በማውራት ወይም በትንፋሽ ሊተላለፍ እንደሚችል ተነገረ
የኮቪድ-19 ዋነኛ መተላለፊያ መንገድ ተብሎ በዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እንዲሁም እንደ የአሜሪካው የበሽታ ቁጥጥር ማዕከል (CDC) ባሉ ተቋማት እንደመመሪያ የተቀመጠው፣ አዲሱ ኮሮናቫይረስ ያለበት ሰው ሲያስነጥስ ወይም ሲያስል በሚወጡ ጥቃቅን ጠብታዎች (Droplets) አማካኝነት ነው። ይኸውም እነዚያ ጠብታዎች በቀጥታ ወደሌላ ሰው መተንፈሻ አካላት ሲገቡ፣ ወይም ያረፉበት ቁሳቁሶችን በነካ እጅ አፍን፣ አፍንጫን ወይም ዓይንን በመንካት ቫይረሱ እንደሚሰራጭ ሲነገር ቆይቷል።
ሆኖም ሰሞኑን ባለሙያዎች አዲስ ትንታኔ ይፋ እያደረጉ ይገኛሉ። በተለይ ተመራማሪዎቹ ለአሜሪካ መንግሥት እንዳስታወቁት፣ በቅርበት በማውራት ወይም በመተንፈስ፣ በአየር አማካኝነት ቫይረሱ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው ሊተላለፍ ይችላል የሚል መላምት አስቀምጠዋል።
አስቀድሞ ከታመነው ከእርጥበታማ ጠብታዎች ባሻገር፣ ተህዋሲያንን በተሸከሙ ጥቃቅን የአየር ነጠብጣቦች (aerosols) አማካኝነት አዲሱ ኮሮናቫይረስ የመተላለፍ እድል እንዳለው ተጠቁሟል። ይህን ተከትሎ የአሜሪካ ፌደራል መንግሥቱ በወረርሽኙ ስርጭት ዙሪያ መመሪያውን ማሻሻል ይኖርበት እንደሆን እየመከረበት ሲሆን፣ የተወሰኑ ግዛቶች ግን የፌዴራሉን መመሪያ ሳይጠብቁ የራሳቸውን መመሪያ ወደማሻሻል እያመሩ ነው።
በማውራት ወይም በትንፋሽ ከተላለፈ ምን ማድረግ አለብን?
የፊት ማስኮችን አዘውትሮ መጠቀም የተሻለው መንገድ ቢሆንም፣ በዓለም ደረጃ ባለው የፊት ማስክ እጥረት ሳቢያና የጤና ባለሙያዎች ወይም የበሽታው ምልክቶች የታዩባቸው እና የተረጋገጠባቸው ሰዎች ብቻ እንዲጠቀሙ ይመከራል።
ሆኖም ማንኛውም ሰው በሚያወራበትም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚሆንበት ጊዜ፦
- አካላዊ ርቀቱን ይጠብቅ፤
- ስካርፍ፣ ሻርፕ እና የመሳሰሉትን በመጠቀም የመተንፈሻ አካላቱን ይሸፍን (እነዚህ ምክሮች በሕክምና አልተረጋገጡም)፤
- በቤት ወስጥ ወይም በመኪና ውስጥ ከሆነ፣ በቂ የአየር ዝውውር እንዲኖር መስኮቶችን ይክፈት (ተህዋሲያንን ሊሸከሙ የሚሽሉት ጥቃቅን የአየር ነጠብጣቦች በቀላሉ በንፋስ ወይም በሚንቀሳቀስ አየር ሊበተኑ እንደሚችሉ ተጠቁሟል)፤
- እንዲሁም ወዲያው ወዲያው መታጠብ፣ አካባቢን ማፅዳት፣ እና የመሳሰሉት ከዚህ ቀደም የተነገሩ የመከላከያ እርምጃዎችን በአግባቡ መከተል።
የኮቪድ-19 ኮሮናቫይረስ የሚተላለፍባቸውን መንገዶች እና ሌሎች መሠረታዊ መረጃዎችን ከዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ድረ-ገጽ በቀጥታ ወደ አማርኛ የተረጎምናቸውን “ጥያቄ እና መልሶች” በዚህ ማስፈንጠሪያ ማግኘት ይቻላል፦ https://ankuar.com/covid19-amharic/
በእነዚህ መረጃዎች ላይ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ማሻሻያ እንዳደረገ፣ እኛም የአማርኛ ትርጉሞቹን እናሻሽላለን።
በማውራት ወይም በትንፋሽ መተላለፉን በተመለከተ፣ የበለጠ መረጃ ለማግኘት የሚከተሉትን ትንታኔዎች መመልከት ይቻላል፦
https://edition.cnn.com/2020/04/02/health/aerosol-coronavirus-spread-white-house-letter/index.html
#ኮቪድ19 #ኢትዮጵያ #COVID19 #Ethiopia
—–
ለተጨማሪ መረጃ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796 ወይም በኢሜል አድራሻችን [email protected] በመጠቀም ማግኘት ይቻላል።
—–
የምስሉ ምንጭ፡ isglobal.org