ከአመጿ ጀርባ
ደራሲ፡ ኤደን ሀብታሙ
የመጽሐፍ ርዕስ፡ ከአመጿ ጀርባ
የገፅ ብዛት፡ 200
ዋጋ፡ 170 ብር
ከአመጿ ጀርባን ለዳሰሳ የመረጥኩት፤ በአብዛኛው በውስጣችን የያዝናቸውና ጮክ ብለን ለማውራት የማንደፍራቸውን ርዕሰ-ጉዳዮች በግልፅ ስለሚያነሳ፣ በግሌ እንደ ሀገር ለማደግ ራሳችንን መፈተሽና ምክንያታዊ የሆኑ ማህበራዊ ሂሶችን መለማመድ፣ መሻሻልና እንደ ግለሰብም ወደ ውስጥ መመልከት እንዳለብን ስለማምን ነው።
በእኔ እይታ፣ ዋና ገፀባህሪዋ ደስታዬ በዛብህ፣ መሆን እንጂ መምሰል የማይሆንላት፣ ሰው መሆን ብቻ የምትችል፣ ያመነችበትን ከማድረግ ወደኋላ የማትል፣ መፈረጅን [ጠብቆ] የማትፈራ፣ ከእውነት ጋር የቆመች፣ ሐቀኛና መልካም ሰው ነች።
- ሶስቱ የህይወቷ ማዕዘኖች፤ ሔኖክ፣ ሥራዋና ቤተሰቦቿ
- ሁለቱ ህይወቷ፤ ከአመጿ በፊትና ከአመጿ በኋላ
- ቦታ፤ የስነልቦና አማካሪዋ (ፋሲካ) ቤት፣ መኖሪያ ቤቷ፣ መፀዳጃ ቤቷና ፈጢራ
ውሸት ስለደከመኝ ለማመፅ ወሰንኩ የምትለው ደስታዬ፣ ሶስቱን የህይወት ማዕዘኖቿን ስትሰናበት፤ የሔኖክ ስንብት በሚያስገርም መልኩ ጥንካሬን ፈጥሮላታል። ቤተሰብ፤ የእናቷ ስንብት ትልቅ ሃላፊነትንና አደራን ጭኖባታል። በሌላ መልኩ ደግሞ አባቷንና ወንድሞቿን በሁለት ዓረፍተ-ነገር መሰናበቷ ሰላምና ነፃነትን ሰጥቷታል። ከመጀመሪያ ሥራዋ ስትሰናበት፤ መገላገል፣ ሸክምን ማራገፍና ነፃ መውጣት ተሰምቷታል።
መፅሐፉ በዋናነት ሶስት ትልልቅ ጉዳዮችን አንስቷል ብዬ አስባለሁ፤ ማህበራዊ ሂስ፣ ወደ ውስጥ መመለስንና የአዕምሮ ጤና ጉዳዮችን።
ማህበራዊ ሂስ፥
ማህበራዊ ህይወት፣ ሀይማኖትና ትዳር በሰፊው ይተቻሉ [ጠብቆ]። አንድን ግለሰብ እንደ አንድ ሰው መቀበልን አለመድንም፤ መፈረጅ እና ራሳችን በሰራንለት ቀለበት ውስጥ ሰተት ብሎ እንዲገባልን እንታገላን። ለዚህም ማሳያ የሚሆነን የእውነት ቀለማት አራት ላይ (ገፅ 61-67) ደስታዬ ከመርማሪው ጋር የምታደርገውን እልህ አስጨራሽ፣ በአላስፈላጊና የግል ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎችን የያዘው ቅጽ የመሙላት ሂደት ነው። በዚሁ ሂደት ውስጥ መርማሪው “ብሔር” ብሎ ሲጠይቃት “እንዴ…ዴ ብሔር ደግሞ ምን ይሰራል የሰረቁብኝኮ ቦርሳ ነው። ብሔር አይደለም!” ስትለው “ገብቶኛል። ቅጹ ላይ ስለሚጠይቅ መሞላቱ ግድ ነው።” ይላታል። ራሳችን የሰራነውን ፎርም መቀየር አቅቶን ሰዎችን በፎርሙ ልክ ለመክተት እንጋጋጣለን።
