የሀገር ውስጥ ስርጭት 55%፤ ንክኪያቸው የማይታወቅ 23% ደርሷል
(ግንቦት 15 ቀን 2012)
ዛሬ ከፍተኛ የኮቪድ-19 የምርመራ ውጤት ተመዝግቧል። ከ3757 የላብራቶሪ ምርመራዎች ውስጥ 61 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።
የዛሬውን ውጤት ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው 45 ሰዎች የጉዞ ታሪክም ሆነ የታወቀ ንክኪ የሌላቸው መሆኑ ነው። ከነዚህም ውስጥ 43ቱ በአዲስ አበባ የተያዙ ናቸው። በአዲስ አበባ ሌሎች በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው 5 ሰዎችም መያዛቸው ተነግሯል።
በሌላ በኩል 11 ሰዎች የጉዞ ታሪክ እንዳላቸው ተገልጿል። ነገር ግን 8ቱ ብቻ በለይቶ ማቆያ የነበሩ መሆናቸውን ከዛሬው መግለጫ መረዳት ችለናል፤ ይኸውም 1 ሰው አማራ ክልል በደሴ ለይቶ ማቆያ፣ እንዲሁም 7 ሰዎች ሱማሌ ክልል በጅግጅጋ ለይቶ ማቆያ የነበሩ ናቸው።
ነገር ግን ስለተቀሩት 3 የጉዞ ታሪክ ስላላቸው ሰዎች መግለጫው፣ «ከአፋር ክልል በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው እና በዱብቲ ለይቶ ማቆያ ያሉ» በማለት ይጠቅሳቸዋል። ከዚህም መረዳት የሚቻለው እነኚህ ሰዎች የጉዞ ታሪክ ቢኖራቸውም በወቅቱ ወደ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ሳይገቡ ከሕብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው የነበሩ መሆናቸውን ነው። ይህንን በአንክሮት ለመመልከት የተገደድንበት ምክንያት አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ እርምጃው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ከሕብረተሰቡ እንዳይቀላቀሉ በማድረግ ረገድ ያስገኘውን ውጤት እየተከታተልን ስለነበር በመሆኑ ነው። (ይህኛው የመግለጫው አረዳዳችን ስህተት ከሆነ፣ ሦስቱ ሰዎች በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ እያሉ እዚያ ከሚገኝ ሌላ ሰው የተላለፈባቸው መሆኑን የሚጠቁም ይሆናል።)
ስለዛሬው ውጤት ጤና ሚኒስቴር የቪዲዮ መግለጫ እንደሚሰጥ ጠቁሟል። ይህንን የሦስቱን ሰዎች ጉዳይ፣ እንዲሁም ያልታወቀ ንክኪ ያላቸው 45 ሰዎች ከየትኛው የሕብረተሰብ ክፍል በተወሰደ ናሙና የተገኙ መሆናቸውን እንደሚያብራራ ይጠበቃል።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ 76,962 ምርመራዎች ተከናውነው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 494 የደረሰ ሲሆን፣ የሀገር ውስጥ ስርጭት ከውጭ ከገቡ ኬዞች በልጧል – 270 (55%) ሆኗል። ከዚህ ቁጥር ውስጥ 115 ሰዎች (ከአጠቃላዩ 23%) የነበራቸው ንክኪ ያልታወቀ ነው። የማኅበረሰብ ስርጭት በከፍተኛ መጠን አሻቅቧል። የዛሬ የምርመራ ውጤት ናሙናው የተወሰደበት የሕብረተሰብ ክፍል በሀገሪቱ (በተለይም በአዲስ አበባ) የማኅበረሰብ ስርጭትን ሁኔታን በተሻለ መልኩ የሚጠቁም ይሆናል።
የዛሬ 23 ሰዎችን ጨምሮ፣ በአጠቃላይ 151 ሰዎች ሙሉ ለሙሉ ከበሽታው ማገገማቸው ተነግሯል። በአሁኑ ሰዓት በጽኑ ህሙማን ክትትል ውስጥ የሚገኝ ምንም ሰው እንደሌለም ተገልጿል።
ከላይ የተያያዘው ምስል አጠቃላይ የኢትዮጵያን የኮቪድ-19 ሁኔታ እስከዛሬ ግንቦት 15 ቀን 2012 ድረስ በዝርዝር ያሳያል።
ቴሌግራም ቻናላችን፦ https://t.me/ankuardotcom
ለወቅታዊ ቁጥሮች፡- https://ankuar.com/covid19-et/