FEATUREDፖለቲካ/ፍልስፍና

“በአንድ ሀገር መኖርህ ብቻውን መንግሥትን ተቀብለሃል አያሰኝም” – ዴቪድ ሂዩም (1711-76)

ዴቪድ ሂዩም ቤርዊክ፣ ስኮትላንድ ነው የተወለደው፡፡ በኤዲንበርግ ዩኒቨርስቲ እየተማረ ሳለ ሕግ አጥንቷል፤ በኋላ ፍላገጎቶ በሥነ-ፅሁፍ አና በፍልስፍና ላይ ቢያተኩርም፡፡ ገና በወጣትነቱ ቤተሰቦቹ የሚከተሉትን የፕረስቢተሪያን እምነት ወደጎን የተወ ሲሆን፣ የስኮትላንድ ሃይማኖታዊ መሠረቶችን የሚቃወም መሆኑም በኤዲንበርግ በ1745 እና በግላስጎው በ1752 የፍልስፍና ሊቃውንትነት ወንበሮችን እንዳያገኝ ገድቦታል።

የመጀመሪያውና ጉልህ ቦታ የሚሰጠው “A Treatise of Human Nature” የተሰኘው የፍልስፍና ሥራው በፈረንሳይኛ ቋንቋ የተፃፈ ሲሆን፣ የታተመውም በ1739-40 ገደማ ነው፡፡ ይሁንና ግን ይህ ሥራው ስኬታማ አልነበረም፡፡ ስለዚህም የተሻለና ይበልጥ ለአንባቢ በሚደርስ መልኩ ዋና ዋናዎቹን አስተምህሮዎች በሁለት ሥራዎች አድርጐ አሳትሟል፡- ሰብዓዊ ግንዛቤን በተመለከተ “An Enquiry Concerning Human Understanding” በ1748፣ እንዲሁም የሞራል መርሆዎችን በተመለከተ «An Enquiry Concerning the Principles of Morals” በ1751 ታትመዋል፡፡ ዴቪድ ሂዩም በውስን ርዕሰ-ጉዳይ ላይ የሚያውጠነጥኑ ሥራዎችንም በማፍለቅ የሚታወቅ ሰፊ ምልከታ ያለው ፀሐፊ ነው፡- የሞራል እና የፖለቲካ ትስስርን አስመልክቶ “Essays Moral and Political” በ1742፤ የፖለቲካ ድርድሮችንና ውይይቶችን አስመልክቶ “Political Discourses” በ1752፡፡

ሂዩም የኢንግላንድን ታሪክ («History of England» በሚል ርዕስ) በስምንት ጥራዞች ከ1754 እስከ 1761 ባሉት ጊዜያት ያሳተመው በኤዲንበርግ ዩኒቨርስቲ ቤተ-መፅሐፍት የኃላፊነት ቦታ በያዘ ጊዜ ነበር፡፡ በጣም ተጨዋችና በቀላሉ ጓዳኛ የማፍራት ተፈጥሮ ያለው ዴቪድ ሂዩም፣ የመጨረሻ ሥራው የሆነው “Dialogues Concerning Natural Religion” ለህትመት የበቃው እርሱ ከሞተ በኋላ በ1779 ነበር፡፡ የሂዩም የፖለቲካ እና የሞራል እሳቤው መነሻ ነጥብ፣ የሰው ልጆች በቀዳሚነት የስሜት እንጂ የሕሊና ወይም የማስተዋል (reason) ፍጡራን አይደሉም የሚለው እምነቱ ነው፡፡ ተደጋግሞ በሚጠቀስ አባባሉ ስለሕሊና “Treatise of Human Nature” ላይ ይህን ይነግረናል፡-

«ሕሊና የስሜቶች ባሪያ ነው፣ ይህን ብቻም መሆን አለበት፤ እናም እነሱን ከማገልገልና ለነሱ ከመታዘዝ በቀር ሌላ ድርሻ እንዳለው አድርጐ ማስመሰልም አይቻለውም፡፡»

