ስለኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ወረርሽኝ ጠቃሚ መረጃዎች
ኮሮናቫይረስን በሚመለከት ተደጋግመው የተነሱ
ጥያቄዎች እና መልሶቻቸው - WHO Q&A on coronaviruses (COVID-19)
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በቅርቡ በዓለም ላይ ስለተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ኮቪድ-19 (COVID-19) ወረርሽኝ በጥያቄ እና መልስ በድረ-ገጹ ያሰፈራቸውን ጠቃሚ መረጃዎች በአማርኛ ተርጉመን ከዚህ በታች አቅርበናቸዋል።
እንግሊዝኛውን ለመመልከት ይህንን ይጫኑ።
ኮሮናቫይረሶች በእንሰሳት እና በሰዎች ላይ ህመም ሊያስከትሉ የሚችሉ በሰፊ የቫይረሶች ቤተሰብ ስር የሚካተቱ ቫይረሶች ናቸው። የተለያዩ ኮሮናቫይረሶች ከመደበኛው ጉንፋን አንስቶ እስከ የከፋ በሽታ የሚደርሱ የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽኖችን በሰዎች ላይ በማስከተል ይታወቃሉ። ለምሳሌ ሚድል ኢስት ሪስፓይራቶሪ ሲንድረም – “መርስ” (Middle East Respiratory Syndrome – MERS) እና ሲቪየር አኪዩት ሪስፓይራቶሪ ሲንድረም – “ሳርስ” (Severe Acute Respiratory Syndrome – SARS) ይገኙበታል። በቅርቡ የተደረሰበት የኮሮናቫይረስ ዓይነት፤ ኮቪድ-19 (COVID-19) ለተባለው የኮሮናቫይረስ በሽታ ምክንያት ነው።
ኮቪድ-19 በቅርቡ በተደረሰበት የኮሮናቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት ተላላፊ በሽታ ነው። ይህ ቫይረስ እና በሽታ በቻይና ዉሃን ግዛት በታህሳስ 2012 ከመንሰራፋቱ አስቀድሞ አይታወቁም ነበር።
በይበልጥ የተለመዱት የኮቪድ-19 ምልክቶች ትኩሳት፣ መደካከም፣ እና ደረቅ ሳል ናቸወ። አንዳንድ ህሙማን ራስ-ምታት (aches) እና ህመሞች (pains)፣ የአፍንጫ መታፈን፣ የአፍንጫ ፈሳሽ መብዛት፣ የጉሮሮ መኮርኮር ወይም ተቅማጥ ሊገጥማቸው ይችላል። ብዙን ጊዜ እነዚህ ምልክቶች አነስተኛ ሲሆኑ የሚጀምሩትም ቀስ በቀስ ነው ። አንዳንድ ሰዎች ቫይረሱ ቢኖርባቸውም፣ ምንም ዓይነት የህመም ምልክቶችን ላያሳዩና ላይታመሙ ይችላሉ። በቫይረሱ የተያዙ አብዛኛዎቹ ሰዎች (80 በመቶ አካባቢ የሚሆኑት) የተለየ ህክምና ሳያስፈልጋቸው ከበሽታው ያገግማሉ። በኮቪድ ከተያዙ ስድስት ሰዎች መካከል አንዱ ለከፍተኛ ህመም ይዳረጋል፤ የመተንፈስ ችግርም ይገጥመዋል። እድሜያቸው የገፋ፣ እንዲሁም እንደ የደም ግፊት፣ የልብ ችግር ወይም ስኳር ዓይነት በሽታዎች ያለባቸው ሰዎች፣ ለከፍተኛ ህመም የመዳረጋቸው ዕድል ከፍተኛ ነው። ትኩሳት፣ ሳል እና የመተንፈስ እክል የገጠማቸው ሰዎች፣ ሕክምና ሊያገኙ ይገባል።
ሰዎች ኮቪድ-19 ቫይረሱ ካለባቸው ከሌሎች ሰዎች ሊይዛቸው ይችላል። ኮቪድ-19 ያለበት ሰው በሚያስል ወይም ወደውጭ በሚተነፍስ ጊዜ ከአፍንጫው ወይም ከአፉ በሚበተኑ ትናንሽ የፈሳሽ ጠብታዎች አማካኝነት በሽታው ከሰው ወደ ሰው ሊሰራጭ ይችላል። እነዚህ ጠብታዎች በግለሰቡ አካባቢ በሚገኙ ቁሳቁሶች እና ማንኛውም ነገሮች ላይ ሊያርፉ ይችላሉ። ሰዎች እነዚህን ቁሳቁሶች እና እቃዎች በነካ እጃቸው ዓይናቸውን፣ አፍንጫቸውን ወይም አፋቸውን ቢሚነኩ ጊዜ ኮቪድ-19 ሊይዛቸው ይችላል። ሰዎች ኮቪድ-19 ያለበት ሰው ሲያስል እና ወደውጭ ሲተነፍስ የሚበተኑትን ጥቃቅን ጠብታዎች ወደውስጥ በቀጥታ በመተንፈስም በኮቪድ-19 ሊያዙ ይችላሉ። ለዚህም ነው፤ ከታመመ ሰው ከ1 ሜትር በላይ መራቅ አስፈላጊ የሚሆነው።
የዓለም የጤና ድርጀት (WHO) ኮቪድ-19 የሚሰራጭባቸውን መንገዶች በተመለከተ እየተካሄዱ የሚገኙ ምርምሮችን እየተከታተለ ሲሆን፣ ወቅታዊ ግኝቶችን ይፋ ማድረጉን ይቀጥላል።
_________________
ኮቪድ-19ን የሚያስከትለው ቫይረስ በአየር አማካኝነት ሊተላለፍ ይችላል?
