FEATUREDአንኳሮች

ጀዋር የራሱ ጉዳይ፣ ሕጉን ግን በአግባቡ እንተርጉመው!

(የሕግ ትንታኔ – በግዛው ለገሠ)
—–

ፖለቲከኛው፣ ‘አክቲቪስቱ’፣ እንዲሁም መደበኛው ሕዝብ ሕግን እንደፈለገ ሲያጣምመው ሳይ ላይገርመኝ ይችላል፡፡ ሕግ አዋቂ ነኝ የሚል ግን ሲነውር መመልከት ያማል፡፡

ቡርቴ (ብርቱካን ሚደቅሳ) ሕጉን ሳትረዳው ቀርታ እንዳልሆነ ፍፁም እምነት አለኝ፡፡ ለኢምግሬሽን የተላከው ደብዳቤም በእሷ ስም አለመሆኑ ለእመንቴ ስል ደስ ብሎኛል፡፡

ጉዳዩ ስለጀዋር ተደርጎ ሲታመስ የነበረ በመሆኑ፣ ለቅርብ ወዳጆቼ ከማስረዳት በቀር ምንም ነገር ፅፌ አላውቅም፡፡ አቢሲኒያ ሎው ላይ አንድ ፅሁፍ በማንበቤ ግን ቅር ተሰኝቼ ይህን እየፃፍኩኝ ነው፤ ጀዋር የራሱ ጉዳይ ብለን ሕጉን ለመደበኛው ሕዝብ ማስረዳት ይጠበቅብናል፤ ሌላው ቢቀር የጋሽ ዳንኤል አፅም ምን ይለናል፡፡ (ዩኒቲ የሕግ ትምህርት ቤት ዲን ነበር፤ ነፍሳቸውን ይማር፡፡)

እዚህ ሀገር ሕግን በተግባር ከመጣስ ባልተናነሰ አዛብቶ መተርጎም እየጨመረ መጥቷል፤ ይህ ከዚህ ቀደም በጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ በምርጫ ቦርዱም (ሕገመንግስቱን ቀና ነው ብለው ባሰቡት መልኩ ግን በስህተት ሲተረጉሙት) ተስተውሏል፡፡ ስለዚህ ለናንተ ስል ዜግነትን መልሶ ስለማግኘት እንዲህ በአጭሩ አስረዳለሁ (አደራችሁን ስታነቡ ስለ አንድ ሰው ብቻ አታስቡ፣ ሕግ እንደዚያ አይታይም፣ ለብዙ ሰው ነው የወጣው)፡፡

1) ኢትዮጵያዊ መሆንህ በምን ይረጋገጣል? ወላጆችህ ወይም ከሁለት አንዱ ኢትዮጵያዊ ከሆኑ፣ በቃ ኢትዮጵያዊ ነህ(የአዋጁ አንቀፅ 3)፡፡ የዜግነት መታወቂያ ወረቀት የማግኘት መብት አለህ፣ ባለስልጣኑም የመስጠት ግዴታ አለበት (አንቀፅ 13)፡፡

2) ኢትዮጵያዊነት በትውልድ ወይም በደም ብቻ ሳይሆን በሕግም ይገኛል፡፡ በዚህ መልኩ ኢትዮጵያዊነትን የሚጠይቁ ሰዎችን ሕጉ «የውጭ አገር ሰው» ይላቸዋል፤ ሲተረጉመውም «የኢትዮጵያ ዜጋ ያልሆነ ማንኛውም ሰው» ይለዋል፡፡(የአዋጁ አንቀፅ 5 – 12 እንዴት የውጭ ሀገር ሰዎች በሕግ ኢትዮጵያ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይተነትናሉ፤ እናም ቃለ መሃላ እና የመሳሰሉት ብዙ የሰነድ ማረጋገጫን ጨምሮ ውጣ ውረዶች አሉት፡፡)

3) በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው አልፈልግም ብሎ የሌላ ሀገር ዜግነት መያዝም ይችላል፡፡ ይህ ዜግነት የመለወጥ መብት ራሱ ንብረት እንደማዞር ዓይነት ተራ መብት አይደለም፤ ኢትዮጵያዊ በመሆንህ ብቻ የምታገኘው «የዜግነት መብት» ነው፡፡ (ይህም በአዋጁ ክፍል ሦስት ስር «የዜግነት መብቶች» በሚል ርዕስ ስር ከተደነገጉት በአንቀፅ 16 የሰፈረ ነው፡፡)

4) ኢትዮጵያዊ ዜግነት ይህን መብት በማስፈፀም መልኩ እንጂ «በማንኛውም መንግሥታዊ አካል ውሳኔ» አይገፈፍም ይላል የአዋጁ አንቀፅ 17፡፡

5) ሆኖም ኢትዮጵያዊነትን መተው መብት ቢሆንም ሕጉ ግን ሜዳ እንዳንቀርበት ስለሆነ ግቡ፣ ለኢትዮጵያዊያን እና ኢትዮጵያዊነት መቆም ስለሆነ መንፈሱ፣ እንዲሁ ከመሬት ተነስተህ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም በማለት ብቻ የምትላቀቀውም አይደለም – ኢትዮጵያዊነት፡፡ ኢትዮጵያዊ (መልኩን)፣ ነብር ዝንጉርጉርነቱን እንደተባለው ነው ነገሩ፡፡ እናም «የሌላ አገር ዜግነት ያገኘ ወይም ሊሰጠው ቃል የተገባለት» ኢትዮጵያዊ ብቻ ነው ይህ መብቱ የሚፈፀምለት፡፡ ይህን እና ሌሎችም የአንቀፅ 19 መስፈርቶችን ካላሟላ ኢትዮጵያዊነቱ በመብትም ቢሆን አይገፈፍም፡፡

6) ሌላ ምሳሌ ለመጨመር ያክል፣ አንድ ኢትዮጵያዊ ከኢትዮጵያዊነት በተጨማሪ ድርብ ዜግነት ይዞ ቢገኝ፣ የሌላ አገር ዜግነት መብቱን መጠቀም ካልጀመረ (ለምሳሌ ካልመረጠ ወይም ሌላ የዜግነት መብቶችን ካላጣጣመ) ወይም ያንን ድርብ ዜግነቱን ከያዘ አንድ ዓመት ካልሞላው፣ ደብል ሲቲዝን መሆኑ በግልፅ እየታወቀ እንኳን «የኢትዮጵያ ዜግነት እንዳለው ሆኖ ይቆጠራል» ይላል ሕጉ፡፡ (አንቀፅ 20 (4))

7) ይህ ሁሉ አልፎ አንድ ኢትዮጵያዊ የሌላ አገር ዜጋ ሆኖ ኢትዮጵያዊነቱን ካጣ በኋላ እንኳን፣ ሕጉ እንደ ተራ የውጭ አገር ዜጋ አይመለከተውም፡፡ ተመልሼ ኢትዮጵያዊ ልሁን ብሎ ቢመጣ የውጭ አገር ዜጋ ነህና ተራ ቁጥር ሁለት ላይ ከላይ በጠቀስኩት የሕግ ዜግነት በማግኛ ሂደት እለፍ አይለውም፡፡ ኢትዮጵያዊነቱ ለጊዜው ቆም ተደረገ እንጂ አልተፋቀም በሚል እሳቤ ከውጭ አገር ዜጎች የተለየ መስፈርት አስቀምጦለታል፡፡ (እንግዲህ የሰሞኑ አተካራ እርሱን የሚመለከት ሲሆን፣ እስካሁን ያየነው የሕጉን መንፈስ እንድታጤኑት የታለመ ነው፡፡)