ያልተለመደ ዓይነት አገላለፅ ነው (ሕሊና የስሜቶች ባሪያ ከሆነ መሆን አለበት የማለውን መጨመር ትርጉም አይኖረውም)፣ ነገር ግን ሂዩም ለማስቀመጥ የፈለገው የሞራል አመለካከቶቻችን (እምነቶቻችን) መሠረታቸውን የሚጥሉትና በተግባርም የሚገለፁት በሕሊና ወይም በማስተዋል ብቃት ነው የሚለውን ምልከታ ማጥቃት ነው፡፡ ይህ ምልከታ የፖለቲካ ሥልጣን በሕሊናዊ መንገድ ሳይገመገም ወይም ከምክንያታዊ መመዘኛች ጋር እንዲጣጣም ሳይጠየቅ እንዲሁ ተቀባይነትን ሊያገኝ ይችላል የሚለውን እሳቤ ፉርሽ ለማድረግ ከሚፈልጉት፣ እንደ ጆን ሎክ ካሉት ዘንድ የሚመደብ ነው፡፡ ሆኖም ይህ በሕሊና እና በስሜት መካከል ያለውን ሰበባዊ (causal) ዝምድና በቅጡ አለመረዳት እንደሆነ ሂዩም ያስገነዝባል፡፡ እንደ እርሱ ሐሳብ፣ ሞራላዊ እምነት ወይም አመለካከት የስሜት ዝርያ ነው፡፡ ይሁንና ግን ያሉን ስሜቶች የሉንም ወይም አይሰሙንም፣ ምክንያቱም በሆነ በተወሰነ መንገድ ስናስብ ቆይተናልና፡፡ በአንፃሩ ደግሞ አሁን እንደምናስበው እናስባለን፣ ምክንያቱም ያሉን የተለዩ ወይም የተወሰኑ የስሜት ዓይነቶች ይሰሙናልና፡፡

አንዳንድ ሰዎች፣ ለራሳቸው በተወሰነ መልኩ አስቸጋሪ በመሆኑ የመላውን ዓለም መውደም ሊመርጡ ይችላሉ፤ ሌላ ሰው ደግሞ ለሌላውም አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ጠቅላላ ውድመትን ሊመርጥ ይችላል፡፡ እንዲህ ያሉትን ምርጫዎች ወጣ ያሉ ወይም ያልተለመዱ አድርገን ልናስባቸው እንችላለን፤ ነገር ግን ምክንያታዊ (irrational) አይደሉም፤ ይህም ማለት እነዚህን ምርጫዎች በማድረግ ረገድ አመክኒዮአዊ ተቃርኖ አይኖርም፡፡ የሞራል እምነቶች ወይም አመለካከቶች፣ አንድ ሰው ስሜቱ የሚሰማው ለእርሱ እንደተሰማው በመሆኑ ምክንያት በምርጫ የሚያዙ አቋሞች ናቸው እንጂ፣ በራሱ መንገድም አስቧል የምንልባቸው አመክኒዮአዊ ድምዳሜዎች አይደሉም፡፡ እናም መንግሥት የሞራል እምነቶችን ወይም አመለካከቶችን ተቋማዊ እንደማድረጉ፣ በቀጥታ በሕሊና ወይም በማስተዋል ብቃት የተፈጠረ ሳይሆን፣ ይልቁንም በሕሊና ግን ደግሞ ለሆነ ዓይነት ስሜት «ባሪያ» በሆነ ሕሊና የተፈጠረ ነው፡፡