እስከዛሬ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፣ ኮቪድ-19 በዋነኝነት እየተላለፈ የሚገኘው ከአየር ይልቅ ከመተንፈሻ አካላት በሚወጡ ጠብታዎች ጋር በሚደረግ ንክኪ ነው። ከላይ “ኮቪድ-19 እንዴት ይሰራጫል?” በሚለው ጥያቄ ስር የቀረበውን መልስ ይመልከቱ።
_________________
ኮቪድ-19 ምንም ዓይነት የህመም ምልክቶችን ከማይታዩበት ሰው ሊተላለፍ ይችላል?
በሽታው በዋነኝነት የሚሰራጭበት መንገድ አንድ ሰው በሚያስል ጊዜ ከመተንፈሻ አካላት በሚወጡ ጠብታዎች አማካኝነት ነው። ምንም ዓይነት ምልክት ከማይታይበት ሰው ኮቪድ-19ን የማስተላለፉ ስጋት በጣም አናሳ ነው። ሆኖም ኮቪድ-19 ያለባቸው ብዙ ሰዎች አነስተኛ ምልክቶች ብቻ ሊገጥሟቸው ይችላሉ። ይህም በተለይ የበሽታው የመጀመሪያ ደረጃዎች ላይ ትክክል ነው። ስለዚህም ኮቪድ-19 ለምሳሌ አነስተኛ ሳል ካለበት እና ምንም ህመም ከማይሰማው ሰው ሊተላለፍ የሚችልበት እድል አለ ማለት ነው። የዓለም ጤና ድርጀት (WHO) የኮቪድ-19 ከሰው ወደ ሰው መተላለፊያ ጊዜ በተመለከት እየተካሄዱ የሚገኙ ምርምሮችን እየተከታተለ ሲሆን፣ ወቅታዊ ግኝቶችን ይፋ ማድረጉን ይቀጥላል።
_________________
ኮቪድ-19 በበሽታው ከተያዘ ሰው ዓይነ-ምድር ሊይዘኝ ይችላል?
ኮቪድ-19 ቫይረሱ ካለበት ሰው ዓይነ-ምድር የመተላለፉ ስጋት አነስተኛ ይመስላል። ቀዳሚ ምርመራዎች ቫይረሱ በአንዳንድ ኬዞች ላይ ዓይነ-ምድር ውስጥ ሊገኝ እንደሚችል ቢጠቁሙም፣ የዚህ ዓይነቱ ሥርጭት የወረርሽኙ ዋነኛ መገለጫ አይደለም። የዓለም የጤና ድርጀት (WHO) ኮቪድ-19 የሚሰራጭባቸውን መንገዶች በተመለከት እየተካሄዱ የሚገኙ ምርምሮችን እየተከታተለ ሲሆን፣ ወቅታዊ ግኝቶችን ይፋ ማድረጉን ይቀጥላል። ሆኖም ይህ አንድ ስጋት እንደመሆኑ መጠን፣ መፀዳጃ ቤቶችን ተጠቅመን ስናበቃ እና ከመመገባችን በፊት እጆቻችንን በመደበኛነት ለማፅዳት ሌላው ምክንያት ነው።
በሁሉም ሰው መተግበር የሚገባቸው የመከላከያ እርምጃዎች
በዓለም የጤና ድርጀት (WHO) ድረ-ገጽ እና በሀገር-አቀፍ እና አካባቢያዊ የጤና ተቋማት አማካኝነት የሚተላለፉ ኮቪድ-19 ወረርሽኝን የሚመለከቱ ወቅታዊ መረጃዎችን በንቃት ይከታተሉ። ብዙ ሀገራት የተረጋገጡ ኬዞች ተገኝተውባቸዋል፣ አያሌ ወረርሽኞችን ተከስተውባቸዋል። በቻይና እና በተወሰኑ ሌሎች ሀገራት ወረርሽኙን በማስቆም ወይም የስርጭት ፍጥነቱን በማቀዝቀዝ ረገድ ተሳክቶላቸዋል። ነገር ግን ሁኔታው የማይገመት በመሆኑ፣ አዳዲስ /ወቅታዊ ዜናዎችን በመደበኛነት ይከታተሉ።
የተወሰኑ ቀላል ቅድመ-ጥንቃቄዎችን በማድረግ በኮቪድ-19 የመያዝ ዕድል ወይም የበሽታውን ስርጭት መቀነስ ይችላለሁ፤
- በየጊዜው እና በደንብ አድርገው እጅዎቾን በአልኮሆል-ነክ የእጅ ማፅጃ ያፅዱ ወይም በውሃ እና በሳሙና ይታጠቡ።
ለምን? እጅዎቾን በሳሙና እና ውሃ መታጠብ ወይም በአልኮሆል-ነክ የእጅ ማፅጃ ማፅዳት፣ እጅዎቾ ላይ ሊኖሩ የሚችሉ ቫይረሶችን ይገድላል። - ከሚያስል ወይም ከሚያስነጥስ ማንኛውም ሰው ርቀትዎን ቢያንስ በ1 ሜትር ይጠብቁ።
