የአብይ መንገድ እና የእንቁልልጬ ፖለቲካ
(በግዛው ለገሠ)
ቀደም ብሎ፣ የትግራይን ምርጫ ተከትሎ፣ ማዕከላዊ መንግሥት ለሁለት ዓመታት ፈራ-ተባ ያለበትን ጉዳይ አንድ ብሎ ጀመረ። ለክልሉ የሚሰጠውን የበጀት ድጎማ፣ የህወሓት ባለሥልጣናትን እያቁለጨለጨ በቀጥታ ወደ ወረዳ እንደሚያወርድ አስታወቀ።
ብዙዎችን ግራ አጋባ፦ ምን የሚሉት እርምጃ ነው? ወረዳም ያሉት ህወሓቶች ናቸው፣ እንዴት ተብሎ ሊፈፀም ነው? የማይሆን ነገር ነው . . . የመሳሰሉት ተባለ። አንድም፣ ጥሌ ከአመራሮቹ እንጂ ከሕዝቡ አይደለም የሚለው አቋሙን ለማስመስከር፤ አንድም በመሃላቸው መጠራጠርን፣ መናናቅን እና መጠባበቅን ለመፍጠር፤ አንድም በዚህ የአስተዳደር እና የመዋቅር መዛባት ለሚከሰተው እክል ህወሓትን በትግራይ ሕዝብ አስወቅሶ እስከመጨረሻው ለማስወገዝ፤ አንድም ደግሞ አብሬያቸው እሰራለሁ ያላቸው የወረዳ አስተዳደሮች በጀቱን ወደታች ማውረድ ትተው ሽቅብ ማፍሰስ ከጀመሩና የሕዝብን “ዳቦ” ለ“ሕገ-ወጥ” አመራሮች አሳልፈው እየሰጡ ስለሆነ ለሕዝቦች መብት ሲል ጣልቃ ገብቶ የመጨረሻ ህልሙን እውን ለማድረግ . . . ሊሆን ይችላል፣ ግራ-አጋቢ እርምጃው። ከእነዚህ ሌላም “አንድምታ” ይኖረዋል።
የእንቁልልጩ “ከረሜላ”
ገና ከለውጡ አንስቶ “እንቁልልጬ” የዚህ ሀገር ፖለቲካ ማጣፈጫ እየሆነ መምጣቱን ስንታዘብ ነበር። በህወሓት እና በብአዴን (ከረሜላው፦ አንዳንዴ አብይ፣ አንዳንዴ ኢሣያስ)፣ በኦህዴድ እና በብአዴን (ከረሜላው፦ አንዳንዴ አብይ፣ አንዳንዴ ፊንፊኔ)፣ በጀዋር እና በአብይ (ከረሜላው፦ የእነሱስ ብዙ ናቸው፦ ኦሮሚያ፣ ኢትዮጵያ፣ ለማ፣ ታከለ፣ የኦሮሚያ አንጋፋ ፖለቲከኞች/ታጋዮች/አርቲስቶች፣ የደቡብ ክልል ብሔር እና ብሔረሰቦች . . .)፣ በአክቲቪስቶች መካከል (ከረሜላው፦ እነዚህስ በተመጠጠ ከረሜላ ነው እርስ በርስ የሚቁለጫለጩት)፣ እንዲሁም በብዙ ሌሎች መካከል እንቁልልጬ መባባል ነበር።
በህወሓት እና በማዕከላዊ መንግሥት (ማለቴ በአብይ) መካከል ሲካሄድ የነበረው እንቁልልጭ አሁንም እንደቀጠለ ነው። የእንቁልልጩ ከረሜላም ያው እንደምታዩት ኢሣያስ ነው። በመካከላቸው ውጥረቱ ጋል ሲል፣ ኢሱ ድንገት ይመጣና ድልድይ ይመርቃል፣ ቡና ይለቅማል – አብይም ኢሱን አቅፎ እንቁልልጬ ይላል። ከሰሞኑ ድንገቴ ጉብኝቱ በኋላ ደግሞ ማስጠንቀቂያም ሰጥቷል – በኢትዮጵያ አንድነት ላይ እጁን የሚያነሳ ካለ ዝም ብሎ እንደማይመለከት ዝቷል። ይህን ስላቅ ነው ብለህ ማለፍ ትችላለህ፤ ግን ስላቅም፣ እንቁልልጭም ብቻ አይደለም – ከዚያ ምን ሆነ? ብሎ መጠየቅ ነው።
አዲስ እዞች ሲቋቋሙ. . .