ፖለቲካን በተመለከተ ይህ የሚያመላክተው ነገርም፣ መንግሥት እና ፖለቲካዊ ግዴታ እንደማኅበራዊ ውል (Social contract) ወይም የተፈጥሮ ሕግ ባሉ ውስብስብ መንገዶች ሳይሆን፣ ሰብዓዊ ፍጡራን ለመሠረታዊ ፍላጎቶችና መሻቶች ለሚኖራቸው ስሜት በሚሰጡ ተግባራዊ ምላሾች አማካኝነት የመነጩ ተደርገው ሊወሰዱ እንደሚገባ ነው፡፡ ዴቪድ ሂዩም እንደሚያስበው፣ ሰዎች በተፈጥሯቸው እርስ በርስ ተግባቢ (sociable) ናቸው፡፡ እንደነሱ ካሉ አምሳያዎቻቸው ጋር ለመኖር ይገፋፋሉ፡፡ ሆኖም ለሌሎች ያላቸው መልካም አመለካከት – ሩህሩህነታቸው (benevolence) – የተገደበ ነው፡፡ ይህም ማለት በቅድሚያ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው የሚያስቡ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ ብቻ ለሌሎች ሰዎች ያስባሉ፡፡ ይህንን ማንነታቸውንና በተጨማሪ ደግሞ በዓለም ላይ ያለው አንጡራ ሀብት አላቂ መሆኑን ከግንዛቤ በመክተት፣ የትም ይሁን የት ሰብዓዊ ፍጡራን በአንድነት ሲሰባሰቡ ግጭቶች መከሰታቸው አይቀሬ ነው፡፡

እንዲያ ያሉ ግጭቶችን አነስተኛ ለማድረግ ሲባል ነው፣ ሰዎች ለዘመናት ዴቪዲ ሂዩም «Rules of Justice» ወይም «የፍትህ ሕግጋቶች» በማለት የሚጠራቸውን ሲፈጥሩ መቆየታቸው – የንብረት ይዞታዎችን ዋስትና እና የውሎችን መከበር ያረጋግጡ ዘንድ የታለሙ ሕግጋቶች፡፡ እነዚህን ሕግጋቶች በቀዳሚነት የቀረፀውን ሕግ አውጪ ልንጠቁም አይቻለንም፤ ይህንንም መሞከር የሚፈይደው ነገር አይኖርም፡፡ ረቂቅ በሆነ የማስተዋል ብቃት (reason) የተገለፁ «የተፈጥሮ ሕጐች» አይደሉም፤ እንዲሁ ተለምዷዊ ሲሆኑ በራሳቸው ብቻ ጠቃሚነት የላቸውም፡፡ በግጭቶች አማካኝነት ለሚነሱ ውስጣዊ ስሜቶች ምላሽ ለሚሰጥ የተግባራዊ አስተውሎ ውጤቶች ናቸው፡፡ ሰብዓዊ ፍጡራን በሚያስቡትና በሚሰማቸው ስሜት፣ ከሞላ ጐደል ሁሉም ተመሳሳይ በመሆናቸው ምክንያት፣ ሰዎች ኑሯቸውን የሚመሩባቸው የፍትህ ሕግጋቶች በከፍተኛ መጠን የወጥነት ባሕሪይን ያሳያሉ፡፡

ዲቪድ ሂዩም እንደሚለው ከሆነ፣ እነዚህ የፍትህ ሕግጋቶች ከመንግሥት አስቀድመው የነበሩ ናቸው፡፡ መንግሥት ሊመጣ የቻለበት ምክንያት፣ የሰው ልጅ ተፈጥሮ እንዳለ ሆኖ፣ ከበላያችን የማስገደድ ሥልጣን ያለው የሆነ አካል ወይም ወኪል ከሌለን በቀር «በፍትህ ሕግጋቶች» መኖር ስለሚሳነን ነው፡፡ አርቀን መመልከት ስለሚሳነን፣ የፍትህ ሕግጋቶቹ ተፈፃሚ ሊሆኑ የግድ ነው፤ የረጅም ጊዜ ጥቅሞቻችንን ወደኋላ በመተው ለአጭር ጊዜ ግቦች ዋጋ እንሰጣለን፡፡ በተረጋጋ ስሜት ውስጥ በሆንን ጊዜ፣ የፍትህ ሕግጋቶቹን በአግባቡ ማስፈፀም የሚችልን አካል መደገፍ ለራሳችን ትክክለኛ ጥቅም ሲባል መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ይህ የጋራ ግንዛቤ ወይም ንቃት ነው፣ በስሜት በተሞሉና ቅርባቸውን በሚመለከቱ፣ ግን ደግሞ ያለጥርጥር ምክንያታዊ በሆኑ ሰብዓዊ ፍጡራን ዘንድ የመንግሥትን መኖር እና ሥልጣን መያዝ የሚያጭረው፡፡