እዚሁ የእውነት ቀለማት አራት ጋር ሌላ የሚነሳው ሃሳብ የሀይማኖት ጉዳይ ነው። የስነ – ልቦና አማካሪዋ ፋሲካ፣ ደስታዬን ለምን ሀይማኖት እንዳይኖራት እንደመረጠች ስትጠይቃት (ገፅ 68)፣ “በእኔ ዓይን፤ በተለይም በእኛ ዓይነቱ “ሀይማኖተኛ” ሀገር የጠፋብን መንፈሳዊነት እንጂ ሀይማኖተኝነት አይመስለኝም። የሚያስተምረውን የሚኖር የሀይማኖት መሪ፤ “ሀይማኖቴ እምነቴ” ብሎ የሚከተለውን እምነት፣ አስተምህሮት የሚሰማና በጣም በጥቂቱ እንኳን የሚኖረው የሀይማኖት ተከታይ ነው ያጣነው። የምናስተምረው፣ የምንማረው እና የምንኖረው ግራና ቀኝ ነው። አብዛኛዎቹ ሀይማኖቶች፣ መስረቅን እና የሌላውን መመኘትን ይኮንናሉ። ከልሂቅ እስከ ደቂቅ የሌላን ስንመኝ፣ ስነቀላውጥና ስንሰርቅ እንውላለን። ወንድሞቻችንን እንደራሳችን እንድንወድ ያስተምራሉ። እኛ፣ እንኳን ሌላውን፣ እራሳችንንም እንደ እራሳችን አድርገን መውደድ አቅቶን ይኸው እንሰቃያለን።” ብላ ትመልስላታለች።
ደስታዬ ገፅ 50 ላይ ስለትዳሯ ስትገልፅ፦ « …ሳስበው … ባሌ እራሴን ባልሆን የሚመርጥ ይመስለኛል። እንደማንኛውም ሚስት፣ “ሚስት ሚስት” የምትሸት (ይቅርታ፤ “ሚስት ሚስት” መሽተት ማለት ማብራሪያ ካስፈለገው፤ ጠብ እርግፍ ብላ፣ ባሏን፣ ልጆቿን፣ ቤቷን የምትይዝ፣ ጥያቄ፣ ንግግር የማታበዛ፣ ብዙ የማትጠይቅ፣ ቁጥብ፣ ስትቀመጥና ስትነሳ፣ ስትበላና ስትጠጣ፣ ክብብ ድርብብ ያለች…) ብሆን የሚመርጥ ይመስለኛል። እራሴን በሆንኩ ቁጥር ፍርሃት ውስጥ ይገባል። መቼ፣ ምን ዐይነት ነገር ውስጥ እንደምገባ አይታወቅማ! የእኔ ነገር፣ አንድ ቀን ተነስቼ ‘አብረን እየኖርን፣ እራሴን መሆን ስላልቻልኩ ትንሽ ጊዜ ልውሰድ፤ … አደራ ልጆቹን እያየሃቸው። ለአንድ … ሁለት ዓመት ብቆይ ነው’ ብዬው ብሄድስ? ደግሞም ልለው እችላለሁ። እሱ በፈራ ቁጥር ነጻነቴን ያፍነዋል። እኔ ደግሞ በታፈንኩ ቁጥር ወደ መፈንዳቱ እሄዳለሁ… »
ወደ ውስጥ መመልከት፥
ለፋሲካ በተገዛ በግ ውስጥ የእናቷ መገለጥ፣ መፀዳጃ ቤት ውስጥ ሆና ድሯን ስታደራ ያየቻት ሸረሪት፣ እና ፈጢራ ላይ የተገለጠላት ብርሃኑ የደስታዬ ራስን የመሆንና ወደ ውስጥ የመመለስ ጉዞዋ ላይ ትልቅ ሚና አላቸው ብዬ አስባለሁ። ደስታዬ እናቷ ስትሞት ሀዘኗን አላየነውም ነበር፤ ከስንት ጊዜ በኋላ ግን የእናቷ በበግ ውስጥ መገለጥና በጉ ሲታረድ የተሰማት ሀዘን፤ እናቷ የዛን ቀን እንደሞተች ያህል እንዲሰማትና ውስጧ የነበረውን ጥልቅ ሀዘን እንድታወጣው አድርጓታል።