ከአንበጣው ፖለቲካ፣ ከድሮኑ ፕሮፓጋንዳ፣ እንዲሁም ከፈንቅል የንቅናቄ ሹክሹክታ ጎን ለጎን ሌሎች ክስተቶች መካሄዳቸውን ቀጥለዋል። [የመተከል ጉዳይ፣ የቤንሻንጉል ጉምዝ እና የአማራ ክልሎች ሁናቴ ራሱን የቻለ ጽሁፍ ያጽፋል፤ በፌዴራሊዝሙ አወቃቀር ላይም ገና ውይይቶች እንደሚያስፈልጉ የሚመሰክር ነው።]
በቀደም ለታ ደግሞ ሠራዊታችን ሁለት ተጨማሪ እዞችን አቋቁሟል። አንዱ ከዚህ ቀደም የነበረ ቢሆንም፣ ከለውጡ በኋላ በተደረገው የመከላከያው ሪፎርም መሠረት የታጠፈው የማዕከላዊ እዝ ነው (ከዚህ ከሚቋቋመው ማዕከላዊ እዝ ያልተናነሰ ኃይል፣ በሪፐብሊካን ጋርድ እና በሌሎች መደበኛ የፀጥታ አካላት ስር እዚሁ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ላይ ሊኖር እንደሚችል እገምታለሁ)። ሁለተኛው የሰሜን ምዕራብ እዝ ነው፤ ያው አካባቢውን እና ሊሸፍን የሚችላቸውን ክልሎች መገመት አያዳግትም።
የትግራይ ነፃነት እና ብልጽግና
አብይ ግን ብልጥነቱ፣ የፓርቲውን ስም “ብልጽግና” ማለቱ። ድንገት ተነስተህ “ብልጽግናን አልደግፍም” ብትል አባባልህ እራሱ አፍራሽ አስብሎ ያስፈርጅሃል። የሆነ ሆነና፣ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆነው ዶ/ር አብርሃም በላይ ዛሬ መግለጫ በትኗል።
ከሁሉም አሳዛኙ፣ የዚህ ሀገር የእንቁልልጭ ፖለቲካ ጥግ ነው። ሁለቱም ወገን በየተራ ነፃነትን እንደ ከረሜላ ይዘው በትግራይ ሕዝብ ላይ ያለማቋረጥ መቀለዳቸው ነው። ህወሓት ቀድሞውኑ ከአብራክህ የወለድከኝ ለነፃነትህ ነውና የማዕከላዊ መንግሥቱን የጭቆና እቅድ እስከዘላለም አብረን እንታገላለን እያለ ይሰብካል። ማዕከላዊው መንግሥትም ከምንም ነገር በላይ የትግራይ ሕዝብ እንደተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃ አለመውጣቱ እንደሚያሳስበው ለማስረዳት ይሞክራል።
ለማንኛውም፣ ዶ/ር አብርሃም ዛሬ ምን አለ? [በነገራችን ላይ፣ ያ የተባለው የኮሮና መድሃኒት ከምን ደረሰ? ይህን የሚጠይቅ አንድ ጋዜጠኛ ይጥፋ? ወይስ መድሃኒቱ “መጋለጥ” ነበር?]