ለምን? አንድ ሰው ሲያስል ወይም ሲያስነጥስ ቫይረስ ሊኖርባቸው የሚችሉ ትናንስ ፈሳሽ ጠብታዎችን ከአንፍጫው ወይም ከአፉ ይረጫል። በጣም በቅርበት ከተገኙ፣ ጠብታዎቹን እንዲሁም የሚስለው ሰው በሽታው ካለበት የኮቪድ-19 ቫይረስን ወደወስጥ ሊተነፍሱት (ሊያስገቡት) ይችላሉ። - ዓይኖችን፣ አፍንጫ እና አፍን ከመንካት ይቆጠቡ።
ለምን? እጆች ብዙ ነገሮችን ይነካሉ ወይም ይዳስሳሉ፣ እንዲሁም ቫይረሶችን ሊይዙ ይችላሉ። ከቫይረሱ ጋር ንክኪ ካደረጉ፣ እጆች ቫይረሱን ወደ ዓይኖች፣ አፍንጫ እና አፍ ሊያጓጉዙ ይችላሉ። ከዚያ በኋላ ቫይረሱ ሰውነት ገብቶ ህመም ሊያሳድርብዎት ይችላል። - እርስዎ እና በአካባቢዎ ያሉ ሰዎች ጥሩ የአተነፋፈስ ንጽህና መጠበቃችሁን ያረጋግጡ። ይህም ማለት፣ በሚያስሉ ወይም በሚያስነጥሱ ጊዜ አፍ እና አፍንጫዎትን ክንድዎትን በማጠፍ ወይም በሶፍት ይሸፍኑ። ከዚያም የተጠቀሙበትን ሶፍት በአፋጣኝ ያስወግዱ።
ለምን? ጠብታዎች ቫይረስ ያሰራጫሉ። ጥሩ የአተነፋፈስ የጽዳት አጠባበቅ በመከተል፣ በአካባቢዎ ያሉ ሰዎችን እንደ ጉንፋን፣ ፍሉ እና ኮቪድ-19 ካሉ ቫይረሶች ይከላከሉ፡፡ - ጤንነት የማይሰማዎት ከሆነ ከቤትዎ አይውጡ። ትኩሳት፣ ሳል፣ እና የመተንፈስ እክል ካጋጠመዎት፣ ሕክምና የሚያገኙበትን መንገድ ይፈልጉ፣ አስቀድመው ይደውሉ። በአካባቢዎ ያለው የጤና ተቋም የሚሰጣቸውን መመሪያዎች ይከተሉ።
ለምን? ሀገር-አቀፍ እና አካባቢያዊ የጤና ተቋማት በአካባቢው ስለሚገኘው ሁኔታ ከማንም የተሻለ ወቅታዊ መረጃ ይኖራቸዋል። አስቀድሞ መደወል የጤና ተቋሙ ወደ ትክክለኛው የጤና አገልግሎት መስጫ በአፋጣኝ እንዲመራዎት ያስችለዋል። በተጨማሪም ይህን ማድረግዎ እርስዎንም ይጠብቃል፣ የቫይረሶችን እና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ስርጭት ለመከላከል ይረዳል። - ኮቪድ-19 በስፋት እየተሰራጨባቸው ስለሚገኙ ከተሞች ወይም አካባቢዎች ወቅታዊ መረጃ ይኑርዎት። ከተቻለ ወደ ሌላ ቦታ አይሂዱ – በተለይም እድሜዎት የገፋ ከሆነ ወይም የስኳር፣ የልብ ወይም የሳምባ በሽታዎች ካሉብዎት።
ለምን? በእነዚህ በአንዳቸው ቦታዎች በኮቪድ-19 የመያዝ ዕድልዎ ከፍተኛ ነው።
ኮቪድ-19 በተሰራጨባቸው አካባቢዎች (ባለፉት 14 ቀናት ውስጥ) ተገኝትው የነበሩ ሰዎች ሊወስዱ የሚገቧቸው የመከላከያ እርምጃዎች
- ከላይ ለማንኛውም ሰው የመከላከያ መመሪያዎች ተብሎ የተዘረዘረውን ይከተሉ።
- ጤነኝነት አለመሰማት ከጀመርዎት፣ እንደ ራስ-ምታት፣ ዝቅተኛ ትኩሳት (37.3 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ወይም ከዚያ በላይ) እና የአፍንጫ ፈሳሽ መብዛት ያሉ አነስተኛ ምልክቶችም ከታየብዎት፣ እስኪያገግሙ ድረስ በቤትዎ እራስዎትን ያግልሉ። አንዳንድ ቁሳቁሶችን ሰው እንዲያቀርብልዎት ወይም እራስዎት ወጥተው ለምሳሌ ምግብ መግዛት የግድ በሚሆንበት ጊዜ፣ ሌሎች ሰዎችን እንዳያስይዙ የመተንፈሻ ጭንብል (ማስክ) ያጥልቁ።
