FEATUREDፖለቲካ/ፍልስፍና

“ነፃነትን የሚገድብ መንግሥት የሕዝቡን ሞራላዊነት ያሰናክላል”፣ ኢማኑኤል ካንት (1724-1804)

ህይወቱ መሳጭ ክስተቶች የተሞሉበት ዓይነት አይደለም፤ በፕሩሺያ ግዛተ-መንግሥት ውስጥ (አሁን ሩሲያ ውስጥ ካሊኒንግራድ በመባል በምትታወቀው) ኩንግስበርግ በምትባል ሩቅ ከተማ ተወልዶ፣ ንቅንቅ ሳይል መሞቻውም እዚያው ሆኗል። በእድሜ ዘመኑ ትዳርን ሞክሮት አያውቅም። በቀን ተቀን ህይወቱ ተደጋጋሚነት የተነሳ፣ በከተማው ነዋሪዎች ተለይቶ ይታወቃል። መልካም ዝና ካለው ቤተሰብ የወጣ ባይሆንም፣ በከተማው ዩኒቨርስቲ ውስጥ መምህር ለመሆን የበቃና ከማንም በላይ ቦታ የሚሰጠው ፕሮፌሰር ነበር። የተገለለ ህይወት ይኑረው እንጂ፣ ኢማኑኤል ካንት በመላው አውሮፓ ይካሄድ ከነበረው ጉልብትና ጋር ጎን ለጎን ተጉዟል። ከዘመኑ ታላላቅ ፈላስፎች መካከል አንዱ እንደሆነም እውቅና ተሰጥቶት ቆይቷል።

“Critique of Pure Reason (1781)”፣ “Groundwork of the Metaphysics of Morals (1785)”፣ “Critique of Practical Reason (1788)”፣ “Critique of Judgment (1790)”፣ እና በሌሎች ዋና ዋና ሥራዎቹ ለሜታፊዚክስ (metaphysics – የነገሮችን ቀዳሚ መርሆዎች የሚያውጠነጥን የፍስልፍና ዘርፍ ሲሆን በማወቅ እና በመሆን ፅንሰ-ሐሳቦች ላይ ያተኩራል)፣ ለኤፒስቲሞሎጂ (epistemology – የእውቀት ፅንሰ-ሐሳብን የሚያጠና የፍልስፍና ዘርፍ)፣ እንዲሁም እርሱ ይበልጥ ለሚታወቅበት ኤቲክስ (ethics – በሰብዓዊ ምግባር ላይ የሚያተኩር የፍልስፍና ዘርፍ) ከፍተኛ አስተዋጽኦዎችን አበርክቷል። ፖለቲካን ጨምሮ፣ በሌሎች ርዕሰ-ጉዳዮች ላይም ያበረከተው ቁምነገር በጉልህነት የሚጠቀስ ነው፤ ነገር ግን በዋናነት እራሱን የቻለ የፖለቲካ ሥራ አልፃፈም። የእርሱ የፖለቲካ እሳቤዎች፣ ተያያዥነት ባላቸው ርዕሰ-ጉዳዮች ስር በተለያዩ ሥራዎችና በተለያዩ ጽሁፎች ውስጥ የሚገኙ ናቸው። በመሠረታዊ መልኩ ለኤቲክስ እና ለሜታፊዚክስ እሳቤዎቹ ማኅበራዊ ነፀብራቆችን የሚፈጥሩ ናቸው።

