FEATUREDፖለቲካ/ፍልስፍና

«ሀገር ተፈጥሯዊ የእድገት ውጤት ነው»፣ ዮኃን ጐትፍሬ ሄርደር (1744-1803)

ጐትፍሬድ ሄርደር፣ አባቱ የመንደሩ መምህር በነበሩበትና ከከተማ ወጣ ባለ የምስራቅ ፕሩሺያ ግዛት ውስጥ ነው የተወለደው። ሕልሙ የሉተራን (የማርቲን ሉተር /1483-1546/) ተከታይ ፓስተር የመሆን ነበር። ወደ ኩንግስበርግ ዩኒቨርስቲ አቅንቶ አውሮፓዊ እሳቤዎችን በስፋት ባስተዋወቀው በኢማኑኤል ካንት የመማር ዕድል አገኘ። ለብዙ ዓመታት በፓስተርነትና በመምህርነት የቆየው ሄርደር በፈረንሳይ፣ ሆላንድ እና ጀርመን በስፋት ተዘዋውሯል። በ1773 ስትራስቡርግ ላይ ከወጣቱ የጀርመን ባለቅኔና ፀሐፌ-ተውኔት ጆኃን ሊፍጋንግ ቮን ጎቴ (1749-1832) ጋር ተዋወቀ፤ ከእርሱ ጋርም በመተባበር ስለ ጀርመን ባሕሪይ እና ሥነ-ጥበብ መፅሐፍ ለማዘጋጀት ችሏል። የሁለቱ ጓደኝነት ሄርደር በዌይማር የመሳፍንቱ ሰባኪ ይሆን ዘንድ ምክንያት ሆኖታል፤ በ1803 እስኪሞት ድረስም በዚያው በዌይማር ቆይቷል።

ሄርደር ፍልስፍናን፣ ታሪክን፣ ሥነ-መለኮትን እና ሥነ-ቋንቋን ጨምሮ በተለያዩ ርዕሶች አስተዋጽኦውን በማበርከት፣ የዘመኑ ከፍተኛ ተፅዕኖ አድራጊ ከሚባሉት ጠበብቶች አንዱ ነበር። መጀመሪያ አካባቢ ትኩረቱን የሳቡት በ17ኛው እና በ18ኛው ክፍለ ዘመናት የአውሮፓ ምሁራን ንቅናቄ፣ የኢንላይትመንት እሳቤች ነበሩ። ነገር ግን አንዳንድ የኢንላይትመንት እሳቤዎችን በመላ ህይወቱ ይዞ ቢቆይም፣ በ18ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ በአውሮፓ አስተሳሰብ ላይ አብዮት ያስነሳው የጥበባት እና የሥነ-ፅሁፍ ንቅናቄ፣ ማለትም ሮማንቲሲዝም ቀደም ብሎ ሰፍኖ በነበረው ኢንላይትመንት ንቅናቄ ላይ የሚሰነዝረውን የመልስ ምት በማጎልበቱ ረገድ በጉልህነት የአንበሳውን ድርሻ የያዘ ነበር።

ከፍተኛ ቦታ ከሚሰጣቸው የሄርደር ሥራዎች ውስጥ “Treatise on the Origin of Language (1772)” የተሰኘው እና ግዙፉ “Ideas for the Philosophy of the History of Mankind (1784-91)” ተጠቃሾች ናቸው። በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ዙሪያ አያሌ ጥራዞችን ማቅረብ የቻለ ቢሆንም፣ ሄርዶር በፖለቲካ ፅንሰ-ሐሳብ ላይ ዋነኛ ወይም እራሱን የቻለ ሥራ አልፃፈም ነበር። በተጨማሪም የጀርመን ሕዝባዊ ህይወት ባሕሪይ እና እርሱም የንጉሣዊ ቤተሰቦች ሰባኪ የመሆኑ ነገር በመፅሐፎቹ ላይ ፖለቲካን በተመለከተ ግልፅ እንዳይሆን አድርጎታል፤ እናም አንዳንድ አክራሪነት የሚንፀባረቅባቸው የሄርደር አመለካከቶች ሙሉ ለሙሉ የሚገለፁት በሚፅፋቸው ደብዳቤቹ ብቻ ነው። ይሁንና የፖለቲካ እሳቤዎቹ ግን እጅግ ወሳኝ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ነበሩ። ሆኖም እነዚህ እሳቤዎቹ ከአጠቃላይ የፍልስፍናው መሠረተ-ታሪክ በተለየ መንገድ ግንዛቤ ይደረግባቸው ዘንድ ያስፈልጋል።