መቼ እና በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ነበር መንግሥት የተፈጠረው? ዴቪድ ሂዩም፣ የፖለቲካ ፀሐፊዎች ለዚህ ጥያቄ ጠንከር ያለ ትኩረት ለምን እንደሚሰጡ አይገባውም፡፡ እርሱ እንደሚያስበው፣ የዚህን ጥያቄ ምላሽ በምንም መንገድ ልናውቅ አንችልም፤ ግምታዊ ድምዳሜ ማስቀመጥም የሚፈይድልን ጥቅም አይኖርም፡፡ መንግሥት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለዋወጠ የመጣና በባሕል (Custom) አዛዥነት ለመመስረት የበቀ እንደሆነ አድርጎ መውሰድ የተሻለው አማራጭ ሳይሆን አይቀርም፤ እናም መንግሥት እንዳለን ማወቃችንና እርሱም ዓላማዎቹን በስኬታማ መንገድ የሚተገብር መሆኑ ለእኛ በቂ ነው። ኤድመንድ በርክ እንዳደረገው ሁሉ፣ ሂዩምም ለዚህ ጉዳይ “ተከድኖ ይብሰል” ፖሊሲን ይጠቁማል።

አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ሥርዓት (መንግሥት)፣ እኛ ከእርሱ የምንፈልገውን የሚያደርግ ከሆነ ጣልቃ ልንገባበት ወይም ልናደናቅፈው አይገባንም፡፡ እንደ ሂዩም እምነት፣ የወጥነት እና የጥቅልነት ባሕሪይ ባላቸው ሕጎች ትግበራውን የሚያከናውን መንግሥት ከምንም በላይ አግባብ ያለው (ተመራጭ) ነው፤ ምክንያቱም በእርሱ ስር ያሉትን በሙሉ የማስደሰት ዕድሉ ከፍተኛ የሆነ የመንግሥት ዓይነት ነውና፡፡ ለሂዩሞ የሚስማማው የመንግሥት ዓይነት የዘውዳዊ (monarchical) እና የሪፐብሊካን ቅይጥ ሆኖ፣ ሁለቱ የሥልጣን ዓይነቶች አንዱ ሌላውን የሚቆጣጠሩበትና የሚገድቡበት (እንደርሱ እይታ) በእንግሊዝ የተዘረጋው ዓይነት መንግሥት ነው፡፡ ሆኖም ውጤታማ እስከሆነና ሕዝቦቹም ድጋፋቸውን በመስጠት ዓላማዎቻቸው እየተተገበሩ እንደሆኑ እስከቆጠሩ ድረስ፣ የመንግሥት ሥርዓቱ ዓይነት ምንም ቢሆን ብዙም ችግር የለውም (ብዙም ለውጥ አያመጣም)፡፡

«ሁሉም የሥልጣን ዓይነቶች፣ ከፈረንሳይ ዘውዳዊ ሥርዓት እስከ የስዊዝ ግዛቶች እጅግ ነፃ ዴሞክራሲ ድረስ፣ በባሕል (Custom) እና በይፋዊ ፈቃድ አማካኝነት ከተመሠረቱ በእኩል መልኩ ሕጋዊ ሆነው ይታዩኛል፡፡»