ለምን? ከሌሎች ጋር ያልዎትን ንክኪ ማስቀረት እና ወደ ሕክምና ተቋማት ከመሄድ መቆጠብ፣ ተቋማቱ ሥራቸውን በውጤታማ መልኩ እንዲያከናውኑና እርስዎን እና ሌሎችን ከኮቪድ-19ም ሆን ከሌሎች ቫይረሶች እንዲከላከሉ ያግዛቸዋል። - ትኩሳት፣ ሳል እና የመተንፈስ እክል ካስከተለብዎ፣ ይህ ከመተንፈሻ አካላት በሽታ ወይም ከሌላ አደገኛ የጤና መታወክ የተነሳ ሊሆን ስለሚችል በአፋጣኝ የሕክምና ምክር ያግኙ። አስቀድመው ይደውሉ፣ እንዲሁም ለጤና ተቋሙ በቅርቡ ያደረጉትን ማንኛውንም ጉዞ ወይም በጉዞዎት የነበርዎትን ንክኪ ይግለፁ።
ለምን? አስቀድሞ መደወል የጤና ተቋሙ ወደ ትክክለኛው የጤና አገልግሎት መስጫ በአፋጣኝ እንዲመራዎ ያስችለዋል። በተጨማሪም ይህን ማድረግዎ የኮቪድ-19 እና የሌሎች ቫይረሶች የመሰራጨት እድልን ለመከላከል ያግዛል።
የመያዝ እድልዎ እርስዎ በሚገኙበት ቦታ ይወሰናል፤ በይበልጥ ደግሞ እርስዎ በሚገኙበት ቦታ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እየተስፋፋ በመሆኑ ላይ ይወሰናል።
ብዙ ቦታዎች ለሚገኙ ሰዎች በኮቪድ-19 የመያዝ የአደጋ ስጋቱ እስካሁን ዝቅተኛ ነው። ሆኖም በአሁኑ ሰዓት በዓለም ዙሪያ በሽታው እየተስፋፋባቸው የሚገኙ ቦታዎች (ከተሞች እና አካባቢዎች) ይገኛሉ። በእነዚህ ቦታዎች ነዋሪ ለሆኑ ወይም በቦታዎቹ ለሚገኙ ሰዎች፣ በኮቪድ-19 የመያዙ አደጋ ከፍተኛ ነው። መንግሥታት እና የጤና ባለሥልጣናት አዲስ የኮቪድ-19 ኬዝ በተገኘ ቁጥር የተጠናከረ እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ። በየአካባቢው በጉዞ፣ በእንቅስቃሴ ወይም በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የሚጣሉ ገደቦችን ተግባራዊ ማድረግዎን አይዘንጉ። በሽታውን ለመከላከል ለሚደረጉ ጥረቶች ተባባሪ መሆንዎ በኮቪድ-19 የመያዝ ወይም የማሰራጨት አደጋን ይቀንሳል።
በቻይና እና በሌሎች ሀገራት እንደታየው የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ማቀብ እና ስርጭቱን ማስቆም ይቻላል። ይሁንና አዳዲስ ወረርሽኞች በፍጥነት ሊነሱ ይችላሉ። ስለሚገኙበት ወይም ሊሄዱ ስላቀዱበት ቦታ ሁኔታ በቂ ግንዛቤ ሊኖርዎት ይገባል። የዓለም ጤና ድርጀት በዓለም ዙሪያ ስላለው የኮቪድ-19 ሁኔታ በየቀኑ ወቅታዊ መረጃዎችን ይፋ ያደርጋል። ይህንን ማስፈንጠሪያ መመልከት ይችላሉ ::
የኮቪድ-19 በሽታ የሚያስከትለው ህመም በአብዛኛው ቀለል ያለ ነው፣ በተለይም በሕፃናት እና ወጣት-ጎልማሶች ላይ። ነገር ግን ከፍተኛ ህመም ሊያስከትልም ይችላል፤ ቫይረሱ ከያዛቸው ከ5 ሰዎች ውስጥ ቢያንስ 1 ሰው የሆስፒታል እንክብካቤ ያስፈልገዋል። ስለሆነም ሰዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዴት እራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ሊያጠቃቸው እንደሚችል መጨነቃቸው መደበኛ ነው።
ስጋቶቻችንን እራሳችንን፣ ቤተሰቦቻችንን እና ማኅበረሰባችንን ለመጥበቅ ወደሚያስችሉ ተግባራት መቀየር እንችላለን። ከእነዚህ ተግባራት መካከል፣ ከሁሉም ቀዳሚው እጆቻችንን በመደበኛነት እና በደንብ መታጠብ እና ጥሩ የአተነፋፈስ ጤና አጠባበቅን መተግበር ነው። ሁለተኛ፣ በቂ እና ትክክለኛ መረጃ ይኑርዎት፡፡ በጉዞ፣ በእንቅስቃሴ እና በስብሰባዎች ላይ ስለሚደረጉ ማንኛውም ገደቦች ጨምሮ ከአካባቢዎ የጤና ባለሥልጣናት የሚሰጡትን ምክሮች ወይም መመሪያዎች ይከታተሉ።
