ለተሰንበት ግደይ – የፅናት ማማ!
በቶክዮ ኦሎምፒክ የ10000ሜ ሴቶች ሩጫ። አየሩ ከፍተኛ ሙቀት ነበረው። በዚህ ወበቅ ሁሉንም በራሷ ፔስ እያስሮጠች ስንቱን እያረገፈች ሩጣለች – ለተሰንበት ግደይ። ብዙዎቹ እያቋረጡ መውጣት ጀመሩ።
ከግማሽ በኋላ የአራት ሴቶች ውድድር ሆነ። ለተሰንበትን ተጣብቀው 5000ሜ ብር ሜዳሊያ ያጠለቀችው የኬንያዋ ኦብሪ፣ 5000ሜ ወርቅ እና 1500ሜ ነሃስ ያጠለቀችው የሆላንዷ ሲፋን ሀሰን ትንፋሽ ለትንፋሽ እየተማማጉ ይታገሏት ጀመር።
ይህ ሁሉ ሲሆን በአስገራሚ አቋም ርቀቷን ጠብቃ በማድፈጥ አራተኛ ሆና ስትከተል የነበረችውን የባህሬኗን ቃልኪዳን ገዛኽኝ የጠበቀ አልነበረም።
ሩጫው እየተገባደደ ሲመጣ ሙቀቱን እና የለተሰንበትን አመራር መቋቋም ያልቻለችው ኦብሪ ወደኋላ አፈገፈገች። ከዚያም ሩጫው በሦስቱ መካከል ሆነ – በኢትዮጵያዊዋ ለተሰንበት እና በትውልደ ኢትዮጵያዊያኖቹ ሲፋን እና ቃልኪዳን።
ባለፉት ቀናት ተደጋጋሚ ማጣሪያዎችን እና ፍፃሜ ውድድሮች ያደረገችውን ሲፋን ሀሰን ጭምር ማድከም እና ተስፋ ማስቆረጥ የሚቻለው በዚህ መልኩ እንደሆነ ለተሰንበት ያመነችበት ይመስላል። ግን አልተሳካም፤ ሲፋን ደብዛዛው ወላፈናዊ ንፋስ እንኳን እንዳይነካት በለተሰንበት ጀርባ ላይ ተጣብቃ መታገሏን ቀጠለች።
ለተሰንበት የምትችለውን ብታደርግም በመጨረሻው ዙር ሲፋን ታግላ ወጣች፤ ቃልኪዳን ተከተለች። ሲፋን ይባስ ተስፈነጠረች፤ ተሳካላት፤ በ10ሺም ወርቅ አጠለቀች። ቃልኪዳን ብር ሜዳሊያ ተቀዳጀች። ሙሉ ውድድሩን በአስገራሚ ብቃት የመራችው ለተሰንበት ሦስተኛ ወጣች።
ለተሰንበት እና ሲፋን ከውድድሩ በኋላ ድካማቸው ይታያል። የባህሬኗ ቃልኪዳን ግን ገና ለመሮጥ የምታሟሙቅ ትመስል ነበር።
25 አትሌቶች በተሳተፉበት በዚህ የቶክዮ ኦሎምፒክ 10000ሜ ሦስቱ ኢትዮጵያዊያንን (እነ ለተሰንበትን) ጨምሮ ስምንት ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወይም ከኢትዮጵያ ጋር የቆየ ቁርኝት ያላቸው አትሌቶች ይገኙበታል። እነዚህም የሆላንዷ ሲፈን፣ የባህሬኗ ቃልኪዳን፣ የስዊዲኗ ምዕራፍ ባህታ፣ የእስራኤሏ ሰላማዊት ተፈሪ እና የኤርትራዋ ዶልሺ ተስፉ ናቸው።
በዚህ ውድድር ሲፋን እና ቃልኪዳንን አለማድነቅ ባይቻልም፣ የለተሰንበትን አስደሳች እና አኩሪ ፅናት መላው ኢትዮጵያዊ ሲያስታውስ እና ሲገረምበት ይኖራል።