FEATUREDፖለቲካ/ፍልስፍና

“ሰዎች በመንግሥት ባይገደቡ ኖሮ ይሄን ጊዜ ተላልቀው ነበር” – ቶማስ ሆብስ (1588-1679)

ዌስትፖርት ነው የተወለደው፤ ማልሜስቡሪይ አቅራቢያ በዊልሻየር፣ ኢንግላንድ። ሀብታም አጐቱ ወጪውን ሸፍኖለት ወደ ማግዳሊን ሆል፣ ኦክስፎርድ ለትምህርት ሰደደው። ቶማስ ሆብስ የመጀመሪያ ዲግሪውን በ1608 እንደያዘ የዴቪንሻየር ኧርል የበኩር ልጅ ለሆነው ዊሊያም ካቬንዲሽ አስጠኚ ሆነ። ከካቬንዲሽ ቤተሰቦች ጋር በነበረው የጠበቀ ትስስር በዘመኑ ስመ-ጥር ከነበሩ ምሁራን ጋር እንዲገናኛ ምክንያት ሆነው፤ በተጠቃሽም በእሱ ላይ ጉልህ ተፅዕኖ ካሳደረው ሰር ፍራንሲስ ቤከን ጋር። ወደ ጥናታዊ ሥራዎች እንዲያተኩርም ጊዜና መንገዱን አመቻችቶለታል።

በ1634 ከዊሊያም ካቬንዲሽ ልጅ ጋር በመሆን አውሮፓን ለመጐብኘት ተነሳ። እናም በፓሪስ፣ ዴካርት እና ጋሴንዲ ጭምር የነበሩበት የሳይንስ ክበብ ምሰሶ የሆነውን ማሪን መርሴን አገኘው፤ በፍሎረንስ ደግሞ ከጋሊሊዮ ጋር ተገናኙ። ወደ ኢንግላንድ ሲመለስም፣ “The Elements of Law Natural and Politic” የተሰኘ ሥራውን ፃፈ። ይህ ሥራው እስከ 1889 ድረስ በጥቅል አልታተመም፤ ነገር ግን በ1650 የመጀመሪያዎቹ 13 ምዕራፎች “HumanNature” በሚል ርዕስ ቀረቡ፤ የተቀረው ደግሞ “De corpore politico” በሚል ሌላ ርዕስ።

በ1640፣ የእርስ በርስ ጦርነቱ ሊፈነዳ ሲቃረብ፣ ሆብስ ወደ ፈረንሳይ ተመልሶ የቀድሞ ውድጅቱን ቀጠለ። በዚህም መርሴን “Meditationes de prima philosophia” በተሰኘው የዴስካርት ሥራ ላይ ምላሽ ይሰጥበት ዘንድ ሆብስን ይጋብዘዋል። በኋላም ከዴስካርት ምላሾች ጋር ሆኖ እንደሶስተኛ ስብስብ “Obiectiones” በ1641 ታትሟል። ቀጣይ የፅሁፍ ግንኙነቶቹ “Discoursdelamethod” ከተሰኘው ስራው ጋር ጎን ለጎን ሆነው በ1637 “Dioptrique” በሚል ርዕስ ለአንባቢ ቀርበዋል።

ከዚህ በኋላ ቶማስ ሆብስ የራሱን ሁነኛ የፅሁፍ ሥራ (magnum opus) ተግባራዊ ለማድረግ ዕቅዱን ዘረጋ። በሦስት ክፍሎች የተዋቀረ እንዲሆን የታሰበ ሥራ ነበር፤ ስለ ቁሳዊ ነገር (matter) ወይም ስለ አካል፣ ስለሰው ልጅ ተፈጥሮ፣ እና ስለ ህብረተሰብ የሚተነትን። የመጀመሪያ ዓላማው ስለነዚህ ርዕሰ-ጉዳዩች በቅደም ተከተላቸው ለመፃፍ ቢሆንም፣ በእንግሊዝ የርስ-በርስ ጦርነት ሊፈነዳ ጫፍ ላይ በመድረሱ ምክንያት ሀገሪቱ የፖለቲካዊ መፍትሔ ጥቆማ እጅግ ያስፈልጋታል ብሎ በማሰቡ፣ በቅድሚያ በሦተኛው ክፍል ሊጀምር ወሰነ፤ እናም በ1642 ስለህብረተሰብ ያዘጋጀው “De cive” በፓሪስ ታተመ። (ስለቁሳዊ ነገር የሚያወሳው “De corpore” በ1655 እና ስለሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚተነትነው “De homine” በ1658 ታትመዋል።) በኋላም በ1651 ነገሮች በኮመንዌልዝ አማካኝነት መረጋጋት ላይ ሲደርሱ፣ እስከ ዕልፈተ ህይወቱ ድረስ ወደኖረባት ኢንግላንድ ተመለሰ። በዚያኑ ዓመት “De cive” የተሰኘውን ሥራውን “Philosophical Rudiments Concerning Government and Society” ሲል የእንግሊዝኛ ትርጉሙን ያሳተመ ሲሆን፣ በብዙዎች እውቅና የተሰጠውን “Leviathan” የተበለ መፅሐፉን በተመሳሳይ ጊዜ ይፋ አደረገ። በ1679 እስኪሞት ድረስ ትጋቱን ሳያቋርጥ በተለያዩ ጉዳዮች አያሌ ሥራዎችን አመንጭቷል፤ በተለይም የእርስ በርስ ጦርነቱን አስመልክቶ “Behemoth”፣ እንዲሁም “The Questions Concerning Liberty, Necessity and Chance” የተሰኘ የጥናት ሥራው ይገኙበታል። ከዚህ ባሻገር የ“Leviathan” የተሻሻለ እትም በላቲን ቋንቋ በ1668 መውጣቱም ይታወቃል።