እንደፈላስፋ የኢንላይትመንት የእውቀት ፍልስፍና ፅንሰ-ሐሳብን (epistemology) ፈትኗል፤ በተለይ ሰብዓዊ ግንዛቤን ወይም አረዳድን በተመለከተ። ባሕሪይ እና የጥበብ ሥራዎችን አስመልክቶ በሰበባዊ (causal) ሕጎች፣ በሁል-አቀፍ ጊዜ-የለሽ እውነት እና በሁል-አቀፍ መመዘኛዎች ላይ ማተኮርን አይቀበልም። የተፈጥሮ ሳይንሶችን በምንረዳባቸው ተመሳሳይ ዘዴዎች ሰብዓዊ ጉዳዮችን መረዳት እንደማይቻል ይሞግታል፤ ይልቁንም በጉዳዮቹ ላይ ተሳታፊ የሆኑትን ወገኖች አመለካከት በመገንዘብ፣ እንዲሁም ከልማዳዊ አኗኗሮችና የድርጊቶቻቸው አንድ አካል የሆነው ባሕሪያቸው ካነገባቸው ዓላማዎች አንፃር በመመልከት ዘዴ ብቻ ነው ሰብዓዊ ጉዳዮችን መረዳት የሚቻለው። በሌላ አገላለጽ፣ ከሰበባዊ (causal) ግንኙነቶች ውጫዊ አፈፃፀም ሳይሆን፣ ከውስጥ ያለውን በመገንዘብ ነው። የሰውን አስተሳሰብ እና ድርጊት ለመረዳት የሚያስፈልገው የሳይንስ ጥናት ሳይሆን፣ ይልቁንም የታሪክ፣ የሥነ-ጽሁፍ፣ የሥነ- ጥበብና በተለይም የቋንቋ ጥናት ነው፤ ይህም አጠቃላይ ታሪካዊ እና ባህላዊ አግባብ ማለት ነው። ይህንን ሁሉ ማድረግ ማለት ታሪካዊ ክስተቶችን፣ ግለስቦችን፣ ማህበረሰቦችን እና ባህሎችን አንድ ጭብጥ እና የራሳቸው ገፅታ ያለቸው (unique) እንደሆኑ መረዳት ማለት ነው።

ቋንቋ ለዚህ መረዳት ወይም ለዚህ ግንዛቤ ማዕከላዊ ነበር። ቋንቋ መላውን የአኗኗር ዘዬና የአንድን ሀገር የጋራ ወይም ድምር ተሞክሮ በመግለፁ ረገድ የአንድን ባሕል የተለየነት (uniqueness) ያረጋግጣል። ቋንቋ እና ሥነ-ጽሁፍ የፖለቲካ ማህበረሰቦችን (ሀገራትን) እና ግለሰቦችን ይቀርፃሉ። ሄርደር፣ እንዲሁ በቋንቋ አማካኝነት ከተገለፀ እሳቤ ባሻገር፣ እራሱ ቋንቋን ያካተተ በጣም ዘመናዊ የእሳቤ መንገድ አለው። ሁሉም የሰብዓዊ ድርጊቶች የራሱ የሰው ልጅ ማንነት መገለጫዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ አንድ ባሕል የአጠቃላዩን የህይወት ራዕይ ድምር ያቀፈና በለውጥ ላይ ያለ ጥቅልነት ስለመሆኑ የሚጠቁሙ የዚያ ባሕል መገለጫዋችም ጭምር ናቸው።

