FEATUREDአንኳሮች

የፓርላማ ወንበር በውርስ ሊተላለፍ ይችላል?

(ብልፅግና ፓርቲ ህወሓትን ወዲያ ብሎ መንግሥት የሆነበት አግባብ እንዴት ይታያል?)

በግዛው ለገሠ (አዲሳባ)

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ አባላቱ ከፌዴራሉ መንግሥት ካቢኔ እና ከሌሎች ሥልጣኖች እየተነሱ መሆኑን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ የመረጠውና መንግሥት መስርተው እንዲመሩት የፈቀደው የኢሕአዴግ ድርጅቶችን ሆኖ ሳለ፣ “በማን አለብኝነት ሕዝብ ያልመረጠው ሌላ አዲስ ድርጅት [ብልፅግናን መሆኑ ነው] ሥልጣን እንዲይዝም ሆነ ሀገር እንዲመራም ማድረግ የሕዝቡን ሥልጣን መቀማትና ሕገመንግሥቱን መርገጥ ነው” ብሏል።

መግለጫውን ሳነበው የህወሓት ባይተዋርነት ተሰምቶኛል፤ መጨረሻ ላይ ያከለው ማስፈራሪያ ግን ከንቱ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ሕግ ተጥሷል ካለ ፍርድ ቤት አሊያም የፌዴሬሽን ምክር ቤት መሄድ ነው፤ “ካልሆነ ግን ይህንን ተከትሎ ለሚፈጠር ሁኔታ . . .” ብሎ ለማስፈራራት መሞከር ግን ከንቱ ነው፤ ለዚያውም ሰበብ የሚፈልግ አካል እያለ። (ገለልተኛ ፍርድ ቤትም ሆነ ዳኛ የታለ የሚል መከራከሪያም ውሃ አያነሳም።)

እኛ ስለ ህወሓት ምን አገባን ብለን፣ “Who cares?!” ብለን ማለፍ እንችላለን። ግን ደግሞ ለሕጉ ስንል፣ ይህንን ጥያቄ ልናነሳ ወደድን፦

ለመሆኑ ብልፅግና በምን መንገድ ነው መንግሥት የሆነው??

ቀላሉ መልስ “የፓርላማ መቀመጫ ወርሶ ነው” የሚለው ነው።

ለመሆኑ የፓርላማ ወንበር እንደሌላ ንብረት ይወረሳል እንዴ?

— ሕጉ ምን ይላል –

ብርቱካን ከመምጣቷ በፊት የነበረው የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 ሥራ ላይ የዋለው ያው ህወሓቶች የበላይ በነበሩበት ጊዜ ነው። ከእሱ ብንጀምር ይሻላልና ነው። ምን ይላል፣ አንቀጽ 33 እና ንዑሥ አንቀጾቹ ስለውህደት ውጤት ይተነትናሉ። እናም አንቀጽ 33/1/ሀ አዲሱ ውህድ ፓርቲ፣ “የተዋሃዱት የፖለቲካ ፓርቲዎች ወራሽ ይሆናል” ይላል። በሁለት ነጥቦች ይህ ንዑሥ አንቀጽ ስለ የፓርላማ መቀመጫ የውርስ ሀብትነት እያወራ ሊሆን እንደማይችል ማሳየት ይቻላል፦

1ኛ – ተጓዳኝ ንዑሥ አንቀጾቹ ፓርቲው እራሱን የቻለ ሕጋዊ ሰውነት እንዳለው አካል ስለመብት እና ግዴታ መተላለፍ፣ ስለፍርድ ቤት ክርክር መተካት እና ስለሂሳብ ሪፖርቶች የሚጥቅሱ በመሆናቸው፣ እንዲሁም ፓርላማ ላይ ወይም ማንኛውም እርከን ላይ ያለን መቀመጫ የሚመለከት ስለመሆኑ በግልጽ ባለማስቀመጡ፤

2ኛ – እና ዋናው ነጥብ ደግሞ ሕገመንግሥቱ የፓርላማ አባላት ተገዥነታቸው ለሕገመንግሥቱ፣ ለሕዝቡ (ለመረጣቸውም ሆነ ላልመረጣቸው ሕዝብ መሆኑን ልብ ይሏል)፣ እና ለሕሊናቸው መሆኑን መደንገጉ ነው። ይህ የሕገመንግሥቱ ድንጋጌ የፓርቲን እና የመንግሥትን ድንበር በግልጽ የሚያመላክትና መንግሥትነት የትጋ እንደሚጀምር የሚጠቁም ነው። በዘፈቀደ የሚወረስ ወንበር የለም የሚለውንም ያመላክተናል።

ታዲያ ብልጽግና እንዴት ሆኖ ነው መንግሥት የሆነው? ልመጣልህ እኮ ነው። እስካሁን ያወራንበት አዋጅ አሁን በቀደም በ2011 ብርቱካን ከመጣች በኋላ ተሽሯል፤ በምትኩ ሌላ አዋጅ አለን። ይህ አዋጅ ምን ይዞ መጣ?