ዴቪድ ሂዩም ለማኅበራዊ ውል መከራከሪያዎች ትዕግስት የለውም፡፡ ለነዚህ መከራከሪያዎች የጆን ሎክ አድናቂ ነኝ የሚል ሁሉ ሊያነበው በሚገባው «Of the Original Contract» ፅሁፉ አማካኝነት ጠንካራ ትችቱን ሰንዝሯል፡፡ ሁሉም ግዴታዎች በመጀመሪያው ወይም ኦሪጅናል በሆነው ውል ላይ የሚመረኮዙ ከሆነ፣ ይህንን ኦሪጅናል ውል እንዳለ የማቆየት ግዴታስ በምን ላይ ይመረኮዛል? የመጀመሪያው ውል የተፈፀመበትን ጊዜና ሁናቴ ማንም ሰው ማስታወስ ወይም መጥቀስ እስካልቻለ ድረስ፣ ከልማድ ወይም ከባሕል ይልቅ ስምምነትን (Consent) እንደ የግዴታ ምንጭነት አድርጐ መውሰድ እንዴት ትርጉም ሊሰጥ ቻለ?

ጆን ሎክ፣ ማኅበራዊ ውል የሚፈፀምበትን መንገድ በተመለከተ በይፋ ያልተገለፀ ስምምነት (tacit consent) የሚል መከራከሪያ አንስቶ ነበር፡፡ ግለሰቦች የሚኖሩበትን ማኅበረሰብ ጥለው ያለመውጣታቸው እውነታ በራሱ፣ ማኅበረሰቡ ለሚስተዳደርበት አወቃቀሮች ስምምነታቸውን ለመስጠታቸው ማስረጃ እንደሆነ ሎክ ይገልፃል፡፡ ይሁንና ግን፣ ዴቪድ ሂዩም ይህ የሚያስኬድ አይደለም ይላል፡፡ ለዚህም ከእንቅልፉ ሲነቃ እራሱን ውቅያኖስ ላይ መርከብ ውስጥ ስላገኘው ሰው ምሳሌ ያነሳልናል።

ይህ ሰው ሳያውቀው ታፍኖ ነው መርከብ ላይ የተጫነው፡፡ እንደማኅበራዊ ውል አቀንቃኞች ከሆነ፣ ሁሉም የመንግሥት ሥልጣን የመጣው በግለሰቡና በግለሰቡ ስምምነት ብቻ ነው። ነገር ግን ያ ስምምነት በይፋ የተገለፀ መሆን አይኖርበትም ይላል ጆን ሎክ፡፡ ታዲያ ያለፈቃዱ መርከብ ላይ የተጫነው ግለሰብ ምንድን ነው ማድረግ የሚገባው? እራሱን ከመርከብ ላይ መወርወር ይችላል፤ ሆኖም ይህ የማይደፈር አማራጭ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ አልያም ደግሞ እዚያው ባለበት መርከቧ ላይ መቅረት ይችላል፤ እናም ይህን ካደረገ በይፋ ባልተገለፀ ስምምነት (tacit consent) መርሆ መሠረት እዚያ በመገኘቱ እውነታ ብቻ የካፒቴኑን ሥልጣን ተቀብሏል ማለት ነው፡፡ ይህም መንግሥቱን እጅጉን የሚጠላ፣ ግን ደግሞ ከመንግሥቱ የሥልጣን ክልል እራሱን የማስወጪያ መንገድ ያጣ «ደሃ ጭሰኛ ወይም የዕደ-ጥበብ ባለሙያ» በትክክል የገጠመው አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሆነ ሂዩም ይገልፃል፡፡ በይፋ ያልተገለፀ (tacit) ስምምነት በመንግሥት ስር የሚኖሩ፣ ሆኖም ይህን የማድረጋቸው ብቸኛ ምክንያት ወደ ሌላ ቦታ መሄድ አለመቻላቸው የሆነ ሕዝቦች የመኖራቸውን እውነታ ከግምት ያላስገባ መከራከሪያ ነው፤ ስሜት የሚሰጥ የስምምነት ዓይነት ለመሆን ይሳነዋል፡፡