ካንት እንደወጣት የዩኒቨርሲቲ መምህርነቱ የኒውተንያን ሳይንስ (ሰር አይዛክ ኒውተንን መሠረት ያደረገ የሳይንስ አስተምህሮ) ከፍተኛ አድናቂ ነበር፤ እንዲሁም የሳይንስን ዋነኛ መሠረቶች የሚያጣጥለውንና በእርግጠኝነቱ (certainty) ላይ ጥያቄ የሚያነሳውን የዴቪድ ሂዩም ጥርጣሬያዊ ፍልስፍና በሚያነብ ጊዜ አስገርሞታል። ዴቪድ ሂዩም፣ የምክንያት እና የውጤት ሂደትን መታዘብ አይቻልም፣ እናም ሁሉም የሳይንስ ሰበባዊ ሕጎች (Causal laws) በተግባር የሚጨበጥ (የሚረጋገጥ) ጠንካራ መሠረት የላቸውም በማለት መከራከሪያውን ያስቀምጣል። የዓለምን ሳይንሳዊ ምልከታ ለመከላከል ሲልም ካንት አብዮታዊ የሆነ የእውነታ (reality) እሳቤን አመጣ፤ መከራከሪያውንም ዓለም አሁን ባለችበት መንገድ የሆነችው አዕምሯችን በዚያ መንገድ ስለቀረፃት ነው በማለት አስቀመጠ። እየኖርን ያለንባት ዓለም በምክንያት እና ውጤት፣ በጊዜ እና በቦታ፣ እንዲሁም በመሳሰሉት ጠባዮች ትገለፃለች፤ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች እኛ ልንረዳው የምንችለውን የዓለም ምስል ለመፍጠር በሕሊናችን ውስጥ ተገንብተዋልና። ከሰው ልጆች ተሞክሮ ወይም ምልከታ ውጪ (ካንት “the thing in itself” ወይም “የአንድ ነገር በራሱ የሚገለፅ ምንነት” በማለት ይጠራዋል) የሆነው ዓለም በትክክል ምን ዓይነት እንደሆነ ማወቅ አይቻለንም። ይሁንና ግን ካንት ይህንን የማይታወቅ ዓለም “World of Noumena” ወይም “የኑሜና ዓለም” በማለት ከሚጠራው ጋር ያጣቅሰዋል፤ ይህም በስሜት ህዋሳት የማይቃኝ የመንፈሳዊነት እና የነፃነት ዓለም ነው።

በሌላ በኩል በስሜት ህዋሳት የሚቃኘው የቀን ተቀኑ ዓለም፣ ማለትም “World of Phenomena” ወይም “የፌኖሜና ዓለም”፣ ሙሉ ለሙሉ የሚተዳደረው በሰበባዊ ሕጎች (causal laws) ሲሆን፣ ይህም የእንስሳት እና የሰብዓዊ ፍጡራን ባሕሪይን ይጨምራል። እንደ ካንት ሐሳብ፣ የራሳችንን ፍላጎት ለማሟላት በምንጥርበት ጊዜ በፍላጎቶቻችን እና እነርሱን ለማሟላት በምንተገብረው መካከል ያለው ዝምድና ሰበባዊ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ሕሊናን ወይም የማስተዋል ብቃትን (reason) የመጠቀማችን እውነታ በመሠረታዊ መልኩ ከሌሎች እንስሳት የተለየን የሚያደርገን አይደለም። እንዲሁ ብቻ እንስሳት የሌላቸውን ተጨማሪ መሣሪያ ይሰጠናል። ይሁንና ግን ሰብዓዊ ፍጡራን በመደበኛ ሁኔታ ታስረው ካሉበት የምክንያት እና የውጤት ፌኖሜና ዓለም ውስጥ ብቻቸውን ወጥተው መራመድ እስከቻሉ ድረስ የተለዩ እና ልዩ ናቸው።

ሰብዓዊ ፍጡራን እንቅስቃሴያቸውን ሞራልን የተከተለ በማድረግ ከፌኖሜና ዓለም መውጣትና የኑሜና ዓለምን መቀላቀል ይችላሉ፡ ይህም፣ ከራስ ፍላጎት በተቃራኒ፣ በሞራል ግዴታዎች መሠረት ከተንቀሳቀሱ ማለት ነው። በዚህ መንገድ ነው የሰው ልጅ ሙሉ ለሙሉ ነፃ እና ሙሉ ለሙሉ ሰብዓዊ ሊሆን የሚችለው። ይህ በካንት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ካሳደረው ከሩሶ አመለካከት ጋር የሚመሳሰል፣ ግን በመጠኑ ለወጥ ያለ ነው። ሰብዓዊ ፍጡራንን በተለየ መልኩ ሰብዓዊ የሚያደርጋቸው ሞራላዊ ምርጫ ለማድረግ ያላቸው አቅም እንደሆነ ሩሳ አስቀምጧል። በድጋሚም ልክ እንደሩሶ ሁሉ፣ ካንት ይህንን ሞራላዊ ምርጫ የማድረግ አቅም ለፖለቲካዊ ነፃነት ማረጋገጫነት ይወስደዋል፤ ሆኖም ለእንዲህ ዓይነቱ ነፃነት የካንት ግንዛቤ እጅግ የተለየና ከፖለቲካ አንፃርም ከሩሶ ይልቅ ይበልጥ ተቀባይነት ያለው ነው።