ስለዚህም የቶማስ ሆብስ የፖለቲካ እሳቤ፣ የእንግሊዝ እርስ-በርስ ጦርነትን እና የ17ኛውን ክፍለ ዘመን ሳይንሳዊ አብዮት ተሞክሮዎች ከታዘበ ሰው የመነጨ ነው። እሳቤውንም እንድንረዳው ይህን እውነታ መገንዘብ አስፈላጊ ነው።

የፖለቲካ እሳቤዎቹን በተለያዩ ጊዜያት ቀምሯቸው ቢታይም፣ ይበልጥ ምሉዕ ሆነውና ተፅዕኖ በሚፈጥር አገላለፅ የቀረቡት “Leviathan” በተሰኘው ሥራው ነው። ፖለቲካን የተመለከተበት መንገድ ራስ-አወቅ በሆነ መልኩ ሳይንሳዊ ነው። ጥያቄዎችን የማንሳት ስልቱ፣ በከፊል ከጋሊሊዮ እና ከቤከን ጋር ከሚያያዘው ነገሮችን በታትኖ ከማገናኘት (resolutive-compositive) ዘዴ የተወሰደ ሲሆን፣ በከፊል ደግሞ በዩክሊድ አቀራረብ ላይ ተመልክቶት ያማለለውን ጥቃቅን ክፍሎችን ለመረዳት ጥቅል ምንነታቸውን ከፋፍሎ በአመክኒዮ የመመርመር ዘዴን (deductive reasoning) ይጠቀማል። ትክክለኛው የፖለቲካ ግንዛቤ ላይ ለመድረስ ከፈለግን፣ በቅድሚያ ህብረተሰባዊ ጥቅሎችን ወደ ትናንሽ ክፍሎቻቸው – በተጠቃሽም ወደ ግለሰብ ሰብዓዊ ፍጡራን – ተንትኖ መረዳት ግድ ይለናል። ከዚያም እነዚያን ክፍሎች ለይተን ጠባይ እና ምግባራቸውን ካጠናን በኋላ፣ እንደ ቀዳሚ መርሆዎች አድርገን በመቁጠር ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ አወቃቀርን በተመለከተ እነሱን በመንተራስ ምክንያታዊ ድምዳሜዎችን መምዘዝ እንችላለን። በዚህ መንገድ፣ እንደ ሆብስ ሐሰብ ከሆነ፣ ፖለቲካን እንደማንኛውም ሳይንስ በሁለት እግሩ በእርግጠኝነት ማቆም ይቻላል፤ እንዲሁም ሰላም እና መረጋጋትን የማረጋገጫ ጥርጥር የለሽ ዘዴዎችን ወደሚያበረክትልን የፖለቲካ ሁኔታ መድረስ ይቻለናል።

በሥነ-ምግባሮች እና በሥልጣኔ ካልተበረዘ ሰብዓዊ ፍጡር ከሆነ ግለሰብ፣ ማለትም ከ«ተፈጥሯዊ» ሰብዓዊ ፍጡር የምናገኘው ምንድነው? ሆብስ ገና በ1630 ገደማ – በይበልጥ ለቤከን ተፅዕኖ ምስጋና ይግባውና – አጠቃላዩን የተፈጥሮ ሥርዓት ሕሊናን ወይም ነፍስን መጠቀም ሳያስፈልግ፣ በአካል ወይም በሰውነት (body) አማካኝነት ማብራራት እንደሚቻል አምኖ ተቀብሏል። “De corpore” ላይ መከራከሪያውን እንዳስቀመጠው፣ የሳይንስ ተግባር የተለያዩ አካላዊ (Corporeal) እንቅስቃሴ ዓይነቶችን ተፅዕኖ መመርመርና መግለፅ ነው፤ ይህ እንደሱ ሐሳብ ለፊዚክስ እውነት እንደሆነው ሁሉ፣ ለፊዚዮሎጂም ሆነ ለሳይኮሎጂ እውነት ነው።