የሄርደር የፖለቲካ እሳቤ የአንድ ሀገር ባሕላዊነት ለፖለቲካዊ ማህበረሰብ እና ለፖለቲካዊ ማንነት እውነተኛው መሠረት መሆኑን በማስረገጥ ላይ ይሽከረከራል። ይህም፣ የፖለቲካ ማህበረሰብ፣ ከማህበራዊ ውል (social contract) ለመነጨ ሉዓላዊ ሥልጣን ተገዢ የሆኑትን ሁሉ በማካተት የተፈጠረ መሆኑን ከሚያስቀምጠው የኢንላይትመንት አመለካከት ጋር ይለያያል። በኢንላይትመንት እሳቤ መንግሥት ማዕከላዊ ነው፤ እንዲሁም ከአብዮቱ በኋላ በፈረንሳይ የብሔረተኝነት እሳቤዎች ሲጎለብቱም ተመሳሳይ ሆኖ ቀጥሏል። ሆኖም የሄርደር ግንዛቤ በዚህ መልኩ አልነበረም። ወጥነት ወይም ተመሳሳይነት እንደሚያስገድድና አካባቢያዊ ልዩነቶችን እንደሚያወድም አድርጎ ለተመለከተው የማዕከላዊ መንግሥት ሥርዓት ጥላቻ አለው። የቢሮክራሲ አደገኝነትን እና ሰዎች በሰፊው የመንግሥት ማሽን ውስጥ አሽከርካሪ ጥርሶች ብቻ እየሆኑ መምጣት የ20ኛው ክፍለ ዘመን ራስ-ምታት እንደሚሆን ይገምታል።

የባሕላዊ ሀገር ግንዛቤው የኢንላይትመንት የማህበራዊ ውል እና የሉዓላዊነት እሳቤዎችን ሊተካ እንደሚችል ሄርደር ያስባል። መንግሥት አርቴፊሻል ፅንሰ-ሀሳብ ሲሆን፣ ሀገር ግን የተፈጥሯዊ እድገት ውጤት ነበር። ይህ፣ ህብረተሰብን፣ በውስጡ ያሉት አካላት በሕብራዊ (harmonious) ዝምድና የተሳሰሩበት አንድነት (organic unity) አድርጎ የመመልከት ራዕይ ነው። ሄርደር ይህንን ሲል የህብረተሰብ አንድ ክፍል ከአጠቃላዩ ወይም ከመላው ያንሳል ማለቱ አይደለም፣ ወይም አንድ ግለሰብ ከአጠቃላዩ ማህበረሰብ ያነሰ መሆኑን አያመለክትም።

የሄርደር የጥሩ ህብረተሰብ ራዕይ ማዕከላዊ መንግሥት የሌለው ነው። አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ፣ ማህበራዊ ሥልጣን በሰፊው ሀገር ውስጥ በተለያዩ ግን ደግሞ አንዳቸው በአንዳቸው ላይ በሚመረኮዙ ማህበረሰቦች እና ክፍል-ክፍል ባላቸው ፍላጎቶች መካከል የሚሰራጭ ወይም የሚከፋፈል በሆነ ጊዜ፣ ተዋረዳዊነት እና አስገዳጅነት በሌላቸው ሁኔታዎች ውስጥ ውጤታማ ሆኖ እንደሚንቀሳቀስ ያምናል። ይህም ሕዝቡ ከሥርዓቱ ጋር አብሮ እንዲጓዝ ወይም እንዲጣጣም ትምህርት ከሚቀስምበት የሽግግር ጊዜ በኋላ ሊመሠረት የሚችል ነው።

ሄርደር ሐሳብን የመግለፅ ነፃነት ጠንካራ አቀንቃኝ ነበር፤ እናም ለዚህ ትምህርታዊ ሂደት ይህ ነፃነት አስፈላጊ እንደሆነ ያስባል። ፍፁም በሆነ የሁሉም እኩልነት ሳይሆን፣ ሁሉም ሰው እኩል ነው፣ እኩል መብቶች እና እድሎች ይገቡታል የሚለውን መርሆ (egalitarian) ይበልጥ በሚቀበል ህብረተሰብ ያምናል። በዘር ሐረግ ከሚወራረስ ዘውዳዊ ሥርዓት (hereditary monarchy) እና ከላይኛው መደብ ሥርዓት (aristocratic) የሚመነጭ ህብረተሰባዊ አመራር ሙሉ ለሙሉ ምክንያት-የለሽ እንደሆነ ይቆጥረዋል። በሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ እያንዳንዱ ሰው መሳተፍ ይችላል፣ ይገባዋልም። እርሱ በሚጠቁመው ሕዝባዊ ተቀባይነት በሚኖረው ሕግ-የለሽ (pluralist-anarchist) ህብረተሰብ ውስጥ ብጥብጥ እና የኃይል ጭቆና ምንም ዓይነት ቦታ ሊኖራቸው አይችልም፤ እንዲሁም መንግሥት ተከታታይነት ባለው ድርድር አማካኝነት በሚመጣ አጠቃላይ ስምምነት የሚገለጥ ይሆናል።