ሂዩም፣ መርሆዎቹ የሰብዓዊ ተፈጥሮ ወይም የጠቅላላው ዓለም ባሕሪይ እውነታዎች ናቸው በተባሉት ላይ መሠረት በሚያደርጉ ወይም ከእነሱ በሚመነጩ የተፈጥሮ ሕግ አስተምህሮ ላይ የነቀፋ መከራከሪያውንም ያቀርባል። እንዲህ ዓይነቱ ነቀሳ (አመጣጥ/derivation) ግልፅ የሆነ ፉርሽነትን (fallacy) ያካተተ ነው። “Treatise of Human Nature” መፅሐፉ ላይ የሚከተለውን አስፍሯል፡-

“እስከዛሬ በገጠመኝ የሞራል ሥርዓት ሁሉ፣ የሥርዓቱ ፈጣሪ ለተወሰነ ጊዜ በመደበኛው የአመክኒዮ መንገድ ሲጓዝ፣ እንዲሁም የእግዚአብሔርን መኖር ሲያረጋግጥ፣ አልያም ሰብዓዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ቅኝት ሲያደርግ ሁልጊዜም ስታዘብ ቆይቻለሁ፤ በድንገት ግን በተለመዱት “ነው” (is) እና “አይደለም” (is not) የአመክኒዮ ድምዳሜዎች ምትክ፣ “መሆን አለበት” (ought) ወይም “መሆን የለበትም” (ought not) ከሚሉት ጋር ያልተያያዘ የአመክኒዮ ድምዳሜ አለማግኘቴ አስገረመኝ። ይህ ለውጥ ለመረዳት የሚያዳግት ነው፤ ሆኖም ይህ ትንሹ ችግሩ ነው። ይህ “መሆን አለበት” ወይም “መሆን የለበትም” አንድ የሆነ አዲስ ነገርን ወይም የማረጋገጥ ስሜትን የሚገልፅ በመሆኑ፣ ሊቃኝ እና ሊመረመር ያስፈልጋል፤ እናም በተመሳሳይ፣ በጥቅሉ የማይሆን ነገር ለሚመስለው፣ ምክንያት ሊሰጥበት ይገባል። – ታዲያ ይህ አዲስ ግንኙነት፣ እንዴት ብሎ ሙሉ ለሙሉ ከእርሱ ከተለዩ ሌሎች የተነቀሰ ወይም የተወሰደ ሊሆን ይችላል።”

በዚህ ፅሁፍ ላይ የሂዩም ነጥብ፣ እርሱ የገለፀው የሞራል አመክኒዮ ዓይነት የፍረጃ ስህተት (category-mistake) በማለት ልንጠራው የምንችለውን ያካተተ መሆኑ ነው። ከዚህ አኳያ፣ በርግጥም ትክክል ነው። ሁሉም ሰዎች (ለምሳሌ) በተፈጥሯቸው ምግብ ካላገኙ ይራባሉ ከሚለው ሐሳብ፣ ማንኛውም ሰው ምግብ የማግኘት “ተፈጥሯዊ መብት” አለው የሚለው እንደማይከተል ግልፅ ነው። ይሁንና የሂዩም በዚህ ረገድ ትክክል መሆን የሚያስከትላቸው ውጤቶች፣ አንዳንድ ጊዜ እንደሚጠቀሰው እጅግ አነቃናቂ ዓይነት አይደሉም። “መሆን አለበት” የሚለውን “ነው” ከሚለው ላይ የመንቀስ ፉርሽነት (fallacy)፣ በትክክልም ፉርሽ ነው የሚባለው ነቀሳው መደበኛ ተዋርዶ (deduction) ከሆነ ብቻ እና ብቻ ነው። በተፈጥሮ አስፈላጊ ስለሆኑ ነገሮች ከምናውቀው አንፃር፣ ነገር ግን ከእነሱ እየነቀስን ሳናወርድ፣ ዝርዝር “የተፈጥሮ መብቶችን” እጅግ በተሳካ መንገድ መቀመር (ማፍለቅ) እንችላለን፤ በዚህ ላይ ምንም ዓይነት ፉርሽነት የለም። በርግጥ እንዲህ ያለውን ዝርዝር፣ ሰዎች በተግባር ከሚያስፈልጓቸው ነገሮች ውጪ ከሆኑ ሌሎች ነገሮች አንፃር እንዴት ማፍለቅ እንደምንችል ማሰቡ አስቸጋሪ ነው። ከዚህ አኳያ፣ የሂዩም ነጥብ እንዳንድ ጊዜ ሲታሰብ እንደቆየው ያህል በተፈጥሮ-ሕግ መከራከሪያዎች ላይ ጉዳት ያስከተለ አይደለም፤ ምንም እንኳን የሞራል ፈላስፎች ስለ የተፈጥሮ ወይም ሰብዓዊ መብቶች ሲያወሩ በትክክል ምን ዓይነት ሐሳብ እየተነሳ ስለመሆኑ አስቀድመው እንዲያስቡ ቢያደርጋቸውም።   

