የወዳጅ ምክር ስለኮሮና ቫይረስ
ወዳጄ፣
– ስንገናኝ ባልጨብጥህ፣
– ምን ያህል ብትናፍቀኝ ባልጠመጠምብህ፣
– ስታወራኝ ሁለት ክንድ ሆኜ ባዳምጥህ፣
– ምሳ እንደባህላች ገባታህ ላይ ባልቀርብ፣
– ከፍቅራችን የተነሳ ልታጎርሰኝ ስትሞክር እምቢኝ ብል፣
– ልታገኘኝ ፈልገህ አይመቸኝም ብልህ፣
– ቤትህ ደስታህን እንድካፈል ብትጋብዘኝና ብቀር፣
– እርምህን ብበላ፣
በእመቤቴ ይዤሃለሁ፣ አትቀየመኝ! እኔም ያንኑ ባይብህ አልቀየምህም!
ጉዳዩ የከፋ ነውና ለጋራ ጥቅም ስንል፣ የሚከተሉትን እናድርግ፦
– የምንነካካው አይታወቅምና እጃችንን ቶሎ ቶሎ እንታጠብ፣
– ጣት የመብላት፣ አፍንጫ የመጎርጎር ልምድ ካለብ እንታቀብ፣
– ሰው ላይ አንሳል፣ አናስነጥስ፣ በተቻለ መጠን እንሸፍነው፣
– በተቻለ መጠን ሰው የተሰበሰበበት ቦታ አንገኝ፣ ግድ ከሆነ እንጠንቀቅ፣
– አፍ መሸፈኛ፣ መደበኛ የፅዳት መከላከያ አካባቢያችን አይጥፋ፣
– ነጋዴ ከሆንን ደግሞ ኮሮና መጣ ብለን ሕዝባችን ላይ የዋጋ ቁለላ እና የእቃ ድበቃ አናካሂድ፣
– ቫይረሱ በቁሳቁስ ላይ ለሰዓታት ሊቆይ ስለሚችል፣ የበር እጀታዎችን እና ሌላ ነገሮችን ከነካን ሳንታጠብ አንብላ፣ እጃችንን አፋችን፣ አፍንጫችን ጋ አናድርስ፣
– እንደኔ ልጆች ካሉህ ደግሞ (ፈጣሪ ተጨምሮበት) በተቻለ መጠን ከውጭ ንክኪ ጠብቃቸው፣
– አረጋዊያን ይበልጥ ተጠቂ ስለሆኑ፣ እባክህ እንክብካቤ አድርግላቸው፣ ግንዛቤም እንዲያደርጉ አድርግ፣
– ወቅቱ ፆም በመሆኑ ቤተስኪያ ሄዶ ማስቀደስ ግድ ሊሆን ይችላል፣ ኦርቶዶክስ ቤተስኪያን ምን መመሪያ እንደምታወጣ አላውቅም፣ ነገር ግን ምዕመኑ እቤት ሆኑ ሱባኤ እና ምህላ እንዲያደርግ ቢደረ ብዬ እኔ ደካማው እመክራለሁ፣
– ሙስሊም ወንድሞቼ፣ በጋራ ሶላት የማድረግን ጥቅም ለእናንተ መንገር ፌዝ ይሆንብኛል፤ ነገር ግን ካሁኑ በጋራ ልናስብበት የሚገባ ይመስለኛል፣
አምላክን እናግዘውና የድርሻችንን እንወጣ፣ እራሳችንን እንጠብቅ፡፡ ከባህላችን እና አኗኗራችን አንፃር፣ ከአብሮ መኖር ልማዳችን አኳያ እኛ ላይ ስጋቱ ይበረታል በማለት ነው ይህን ሁሉ መዘብዘቤ፡፡
ወዳጄ፣ ወዳጅነታችን ይቀጥል! ግን ከላይ የዘበዘብኩት ላይ ያንተንም የተሻለ መረጃና ምክር ጨምረህበት ለሌሎች ወዳጆቻችንም አጋራ! በርታልኝ!
_____________
በግዛው ለገሠ