“በተለይም በስሙ እየተነገደበት ያለው የትግራይ ህዝብ ከወንድም ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመተባበር ነጻነቱን በብልሃት ማወጅ ይጠበቅበታል” አለ – ዶ/ር አብርሃም በላይ። የትግራይ ሕዝብ ነፃነቱን የሚያውጀው እንዴት ነው? ከዚህ ቀደም እንዳወጀው? ብልሃቱስ ምን ዓይነት ብልሃት ነው? በነፃነት እንቁልልጭ መጫወት ለማንኛውም ሕዝብ ያማል፤ በተለይ ለትግራይ ሕዝብ ደግሞ በቁስል ላይ እንጨት እንደመስደድ ነው።
ዶ/ር አብርሃም ከላይኛው በተጨማሪ፣ መንግሥት የሚወስዳቸውን “የተጠኑ ፖለቲካዊ እርምጃዎች” እንዲደግፍ ለሕዝቡ ጥሪ አቅርቧል። “ፖለቲካዊ” ማለታቸው አንድ ነገር ቢሆንም፣ እንደከዚህ ቀደሞቹ የፕሮፓጋንዳ እና የፖለቲካ እርምጃዎች እነዚህኛዎቹም የከሸፉ ጊዜ፣ ለሌላ ዓይነት እርምጃዎች በር መክፈት ብቻ ሳይሆን ለማዕከላዊ መንግስቱ “ጀስቲፊኬሽኖችን” የማከማቸት ሚና ይኖራቸዋል።
[ህወሓት አሸነፍኩ ብሎ በትግራይ ሥልጣኑን ቢቀጥል ድሮም ችግር እንደሌለበት፣ ችግር የሚፈጠረው ግን ሌላ ፓርቲ ያሸነፈና የክልሉ መንግሥት የሆነ ለታ እንደሆነ እዚሁ ፓርላማ ወንበር ላይ ተቀምጦ የተናገረው አብያችን፣ በቀደም ደግሞ የህወሓት ሕገ-ወጥነት በሕግ ብቻ እንደሚፈታ ሲመልስ፣ “ሾርት ሚሞሪ” ያለው ማን ጋር እንደሆነ ግር ይለናል። በሌላ በኩል አፈ-ጉባኤው ታገሰ ጫፎ በማይገኙ የትግራይ ተወካይ የፓርላማ አባላት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንወስዳለን ብሏል – በሺህዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ክልል ቢሮዎች ሠራተኞች የደመወዝ ጥያቄ የህወሓትን ናላ እንደተጠበቀው አያዞረውም ብለው ነው መሰለኝ 38 ሊጨምሩትለ ነው።]
የአብይ አጣብቂኝ/እድል. . . .
አንዳንድ ጊዜ በአብይ አልፈርድም። በተለይ ከኢሣያስ ጋር የፈጠረው ነገር በለውጡ ሂደት ውስጥ ካደረጋቸው ቁልፍ ተግባራት ዋነኛው ይመስለኛል። ወደድንም ጠላንም የተሳካ እንቁልልጭ ነበር (ቢያንስ እስካሁን)፤ ነገር ግን ከህወሓት ጋር ላለው አተካራ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ነው – ምናልባት ስር የሰደደ ከሆነ፣ ግብጽን ጨምሮ የአጎራባች ሀገራት የአካባቢው ፖለቲካ ላይም ተጽዕኖ ይኖረዋል። [አያድርገውና ኢሣያስ ቢሞት፣ ወይ ቢገለበጥ፣ አጠቃላይ “ሲናሪዮው” የመቀየር እድሉ ሰፊ ይመስለኛል።]
አብይ ግን አብሮት የሚበር ወፍ ያለ አይመስለኝም። ታዬ ደንደአም በለው ዶ/ር አብርሃም ክንፋቸው የረገፈ ወፎች ናቸው፤ እንደ ሙፈሪያት ያሉት ደግሞ የአበራረር ስልታቸው ከአብይ ጋር ስለመግጠሙ እራሳቸውም ገና ለይተው አላወቁትም። እነ ደመቀ ደግሞ ጭራሽ ክንፍም የላቸውም፤ በ“ኬጅ” ይዘሃቸው መዞር ነው [5 ብር አሉት፣ ጨካኞች!]።