— አንቀጽ 92 (3) –

አዲሱ አዋጅ “የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011” ተብሎ የቀድሞ ሦስት አዋጆችን ሽሮ እና ማሻሻያቸውን በአንድነት አጣምሮ የመጣ ነው። ለውጡን ተከትሎና የለውጡንም ሂደት በሁነኛነት ለማቀላጠፍ የፀደቀ አዋጅ ነው። የለውጡ ውጤትም ነው፤ ማስቀጠያም ነው ማለት ይቻላል።

ወደ ጉዳዬ ልመለስና፣ ይህ አዋጅ ብዙ መልካም ነገሮችን አሻሽሎና አካትቶ ነው የመጣው፤ በተለይ የምዝገባ መስፈርቱን እስማማበታለሁ። ነገር ግን ከላይ በተሻረው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ላይ የተመለከትነው አንቀጽ 33፣ አሁን አዲሱ ላይ አንቀጽ 92 የተባለ አቻ አለው። ሁለመናቸው አንድ ነው። የበፊቱ ሁለት ዋና ንዑሥ አንቀጾች ሲኖሩት፣ ከአዲሱ ጋር ይዘታቸው ቃል በቃል አንድ ናቸው። አዲሱ ውህድ ፓርቲ የተዋሃዱት የፖለቲካ ፓርቲዎች ወራሽ እንደሚሆንም ሁለቱም ይደነግጋሉ። ሆኖም አዲሱ አዋጅ አንድ ንዑሥ አንቀጽ ጨምሯል፤ 92 (3) የሚባል። ይሄን ንዑሥ አንቀጽ በጥንቃቄ አርቆ የጨመረው ሰው በትክክል መጪ ውህደት በራዕይ የታየው ካልሆነ በቀር ማንም ሊሆን አይችልም።

ከላይ እንደጠቀስነው ሁለቱም አቻ አንቀጾች ውህደት ስለሚያስከትለው ውጤት የሚደነግጉ ናቸው። በአዲሱ አዋጅ የተጨመረውን ንዑሥ አንቀጽ እንካቹ አንብቡት፦

“ውህደት የፈጠሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባል የነበረና በማናቸውም ደረጃ ያሉ ምክር ቤቶች ተመራጭ ሆኖ በማገልገል ላይ የነበረ ሰው በውህደቱ የተፈጠረው የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኖ መቀጠል የማይፈልግ ከሆነ የግል ተመራጭ እንደሆነ ተቆጥሮ የቀረውን የምርጫ ዘመን ያጠናቅቃል።”

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በውህደቱ ምክንያት የሚፈጠር የመንግሥት ኦናነት “vacuum” አይኖርም ብዬ የፃፍኩት አጭር ጽሁፍ ነበር። ይህንኑ ከላይ ያነበባችሁትን የአዋጁን አንቀጽ 92 (3) መሠረት አድርጌ ነበር መከራከሪያ ያቀረብኩት።

ይህንን አዲሱን ተደማሪ ንዑሥ አንቀጽ ገልብጠን ስናነበው ነው፣ ዓላማው የፓርላማ ወንበር የውርስ ሀብት ሊሆን እንደሚችል ለማስረገጥ የተካተተ መሆኑን የምንረዳው። ለምሳሌ፣ አንድ የቀድሞ ኦህዴድ አባል ፓርቲው ወደ ብልጽግና ሲዋሃድ አልተስማማኝም ካለ፣ ከአዲሱም ከአሮጌውም ፓርቲ ያለውን ግንኙነት አቋርጦ እንደ የግል ተወዳዳሪ የፓርላማ አባልነቱን ይቀጥላል። ይህ ቀጥታው ነው። ሲገለበጥ ደግሞ፣ አለመስማማቱን ካልገለፀ እርሱም የአዲሱ ፓርቲ አባል ሆኖ መቀጠሉ፣ ፓርላማ ያለውም መቀመጫም የአዲሱ ውህድ ፓርቲ ውርስ እንደሆነ ቅድመ-ግምት (presumption) እየተወሰደ ነው – በሕጉ ድንጋጌ መሠረት ማለት ነው።