እራስዎን እንዴት መከላከለ እንዳለብዎ ተጨማሪ መረጃ እዚህ ያግኙ::
ኮቪድ-19 ሰዎችን እንዴት ሊጎዳ እንደሚችል ገና እየተማርን ቢሆንም፣ በእድሜ የገፉ እና ከዚህ ቀደም የሕክምና ችግሮች (እንደ ከፍተኛ ደም ግፊት፣ የልብ በሽታ፣ የሳንባ በሽታ፣ ካንሰር ወይም ስኳር በሽታዎች) ያሉባቸው ሰዎች ከሌሎች ይልቅ በይበልጥ አደገኛ ህመም እንደገጠማቸው ታይቷል።
አይደሉም። አንቲባዮቲክስ (antibiotics) በባክቴሪያ ምክንያት ለሚከሰቱ በሽታዎች ብቻ እንጂ በቫይረሶች ላይ አይሰሩም፡፡ ኮቪድ-19 በቫይረስ ምክንያት የሚመጣ በሽታ ነው፤ ስለዚህ አንቲባዮቲክስ ውጤት የላቸውም። አንቲባዮቲክስ ኮቪድ-19ን ለመከላከልም ሆነ ለማከም ጥቅም ላይ ሊውሉ አይገባም። ጥቅም ላይ መዋል የሚገባቸው በሐኪም ትዕዛዝ በባክቴሪያ የሚመጡ በሽታዎችን ለማከም ብቻ ነው።
ከምዕራቡ ዓለም የተሰሩ፣ ባህላዊ ወይም በቤት ውስጥ የተሰሩ አንዳንድ ዘዴዎች ምቾት ሊሰጡ ወይም የኮቪድ-19 የህመም ምልክቶችን ሊቀንሱ ቢችሉም፣ አሁን ሥራ ላይ ያለ መድኃኒት በሽታውን መከላከል ወይም መፈወስ ስለመቻሉ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም። የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ኮቪድ-19ን ለመከላከል ወይም ለመፈወስ በሚል አንቲባዮቲክስ ጨምሮ ማንኛውንም መድኃኒቶች በመጠቀም የሚደረግ የራስ ሕክምናን አይመክርም። ይሁንና በአሁን ሰዓት የምዕራብ እና የባህል መድኃኒቶችን ጨምሮ የተለያዩ የሕክምና ሙከራዎች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ። የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የሕክምና ግኝቶች እንደተደረሱ ወቅታዊ መረጃዎችን ይፋ ማድረጉን ይቀጥላል።
እስካሁን የለም። እስከዛሬ ድረስ ኮቪድ-19ን ለመከላከል ወይም ለማከም የሚውል ምንም ዓይነት ክትባት እና የተለየ ፀረ-ቫይረስ (antiviral) መድኃኒት የለም። ሆኖም፣ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ህመሞችን ለማስታገስ የጤና እንክብካቤ ማግኘት ይኖርባቸዋል። በአደገኛ ህመም ላይ የሚገኙ ሰዎች በሆስፒታል ሕክምና ማግኘት አለባቸው። ሰዎች ጥሩ እንክብካቤ ካገኙ ያገግማሉ።
አንዳንድ ክትባቶች እና የመድኃኒት ሕክምናዎች በምርመራ ላይ ይገኛሉ። በክሊኒካዊ ሙከራ አማካኝነት እየተጣሩ ይገኛሉ። የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ኮቪድ-19ን የሚከላከሉ ወይም የሚያክሙ ክትባቶችን እና መድኃኒቶችን ለመስራት የሚደረጉ ጥረቶች እያቀናጀ ይገኛል።
እራስዎን እና ሌሎችን ከኮቪድ-19 ለመከላከል እጅግ ውጤታማዎቹ መንገዶች እጅዎትን ወዲያው ወዲያው ማፅዳት፣ ሲያስሉ በታጠፈ ክንድዎ ወይም በሶፍት መሸፈን፣ እና ከሚያስሉ ወይም ከሚያስነጥሱ ሰዎች እራስዎን ቢያንስ በ1 ሜትር ማራቅ ናቸው። (መሠረታዊ አዲሱን ኮሮናቫይረስ የመከላከያ መንገዶች ይመልከቱ።)