8)- በቀላል አማርኛ፣ ሕጉ ኢትዮጵያዊነትን መልሶ ማግኘትን በተለየ መልኩ ማየት የፈለገበት ዋና ምክንያት፣ ቀድሞውኑ በትውልድ/በደም የተፈጠረን ዜግነት (ማንነት) በሕግ መልሼ ልስጥ ብል ይሳቅብኛል ብሎ አፍሮ ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ በመብት አማካኝነት የተገፈፈ ዜግነት እንደገና የምንጎናፀፈው በመብትና በተለየ ሂደት እንጂ እንደሌላ የውጭ ሀገር ዜጋ በመቆጠር አለመሆኑን፣ ክብራችንን እያረጋገጠልን ነው፡፡

9) እናም ይህ የተለየ ሥርዓት አንቀፅ 22 (1) ላይ ይገኛል፡፡ አስቀድሞ ኢትዮጵያዊ የነበረና በሕግ የሌላ አገር ዜግነት ያገኘ ሰው፣ አንደኛ ኢትዮጵያ ተመልሶ መኖሪያውን እዚህ ካደረገ፣ ሁለተኛ ይዞት የነበረውን የሌላ አገር ዜግነት ከተወ፣ ሦስተኛ ዜግነት እንዲመለስለት ለኢሚግሬሽን (ለባለሥልጣኑ) ካመለከተ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን መልሶ ያገኛል ይላል፡፡ በቃ ሌላ ርቀት አይጠበቅበትም፤ ቅድመ-መርሆ (presumption) ተወስዷል በሕጉ፤ የአመልካቹ የማስረዳት ግዴታው (burden of proof) ተላልፏል ለባለሥልጣኑ፡፡ እነዚህ ሦስት ነገሮች ከተሟሉ ባለሥልጣኑ «ከዚህ በኋላ ዜጋ ሆነሃል» የማለት ሥልጣንም፣ ኃላፊነትም፣ ግዴታም የለበትም፡፡ ሆኗላ!

10) ዜግነትን መልሶ ለማግኘት የባለሥልጣኑን ወይም የኢሚግሬሽንን ውሳኔ እንደ መስፈርት እንዲቆጠር ቢፈልግ ኖሮ አራተኛ አድርጎ ይጨምረው ነበር፡፡ (ዋናው ዓላማው፣ ከላይ ተራ ቁጥር 4 ላይ እንደገለፅኩት የመንግሥታዊ አካል ውሳኔንም መገደብ ነው፡፡) ይልቁንም የአዋጁ መሠረታዊ ድንጋጌዎች ከላይ ባየነው አንቀፅ 22 ይጠናቀቃሉ፡፡

11) ሆኖም አዋጁ «ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች» በሚል ርዕስ ስር ጥቂት አንቀፆችን ከኋላ ይጨምራል፤ እንደማንኛውም አዋጅ መሸጋገሪያ እና ማስፈፀሚያ ሥነ-ሥርዓታዊ ሁኔታዎችን «ልዩ ልዩ» በማለት ያስቀምጣል፡፡ እንግዲህ ከመግቢያዬ ላይ ቅር አሰኘኝ ያልኳቹ የአቢሲኒያ ሎው ፅሁፍ እዚህ ውስጥ የተካተተን ድንጋጌ እንደመስፈርት ማንሳቱ ነው፡፡