የእርሱ ቁሳዊነት ወይም ማቴሪያሊዝም (ቁስን መሠረት ባደረገ ትንታኔ ላይ ያነጣጠረ አስተምህሮ) ለሰው ልጅ ባሕሪይ ምልከታው ማዕከል ነው። (ይህ ቁሳዊነቱም በእርሱ ዘመን በነበሩት ፈላስፎች ዘንድ በኢ-አማኝነትን /atheist/ ተፈርጆ እንዲወገዝ አድርጎታል።) እንደሱ ሐሳብ፣ የእያንዳንዱ ሰብዓዊ ፍጡር አካል እንደሰዓት መቁጠሪያ ዓይነት ውስብስብ ማሽን እንጂ ሌላ አይደለም። እንዲህ ዓይነት ገለፃውን በስፋት ያዳበረው “Decorpora”ላይ ነው። ልብ ስፕሪንገግ (ተለጣጭ) ናት፤ ነርቮች ገመዶች ናቸው፤ እንዲሁም መገጣጠሚያዎች (joints) ደግሞ ለአጠቃላዩ አካል መንቀሳቀስን የሚፈጥሩ ተሽከርካሪዎች (ጐማች) ናቸው። የአካል ባሕሪይ፣ በስሜት ህዋሳት በኩል ከውጫዊው ዓለም ለሚመጡት ቀስቃሾች (Stimuli) ተከታታይ ምላሾችን መስጠት ነው። አንዳንድ ቀስቃሾች፣ የእኛን «መሠረታዊ እንቅስቃሴ» ስለሚያሻሽሉ፣ ደስታን የሚሰጡ (pleasurable) ናቸው። እነዚህን ጥሩ ወይም “good” እንላቸዋለን። እነሱን አስመልክቶ ያለን ስሜን የመፈለግ ወይም የመሻት ዓይነት ነው፤ እናም እንዲበረክቱና የቆይታ ጊዜያቸው እንዲራዘም እንተጋለን። ደስታ በገነነበት (በገዘፈበት) ሁኔታ ውስጥ በሆንን ጊዜ፣ ያ ሁኔታችን “felicity” ወይም ምሉዕ ደስተኝነት ይባላል።

የእኛን መሠረታዊ እንቅስቃሴዎች የሚገድቡ ሌሎች ቀስቃሾች (stimuli) ደግሞ የሚያሳምሙ (painful) ናቸው። እነዚህን መትፎ ወይም “evil” እንላቸዋለን፤ ለእነሱ ያለን ስሜትም የጥላቻ ዓይነት ሲሆን፤ ልናስወግዳቸውም እንተጋለን። «ጥሩ» እና «መጥፎ» ሌላ ምንም ትርጉም የላቸውም – «ደስታ አምጪ» እና «አሳማሚ» ከመሆን በቀር፤ ለምንፈልጋቸው ነገሮች እና ለምንጠላቸው (ለማንፈልጋቸው) ነገሮች ያወጣናቸው መጠሪያ ስሞች ናቸው። (ሆብስ የቋንቋ ምልከታው  “ስማዊ” ወይም ኖሚናልስት ነው። ስማዊነት ወይም nominalism – በተመሳሳይ ቃል የሚፈረጁ የተለያዩ ነገሮች ከስም በቀር ምንም የሚጋሩት ነገር የለም የሚል ፍልስፍና ነው።)  «ማስተዋል» (ወይም reason – የማሰብ ኃይል) ምሉዕ ደስተኝነትን በአግባቡ ማሳካት የሚያስችለን ወይም ተቃራኒውን እንድናስወግድ የሚያደርገን ወሳኝ ከፍል ነው። እኛ የምንፈራው እና ከምንም ነገር በላይ ልናስወግደው የምንፈገው ሞት ሲሆን፣ ሞት የምሉዕ ደስተኝነት ቀጣይነትን የማይቻል የሚያደርግ ክስተት ነው። የግለሰቦች ደርጊት ሁልጊዜ እስከተቻላቸው ድረስና በተቻለቸው ዘዴ ሁሉ በህይወት እንዲቆዩ የሚያደርጋቸውን መንገድ የተከተለ መሆኑ የተሞክሮ እውነታ ነው።

ሆብስ ይህን ምልከታ በመንተራስ፣ ለእያንዳንዱ ሰው ተፈጥሮውን እንደነበረ ለማቆየት የራሱን ጉልበት እንደራሱ ፈቃድ ይጠቀም ዘንድ የተፈጥሮ መብት ወይም ቀድሞውኑ የነበረ መብት መስጠት እንዳለብን “Leviathan”ላይ አስፍሯል። «መብት» የሚለውን ሰዎች አሁን በተግባር ስለሚፈፅሙት ድርጊት የተሰጠ ከሚመስለው እውነታን መሠረት ካደረገ ጥቅላዊ ድምዳሜ ላይ አንጥሮ ማውጣት ጥያቄ የሚያስነሳ የአመክኒዩ አካሄድ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ሆብስ ባለመብት መሆን ምን ስለመሆኑ የተለየ ሐሳብ እንዳያስቀምጥ በራሱ የማቴሪያሊስት ሳይኮሎጂ ተገድቧል፤ እናም በመብት እሳቤ ላይ መቀጠሉን የመረጠበት ምክንያት፣ ህብረተሰብን እና መንግሥትን የምንፈጥረው፣ እንደሱ ሐሳብ፣ የራሳችንን  “የተፈጥሮ መብት” አሳልፈን ስንሰጥ ነው።