አብይ ለኦህዴድም፣ ለብአዴንም አይመችም – አብይ የራሱ መንገድ አለው። ለኦህዴድ አመራሮች፦ የአብይን መንገድ መቃወም አንድም ለብአዴን እድል መስጠት ይሆናል፣ አንድም ደግሞ ያኔ በህወሓት ሜዳ ላይ፣ ከዚያም በብልጽግና ሜዳ ላይ ማኖ ያልነካ ሁነኛ እና ተጋፋጭ የሆነ የኦህዴድ አመራርን ይጠይቃል – በአሁን ሰዓት ለቁጥር አንድ የለም። በተመሳሳይ ለብአዴን አመራሮች፦ የአብይን መንገድ መቃወም ማለት ቀጥኖ እና ሳስቶ ያለውን የአብይ እና የኦህዴድ (እና የብዙ ኦሮሞ ኃይሎች) ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠነክር ማድረግ ነው። ስለዚህ ሁለቱም ወገኖች ተጠባብቀው፣ ተደጋግፈው ይቀጥላሉ [ሽመልስን ካባ ማልበስ ምን ይሉታል ብለህ እንኳን አልተገረምክም?!]።
ይህ አብይ የሚገኝበት ከባድ አጣብቂኝ ሊመስለን ይችላል፤ ነገር ግን አጣብቂኝ አይደለም – እንዲያውም እድል (ኦፖርቹኒቲ) ነው። በዋነኝነት የሀገሪቱ ነባር የፖለቲካ ሁኔታ የፈጠረው፣ ግን ደግሞ አብይ አክሎበት ጥቅም ላይ እያዋለው ያለው “ኦፖርቹኒቲ” ነው። ታዲያ በዚህ የተወሳሰበ የፖለቲካ ትዕይንት ውስጥ ሆኖ፣ አብያችን ፓርላማ ቀርቦ “ስሜ ጠፋ ብሎ ጋዜጠኛ ማሰር” ነውር እንደሆነ ይነግረና – ስለ ጋዜጠኛ ተመስገኝ ደሳለኝ የባለፈው እስር ሲያወራን።
የተመስገን ደሳለኝ ነገር . . .
ተሜ ታሰረ ሲባል፣ እውነቱን ለመናገር ብዙም አልገረመኝም። ለእስር የሚያበቁ ጽሁፎች ይፅፋል ማለቴ ሳይሆን፣ አሁንም ማሰር መብቱ እንደሆነ የሚያምን መንግሥት እንዳለን ስላልዘነጋሁ ነበር (ማሰር ኑሮበት ሲያስር እንኳን፣ ማሰር መብቱ ሳይሆን ግዴታው እንደሆነ የሚረዳ ፖሊስ እና መንግሥት ሊኖረን ይገባል)።
እናም ያስደነገጠኝ የተሜ መታሰር ሳይሆን፣ ከመቅጽበት የተጀመረው የሶሻል ሚዲያ ካምፔይን (ዘመቻ) ነበር። ተመስገንን እና ዋና አዘጋጁን ይዘዋቸው የሄዱት ፖሊሶች በትክክል በምን ምክንያት እያሰሯቸው እንደሆነ ቢያንስ እስከ ምሽት ድረስ አልነገሯቸውም። የተመስገን ወንድም ማታ ጎብኝቶት እንደፃፈው፣ ሀሰተኛ መረጃ አስተላልፈሃል እንጂ ሀሰተኛ የተባለው መረጃው የትኛው እንደሆነ እራሱ ተመስገንም እንኳን አያውቅም ነበር። ነገር ግን ገና ታሰረ ከመባሉ የአዳነች አቤቤ ስም በየገፁ ተጥለቀለቀ – የመጽሔቱ አንድ ጽሁፍ የተወሰኑ መስመሮች ስክሪንሾት ሆነው በየቦታው ተነጠፉ።
