወደ እንግሊዝ ተመልሶ እጅግ የሚታወቅለትን “The Rights of Man” የተሰኘ ሥራውን በ1791 አሳተመ። በዚህ መፅሐፉ ቀዳሚው ዓላማው ኤድመንድ በርክ “Reflections on the Revolution in France” በተሰኘው ሥራው የፈረንሳይ አብዮትን የነቀፈበትን ሁኔታ መመከትና የፈረንሳይ አብዮተኞችን መደገፍ ነበር። ይሁን እንጂ አያይዞም በዘር ሀረግ ወይም በውርስ የሚተላለፍ መንግሥትን ያወገዘ ሲሆን፣ ለእኩል ፖለቲካዊ መብቶችም ተከራክሯል። እናም መፅሐፉ በእንግሊዝ እንዳይሰራጭ ታገደ፤ ፔይንም ሀሰተኛ ወሬ በማሰራጨት ሕዝብን ለአመፅ ለማነሳሳት ሞክረኻል ተብሎ ለእስር ይፈለግ ጀመር። እርሱ ግን ወደ ፈረንሳይ ሸሽቶ ገብቷል፤ በዚያም የጀግና አቀባበል ተደረገለት።

የፈረንሳዮቹ አክብሮት የጀግና አቀባበል በማድረገግ ብቻ አላበቃም፣ በብሔራዊ ጉባኤ መረጡትና የአብዮቱ የፖለቲካ አንጃ ከነበሩት ከጊሮንዲኖች ጋር ተቀመጠ። ይሁንና አክብሮቱ ግን በዚህ አልቀጠለም። በዘር ሀረግ የሚወራረስ ዘውዳዊ ሥርዓትን አጥብቆ ይቃወም የነበረ ይሁን እንጂ፣ ፔይን በአብዮቱ የተወገደው ንጉሥ በሞት ይቀጣ-አይቀጣ በሚለው ድምፅ አሰጣጥ ላይ “አይቀጣ” ሲል ድምፁን ሰጠ። ይህ ድርጊቱ ህይወቱን ሊያሳጣው ምንም አልቀረውም ነበር። ጃኮቢኖቹ አሰሩት። (ጃኮቢንስ – Jacobins – በ1789 አብዮቱን ተከትሎ በፓሪስ የተቋቋመ የአክራሪ ዴሞክራቲክ ክበብ አባላት መጠሪያ ነው።) በእስር ቤት እያለ ነበር “The Age of Reason”የተሰኘውን በሃይማኖት ላይ ትችት የሚሰነዝር ሥራውን የመጀመሪያ ክፍል የፃፈው።

ፔይን፣ ከአብዮቱ ዋነኛ መሪ­ዎች አንዱ የነበረው ሮቤስፒሬ የፈላጭ ቆራጭነት ቦታውን ሲያጣ እንደገና ወደ ፓርላማ አባልነቱ እንዲመለስ የተደረገ ቢሆንም፣ በ1803 ወደ አሜሪካ ተመልሷል። “The Age of Reason” ሥራው ክርስትና ሃይማኖትን የሚያጥላላ በመሆኑ ምክንያት ከአብዮቱ በፊት የነበረውንና ያጣጣመውን ተወዳጅነት እንዲያጣ አድርጎት ነበር፤ ሆኖም በኒው ዮርክ ግዛት የእርሻ መሬት ተሰጥቶት የዕድሜውን የመጨረሻ ስድስት ዓመታት በዚያ ተረጋግቶ ለማሳለፍ ችሏል።