አይደለም። ኮቪድ-19ን የሚያስከትለው ቫይረስ እና እ.አ.አ በ2003 የተከሰተውን ሲቪየር አክዩት ሪስፓይራቶሪ ሲንድረም – ሳርስ (SARS) የሚያስከትለው ቫይረስ ከዘረ-መል አኳያ ዝምድና አላቸው፤ ነገር ግን የሚያስከትሏቸው በሽታዎች በጣም የተለያዩ ናቸው።
ሳርስ ከኮቪድ-19 ጋር ሲነፃፀር ይበልጥ ገዳይ ነገር ግን ተላላፊነቱ እጅግ ዝቅተኛ የሆነ ነው። እ.አ.አ ከ2003 በኋላ በየትኛውም የዓለም ክፍል ምንም ዓይነት የሳርስ ወረርሽኝ አልተከሰተም።
የኮቪድ-19 ምልክቶች ህመም (በተለይ ሳል) ካለብዎ ብቻ ወይም ኮቪድ-19 ሊኖርበት የሚችልን ሰው እየተንከባከቡ ከሆነ ብቻ ማስክ ያድርጉ። የሚወገዱ መተንፈሻ ጭንብሎች (ፌስ ማስክ) ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉት ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው። ካልታመሙ ወይም የታመመ ሰው እየተንከባከቡ ካልሆነ፣ የመተንፈሻ ጭንብል እያባከኑ ነው። በዓለማቀፍ ደረጃ የመተንፈሻ ጭንብል እጥረት አለ፤ ስለሆነም የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ሰዎች የመተንፈሻ ጭንብልን ለትክክለኛ ዓላማ ይጠቀሙ ዘንድ ያስገነዝባል።
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የአስፈላጊ ሀብቶች ያልተገባ ብክነትን እና የጭንብሎች አላግባብ አጠቃቀምን ለማስወገድ ምክንያታዊ የሕክምና ጭንብል አጠቃቀን ይመክራል (የጭንብል አጠቃቀም ምክሮችን እዚህ ይመልከቱ)።
ራስዎን እና ሌሎችን ከኮቪድ-19 ለመከላከል እጅግ ውጤታማዎቹ መንገዶች እጅዎትን ወዲያው ወዲያው ማፅዳት፣ ሲያስሉ በታጠፈ ክንድዎ ወይም በሶፍት መሸፈን፣ እና ከሚያስሉ ወይም ከሚያስነጥሱ ሰዎች እራስዎን ቢያንስ በ1 ሜትር ማራቅ ናቸው። (መሠረታዊ አዲሱን ኮሮናቫይረስ የመከላከያ መንገዶች ይመልከቱ።)
- ጭንብል በጤና አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞች፣ በተንከባካቢዎች እና እንደ ትኩሳት እና ሳል ያሉ የመተንፈሻ አካላት ህመም ምልክቶች በታዩባቸው ግለሰቦች ብቻ ጥቅም ላይ መዋል እንዳለባቸው ያስታውሱ።
- ጭንብሉን በእጅ ከመንካትዎ በፊት፣ እጅዎትን በአልኮሆል-ነክ የእጅ ማፅጃ ወይም በውሃ እና በሳሙና ያፅዱ።
- ጭንብሉን ያንሱና ያልተቀደደ ወይም ያልተቆረጠ መሆኑን ያረጋግጡ።
- የላይኛው የጭንብሉ አካል (ሽቦ ያለበት) የትኛው እንደሆነ ይመልከቱ።
- ትክክለኛው የጭንብሉ ገጽ (ቀለም ያለው) ወደውጭ ወይም ከእርሶ በተቃራኒ መሆኑን ያረጋግጡ።
- ጭንብሉን ፊትዎ ላይ ያድርጉ። የጭንብሉን የላይኛውን ጫፍ ወይም ሽቦውን ከአፍንጫዎ ቅርፅ ጋር እንዲስተካከል አድርገው በመጫን ያጣሙት።
- አፍዎን እና ጉንጮን እንዲሸፍነውም የጭንብሉን የታችኛው አካል ወደታች ይጎትቱት።
- ከተጠቀሙበት ብኋላ ጭንብሉን ያውልቁ፤ ከጆሮዎት ላይ ላስቲኩን ሲያላቅቁ የመበከል እድል ካላቸው የጭንብሉን አካላት ጋር ንክኪን ለማስወገድ ጭንብሉን ከፊትዎን እና ከልብስዎት ያርቁ።