የዘመቻ መልክ እንዳለው በግልጽ ያስታውቅ ነበር። ለወትሮው የአብይ እና የመንግሥት (ወይም የለውጡ) ተሟጋቾች ነበሩ፣ ዘመቻውን አስጀምረው ያቀጣጠሉት። ታከለ ኡማ ወርዶ አዳነች አቤቤ ስትተካ፣ እነዚሁ አክቲቪስቶች የአብይን ውሳኔ አሳማኝ ለማድረግ አዳነችን በመጀመሪያው ንግግሯ እንደተዓምር ሲያሞግሷት ነበር። ተመስገን ሲታሰር ግን እርቃኗን አስቀሯት፤ ማኖ መንካቷን አራገቡ ወይም እንደማንኛውም ኦህዴድ የነካችውን ማኖ (ተመስገን ይፋ አደረገው) እነሱ በብርሃን ፍጥነት አስተጋብተው አዳረሱት።
ለአዳነች አቤቤ ተቆርቁሬ እንዳይመስልህ። አዳነችም ሆነች ማንኛውም የኦህዴድ አባል “ትብላው ብሬን” ሊዘፈንለት የሚያስችል አቋምም ሆነ ንጽህና የለውም። እንዲያው ግን የዚያን ዕለት የተደረገውን ዘመቻ አብይ እራሱ ፓርላማ ላይ ሲደግመው፣ ለእርሱ አዝነን የበታቾቹን እንድንወቅስለት ነው? ኦሮሚያ ላይ ልደቱ በተደጋጋሚ ሕገመንግሥቱ አናቱ ላይ እየተናደ ወራት ሲቆጠሩና አብይ ትናንት መጥቶ ድርጊቱን ሲኮንን፣ ኃጢያት ሽግግር እና “ብሌም ሺፍት” ማድረጉ ነው? አዳነችን እንደፈለገ፣ እንዲሁ መቶ ምናምን ሕዝብን እንደቂል ማየት ለራስ እንኳን አይከብድም? [የእስጢፍ አባት ይህን ቢሰሙ “ሸም ነው! ሸም ነው!” ይሉ ነበር።]
መዝጊያ . . .
ለማንኛውም፣ አጭር ነገር ለመፃፍ አስቤ ነው እንዲህ የረዘመብኝ [ጽሁፍ ናፍቆኝ ነበር]። አንድ ነገር ብዬ ላብቃ፦ ይሄ እንቁልልጭ፣ ይሄ በሁለት ቢላ መብላት፣ ይሄ ጠላትነትን/ባላንጣነትን ለራስ ግብ ማዋል፣ ይሄ አንድ መንገድ ብቻ ነው ያለው እያሉ ሌሎቹን በሙሉ መዝጋት፣ . . . እንኳን ፖለቲከኞቹን እኛንም ሰልችቶናል። ኢትዮጵያ አንድ ነች፤ ግን ብዙ ልጆች፣ ብዙ ሀሳቦችም አሏት። እንደ ህወሓት (ወይም ኢሕአዴግ) እኔ አውቅላታለሁ ማለት ተስፋ በቆረጡ ሕዝቦች ዘንድ አዋቂ እና አዳኝ ሊያስመስል ይችላል። ከዚያ አልፎ ለራስም እውነት እየመሰለ ይመጣል። ነገር ግን አሁንም የዘገየ አይመስለኝም፤ ራዕይን ማጋራት መልካም ቢሆንም አስገድዶ “ኢንስቶል” ማድረግ ግን “ሳይበር ክራይም” ነው – ሀገሪቱንም እንደቆመች ያስቀራታል።
ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ አንድም የፖለቲካ እስረኛ የለም እያለ ደጋግሞ ሲናገር ኑሮ፣ ለውጡ ሲመጣ ያኔ ክዶ እንደነበር እንኳን በቅጡ አላመነም። ባለንበት ላለመርገጥ ከሆነ የጋራ ራዕያችን፣ ዛሬ በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት የታሰሩት በሙሉ ሊፈቱ ይገባል። ጀዋር መሐመድን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች፣ እንዲሁም በፖለቲካ ምክንያት በየጥጋ ጥጉ መታሰራቸው እንኳን በይፋ የማይታወቅ ወጣቶች ጊዜው ሳይረፍድ ሊፈቱ ይገባል። መንግሥቱ ኃይለማርያም “ምንም ቢሆን ሀገሩን ይወድ ነበር” የሚለውን የመሰለ የዘቀጠ አባባል የለም። ፍርሃቴ ይህ አባባል ለአብይም እንዳይደገም ነው።
አበቃሁ!