Ankuar

Politics, culture and society in Ethiopia

FEATUREDPoliticsአንኳሮች

ይህ መተራመስ አደጋ አለው!

አብያችን አጣብቂኝ ውስጥ የገባ ይመስለኛል። ከውጭ ጫናው ባሻገር የውስጥ የፖለቲካ ውጥረቱ እያየለ ይመስላል። በርግጥ አንዱ የሌላኛው ምክንያት ናቸው። ምዕራባዊያኑ መንግሥትን “ኮርነር” ለማድረግ የመንግሥትነት ማገሩን መነቅነቅ ቁልፉ መላ እንደሆነ ገብቷቸዋል። በዚህም የነ ወልቃይት ጠገዴና ራያ ጉዳይን አጽንዖት መስጠታቸውን መመልከት ይቻላል።

የአማራ ኃይል ቦታዎቹን ከተቆጣጠረ በኋላ የመጣው ቢመጣ እንደማይለቅ ፅኑ አቋሙ እንደሆነ ከወራት በፊት አሳውቋል። የፌደራል መንግሥቱ ለዚህ ጉዳይ ገና ድሮ መፍትሄ ሊያበጅለት ሲገባ በቸልታ ሲመለከተው ቆይቷል። ለዚህም የመጀመሪያው ምክንያቱ ህወሓት መልሶ እንደሚያንሰራራ አለመገመቱ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ዋናው ምክንያቱ ግን ብአዴን በአቋሙ መፅናቱ ጊዜው የምርጫ ወቅት በመሆኑ ብልጽግና የክልሉንም ሆነ የፌደራል መንግሥቱን መቀመጫዎች በሚገባ ለማሸነፍ ስለሚያስችለው ነበር።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የአብይ፣ የኦህዴድ እና የብአዴንን የተሳሰረ የፖለቲካ ህልውና ለማብራራት አንድ ጽሁፍ ጽፌ ነበር። ኦህዴድ በኦሮሚያ ቢሸነፍ አብይም ሆነ ፓርቲው ለብአዴን የሚኖራቸው ፋይዳ ይመነምናል፤ ስለሆነም አብያችን የተጠላውን የኢሕአዴግ የካድሬ መዋቅር ይበልጥ አጠናክሮና ሁሉኑም ተቃዋሚዎቹን አስወግዶ ኦሮሚያ ላይ ማሸነፍ ነበረበት። ብአዴን ደግሞ ስር የሰደዱ የአማራነት የጀርባ እና የፊት ንቅናቄዎች በማጠናከርና የዋነኛ ተቃዋሚውን የአብንን እና የአማራ አክቲቪስቶችን ድምፅ በማስተጋባት በክልሉ እንደሚያሸንፍ ማረጋገጥ ነበረበት። የነ ወልቃይት ጉዳይም ከሁሉም በላይ ጠቅሞታል።

ዛሬ ግን ምርጫው አልፏል፤ ብልጽግና በኦሮሚያም፣ በአማራም፣ በፌደራልም አሸንፏል። ይህም ማለት አብይም፣ የኦህዴድ ካድሬም፣ የአማራ ኃይልም እኩል ሚዛን ላይ ይገኛሉ። ሆኖም ከሁሉም አስተማማኝ የኋይል ሚዛን ላይኖረው የሚችለው አብይ ነው – በተለይ በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው ግለሰቦች እና ተቋማት (በተለይ በሰሞኑ የሰሜን ጦርነት የመንግሥት ውሳኔዎች ላይ) የአብይን የኃይል ሚዛን የማዛባት አቅም ሊኖራቸው ይችላል።

እስካሁን ባየነው ሂደት፣ እንዲሁም በፌዴራል መንግሥቱ ውሳኔዎች እና በአማራ ኃይሎች መግለጫዎች መሠረት የፌደራል መንግሥቱ በነ ወልቃይት ጉዳይ የመሳተፍ ፍላጎት ያለው አይመስልም። አብይ ያን ሰሞን “የአማራ ልዩ ኃይል ቦታዎቹን የተቆጣጠረው በፌደራል መንግሥት ትዕዛዝ ነው” ብሎ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ የአማራ ክልል በግንባር ቀደምነት የሰሞኑን “የህልውና” ዘመቻ መምራቱ እና በሌሎች ሁኔታዎች ያ የአብይ አባባል ቀድሞውኑ መውጫ ቀዳዳ የማበጀት እንደነበር የሚያረጋግጥ ይመስላል። የአማራ ክልል አማራ የሆኑ የቀድሞ የሠራዊቱን አባላት ጨምሮ የየክልሉን ልዩ ኃይሎች ጥሪ በማድረግ ወደ ሰሜን ሲያመጣ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊቱ ከአቅም በታች ሆኖ እንዳልሆነ ግልፅ ነው።

ይሄ ሁሉ እንግዲህ የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም ከማድረጉ፣ ተከትሎም (ወይም አስቀድሞም) ሠራዊቱን ከትግራይ እንዲወጣ ከማድረጉ ጋር የመጣ የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ውጥረት ይመስለኛል። አብይ ሠራዊቱን ከትግራይ ለማስወጣት ሲወስን ውሳኔው እነ ወልቃይትንም ይጨምር ነበር? መከላከያ ሠራዊቱስ ይህን ውሳኔ እንዴት አየው? ድርድር ከሆነም ተኩስ አቁም አንድ ነገር ሆኖ፣ ለቀን ወጥተን እንዴት ነው ውይ ወደ ድርድር የሚኬደው? በሚል ያለመስማማት ሁኔታ ተፈጥሮ ይሆን? ኦህዴድ የኦሮሚያ ልዩ ኃይልን ወደ ሰሜን የላከው ከብአዴን ጋር ያላቸውን ከፍተኛ የፖለቲካ ሥልጣን ለማጠናከርና በእነሱ እና በአብይ መካከል ያለውን የኃይል ሚዛን ለማዛባት ነው ወይስ ልክ እንደሌሎቹ ክልሎች ለሀገር ህልውና ተቆርቁሮ ብቻ ነው? (እዚህ ላይ የኦህዴድ ራስ የሆነው አብይ መከላከያውን በቀጥታና በግንባር ቀደምነት ማሰማራት ሲችል፣ እስከ ትናንት ድረስ የተናጠል ተኩስ አቁሙን እያከበረ ስለመሆኑ መፃፉን ማስታወስ ያሻል።)

ለማንኛውም የመንግሥት ህልውና አደጋ ላይ መሆኑ እየተሰማኝ ነው። የውጭ ጫናን ለመቋቋም የውስጥ አንድነት መሠረታዊ ነው። ይህንን የውስጥ አንድነት መፍጠር እና ማፅናት የሚቻለው ደግሞ በፌደራል መንግሥቱ ይመስለኛል። የፌደራል መንግሥቱን ጥንካሬ ከመቼውም በበለጠ ማረጋገጥ የሚያስፈልግበት ጊዜ ይመስለኛል። እንደሰሞኑ የሚታየው መተራመስ መንግሥትን በቀዳሚነት፣ ከዚያም ሀገርን በተከታይነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው።

(ይህን የምፅፈው «አብይ ምን አደረገ፣ እገሌ ምን አደረገ፣ ማነው ጥፋተኛው ማለት ለአሁን አያስፈልግም» የሚለውን የአቶ አገኘውን ምክር በጊዜያዊነት ሰምቼና ተቀብዬ፣ ነገሩን ሁሉ አብይ ላይ ላለመጠቆም በመምረጤ ነው።)

—–

በግዛው ለገሠ
10/11/13

ፎቶ፡ AFP via Getty Images

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.