— የአረቃቀቁ ብልሃት —

ከላይ ሕጉ “ወራሽ ይሆናል” ማለቱ የፓርላማ መቀመጫን ማለቱ አይሆንም በማለት በ2ኛነት ያስቀመጥነውን መከራከሪያ፣ ማለትም የፓርላማ አባል ተገዥነቱ ለሕገመንግሥቱ፣ ለሕዝቡና ለሕሊናው ነው የሚለውን የሕገመንግሥቱን ድንጋጌ፣ በዚያውም የፓርቲነትን እና የመንግሥትነትን ድንበር መጣስ ይሆናል ያልነውን ሀሳብ ለመመከት ሲባል ሳይሆን አይቀርም፣ አዲሱ ንዑሥ አንቀጽ እንዲህ የተረቀቀው። ይህን ጥያቄ ስታነሳ፣ “ለሕገመንግሥቱስ፣ ለሕዝቡስ፣ ለሕሊናውስ እንዳይገዛ ማን ከለከለው? እንዲያውም ይህን ለማስረገጥ ነው የንዑሥ አንቀጹ መጨመር” በማለት አርቃቂዎቹ ቢመልሱልህ፣ “ከባድ ጊዜ ላይ ነው ያለነው!” ከማለት ውጪ ምን ትላለህ?

— አብላጫ መቀመጫ —

ኢሕአዴግ የተባለው የፓርቲዎች ግንባር ነበር እስከዛሬ አብላጫ መቀመጫውን ይዞ መንግሥትነትን ይመራ የነበረው፡፡ ከብልጽግና ውህደት በፊት ይህ ግንባር ፈርሶ ቢሆን ኖሮ፣ አብላጫ መቀመጫ ያለው ፓርቲ ስለማይኖር፣ በሕገመንግሥቱ መሠረት በፕሬዝዳንቱ ጋባዥነት ፓርላማ ውስጥ ያሉት ፓርቲዎች ሌላ ግንባር ወይም ጥምረት በአንድ ሳምንት ውስጥ እንዲፈጥሩና ሌላ መንግሥት እንዲመሰርቱ ይጠየቁ ነበር፡፡

ነገር ግን ከግንባሩ መፍረስ የብልፅግና ውህደት ቀደመና አብላጫ መቀመጫውን ያዘ፡፡ ህወሓት እንዳነሳው ዓይነት ማንኛውንም ጥያቄ ብታነሳ፣ «መቼ አብላጫ መቀመጫ ያለው ፓርቲ ጠፋና!» ትባላለህ፡፡

እንግዲህ አንቀጽ 92 (3) ቀላል አንቀጽ እንዳልሆነ ትረዳለህ፡፡ የብልፅግና አርክቴክቶች እንዴት የአብላጫ መቀመጫን የመንግሥትነት መስፈርት «Bypass» ለማድረግ እንደተጠቀሙበት ትረዳለህ፡፡

* * *

ለማንኛውም ይህን ሁሉ መዘብዘቤ ለህወሓት ተቆርቁሬ አይደለም፤ የሀገራችን ሕግ እና ሥርዓቱ ስለሚያሳስበኝ ነው። “የስዬ ሕግ” በመባል የሚታወቀውን አዋጅ ማንም ያስታውሰዋል፤ የዳኛ ብርቱካንን የአሁኗን የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር ቁርጠኛ ውሳኔ ለመመከት የወጣ የጥድፊያ ሕግ ነበር። እንዲህ ያሉ አያሌ ሕጎች እንዳሉን መንግሥትም አይክድም።

ነገር ግን የለውጡ ውጤት እና የለውጡ መሠረታዊ ማቀላጠፊያ የሆነው ይህ አዲሱ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ፣ በተለይም በዚህ ጽሁፍ የተመለከትነው ዋነኛ ንዑሥ አንቀጽ 92 (3)፣ “የስዬ ሕግ” ባህሪይን የወረሰ ከሆነ እውነትም ከባድ ጊዜ ላይ ነን። ምክንያቱም ከሕግ የበላይነት መርሆዎች አንዱ፣ እራሱ ሕጉ ሲወጣ መሠረታዊ የሕግ አወጣጥ መርሆዎችን መከተል አለበት የሚል ነው።

እስካሁን ባየነው መጠነኛ ትንታኔ፣ የህወሓት መከራከሪያ ውሃ ያነሳል? መልሱን ለእናንተው ትቼዋለሁ፤ ምክንያቱም ስለ ህወሓት ምን አገባኝ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.