የሆብስ ቁሳዊ (ማቴሪያሊስት) እና ሄዶኒስት (ለሰው ልጅ ህይወት ከፍተኛ መልካም ነገር እና ትክክለኛው ግብ ደስታ ነው የሚል አስተምህሮ) ሳይኮሎጂው፣ በሚያስደንቅ ዝርዝር እና ተያያዥነት ተብራርቷል፤ ምንም እንኳን ዲተርሚኒዝም (ማንኛውም ድርጊት እና ክስተት ከፈቃድ ውጪ በሆኑ ምክንያቶች ይወሰናል የሚል ፍልስፍና) እና ነፃ ፈቃድን (free will) በተመለከተ፣ የቱም ጋ በተሟላ መልኩ ያልመለሳቸውን ጥያቄዎች ያስነሳ ቢሆንም። በግልጽ ባያመለክተውም፣ በሕሊናው ውጤቱ መጥፎ ከሆነ እራስን ማስቀደም (egoism) ጋር የተያያዘ ነው። ይህ የሆብስ አመለካከት በመንግሥት ምንነት እና ዓላማዎች ግንዛቤው ላይ መሠረታዊ ሆኖ ይታያል። እያንዳንዱ ግለሰብ፣ በሳቢ እና ገፊ የደስታ እና የህመም ኃይሎች አማካኝነት የሚንቀሳቀስ እራሱን በራሱ የቻለ ማሽን እንደመሆኑ፣ ማንም ቢሆን ለራሱ የተቻለውን ያህል ከፍተኛ ደሰታና በተቻለ መጠን ዝቅተኛውን ህመም እንጂ ሌላ የሚፈቅድበት ምንም ምክንያት የለውም።

ሆብስ፣ ሩህሩህ መሆን የማይቻለን ነን ብሎ አያምንም። በሌላ ሰው መደሰት እንኳን ለራሳችንም ደስታ ማግኘት እንችላለን፤ ነገር ግን አንዳንድ ስሜቶች ድንገተኛ እና ራስን ያማከሉ በሆኑት የመደረብ (የመከለል) እጣ ይገጥማቸዋል፤ በተለይም አደጋ በሚፈጠርበት ሁኔታ፣ ወይም ሰዎች በሚፈልጓቸው እና በሚያስፈልጓቸው ነገሮች መጠን ላይ እጥረት በሚኖር ጊዜ።

ሰዎች ምንም ዓይነት መንግሥት በሌለበት ዓለም (ሆብስ «State of Nature» ሲል ይጠራዋል) ኖረው ቢሆን ኖሮ ወጤቱ ቀውስ በሆነ ነበር፣ ወይም በዚያ ዓለም ያለው ሀብት አላቂ ቢሆን ኖሮ የውድመት ውጤት ይኖረው ነበር። ሰዎች በመንግሥት ያልተገደቡ ከሆኑ የየራሳቸውን ደስታ ለማበራከትና ህመም እና ሞትን ለማስወገድ በሚያደርጓቸው ጥረቶች በማያቋርጥ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ይገባሉ። የያዙትን የማጣት ተከታታይ ስጋት ስለሚያድርባቸውም፣ እራሳቸውን ከሌሎች ቁጥጥር ውስጥ ከማውጣትና ሌሎችን በቁጥጥር ስር ከማድረግ አታካች ትንቅንቅ ነፃ የሚሆን የለም። ሁሉም ሰው በተፈጥሮው ዘላቂና ያላሰለሰ በሆነና በሞት ብቻ ሊቋጭ በሚችል የሥልጣን መሻት ውስጥ ነው። መንግሥት በሌለበት፣ ማንኛውም ገደብ እንዲቀበል ወይም ለሌላ ሰው ግዴታ እውቅና እንዲሰጥ የሚጠየቅ አይኖርም። እናም እያንዳንዱ ሰው ማንኛውንም ነገር በተመለከተ የራሱን ተፈጥሮ ለማቆየት፣ የራሱን ጉልበት እራሱ በፈቀደው መንገድ ለመጠቀም ለተፈጥሯዊ መብቱ ትኩረት ይሰጣል። በውጤቱም የተፈጥሮ መብት ሁሉንም ነገር የማድረግ (የማግኘት) መብት ይሆናል። “Leviathan” ላይ «ስለዚህም ሁለት ሰዎች አንድን ነገር ቢፈልጉ፣ ሆኖም በአንድነት ሊጠቀሙት (ሊያጣጥሙት) ባይችሉ ጠላቶች ይሆናሉ፤ እንዲሁም አንዱ ሌላኛውን ለማጥፋት ወይም ለማንበርከክ ይተጋሉ» ይላል።