ሄርደር በልማዳዊ ወይም በባሕላዊ አሰራር ማዕከላዊነት ላይ አፅንኦት የሰጠ ቢሆንም፣ ለውጥን ከሚቃወሙ የባሕል አራማጆች /traditionalists/ በተቃራኒው በባሕል እና በለውጥ (በመሻሻል) መካከል ተቃርኖን አይመለከትም። የኢንላይትመንት የመሻሻል እሳቤዎች ጥልቀት የሌላቸው እንደሆኑ፣ ነገር ግን የመሻሻል እሳቤ በራሱ እንደዚህ እንዳልሆነ ያመናል። ህብረተሰብ፣ እንደባሕላዊ አሰራሮች በጊዜ ለውጥ ይዳብራል፤ የአኗኗር ዘዬዎች የራሳቸውን ውስጣዊ ዓላማ ይከተላሉ፤ ግለሰቦች የወረሷቸውን መርሆዎች እና ዘዴዎች ፈጠራ በተሞላበት መልኩ ጥቅም ላይ ያውላሉ። ለአጠቃላዩ የሰው ዘር ሰብዓዊ እምቅ ተሰጥዖን በተለያዩ መንገዶች ያለገደብ ከመግለጥ ወይም ከማውጣት ሌላ ጥቅል፣ ተመሣሣይ፣ ሁል-አቀፍ የሆነ ዕቅድ የለም። ይህም የዝግመተ-ለውጥ ባሕሪይ ያለው ታሪክን በአዲስ መንገድ መመልከትን ያካትታል፤ በዚህም ቀድሞ የነበረ የነገሮች ሁኔታን ዳግም እንዲፈጠር ማድረግ የማያጠያይቅ ነው። እንዲህ ያለውን እምቅ ተሰጥዖን የመግለጥ ተግባር የሚካሄደው በብሔራዊ ባሕሎች ውስጥም ሆነ በብሔራዊ ባሕሎች መካከል በተለያየ ፍጥነትና በተለያዩ አቅጣጫዎች ነው። የዓላማዎች ወይም የእሴቶች ተፈጥሯዊ ሕብራዊነት (harmony) የለም። በእያንዳንዱ ብሔራዊ ማህበረሰብ ሁሉም በሕብራዊ ዝምድና የተሳሰሩበትን አንድነት (organic unity) ለማስጠበቅ ማብቂያ የሌለው መግባባት እና ማስተካከያ አስፈላጊ ሲሆን፣ ድርድር ተደርጎበት ተፈፃሚ ሊሆንም ይችላል።

ሄርደር እንደ ብሔራዊ ባሕሎች አድርጎ የተመለከታቸው የታሪክ መሠረታዊ ክፍሎች እና የሰው ዘር መሠረታዊ ክፍፍሎች፣ እያንዳንዳቸው በየራሳቸው መንገድ የመጎልበት መብት አላቸው። ለየትኛውም ዓይነት ኢምፔሪያሊዝምም ሆነ ለዘረኝነት ከፍተኛ ጥላቻ ነበረው፤ ስለዚህም የማዕከላዊ እና የምስራቅ አውሮፓ መድብለ-ብሔር ስርወ-መንግስታትን እንደሚቃወመው ሁሉ፣ ነጭ ባልሆኑ ዜጎች ላይ የአውሮፓውያንን የበላይነት ይቃወም ነበር። ፈጣሪ ለየትኛውም ዘር፣ ለየትኛውም ሀገር አያደላም።

በጥቅሉ ሄርደር ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው የብሔረተኝነት (nationalism) ጠንሳሽ ነበር፤ ነገር ግን የእርሱ ብሔረተኝነት ከአብዮታዊዋ ፈረንሳይ ወይም በማስከተል በጀርመን ከተፈጠረው በጣም የተለየ ነው። በፈረንሳይ አብዮታዊ ብሔረተኝነት ያስከተለው ነገር ተገማችነት ነበረው። ሁሉም ፅንሰ-ሐሳባዊ ትኩረት በመንግሥት ላይ ያነጣጠረ ነበር፤ ይህም መንግሥትን እንደተጣመረ የሕዝባዊ ሉዓላዊነት አንድ ፈቃድ መገለጫ አድርጎ በመውሰድ። የጀርመን ብሔረተኝነትም መንግሥትን ከማምለክ አይለይም።