የፔይን የፖለቲካ እሳቤ ቀጥ-በቀጥ የሆነ የአክራሪ-ሊበራል አይዲዮሎጂ ተብሎ ሊገለፅ የሚችል ነው። ያለፈው ዘመን የጨቋኝ ሥርዓት (tyranny) እና የአላዋቂነት ታሪክ ነው ብሎ ያስባል። የሰው ልጆች ታሪክ የአጉል እምነት (superstition) እና አንድን ሥርዓት ምክንያታዊ ባልሆነ መልኩ የመቀበል ባሕሪይ አለው። ፔይን በተለይ ዘውዳዊ ሥርዓት ላይ ጥላቻ አለው። በዘር ሀረግ የሚወራረስ ዘውዳዊ ሥርዓት ተፈጥሮአዊ እና ምክንያታዊ ያልሆነ እንደሆነ ያስረግጣል። በንጉሦች እና በተገዢ­ዎች መካከል ምንም ዓይነት መሠረት የሌለውን ልዩነት ይፈጥራል። ብቃት እና ሞራላዊ ባሕሪይን ከግምት ሳያስገባ ሰ­ዎችን የሥልጣን ቦታ ላይ ያስቀምጣል። የመበላለጥ እና የኢ-ፍትሃዊነት ሁኔታዎ­ችን ያመነጫል፣ ያጠናክራል። ንጉሦች እና ጋሻጃግሬዎቻቸው ዝም ብለው ጥገኛ-ተሀዋሲያን (ፓራሳይቶች) ናቸው። በሺዎ­ች የሚቆጠሩ ተገዢዎቻቸው በስቃይ ውስጥ እየኖሩ ሳለ ከሕዝብ በሚሰበሰበው ግብር እየተደጎሙ የቅንጦት ህይወት ይመራሉ። ተገዢዎቻቸው ዋጋ ሊከፍሉና ሊዋደቁበት፣ ንጉሦቹ ለራሳቸው ዝና ሲሉ ጦርነት ያካሂዳሉ። እውቀት ወይም ምክንያታዊነት በዚህ ዘመን ማንሰራራቱ ያለፈውን ዘመን ስህተቶች ጠራርገን እናፀዳ ዘንድ ያግዘናል (ይህ በርግጥም ለኤድመንድ በርክ የሚያስፈራው አመለካከት ነበር)። አሁን የሚያስፈልገው ምክንያታዊ የሆነ የህብረተሰብ መልሶ-ግንባታና እርሱን የሚያስተዳድር ትክክለኛ የመንግሥት ሥርዓት ዓይነትን ተግባራዊ ማድረግ ነው።

መንግሥት ቢጎዳንም ጥለን የማንጥለው ነገር ነው፤ መንግሥት አስፈላጊ-ጎጂ ነው። ያለ እርሱ መኖር አንችልም፤ ነገር ግን በማያሻማ መልኩ የግለሰብን እንዳሻው የመሆን መብት የሚጥስ ነው። ስለዚህ የመንግሥት ጉልበት እያነሰ በመጣ ቁጥር የተሻለ እየሆነ ይመጣል። መንግሥት የሰውን መብት በማስጠበቅ ተግባር ላይ እራሱን ሊወስን (ሊገድብ)፣ እንዲሁም ከዚህ የዘለለ ተግባር ላይኖረው ይገባል። በተጨማሪም መንግሥታቸው ለሆነላቸው ሕዝቦች ኃላፊነት ሊኖርበትና በራሱ ሕዝቦች ሊወገድ የሚችል መሆን ግድ ይለዋል። በሰዎ­ች መካከል ተፈጥሯዊ የሆነ መተዛዘን እና የፍላጎቶች ሕብራዊነት (harmony) አለ፤ ስለዚህም ግንኙነታቸውን ለማስተዳደር የሚያስፈልገው የመንግሥት መጠን ትልቅ አይደለም። ፔይን ከጆን ሎክ የሕዝባዊ ሉዓላዊነት አስተምህሮት ይበልጥ ከረር ባለ መልኩ፣ ሕብረተሰብ በማኅበራዊ ውል (social contract) እደተፈጠረና ስለዚህም ሕዝቡ በፈቀደው ጊዜና ሁኔታ መንግሥትን የማውጣትም ሆነ የማውረድ ፍፁም መብት እንዳለው ይናገራል።

መገመት እንደሚቻለው ሁሉ፣ ፔይን ዴሞክራት ነው። መንግሥት የኖረበት ምክንያት የአጠቃላይ ሀገሪቱን እና የሕዝቡን ጉዳዮች ለማስተዳደር እንደመሆኑ፣ የአንድ ግለሰብ ወይም ቤተሰብ ወይም አንጃ ንብረት ሊሆን አይችልም። ሁሉም ሰው እኩል ነው። ሙሉ ለሙሉ በወንዶች መራጭ እና ተመራጭነት ላይ መሠረት ያደረገ የውክልና ዴሞክራሲ (representative democracy) ብቸኛው ምክንያታዊ የሆነና ስለዚህም ብቸኛው ተቀባይነት ያለው የመንግሥት ዓይነት ነው። እንዲህ ባለ መንግሥት ስር ሕዝቡ በሰላም እና በብልፅግና መኖር ይቻለዋል። ግብር መጣል የሚችለው አጠቃላዩ ሕዝብ ምክንያታዊ ናቸው ብሎ ያሰባቸውን የግብር ዓይነቶች እና መጠኖች ብቻ ይሆናል፤ እንዲሁም አጠቃላዩ ሕዝብ ጦርነቶችን የመደጎም ፍላጎት እንደማይኖረው ፔይን ይገምታል። ሆኖም የዘመኑ የኢንግላንድ የፖለቲካ አደረጃጀት የልዩ መብት ባለቤትነትን (privilege) እና መበላለጥን በደፈናው ዘርግቷል። ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ነፍሶችን ያቀፈው የዮክሻየር አውራጃ፣ ሁለት የአውራጃ ተወካይ የፓርላማ አባላት አሉት፤ 20 ሺህ የማይሞላ ሕዝብ ያለውም ሩትላንድ እንዲሁ የተወካዩ ቁጥር ተመሳሳይ ነው። 60 ሺህ የሚሆን ሕዝብ ያለበት ማንቺስተር ደግሞ ከነጭራሹ የፓርላማ ተወካይ እንዲኖረው አልተፈቀደም። በሌላ በኩል ምንም ሰው የለባትም ልትባል የምትችለው ኦልድ ሳረም ሁለት አባላት አሏት። እውን ዴሞክራሲ የዜጎችን ፍላጎት የሚወክል ነው ከተባለ ትርጉም በሚሰጥ ውክልና የተዋቀረ ሊሆን ይገባዋል።