እናም፣ ሆብስ «State of Nature» ብሎ የሚጠራው ሕግ እና ሥርዓት የሌለበት ዓለም ውስጥ የነበረው ሁኔታ ያልተቋረጠ ግጭት ይስተዋልበት ነበር፤ “እያንዳንዱ ሰው በእያንዳንዱ ሰው ላይ ጦር የሚሰብቅበት» ዓለም። እየተካሄደ ያለ ጦርነት ሳይኖር እንኳን፣ በሁሉም ሰው ዘንድ የግጭት ፍርሃት ይኖራል፤ አንድም ሰው ሌሎች ጥቃት አይሰነዝሩብኝም የሚል እምነት የለውምና። ከአደጋ ነፃ ከመሆን አንፃር፣ የትኛውም ሰው ከሌሎች በበለጠ የላቀ ጥንካሬ የለውም። አንዳንዶች የሚያንሳቸውን አካላዊ ጥንካሬ በብልጥነት ያካክሱታል፤ እናም ደካማው ብርቱውን ለመቋቋም በአንድነት ማበር ይችላል ማለት ነው። በመንግሥት አልባ ዓለም አንድም ሰው ደህንነት የለውም። ሆብስ፣ አንዳንድ የፖለቲካ ንድፈ-ሐሳብ አጥኝዎች ከተስማሙበት በተፃራሪው፣ መንግሥት አልባው ዓለም ታሪካዊ እውነታ ነበር የሚል አፅንኦት የለውም። ነገር ግን እንደሚያስበው፣ የተጣሉብን ሁሉም ገደቦች የሌሉ ቢሆን ኖሮ ሕይወት ምን ይመስል እንደነበር ግልፅ በሆነ መልኩ ብቻ በአዕምሯችን መሳል እንችላለን። ሆብስ አጽንኦት ሰጥቶ እንደሚጽፈው፣ በስልጡን ማኅበረሰብ ውስጥ እንኳ አንድም ሰው የትኛውንም ሰው አያምንም። ከመኖሪያ ቤታችን ስንወጣ በሮቻችንን እንቆልፋለን፣ መሣሪያ እናነግባለን፤ ንብረቶቻችንን እንሸሽጋቸዋለን፤ ሌላው ቀርቶ የሚጠብቀን ሕግ እያለ እንኳን ማንኛውም ሰው ሌባ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለን።

ሰብዓዊ ፍጡራን ቁጥጥር ያልተደረገባቸው ወይም ያልተመሩ ቢሆን ኖሮ፣ ሁኔታው የስጋትና አሳዛኝ ነበር የሚሆነው። በይበልጥ የሚጠቀስለትን የሆብስ ሐረግ እንጠቀምና፣ ሕይወት «ብቸኝነት፣ አሳዛኝ፣ አስጠሊታ፣ ጭካኔያዊ እና አጭር» ይሆን ነበር። ነገር ግን ይህ እውነታ በራሱ፣ መንግሥት በሌለበት ዓለም ሰዎች ከሁሉም ፈጣኑንና በበለጠ ውጤታማ መንገድን ለማግኘት በተፈጥሮ ባለቸው እራስን የመጠበቅ ደመነፍሳዊ ስሜት ይመሩ የነበረ መሆኑን ለማረጋገጥ በቂ ነው። በመንግሥት አልባ ዓለም ውስጥ ያሉ አስከፊና የቅርብ አደጋዎችን ለማስወገድ የሚያስችለው ብቸኛው መንገድ፣ ሆብስ «የተፈጥሮ ሕጐች» ብሎ በሚጠራቸው ምክንያታዊ መርሆች መሠረት መንቀሳቀስ እንደሆነ እያንዳንዱ ግለሰብ የሚገነዘበው ነው። «የተፈጥሮ ሕግ» ትርጓሜም እንደሚከተለው ነው፡-

“አንድ ሰው ሕይወቱን የሚጎዳ ነገርን እንዳይፈፅም የሚከለክል፣ ወይም ሕይወቱን የሚጎዳውን ነገርሚያቆይበትን ዘዴ የሚነጥቅና ይህን ነገር በተሻለ መልኩ ማቆየት ይቻላል ብሎ ያሰበበትን መንገድም የሚያስወግድ በማስተዋል የተገኘ እይታ ወይንም አጠቃላይ ድንጋጌ” ማለት ነው።