ዴቪድ ሂዩም፣ የመጀመሪያው ዩቲሊታሪያን (ድርጊቶች ጠቀሜታ ካላቸው ወይም አብላጫውን የሚጠቅሙ ከሆነ ትክክል ናቸው የሚለውን የሥነ-ምግባር ፍልስፍና ተከታይ) ተብሎ ሊገለፅ የሚችል ነው። ጀርሚ ቤንትሃም፣ “Treatise of Human Nature” በተሰኘው የሂዩም ሥራ እጅግ ተደንቋል፤ እንዲሁም የምናደርገውን እንድናደርግ የሚያነሳሳን ምን ስለመሆኑ የሚያብራራው የሂዩም እሳቤ ተፅዕኖ እንዳሳደረበት ግልጽ ነው፡፡ እንደሂዩም እምነት አንድን መንግሥት የምንመለከተውና የምንገመግመው እንደ ስምምነት፣ ውል፣ አልያም የተፈጥሮ ሕግ ዓይነት ውስብስብ እሳቤዎች ጋር የተጣጣመ መሆኑን ለመለካት በምናደርገው ሙከራ ሳይሆን ታሪካዊና ተግባራዊ ጉልብትናውን መሠረት በማድረግና እንድንቀበለው ወይም እንድንደግፈው የሚያስችሉ ውጤቶቹን በማጣቀስ ነው፡፡ ዴቪድ ሂዩም («ቶሪ» ወይም የእንግሊዝ ኮንዘርቫቲቭ ፓርቲ አባል/ደጋፊ ነበር የሚባለው የተሳሳተ ነው) እራሱን ከፖለቲካ ፓርቲዎች ያራቀ ቢሆንም፣ በሁልጊዜ ባሕሪይው ኮንዘርቫቲቭ ነው፡፡

ለበለጠ ንባብ

ቀዳሚ ምንጮች

New Letters of David Hume, ed. R. Kilbansky and E.C. Mossner (Oxford: Clarendon Press, 1954).

Enquiries Concerning Human Understanding and Concerning the Principles of Morals, ed. E. Selby-Bigge (Oxford: Clarendon Press, 1975).

A Treatise of Human Nature, ed. L.A. Selby-Bigge (Oxford: Clarendon Press, 1978).

The History of England from the Invasion of Julius Caesar to the Revolution of 1688, ed. W.B. Todd (Indianapolis, IN: Liberty Classics, 1983–5).

Essays Moral, Political and Literary, ed. E. Miller (Indianapolis, IN: Liberty Classics, 1985).

ተቀፅላ ምንጮች

Forbes, D.: Hume’s Philosophical Politics (Cambridge: Cambridge University Press, 1975).

Mackie, J.L.: Hume’s Moral Theory (London: Routledge & Kegan Paul, 1980).

Miller, D.: Philosophy and Ideology in Hume’s Political Thought (Oxford: Clarendon Press, 1981).

Whelan, F.G.: Order and Artifice in Hume’s Political Philosophy (Princeton, NJ: Princeton University Press, 1985).

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.