12) አንቀፅ 23 የዜግነት ጉዳይ ኮሚቴ ስለመቋቋሙ፣ ስለአባላቱና ሥልጣን እና ተግባሩ ይዘረዝራል፡፡ እናም ንዑስ አንቀፅ 2/ሐ፣ የኢትዮጵያ ዜግነትን መልሶ ለማግኘት ማመልከቻ ሲቀርብ ከላይ ያየናቸውን ሦስት ሁኔታዎች (እኛ መስፈርቶች ያልናቸውን) መሟላታቸውን የማረጋገጥ ሥልጣን ኮሚቴው እንዳለው ይገልፃል፡፡ ያረጋግጥ ጥሩ ነው፤ አጭበርባሪ ይኖራል፡፡ ግን ተሟልተው ከተገኙስ ኮሚቴው ወይም ባለሥልጣኑ ምን ያደርጋሉ? ምንም! ምክንያቱም ቅድም ያየነው አንቀፅ 22 (1) ጉዳዩን ጨርሶታል፣ ከተሟሉ ኢትዮጵያዊ ሆኗል ብሏል፡፡ ማለትም፣ ሰውዬው ኢትዮጵያ መኖር ከጀመረ፣ የሰው ሀገር ዜግነቱን ከመለሰ፣ ኢትዮጵያዊነቱ እንዲመለስለት ካመለከት ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በቀላል አማርኛ፣ ካልተሟሉ ኢትዮጵያዊ አይደለም፡፡

13) ሌላው ቀርቶ እነዚያ ሁኔታዎች መሟላታቸውን ኮሚቴው የሚያረጋግጠው በባለሥልጣኑ ሲመራለት ብቻ ነው (አንቀፅ 23 (3))፡፡ ባይመራለትስ፣ በቃ አልተመራለትም፣ ፕሪዘምሽኑ ይቀጥላል፤ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡

13) ሌላ ግልፅ ማስረጃ ላሳይ፣ እዚያው ከኮሚቴው ሥልጣን እና ተግባር መሃል አንቀፅ 23 2/ሀ ላይ የሌላ አገር ዜጎች በሕግ የኢትዮጵያ ዜግነት ለማግኘት የሚያቀርቡትን ማመልከቻ ኮሚቴው የመመርመር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ መርምሮ ምን ያደርጋል፣ ሂደቱስ እንዴት ነው የሚለው ሁሉ በዝርዝር በአዋጁ ከላይ ባሉ ድንጋጌዎች ተገልጿል፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንቀፅ 11 (3) ላይ፣ ኮሚቴው መርምሮና ውሳኔ ሀሳብ ሰጥቶ፣ ከዚያም ባለስልጣኑ የሕግ ዜግነት ጥያቄው ተቀባይነት አለው ብሎ ሲያምን አመልካቹ ተጠርቶ ቃለ መሃላ እንዲፈፅም ተደርጎ «የምስክር ወረቀት» ይሰጠዋል፡፡ ቀድሞውኑ በደሙ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው ግን ድጋሚ ኢትዮጵያዊ እንዲሆን ቃለ መሃላ አይጠበቅበትም፤ «ደሙ ይበቃል» ብሏል ሕጉ፡፡ የምስክር ወረቀትም እንደዚያው፡፡

——

በአጠቃላይ፣ ስለፕሪዘምሽን እና በርደን ኦፍ ፕሩፍ የማይረዳ ሰው እንደፈለገ ቢፅፍና ቢያወራ ምንም አይደለም፡፡ ግን ሕግ አውቃለሁ የሚለውም ሳይቀር፣ አውቆም ይሁን በእንዝላልነት ያልሆነ ነገር ሲዘባርቅ ይደብራልና ነው እንዲህ ጊዜዬን መግደሌ፡፡ አራት እና አምስት ዓመት የለፋንበትን የሕግ ትምህርት ለእኩይ ተግባር ማዋል እንዲሁ ንፉግነት ብቻ አይደለም፤ እኩይነትም ነው፡፡ ነግ በኔ ነው፤ ዛሬ በአንድ ግለሰብ ምክንያት አጣመን የተረጎምነው ሕግ፣ ነገ እያንዳንዳችን ልንዳኝበት መሆኑ ሊያሳስበን ይገባል፡፡

ጀዋር ግን የራሱ ጉዳይ ፡)

/እስካሁን የተነተንኩት አዋጅ «የኢትዮጵያ ዜግነት አዋጅ ቁጥር 378/1996» ይባላል፡፡ ከታች አግኙት፡፡/

አበቃሁ!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.