እንዲህ ባለ ዓለም ውስጥ የሚኖር ግለሰብ፣ (1ኛ) ሰላም መሻት ምክንያታዊ አስፈላጊነት ያለው መሆኑን፤ (2ኛ) እርስ-በርስ ላለመቆራቆስ ሰላም ማስፈኛው መንገድ ከሌሎች ጋር ስምምነት ማድረግ መሆኑን፤ እንዲሁም (3ኛ) ስምምነት ውስጥ ከተገባ በኋላ ስምምነቱን ሌሎች ጠብቀውት የተቀሩት ከጣሱ፣ እርስ-በርሱ ከመጣረሱ አግባብ የተነሳ ምክንያታዊነት የሌለው መሆኑን ይገነዘባል። እንግዲህ በዚህ የተያያዘ አመክኒዮ አማካኝነት ማኅበረሰብ ይፈጠራል። የሚፈጠረውም በስምምነት ነው፤ ይህንንም ሆብስ ኮምፓክት (compact) ብሎ ይጠራዋል። ስምምነቱ የሚደረገውም በግለሰቦች ሲሆን፣ አንዳቸውም ቢሆኑ ለሌላኛቸው ደህንነት መጠበቅ ግድ ባይሰጣቸውም የራሳቸው ደህንነት ሊጠበቅ የሚችለው ሌሎችን ላለመጉዳት በሚያደርጉት ስምምነት ብቻ መሆኑን በተገነዘቡ ግለሰቦች አማካኝነት ማኅበረሰብ ይፈጠራል።

ሆኖም «ሰዎች ቃል-ኪዳናቸውን እንዲፈጽሙ ለማድረግ የቃላት ኃይል እጅግ ደካማ ነው» ይላል “Leviathan” ላይ። ጉልበት የሌለው ስምምነት ወይም ኮምፓክት (ማለትም በማንም ሰው ላይ ሊተገበር የማይችል ስምምነት) ዋጋ አይኖረውም፤ ምክንያቱም ከተዋዋይ ወገኖቹ አንዳቸውም ሌላኛዎቹ ቃል-ኪዳናቸውን አይጥሱም የሚል እርግጠኝነት በጭራሽ የላቸውምና። «ሰይፍ አልባ ስምምነቶች ቃላት ብቻ እንጂ ምንም አይደሉም፣ እናም ሙሉ በሙሉ ሰውን ለመጠበቅ ኃይል አይኖራቸውም።» ይህን ለማስወገድ ተዋዋዮቹ በኮምፓክቱ ውስጥ ሁሉንም የሚከላከልና የኮምፓክቱን አንቀጾች የሚተላለፉትን የሚቀጣ አንድ ሉዓላዊ ሥልጣን ያለው ኃይል ማካተታቸውን እርግጠኞች መሆን አለባቸው። ሰዎች ይፈፅሙታል ብሎ ሆብስ የሚያስበው ስምምነት ወይም ኮምፓክት የሚከተለው ቅርፅ አለው፡-

«ለዚህ ሰው፣ ወይም ለዚህ የሰዎች ጉባኤ፣ ራሴን የማስተዳደር መብት አስተላልፋለሁ፣ ሥልጣንም ሰጥቻለሁ፤ ሆኖም፣ አንተም የራስህን መብት ለእርሱ የምታስተላልፍ፣ እና በተመሳሳይ መንገድም ሁሉንም እርምጃዎቹን እውቅና መስጠት ይጠበቅብሀል።»

መንግሥት፣ በቀዳሚነት ሕግ በማውጣት እና ያወጣውን ሕግ ተግባራዊ በማድረግ፣ በመንግሥት-አልባ ዓለም ለመከወን አዳጋች የሆነውን ሕዝባዊ ሥርዓትና ደህንነት ያሰፍናል። (አልፎ አልፎ ሆብስ ካለው እይታ በተፃራሪ) መንግሥት እነዚህን ግቦች በማስገደድ ብቻ ማሳካት አይቻለውም። እናም፣ ከዚህ በተጓዳኝ፣ የሞራል አስተምህሮዎችን በትምህርት አማካኝነት በዜጎች ላይ ያሰርፃል።

ሆብስ፣ «Of the Commonwealth» በተሰኘው የ“Leviathan” ቁጥር ሁለት መጽሐፉ፣ ስለተለያዩ የመንግሥት ዓይነቶች ይፅፋል፤ በሆብስ አስተሳስብ፣ በመርህ ደረጃ ሉዓላዊ ሥልጣን በየትኛውም ዓይነት መንግሥት ላይ ሊያድር ይችላል። ያም ሆኖ በይበልጥ ይህ ሥልጣን ሊተገበር የሚችለው በንጉሥ ነው። ሆብስ፣ ንጉሥ ሲልም ፍፁም ሥልጣን ያለው ንጉሥ ማለቱ ነው። ያልተከፋፈለ ሥልጣን በመሆኑም፣ ንጉሣዊ ሥልጣን በይበልጥ ውጤታማና ዘላቂ ነው የሚል ምልከታ አለው። የሰው ተፈጥሮ እንዳለ ሆኖ፣ የሥልጣን ክፍፍል በሚኖር ጊዜ፣ ሁሉም የሥልጣን ተጋሪዎች ካላቸው የሥልጣን ድርሻ የላቀ መፈለጋቸው እርግጥ ነውና ብዙም ሳይቆዩ ከተጋሪዎቻቸው ላይ ሥልጣን ለመንጠቅ ይሞክራሉ፤ በዚህም አንድ ሉዓላዊ (መንግሥት) ሊያሳካቸው ይገባል ተብለው የሚታሰቡትን – ፀጥታ እና ቀጣይነት – እንኳን እውን ማድረግ ይሳናቸዋል።