ይሁንና ግን፣ ግለሰቦች ሊተገብሩት የሚገባው ሞራላዊ ምርጫ ምንድነው የሚለው ጋር ስንመጣ፣ ካንት በግለሰባዊነት ላይ ጠንካራ አቋም አለው። “Foundations of the Metaphysics of Morals” በተሰኘው ሥራው ላይ እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን የሞራል ሕግጋቶች የመወሰን ምርጫ የእርሱ እንደሆነ መከራከሪያውን ያስቀምጣል። ግለሰቡ የራሱን የሞራል ሕግጋቶች የሚወስነው ካንት “categorical imperative” በማለት በሚጠራው መርህ ነው። “categorical imperative” ወሰብሰብ ያለ መርህ ሲሆን፣ አንድን ድርጊት የምንተገብርበት መንገድ ሌሎች በተመሳሳይ ሁኔታዎች ይተገብሩት ዘንድ በምንፈልገው መንገድ እንዲሆን የሚጠይቅ ነው።

ለካንት በማንኛውም ሁኔታዎች ትክክል የሆነውን ነገር የማድረግ ሞራላዊ ግዴታ ያልተበረዘ እና ያልተገደበ (categorical) ወይም ፍፁም (absolute) ነው። በሌላ በኩል የምንፈልገው ቢሆን እንኳን አንድን ግብ ለመምታት ስንል የምንተገብረው ድርጊት ተመርክዞአዊ ውሳኔ (hypothetical imperative) ብቻ ነው፤ ይህም ለካንት በጭራሽ ሞራልን አይወክልም። ያልተበረዘ ወይም ያልተገደበ የሞራል ኃላፊነት (categorical imperative) ከተግባር አኳያ ሲታይ ሰዎችን መመልከት ያለብን እነሱ እኛን እንዲመለከቱን በምንፈልገው መልኩ ነው ማለት ነው። ይህም ሁልጊዜ ለሰዎች የምናሳው ፀባይ እንደመጨረሻ ግብ እንጂ አንድን ነገር ለማግኘት አይደለም ከሚለው ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ካንት ያምናል። በተጨማሪም ሰብዓዊ ፍጡራን የራሳቸውን የሞራል ሕግጋቶች ለራሳቸው የመስጠት አቅም ስላላቸው፣ ሁሉም ሰብዓዊ ፍጡር ተቆጥሮ በማያልቅ ወይም ገደብ በሌለው ሞራል የተሞላ ነው፤ በተመሣሣይም ሁሉም ሰብዓዊ ፍጡር የነፃነት እና የፈቀደውን የማድረግ (እራሱን የማስተዳደር) መብት አለው።

እዚህ ላይ ፖለቲካዊው ጥያቄ፣ እንዲህ ዓይነት ሰብዓዊ ፍጡራን ላሉበት ሕብረተሰብ የሚስማማው የመንግሥት ዓይነት የትኛው ነው? የሚለው ነው። የካንት ምላሽም (በቅድሚያ “Critique of Pure Reason” ላይ በገፅ 312 ጠቅሶት በሌሎች ጽሁፎቹ እንዳዳበረው) ሪፐብሊካን መንግሥት ሊሆን ይገባዋል የሚል ነው። ካንት “ሪፐብሊካን” ሲል ከሁሉም በላይ ሕገመንግሥታዊ መንግሥት ማለቱ ሲሆን፣ ነገር ግን ይህ መንግሥት እያንዳንዱ ሰው ከሌሎች ሰዎች ነፃነት ጋር የተጣጣመ ከፍተኛ ነፃነትን በተጎናፀፉበት መርህ ላይ መሠረት ያደረገ መንግሥት ነው። እንዲህ ዓይነቱ መንግሥት ሕሊና ላላቸው ፍጡራን ሁሉ እንደሚያስፈልግና ለዚህ ዓይነቱ መንግሥት መምጣት እንድንታገል የሞራል ግዴታ እንዳለብን ካንት ያስባል።

የኢማኑኤል ካንት የመልካም መንግሥት እሳቤ በእሱ ዘመን ከነበረው ለዘብተኛ የሊበራል አስተሳሰብ ጋር አብሮ የሚሄድ ነው (ምንም እንኳን በግዞት ጠያቂ /Authoritarian/ ወይም በጥብቅ ሥርዓት ውስጥ እንደመኖሩ፣ የእርሱ እሳቤዎች ከነበረበት ሁኔታ አንፃር በከፍተኛ ደረጃ አክራሪ ቢሆኑም)። በርካታ የዜጎች ነፃነቶች፣ በሕገመንግሥት የሚመራ ንጉሣዊ ሥርዓት፣ እንዲሁም ሁል-አቀፍ ባይሆንም እንኳን በሰፊ ሕዝብ አማካኝነት የተመረጠ የሕግ አውጪ አካል – በካንት እሳቤዎች ውስጥ የተካተቱ ነጥቦች ናቸው። (ሁል-አቀፍ ያልሆነው ምርጫ – ሴቶች፣ በአነስተኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ እና አሽከሮች ለቀን ተቀን ህይወታቸው በሌሎች ላይ ጥገኛ በመሆናቸው ገለልተኛ ሆነው ይመርጣሉ ተብሎ ስለማይጠበቅ የተገለሉበት ወይም ከመሳተፍ የተገደቡበት ነው።)