- ከተጠቀሙበት በኋላ በዝግ የቆሻሻ መጣያ ውስጥ ያስወግዱት።
- ጭንብሉን ከነኩ ወይም ካስወገዱት በኋላ የእጅ ጽዳትዎን ይጠብቁ – አልኮሆል-ነክ የእጅ ማፅጃ ይጠቀሙ፣ ወይም በዓይን የሚታይ ቆሻሻ ካለብዎት በሳሙና እና በውሃ ይታጠቡ።
ኢንኩቤሽን ፔሬድ (incubation period) ማለት አንድ ሰው በቫይረሱ ከተያዘበት አንስቶ የበሽታውን ምልክቶች ማሳየት እስከሚጀምርበት ድረስ ያለው ጊዜ ነው። የኮቪድ-19 ኢንኩቤሽን ፔሬድ በአብዛኛው ከ1-14 ቀን ይገመታል፤ በአብዛኛው የተለመደው አምስት ቀናት አካባቢ ነው። እነዚህ ግምቶች ተጨማሪ የመረጃ ግብዓቶች እንደተገኙ ይሻሻላሉ፡፡
ኮሮናቫይረሶች በእንሰሳት ላይ የተለመዱ ሰፊ የቫይረሶች ቤተሰብ ናቸው። አልፎ አልፎ ሰዎች በእነዚህ ቫይረሶች ሊያዙ የሚችሉ ሲሆን ወደሌሎች ሰዎችም ሊያስተላልፏቸው ይችላሉ። ለምሳሌ ሳርስ-ኮቭ ከሲቪየት ድመቶች ተያያዥነት የነበረው ሲሆን መርስ-ኮቭ ደግሞ በድሮመዳሪ ግመሎች የሚተላለፍ ነው። የኮቪድ-19 አመንጪ ሊሆኑ የሚችሉ እንሰሳት የትኞቹ እንደሆኑ እስካሁን አልተረጋገጠም።
ወደ እንሰሳት ገበያ ከሄዱ፤ እራስዎን ለመጠበቅ ከእንሰሳት ጋር ወይም ከእንሰሳቱ ጋር ከተነካኩ ነገሮች ጋር ቀጥተኛ ንክኪን ያስወግዱ፡፡ ሁልጊዜም ደህንነታቸው የተጠበቀ ምግቦችን የመመገብ ልማድ ይኑርዎት። ያልበሰሉ ምግቦች ብክለትን ለማስወገድ ጥሬ ሥጋ፣ ወተት ወይም የስጋ ክፍሎች በጥንቃቄ ይያዙ/ያስቀምጡ፣ እንዲሁም ጥሬ ወይም በአግባቡ ያልበሰሉ የእንሰሳት ተዋፅዖዎችን ከመመገብ ይቆጠቡ።
በሆንግ ኮንግ አንድ ውሻ በቫይረሱ የተያዘ መሆኑ ቢታወቅም፤ እስካሁን ድረስ ውሻ፣ ድመት ወይም ማንኛውም የቤት እንሰሳ ኮቪድ-19ን ስለማስተላለፉ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም። ኮቪድ-19 በዋናነት የሚሰራጨው በቫይረሱ የተያዘ ሰው ሲያስል፣ ሲያስነጥስ፣ ወይም ሲያወራ በሚመነጩ ጠብታዎች አማካኝነት ነው። ራስዎን ለመጠበቅ እጅዎትን ወዲያው ወዲያው እና በደንብ ያፅዱ።
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በዚህ እና በሌሎች የኮቪድ-19 ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚካሄዱ ምርምሮችን መከታተሉን ይቀጥላል፤ ግኝቶች በተደረሱ ጊዜ በአፋጣኝ ይፋ ያደርጋል።
ኮቪድ-19ን የሚያስከትለው ቫይረስ በቁሶች ላይ ለምን ያህል ጊዜ መኖር እንደሚችል እርግጠኝነት የለም፤ ነገር ግን ባህሪው እንደሌሎቹ የኮሮና ቫይረሶች ይመስላል። ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ኮሮናቫይረሶች (እንዲሁም የኮቪድ-19 ቫይረስ ቅድመ-መረጃዎች እንደሚጠቁሙት) ከጥቂት ሰዓታት ጀምሮ እስከ ብዙ ቀናት በቁሶች ላይ ሊኖር ይችላል። ይህም በተለያዩ ሁናቴዎች ሊለዋወጥ ይችላል (ለምሳሌ በቁሱ ዓይነት፣ የአካባቢው ሙቀት ወይም እርጥበት)።