ሌላው ብዙ ጥያቄዎቿን የመለሰላትና ራሷን እንድትፈትሽ፣ እንድታዳምጥ፣ የጥያቄዎች ሁሉ መልስ እርሷው ዘንድ እንደሆነ ያመላከታት ከብርሃኑ ጋር የነበራት ምናባዊ ውይይት ነው፤ ይህንን ምናበዊ ውይይት ስጋ አልብሶ ያሳያት ሊቁ ነው።
ገፅ 194 ላይ ደስታዬ ስለተጓዘችበት መንገድ ስትገልፅ ከአመጼ ጀርባ ያለው ቁምነገር ራስን የመሆን እና ወደ ውስጥ የመመለስ ከባድ ሂደት መሆኑ ዘግይቶም ቢሆን ገባኝ ትለናለች።
የአዕምሮ ጤና፥
የደስታዬ አባት ጦር ሜዳ ባጣቸው ጓደኞቹ ምክንያት ሌላ ሰው ሆኖ መምጣቱ፣ የሔኖክ ራሱን ማጥፋት፣ ገፅ 119 ላይ ደስታዬ MDD (major depression disorder) ተጠቂ መሆኗን በራሷ ቋንቋ መግለጿ ስለ አዕምሮ ጤና ጉዳይ ልብ እንድንል የተፈለገም ይመስላል።
* * *
በአጠቃላይ ማህበራዊ ሕይወታችን ማስመሰል የበዛበት፣ ለታይታ የሚደረጉ ነገሮች የበዙበት እንደሆነ ደስታዬ ትገልፃለች። መፅሐፉ ራሳችንን ሳናውቅ፣ አቅማችንን ሳናውቅ፣ የምንፈልገውን ሳናውቅ፣ መኖር ሳንጀምር ራሳችን በፈጠርነው አስተሳሰብ ታስረን እንሞታለን፤ ራሳችን ለፈጠርነው ሥርዓት ተገልጋይ ሳይሆን አገልጋይ ሆነን እናልፋለን የሚል ሃሳብን ያነሳል።
ይህን መፅሐፍ ብታነቡት ታተርፋላችሁ። በመጨረሻም ከመፅሐፉ የወደድኩትን ገፅ 50 ላይ የሚገኝ አንድ አንቀፅ ጋብዤ ልሰናበታችሁ።
« …እስካሁን እንደገባኝ ከሆነ ሰው መሆን ብቻ ነው የምችለው። ከምወስደው ኃላፊነት ጋር መጣበቅ አልችልም። አንዳች የሚያጣብቅ “ሙጫዊ” ንጥረ ነገር እጥረት በውስጤ አለ። የሚሰጡን ወይንም የምንወስዳቸው ኃላፊነቶች ከመጋነናቸው የተነሳ የእኛ ማንነት ይመስሉናል። እኔ ደግሞ ይሰለቹኛል፤ ያፍኑኛል። እኔ ሚስት ብቻ፣ እናት ብቻ፣ ሥራዬ ብቻ፣ ጾታዬ ብቻ አይደለሁም። እነዚህ በጣም ውስን መጫወት ያለብኝ ኃላፊነቶች ናቸው። “እንዴ … ሴት፣ ሚስት፣ እናት፣ የተማርሽ … ምናምን አደለሽም እንዴ?” ብለው ሊያስሩኝ ሲነሱ ያፍነኛል። እውነት! የሰጡኝ ሚጢጢ ስም ስለሚጠብ ያፍነኛል። ‘ዞር በሉልኝ’ ብዬ ወጣ እልና፣ ትንፋሽ ወስጄ ወደ እራሴ ስመለስ፣ የተሻለች ሴት፣ ሚስት፣ እናት፣ ሠራተኛ … ሆኜ እራሴን አገኘዋለሁ። እነዚህን ኃላፊነቶች ለመወጣት ግን መጀመሪያ ወደ ቀልቤ መመለስ አለብኝ። አስቢው እስቲ እራሴን ሳልሆን እንዴት ሴት፣ ሚስት፣ እናት፣ አስተማሪ፣ ሹፌር፣ መሀንዲስ፣ ሊስትሮ፣ ሐኪም … መሆን እችለለሁ?»
በማህደር አካሉ