በርግጥም፣ ሄርደር እጅጉን ተፅዕኖ ያሳደረበት ሔግል፣ መንግሥትን ከሞራል አንፃር የግለሰብ የበላይ አድሮጎ በማሞገስ፣ የዘመኑን የፕሩሺያ መንግሥት የአንድ መንግሥት የመጨረሻ እድገት ጫፍ እንደሆነ ይመለከተው ነበር። የ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ የጀርመን ብሔረተኞች በጀርመን ባሕል የበላይነት ላይ የሙጥኝ በማለት ለሌሎች ሕዝቦች ጥላቻ ያለውን የጀርመን ብሔረተኝነት ጫፍ ድረስ ወሰዱት። እጅጉን ቅጥ ያጣ ሀገር ወዳድ እና ዘረኛ ከመሆን ባለፈ ለመንግሥት ሲሉ ግለሰብን ደስ እያላቸው ሊሰዉ ይችላሉ። ሆኖም የሄርደር ይበልጥ ቀጥተኛ ተፅዕኖ የጀርመን ሮማንቲክስ (German Romantics) በመባል በሚጠሩት የጠቢባን ቡድን ላይ ነበር። ፍሬድሪሽ ሼግል፣ ኖቫሊስ፣ እና (ብዙውን ጊዜ ከሄርደር ጋር ተያይዞ የሚነሳው) አደም ሙለር የመሳሰሉ የጀርመን ሮማንቲሲዝም ተከታዮች በባሕል እና በታሪክ፣ እንዲሁም በተለያዩ አካላት መካከል ልዩ የሆነ ሕብራዊነትን በመቅረፅ ረገድ በፖለቲካ አስፈላጊነት ላይ የሄርደርን ተፅዕኖ ተከትለዋል። ይሁንና ግን ከሄርደር ጋር ሲነፃፀሩ የእነርሱ እሳቤ የመካከለኛውን ዘመን ፊዩዳሊዝም አምሳያ ያደረገና ለዘልማዳዊ አሪስቶክራሲ ህብረተሰባዊ አመራርን የተመኘ የኋሊት ተመልካች ራዕይ ነበር።

እንደ የፖለቲካ ፈላስፋ፣ ሄርደር ጉድለቶች ነበሩበት። ግልፅ እና የተሟላ እሳቤዎችን አያስቀምጥም። ሆኖም ከዘመኑ እጅግ ተፅዕኖ አድራጊና በፈጠራ የተሞሉ ጠበብቶች አንዱ ነበር። እንደ ሮማንቲሲዝም፣ የጀርመን ሐሳባዊነት (idealism) እና ብሔረተኝነት በመሳሰሉ የዘመኑን ንቃተ-ሕሊና በቀረፁ ዋና ዋና የምሁራን ንቅናቄች ላይ በከፍተኛ መጠን ተፅዕኖ በማሳደር ታሪካችንን እና እራሳችንን የምንረዳበትን መንገድ ለውጧል። የእርሱ የባሕል ብሔረተኝነት እሳቤ፣ የሕዝቡ ሉዓላዊነት በብሔራዊ መንግሥቱ አማካኝነት ይገለጣል ከሚሉት የፈረንሳይ ብሔረተኛ እሳቤዎች ጋር ሲጣመር፣ ላለፉት ሁለት ክፍለ ዘመናት አብዛኛውን የዓለም ፖለቲካ የቀረፀውን የብሔረተኝነት ዓይነት ፈጥሯል።

ለበለጠ ንባብ

ቀዳሚ ምንጮች

Reflections on the Philosophy of the History of Mankind (Chicago, IL: University of Chicago Press, 1968).

Herder on Social and Political Culture, ed. F.M. Barnard (Cambridge: Cambridge University Press, 1969).

ተቀፅላ ምንጮች

Barnard, F.M.: Herder on Nationality, Humanity and History (Montreal; Ithaca, NY: McGill-Queen’s University Press, 2003).

Herder’s Social and Political Thought: From Enlightenment to Nationalism (Oxford: Oxford University Press, 1965).

Berlin, I.: Vico and Herder (London: Hogarth Press, 1976).

Norton, R.E.: Herder’s Aesthetics and the European Enlightenment (Ithaca, NY: Cornell University Press, 1991).

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.