አንድ ቁስ ቫይረስ ይኖርበታል ብለው ካሰቡ፣ ቫይረሱን ለመግደል እና ራስዎን እና ሌሎችን ለመከላከል በቀላል የንፅህና መጠበቂያ ያፅዱት። እጅዎትን በአልኮሆል-ነክ የእጅ ማፅጃ ወይም በውሃ እና በሳሙና በመታጠብ ያፅዱ። ዓይንዎትን፣ አፍዎትን፣ ወይም አፍንጫዎትን ከመንካት ይቆጠቡ።
አዎ፣ የለውም። በቫይረሱ የተያዘ ሰው የንግድ እቃዎችን የመበከል እድሉ አናሳ ሲሆን፣ ከተንቀሳቀሰ፣ ከተጓጓዘ፣ እንዲሁም ለተለያዩ ሁኔታዎች እና የሙቀት ዓይነቶች ከተጋለጠ እቃ ላይ ኮቪድ-19ን በሚያስከትለው ቫይረስ የመያዙ አደጋም አናሳ ነው።
የሚከተሉት በኮቪድ-19 ላይ አይሰሩም፣ እንዲሁም ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ፡-
- ሲጋራ ማጬስ
- ጭንብሎችን ደራርቦ ማድረግ
- አንቲባዮቲኮችን መውሰድ (ከላይ “ኮቪድ-19ን መከላከል ወይም መፈወስ የሚችሉ መድኃኒቶች ወይም ህክምናዎች አሉ?” ለሚለው ጥያቄ የተሰጠውን መልስ ይመልከቱ)
ይበልጥ ከፍተኛ የሆነ ህመም የመከሰቱን አደጋ ለመቀነስ፣ በማንኛውም ሁኔታ ትኩሳት፣ ሳል እና የመተንፈስ ችግር ካለብዎት በአፋጣኝ የሕክምና እንክብካቤ ያግኙ፣ እንዲሁም የቅርብ ጊዜ የጉዞ ታሪክዎን ለጤና አገልግሎት ሰጪው መናገርዎን ያረጋግጡ።
ሳርስ-ኮቭ-2 (SARS-CoV-2) በመባል የሚጠራው፣ ኮቪድ-19ን የሚያስከትለው ኮሮናቫይረስ (CoV) ምንጩ በአሁን ሰዓት አይታወቅም። አሁን የሚገኙት ማስረጃዎች በሙሉ የሚጠቁሙት፣ ሳርስ-ኮቭ-2 ተፈጥሯዎ እንሰሳ ምንጭ እንዳለውና የተፈበረከ አለመሆኑን ነው። የሳርስ-ኮቭ-2 የስነ-ህይወት መንሰራፊያው ይሆናሉ ተብሎ በይበልጥ የሚገመቱት የሌሊት ወፎች ናቸው። ሳርስ-ኮቭ-2 የዘረ-መል ዝምድና ካላቸው የቫይረሶች ስብስብ ውስጥ ይመደባል፤ ይህ ስብስብ ከዓመታት በፊት ተከስቶ የነበረውን “ሳርስ-ኮቭ” እና ሌሎች ከሌሊት ወፎች ግንኙነት የሌላቸው የኮሮናቫይረስ ዓይነቶችንም ይጨምራል። መርስ-ኮቭ (MERS-CoV) የተባለውም ከዚህ ስብስብ ውስጥ ይመደባል፤ ነገር ግን ዝምድናው አነስተኛ ነው።
ኮቪድ-19 በሽታን የሚያስከትለው ቫይረስ በዋነኝነት የሚተላለፈው፣ በቫይረሱ የተያዘ ሰው ሲያስል፣ ሲያስነጥስ ወይም ሲያወራ በሚመነጩ ጠብታዎች አማካኝነት ነው። እነዚህ ጠብታዎች ክብደት ስላላቸው አየር ላይ ተንጠልጥሎ ለመቆየት አያስችላቸውም። ወዲያውኑ ወደ መሬት ወይም ወደሌላ ቁስ-አካሎች ላይ ይወደቃሉ።
ኮቪድ-19 ካለበት ሰው በ1 ሜትር ርቀት ውስጥ ከሆኑ ቫይረሱን ወደ ውስጥ ከተነፈሱት፣ ወይም በቫይረሱ የተበከሉ ቁስ-አካሎችን ነክትው ዓይኖትን፣ አፍንጫዎትን ወይም አፎትን መልሰው ከነኩ በቫይረሱ ሊያዙ ይችላሉ።
እነዚህን በኮሮና ቫይረስ እና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዙሪያ በተደጋጋሚ የሚነሱ ጥያቄዎች እና ምላሾቻቸውን በእንግሊዝኛ ያጠናቀረው የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ሲሆን፣ ወደ አማርኛ ተርጉሞ ያቀረበው አንኳር (ANKUAR.COM) ነው።
ለትርጉሙ እና ለትየባው፣ እንዲሁም ይዘቱ ላይ ግብዓት ላበረከቱ የአንኳር ተባባሪዎች ምስጋናችንን እያቀረብን፣ የዓለም ጤና ድርጅት የሚያደርጋቸውን ማሻሻያዎች እየተከታተልን ለማካተት እንሞክራለን።