ፔይን የማኅበራዊ ዋስትና እርምጃዎች ቀዳሚው አቀንቃኝ ነው። “The Rights of Man” በተሰኘው ሥራው መንግሥት ደሃው ሕዝብ ነፃ ትምህርት እንዲያገኝ፣ በዕድሜ የጠኑት ጡረታ እንዲጠበቅላቸው፣ እንዲሁም የሥራ እድል እንዲበራከት ማድረግ እንዳለበት ጠቁሟል። “Agrarian Justice (1796)” በተሰኘ ሥራው፣ የበለጠ እኩልነት የሰፈነበት ሕብረተሰብ እና ጠንካራ የማኅበራዊ ዋስትና ሥርዓት ለመፍጠር ሪዲስትሪቢዩቲቭ ወይም ለተሰበሰበበት የሕብረተሰብ ክፍል ልማት ላይ መልሶ የሚያውል የግብር አሰባሰብ ሥርዓትን ይደግፋል። በተወሰኑ መንገዶች የእርሱ እሳቤዎች ወደኋለኛው ሶሻሊዝም የሚጠቁሙ ናቸው፤ ምንም እንኳን ንብረት በመያዝ መብቶች እና በንግድ ጠቀሜታ­ዎች ላይ ያለው ጠንካራ እምነት ከሊበራል ጎራ ቢያቆየውም። ይሁንና ግን ሰፊ የማኅበራዊ ዋስትና አድራጎትን በመጠቆምና በተመሳሳይ ሰዓት ደግሞ መጠነ-ትንሽ መንግሥት እና ግብር እንዲኖር በመፈለግ ረገድ ያሉትን ግጭቶች የተረዳ አይመስልም።

ፔይን ታላቅ ስብዕና ያለው ሰው መሆኑ ግልፅ ነው። በፈረንሳይ ባልተደላደሉ ሁኔታዎ­ች ውስጥ እየኖረ ሳለ “The Rights of Man” ከተሰኘው መፅሐፉ ምንም ዓይነት ትርፍ የማግኘት ዓላማ እንዳልነበረውና መፅሐፉን ለማባዛት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ማባዛት እንደሚችል አስታውቆ ነበር። በዚህም ምክንያት የመፅሐፉ 200 ሺህ ቅጂዎ­ች በ1791 እና በ1793 በርካሽ ተሽጠዋል። ቶማስ ፔይን ውስብስብ ጉዳዮችን በቀላሉ በተሰናዳ ሁኔታ ማቅረብ የሚችልና በተለየ መልኩ የፋምፍሌት ፀሐፊ ነበር። የእርሱ ጉልህነት ከኦሪጂናል ሐሳብ አመንጪነት እና ከእሳቤው ጠጣርነት ይልቅ፣ የፖለቲካ እሳቤ­ዎችን በማንኛውም የዕድሜ ክልል ላለ መደበኛ ሰው በግልፅ ማስረዳት መቻሉ ላይ የሚመረኮዝ ነው።

ለበለጠ ንባብ

ቀዳሚ ምንጮች

Paine: Political Writings, ed. B. Kuklick (Cambridge: Cambridge University Press, 2000).

ተቀፅላ ምንጮች

Claeys, G.: Thomas Paine: Social and Political Thought (Boston, MA: Unwin Hyman, 1989).

Harmer, H.: Tom Paine: the Life of a Revolutionary (London: Haus, 2006).

Keane, J.: Tom Paine: A Political Life (Boston, MA: Little, Brown, 1995).

Philp, M.: Paine (Oxford: Oxford University Press, 1989).

Williamson, A.: Thomas Paine: His Life, Work and Times (London: Allen & Unwin, 1973).

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.