መንግሥት፣ አፈጣጠሩ በኮምፓክት ወይም በውል አማካኝነት ይሁን እንጂ፣ ከተዋዋይ ወገኖች ጋር በአንድነት ተዋዋይ አይደለም። ስለዚህም፣ ውል ጥሷል በሚል (ከሥልጣኑ) ሊወገድ አይችልም። ምክንያቱም፣ እንዲያ ማድረግ የሚቻል ቢሆን ኖሮ፣ ሥልጣኑ ሉዓላዊነት ሊኖረው አይችልምና ነው። ሆኖም ግን ማሟላት የሚጠበቅበት ሁኔታ አለ – ለተገዢዎቹ ከለላ እና ጥበቃ በማድረግ ረገድ ያልተቋረጠ የፈቃደኝነት እና የውጤታማነት ቅድመ ሁኔታ። ይህ ቅድመ ሁኔታ እስከተሟላ ድረስ ማንም ሰው ሉዓላዊውን አለማክበርም ሆነ መቃወም አይቻለውም። ነገር ግን፣ መንግሥት የተገዢውን ሕይወት አደጋ ላይ ከጣለ፣ ወይም የተገዢውን ሕይወት መከላከል ካልቻለ፣ የተገዢው ራስን የመከላከል «የተፈጥሮ መብት» በድጋሚ ራሱን ያረጋግጣል። ማንም ሰው የተፈጥሮ መብቱን ሙሉ በሙሉ አሳልፎ ይሰጣል ተብሎ አይጠበቅም፤ ሰዎች በአንድ መንግሥት ስር ለመተዳደር የፈቀዱት ሕይወታቸው ይጠበቅ ዘንድ በሚል ነውና። ሕይወቱ በመንግሥት አደጋ የተጋረጠባት ተገዥ – ለምን የሞት ፍርደኛ የሆነ ወንጀለኛ አይሆንም – ከተቻለው የመከላከል፣ አልያ ደግሞ የማምለጥ መብት አለው። በተመሳሳይ፣ በወራሪ ጠላት ሽንፈት የገጠመውን ገዥ፣ ተገዢዎች የማክበር ግዴታ የለባቸውም። በእንዲህ ባለ ጉዳይ፣ ሉዓላዊው ሉዓላዊነቱ ያከትማልና ተገዢዎቹ ካለአንዳች ገደብ አጋርነታቸውን ለወራሪው የማድረግ መብት ይኖራቸዋል፤ ማለትም፣ ከተሸነፈው የቀድሞ መንግሥት በተሻለ ሊጠብቃቸው ለሚችል ለሌላ አካል።

ሉዓላዊ ሥልጣን የተሰጠው ሰው (ንጉሡ)፣ ወደአምባገነንነት እንዳይለወጥ በተፈጥሮው እንደተቀረው ሰው ለራሱ የሚመች መስተጋብሮአዊ ሁኔታን ለማምጣት የሚሻ በመሆኑ እውነታ  ይገደባል። እናም፣ ተገዢዎቹን ከውስጥ ስጋቶችና ከውጫዊ አለመረጋጋቶች ሊጠብቅ በሚያስችል ተጣጥሞሽ፣ ተገዢዎቹ ነፃነት እንዲኖራቸው ይፈቅድላቸዋል። በተመሳሳይ፣ በተቻለ መንገገድ ቅዋሜ እንዳይፈጠር በሚያደርግ መልኩ የቁሳዊ ነገሮችንና የሌሎች ጥቅሞች ክፍፍሎሾች አለመጓደላቸውን በትኩረት ይከታተላል። ሁሌም በሰብዓዊ ፍጡራን ግንኙነት ሊፈጠር የሚችለውን ግጭት ለማምከን እንዲቻል፣ በመንግሥቱ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ነገር የተዋቀረ መሆን አለበት። በአንድ መንግሥት ውስጥ አንድ የመንግሥት ሃይማኖትና የዚህ መንግሥት ርዕሰ-ብሔር በተመሳሳይ የቤተ-ክርስቲያኗ የበላይ የሆነው መሆኑ አስፈላጊ እንደሆነ ያስባል – ሆብስ። ካለው የእንግሊዝ የእርስ-በእርስ ጦርነት ተሞክሮው አንፃር፣ ሆብስ እንደሚለው፣ የትኛውም ዓይነት ሌላ አደረጃጀት ወደ አንጃነት እና ሽኩቻ ያመራል። ምንም እንኳን ሃይማኖት የግል ጉዳይ ቢሆንም፣ የሃይማኖት መንግሥታዊ ገጽታዎች የግድ ከመንግሥታዊ ሥልጣን ጋር ሙሉ በሙሉ በተዋረድ የተቀመጡ መሆን አለባቸው። መፅሐፍ ቅዱስ አሻሚ በሆነበት ስፍራ፣ አሳሪ ትርጓሜ የሚኖረው የመሪው መሆን አለበት። መሪው፣ የትኛው የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል ሃይማኖታዊ ገዢነት እንዳለው ይወስናል፤ እንዴት ባለ መልኩ ሃይማኖታዊ ትግበራዎች መከናወን እንዳለባቸው ይወስናል፤ ቤተ-ክርስቲያን እንዴት መደራጀት አለበት የሚለውን ይወስናል። በ“Leviathan” መፅሐፉ ክፍል አምስት ላይ፣ ሆብስ ትኩረቱን የሚያደርግባት የሮማ ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ከመንግሥት ሥልጣን ጋር ተጣጥሞሽ የላትም ምክያቱም ተከታዮቿ ለመንግሥት ከሚሰጡት ታማኝነት በበለጠ ለእርሷ እንዲሰጡ ትጠይቃለችና።