ካንት ለዚህ ዓይነቱ መንግሥት ስኬታማነት ከፍተኛ እምነት አለው። ጦርነትን፣ ወንጀልን እና የሰው ልጅን አሰቃቂ ሁኔታዎች በውጤታማነት እንደሚቀንስ ያምናል። ለዚህም ሰዎች ነፃ እስካልሆኑ ድረስ ሙሉ የሆነ የሞራል ግባቸውን ማሳካት እንደማይችሉ በማመኑ ምክንያት ነው። ለሕዝብ ጥቅም በሚል ዓላማ ነፃነትን የሚገድብ የተሻለ የሚባለው የመንግሥት ፖሊሲ እንኳን የሕዝቦች ሞራላዊ እድገት እንዲሰናከል ያደርጋል፤ ይህም በዓለም የሚታየውን አብዛኛውን ጥፋት ያስረዳል። ሪፐብሊካን መንግሥት በሚመሠረትበት በማንኛውም ጊዜ ሕዝቦች ከመቼውም በበለጠ የበሰሉ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው እና ምክንያታዊ ሊሆኑ ግድ ነው።

የሪፐብሊካን መንግሥት ቢንሰራፋ የመልካም ነገሮች ሁሉ ጠላት እንደሆነ አድርጎ የሚወስደውን፣ ጦርነትን ሊያስወግድ እንደሚችል ካንት እምነት አለው። ይሁንና ግን ሪፐብሊካን የሆነ የዓለም መንግሥት እውን ይሆናል ብሎ አያምንም። ሆኖም ሁሉም ዓለማቀፋዊ ግጭቶች ሊፈቱ በሚችሉበት መልኩ ዘለቄታዊ ሰላምን ቀስ በቀስ ሊያረጋግጥ የሚችለው የሪፐብሊካን መንግሥታት ማኅበር ወይም “League of Republican Governments” ነው። ይህንን ካንት ከፍተኛው የፖለቲካ ግብ አድርጎ ይወስደዋል። ጊዜ ሊወስድ ይችላል፣ ነገር ግን የሰው ልጆች የመጨረሻ እጣፈንታ ይህ እንደሆነ ጥርጥር የለውም።

የሰው ልጆች ምቹ ወደሆነ መፃዒ-ዕድል እያቀኑ ስለመሆናቸው የካንት ልበ-ሙሉነት የምክንያታዊነት እና የትምህርት የቀስ-በቀስ መሠራጨትን በተመለከተ በአጠቃላዩ የአብርሆት (Enlightenment) እምነት ላይ ብቻ መሠረት ከማድረግ የዘለለ አልነበረም። የሰው ልጆች “መሻሻል” በተፈጥሮ ዋስትና የተሰጠው ስለመሆኑም ጭምር ያምናል። ካንት “Idea for a Universal History with Cosmopolitan Purpose” በተሰኘው ሥራው ላይ የሰው ልጅ ሁሉም ተፈጥሯዊ ብቃቶች ሙሉ ለሙሉ ይዳብሩ ዘንድ በአንድ ሀገር ውስጥም ሆነ በሀገራት መካከል ሰዎችን እንከን-የለሽ ወደሆነ ሕገመንግሥት የሚመራ የተፈጥሮ “ድብቅ እቅድ” እንዳለ ጽፏል። ይህ “እቅድ” ተፈፃሚ ይሆናል፤ ምክንያቱም ተፈጥሮ የሰው ልጆች ውስጥ ካንት “unsocial sociability” በማለት የሚጠራውን “በሕብረተሰብ ያለመታቀፍ ትንቅንቅ የሰፈነበት ማኅበራዊነት” ባሕሪይን በሰው ልጆች ላይ ተክላለችና።

