COVID-19FEATUREDHealthNewsUncategorized

ኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ የመጀመሪያ ሰው መገኘቱን ይፋ አደረገች

  • ጃፓናዊ
  • እድሜ 48
  • የካቲት 25 ከቡርኪና ፋሶ ወደ ኢትዮጵያ ገባ

የጤና ሚኒስቴር ከሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን የሰጠውን ሙሉ መረጃ ከዚህ በታች ያንብቡ።

በአገራችን፣ የኮሮና ቫይረስ ያለበት የመጀመሪያው ሰው ተገኝቷል
መጋቢት 4/2012 ዓ/ም

_______

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ በቫይረሱ የተያዘ ግለሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱን አረጋገጠ፡፡

ግለሰቡ፣ የ48 አመት የጃፓን ዜጋ ሲሆን፣ የካቲት 25/ 2012 ዓ/ም ከ ቡርኪና ፋሶ ወደ አዲስ አበባ መምጣቱ ታውቋል፡፡ ኢትዮጵያ፣ በሽታው ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ በተዘረጋው የተጠናከረ የበሽታዎች ቅኝት ስራ፣ የመጀመሪያውን ታማሚ ለመለየት ችላለች፡፡ ከበሽተኛው ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው ግለሰቦችም የመለየትና ክትትል የማድረግ ስራ ተጀምሯል፡፡ ታማሚው፣ አስቀድሞ በተዘጋጀው የለይቶ ማከሚያ፣ ተገቢው የሕክምና ክትትል እየተደረገለት ሲሆን፣ እስካሁን ባለው ሁኔታ የከፋ የጤና እክል አልገጠመውም፡፡

የኮሮና ቫይረስ አገራችን ውስጥ መገኘቱ፣ የጀመርናቸውን እርምጃዎች እንድናጠናክር እንጂ እንድንደናገጥ ሊያደርገን አይገባም። መደናገጥ እና አጉል ፍራቻ፣ ከበሽታው እኩል አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህ በሽታ የሚያዝ አብዛኛው ሰው፣ ቀላል ህመም ከያዘው በኋላ ይድናል። ነገር ግን እድሜያቸው በገፉ ወይም ተጨማሪ በሽታ ባላቸው ሰዎች ላይ፣ህመሙ የከፋ ሊሆን ይችላል።

የኢትየጲያ መንግስት እና የጤና ሚኒስቴር፣ በሽታው ቻይና ከተገኘበት ወቅት ጀምሮ፣ ቫይረሱ ወደ አገር እንዳይገባ፣ ከገባም ጉዳቱን ለመቀነስ፣ በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። ብሄራዊ የሚኒስትሮች ኮሚቴ በክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ ተቋቁሞ፣ የመከላከል ጥረቱን እየመራ ይገኛል። በተጨማሪም፣ በጤና ሚኒስተርና በህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የሚመራ ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ አባላት ያሉት የቴክኒካል ግብረ ሃይል ቅንጅታዊ አሰራሩን እየመራ ይገኛል።

መንግስትም፣ የበሽታውን አሳሳቢነት በመረዳት፣ በጀት የመደበ ሲሆን ተጨማሪ በጀት እያፈላለገ ይገኛል። ለዚሁ በሽታ መካላከል ሲባል፣ በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ውስጥ የድንገተኛ ኦፕሬሽን ማእከል ተቋቁሞ፣ ሃያ አራት ሰአት እየሰራ ይገኛል። በዚህ በሽታ ለተጠረጠሩ ግለሰቦች ማቆያ የሚሆኑ የተለዩ የጤና ተቁማት ተዘጋጅተዋል። በዚህ በሽታ የታመሙ ሰዎችን ለማከምም፣ የካ ኮተቤ ሆስፒታል አስፈላጊው የህክምና መሳሪዎች እና ባለሙያዎች ተሟልተውለት ዝግጅቱን አጠናቋል። ዝግጅቱን ለማጠናከር ተጨማሪ ባለሞያ የመቅጠር ሂደት ተጀምሯል፡፡

የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መንግስት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት እና ለመቆጣጠር ተገቢውን እርምጃ እየወሰደ መሆኑን እያረጋገጡ፣ ማህበረሰቡ የሚከተሉትን የመከላከያ መንገዶችን ችላ ሳይል እና ሳይደናገጥ ተግባር ላይ በማዋል፣የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የበኩሉን እንዲወጣ ያሳስባል።
● ሳል ወይም ትኩሳት ካለው ግለሰብ ቢያንስ ሁለት የአዋቂ እርምጃ ርቀት ያህል መራቅ
● እጅዎን በአግባቡ ሳይታጠቡ አይንና አፍንጫዎን አይንኩ
● ከሰዎችጋር አይጨባበጡ፣
● እጅን በንጹህ ውሃና ሳሙና አዘውትረው ይታጠቡ፣
● ሰዎች ወደ በሚበዙባቸው ቦታዎች በተለይም የህመም ስሜት ካልዎት አይሂዱ፣
● በሚያነጥሱበት እና በሚያስሉበት ጊዜ አፍና አፍንጫዎን በሶፍት ወይም ክርንዎን አጥፈው በመጠቀም
ወደ ሌሎች እንዳያስተላልፉ ይጠንቀቁ፣ የተጠቀሙበትን ሶፍትና ተመሳሳይ ነገሮች በቆሻሻ ክዳን ባላቸው
ማጠራቀሚያ ያስወግዱ፣
● በስራ ቦታ፣በትራንስፖርት እና መኖሪያ ወይም የመኝታ ክፍል መስኮት በመክፈት በቂ አየር እንዲኖር
ያድርጉ፣
● መረጃዎችን ከአስተማማኝ ምንጮች ብቻ በመቀበል፣ የተሳሳቱ መረጃዎች የሚያስከትሉትን መደናገር እና
ፍርሀት እርሶም ይከላከሉ!

የበለጠ መረጃ ሲያስፈልግ ነጻ በሆነው 8335 የስልክ መስመር ላይ መደወል ይቻላል፡፡

ፎቶ፡ ከጤና ሚኒስቴር የፌስቡክ ገጽ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.