ሆብስ፣ ሕሊናን ወይም ምክንያታዊነትን መሠረት ባደረገ የተገዢዎቹ ፈቃድ ወይም ስምምነት ላይ መሠረት ያደረገና ለጋራ ጥቅማቸው የቆመ ፍፁም (ያልተገደበ) መንግሥትን ፅንሰ-ሐሳብ ማፍለቁ አጠያያቂ አቋም ያስይዘዋል። የሆብስ ፅሁፎች ግልፅነት፣ ጥንካሬ እና ቀጥተኛነት፣ እንዲሁም የመከራከሪያዎቹ ቅልብጭ ያሉ መሆን የፖለቲካ ተማሪዎችን ከሦስት ክፍለ ዘመናት በላይ ያስደመሙ ናቸው። መሠረታዊ ነጥቦቹን ነቅሶ ለተመለከተ፣ የእርሱ አስተምህሮ በጣም ቀላል ነው። ከሰብዓዊ ባሕሪይ የመጨረሻ መጥፎ ምልከታ አንፃር ሲታይ፣ ሰዎች ብዙ ቁጥር ኖሯቸውና ለማንኛውም የጊዜ መጠን ያህል አንድነት መስርተው መኖር የሚቻላቸው፣ ያላቸውን የአጥፊነት ዝንባሌዎች መቆጣጠር ወይም መገደብ በሚችል መንግሥት ስር ከተዳደሩ ብቻ ነው። ድህነትም (ነፃ መውጣትም) መሠረት የሚያደርገው ይህንን ለማወቅ ምን ያህል ምክንያታዊ ወይም የምናስተውል በመሆናችን እውነታ ላይ ነው። አንዳንዶቹ አስደናቂ፣ አንዳንዶቹ የማይመስጡ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ሊሳቅባቸው የሚችሉ ቢሆኑም፣ የሆብስን ፅንሰ-ሐሳብ የመቃወምም ሆነ ምላሽ የመስጠት ሙከራዎች መሰንዘር የጀመሩት “Leviathan” የተሰኘው መፅሐፉ ገና እንደታተመ ነበር። ሆኖም ምንም ነገር ቢመጣ በቀንዲልነት ከተቀዳጀው ቦታ ላይ የሚያነሳው ያለመኖሩ ሐቅ መጠኑ ሰፊ ነበር። ሆብስ፣ ከእንግሊዝ እጅግ አስደናቂ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ የፅንሰ-ሐሳብ አፍላቂዎች አንዱ እንደሆነ ቆይቷል። በተጨማሪም ለህይወቱ የሚያሰጉ አደጋዎች በተንዣበቡባቸው ጊዜያት፣ በብዙሃኑ ዘንድ ይሁንታ የማይሰጣቸው ምልከታዎችን ማቅረብ የቻለ ከፍተኛ ምሁራዊ ወኔን ያነገበ ፀሐፊ ነበር። በርግጥም ከዚያ በኋላ የታዩ ፖለቲካን እና ፖለቲካዊ ባሕሪይን ፍልስፍናዊ በሆነ መንገድ ለመመልከት የተደረጉ ሁሉም ሙከራዎች፣ ሆብስን መሠረት ያደረጉ ሊሆኑ ተገደዋል።

ለበለጠ ንባብ

ቀዳሚ ምንጮች

De cive, ed. H. Warrender (Oxford: Clarendon Press, 1983).

Leviathan, ed. R. Tuck (Cambridge: Cambridge University Press, 1991).

ተቀፅላ ምንጮች

Aubrey, J.: Brief Lives, ed. O.L. Dick (Harmondsworth: Penguin, 1982).

Hampsher-Monk, I.: A History of Modern Political Thought (Oxford: Blackwell, 1992).

Raphael, D.D.: Hobbes (London: Allen & Unwin, 1977).

Skinner, Q.: Visions of Politics, vol. 3: Hobbes and Civil Science (Cambridge: Cambridge University Press, 2002).

Warrender, H.: The Political Philosophy of Hobbes (Oxford: Oxford University Press, 1957).

Watkins, J.W.N.: Hobbes’s System of Ideas (London: Hutchinson, 1973).

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.