የሰው ልጆች በተፈጥሯቸው ማኅበራዊ ፍጡራን ሲሆኑ፣ በዚያው ልክ ደግሞ ባሕሪያቸው ወደ ፀረ-ሕብረተሰብነት አጠንክሮ ማድላትን ያሳያል፦ ጉጉ፣ ለራሳቸው እንጂ ለሌሎች የማይገዳቸው፣ እንዲሁም ግልፍተኛ /ኃይለኛ/ ናቸው። እነዚህ ባሕሪይዎች ወደ ግጭት፣ ወደ ወንጀል፣ ወደ ጨቋኝ ሥርዓት እና ወደ ጦርነት የሚመሩ ቢሆኑም፣ መጨረሻ ላይ ግን ወደ ተቃራኒዎቻቸውም የሚመሩ ናቸው። የወንጀል አሰቃቂነትና ሕዝባዊ ብጥብጥ፣ ሰዎች ሥርዓት ያበጁ ሕብረተሰቦችን ከሕጎች እና ከተቋማት ጋር እንዲፈጥሩና ቀስ-በቀስም በነፃነት መርሆዎች መሠረት በምክንያታዊ የሕግ ሥርዓት ውስጥ የመኖርን አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ ያስገድዷቸዋልና። እንደ ካንት እምነት፣ የጦርነት አስከፊነት ለሰው ልጆች ተመሣሣይ ትምህርትን ይሰጣል፣ እናም በኋላ ላይ የሚከተለው ውጤትም ዘለቄታዊ ሰላም ይሆናል።

የካንት ፖለቲካዊ ጽሁፎች የአብርሆት (Enlightenment) ዘመን ተስፈኛነትን የሚያስታውሱ ቢሆኑም፣ “መሻሻል” የሰው ልጅን ጥፋት የመስራት አቅም እስከምን ድረስ ያስወግዳል የሚለውን በተመለከተ በተወሰነ መልኩ ግልፅ ያለመሆን ነገር አለ። ምናልባትም ዛሬ የፀለምተኝነት ምልከታን ይበልጥ አሳማኝ ሆኖ እናገኘዋለን። በመሠረታዊነት የሚጠቀሱት፣ ካንት እጅግ የሚደነቅበትና እስከዛሬም ድረስ የሚነሳው የሞራል ፍልስፍናውን አስመልክቶ በተከተለው አካሄድ ላይ የሚያንዣብቡ ጥያቄዎች ናቸው። ሀያሲዎቹ የተለያዩ የሆኑ ያልተበረዘ ወይም ያልተገደበ የሞራል ግዴታዎች (categorical imperative) ካንት እንደጠቆመው ተመሣሣይ ነገርን የሚያመለክቱ ስለመሆናቸው ጥያቄ ያነሳሉ። ካንት እንደሚያስበው፣ ሁሉም ሰው ሙሉ ለሙሉ ምክንያታዊ (rational) ከሆነ ሁሉም ተመሣሣይ የሞራል ድምዳሜች ላይ ይደርሳል የተባለውም እንዲሁ እጅግ አጠያያቂ ነው። ይሁንና ግን ከሁሉም በላይ ገላጭ የሆነው ትችት – ሄግል እንዳብራራው – ካንት የሰጠን ነገር ሁሉ ይዘት-አልባ ቀመር ነው የሚለው ነው። አንዳንዶች ደግሞ ችግሮችን በብልሃት የመፍታት አቅም ኖሮት ማንኛውንም ነገር (ማለት በሚቻል መልኩ) ለማረጋገጥ ጥቅም ላይ ማዋል የሚቻል ቀመር ስለመሆኑ መከራከሪያቸውን ያሰቀምጣሉ። እነዚህ ትችቶች ይኑሩ እንጂ፣ የኢማኑኤል ካንት የፖለቲካ እሳቤዎች እጅግ ጠንካራ፣ አሳማኝ እና ተፅዕኖ አድራጊ ከሆኑት የሊበራል እሴቶች መከራከሪያዎች መካከል መሆናቸው አልቀረም።

ለበለጠ ንባብ

ቀዳሚ ምንጮች፡-

Critique of Pure Reason, ed. N. Kemp Smith (Basingstoke: Macmillan, 1933).

Foundations of the Metaphysics of Morals and What is Enlightenment?, ed. L.W.Beck (Indianapolis, IN: Bobbs Merrill, 1959).

Kant’s Political Writings, ed. H. Reiss (Cambridge: Cambridge University Press, 1971).

ተቀፅላ ምንጮች፡-

Caygill, H.: A Kant Dictionary (Oxford: Blackwell, 1995).

Gayer, P.: The Cambridge Companion to Kant (Cambridge: Cambridge University Press, 1992).

Saner, H.: Kant’s Political Thought (Chicago, IL: Chicago University Press, 1973).

Williams, H.: Kant’s Political Philosophy (Oxford: Blackwell, 1983).

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.