COVID-19FEATUREDNews

በምዕራብ ኦሮሚያ ተቋርጦ የነበረው የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ዛሬ ተለቀቀ

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዛሬው እለት እንዳስታወቁት፣ በምዕራብ ኦሮሚያ እና አካባቢው ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ የነበረው የስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎት ከዛሬ ጀምሮ ክፍት ይደረጋል ተብሏል።

አገልግሎቱ ተቋርጦ የነበረው በአካባቢው በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት ቢሆንም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አማካሪ የሆኑት አቶ ሌንጮ ባቲ ከዚህ ቀደም ከአል-ጀዚራ ጋር በነበራቸው ቆይታ በሀገሪቱ ምንም ዓይነት የተቋረጠ የቴሌኮም አገልግሎት እንደሌለ ተናግረው ነበር።

በቅርቡ በተለይም የመጀመሪያው የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ተጠቂ በኢትዮጵያ መገኘቱ ከተረጋገጠ በኋላ፣ በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ጨምሮ በተለያዩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ መገናኛ ብዙሃን የቴሌኮም አገልግሎት መቋረጡ ስለወረርሽኙ በቂ መረጃ ለማድረስ እክል እንደሆነ ሲዘገብ ሰንብቷል።

አቶ ሽመልስ በዛሬ መግለጫቸው፣ የኦሮሚያ ክልል እና የፌደራል መንግሥት በአካባቢው በጋራ ሲያካሄዱት የነበረው ሥራ መጠናቀቁን ጠቁመው፣ በአሁን ሰዓት በአካባቢው ሰላም እና መረጋጋት መስፈኑን አስታውቀዋል። ፕሬዝዳንቱ በቅርቡ በአካባቢው በአካል ጉብኝት አድርገው መመለሳቸው ይታወቃል።

Picture: The Reporter Ethiopia

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.