የጀዋር “ፕሮግሬሲቭ ፓትሪዮቲዝም/Progressive Patriotism
በግዛው ለገሠ
ባለፈው ሰሞን የፖለቲካ ፆም ላይ ነኝ ብዬ አርፌ በተቀመጥኩበት፣ የጀዋር ስም ደጋግሞ ሲነሳ፣ ደግሞ ምን ጽፎ ነው ብዬ አነበብኩት።
በቀደም ጋበዘኝና አብረን አፈጠርን። ድንቅ እና ውድ ሰዎችንም በዚያ ምሽት በማግኘት ደስ ተሰኝቻለሁ – ልዩ ምሽት ነበር።
እናም፣ “በጽሁፍህ ወዲያም-ወዲህም ያለው ወገን አልተደሰተም” አልኩት። “እንደጠበኩት ነው” አለኝ። ጊዜ ካላችሁ ወይም አመቻችታችሁ አንብቡት – አንዳንድ ያነሳቸው ነጥቦች ቀጣይ ውይይቶችን የሚጋብዙ ናቸው።
ያም ሆነ ይህ፣ ስለጽሁፉ የተወሰኑ ነጥቦችን ለማንሳት እወዳለሁ።
1) በመጀመሪያ ደረጃ የጽሁፉ ዋነኛ “ታርጌት ኦዲየንስ” የኦሮሞ ኤሊት ወይም የፖለቲካ ተዋናይ ነው። በኦሮምኛ መፃፉ በራሱ ጠቋሚ ቢሆንም፣ እኔ ግን የኦሮሞ ሕዝብ ትግል አካሄድ የሚያሳስበው ሁሉ ሊያነበው ይገባል ብዬ አምናለሁ። ሌሎች በትችት እና በነቀፋ መልክ የሚያቀርቡትን ብቻ መከታተል ሙሉ ምስሉን ላይሰጥ ይችላል።
2) ጽሁፉ በዋነኛነት ቀጣዩን የኦሮሞ ትግል ምዕራፍ በተመለከተ ለመምከር የታለመ ነው። የኦሮሞ ትግል እስካሁን አራት ምዕራፎችን እንደተሻገር በዝርዝር ይተነትናል፣ እነዚህም የመነቃቃት፣ የመልሶ-ግንባታ፣ የግዛት ምስረታ፣ እና የሥልጣን መቆጣጠር ምዕራፎች ናቸው። እናም አሁን አራተኛው ምዕራፍ ላይ ይገኛል – የኦሮሞ ትግል ኦሮሞን የሥልጣን ባለቤት አድርጓል። ጀዋር በጽሁፉ ይህን በግልጽ ያስቀምጣል።
3) የኦሮሞ ትግል አምስተኛ ምዕራፍ እንደሚያስፈልገው የጀዋር ጽሁፍ ይተነትናል። ምክንያቱም አራተኛው የኦሮሞ ትግል ምዕራፍ ያስገኘው ሁናቴ የኦሮሞ ትግል ማዕከል እና ግብ ለሆነው የኦሮሞ ሕዝብም ሆነ የመላው የሀገሪቱ ሕዝብ ምቹ አይደለም። እንዲያውም በዚህ ከቀጠለ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው። ለምን እና በምን ምክንያቶች ምቹ እንዳልሆነ፣ እንዲሁም የሚያስከትለው ጉዳት በሰፊው ይተነትናል።
4) ሌላው ጎራ ‘ተረኝነት’ የሚለውን፣ ጀዋር የኦሮሞ ትግል ኦሮሞን ለሥልጣን እንዳበቃ በግልጽ ቢያስቀምጥም፣ ሁኔታው የኦሮሞን ሕዝብ እንዳልጠቀመና አካሄዱም እንደማይጠቅም የሚያስረዳው ከመነሻው በኦሮሞ ሕዝብ እና እስከዛሬ በነበሩት አገዛዞች (የመንግሥት ሥርዓቶች) መካከል የነበረውን እና ያለውን ግንኙነት ለይቶ በመተንተን ነው። አሁን ያለው የብልጽግና መንግሥት እንደ አንድ አገዛዝ በጽሁፉ ላይ ተተንትኗል – የኦሮሞ ሕዝብ ላይ እያደረሰው ያለው ጭቆናም ተገልጿል። ምሳሌ እያነሳሁ ተጽዕኖ እንዳላደርግባችሁ ብፈራም፣ አንድ ቦታ ላይ በብልጽግና ዘመን የሞተው የኦሮሞ ሕዝብ ቁጥር በአጼ ኃይለ ሥላሴ፣ በደርግ እና በኢሕአዴግ ዘመን ከሞተው እንደሚልቅ ይጠቅሳል።
5) የጽሁፉ ዋና ማጠንጠኛ እና ግብ የኦሮሞ ትግል ቢሆንም፣ ስለአጠቃላይ የሀገሪቱ እጣ-ፈንታ እና ሀገራዊ መፍትሄዎች የሚያነሳቸው ነጥቦች አሉ። ሆኖም በቂ እና ጥልቅ አይደሉም፣ ይህንንም ለጀዋር አንስቼለታለሁ (ሌላ ሰፊ ጽሁፍ በእንግሊዝኛ እየፃፈ መሆኑን በቀደም በነበረን ቆይታ ነግሮኛል)። የኦሮሞ ትግል ኦሮሞን ለሥልጣን በማብቃት ስኬታማ ቢሆንም፣ ስኬቱ ፋይዳ-ቢስ ሆኖ እዳይቀር፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር መከራዋ እንዲያበቃ የኦሮሞ ትግል ሌላ አምስተኛ ምዕራፍ ያስፈልገዋል። ይህም ‘ዲሞክራታይዜሽን’ ነው። ጀዋር ይህንን ቀጣይ ምዕራፍ እንዴት መካሄድ እንዳለበት ጽፏል። የተወሰኑት ነጥቦቹ የተተነተኑበት መንገድ የዳበረ አይደለም፣ የአንድ ወገን እይታ በዝቶባቸው ተመልክቻለሁ። ሰፊ ክርክር እና ውይይትም የሚጠይቁ ናቸው። እርሱም እንደመነሻ ያነሳቸውና ሌሎች ምልከታዎችንም እንደሚጠይቁ ገልፆልኛል።
6) ለአምስተኛው ‘ዲሞክራታይዜሽን’ ምዕራፍ ያስፈልጋሉ ያላቸው መፍትሔዎች እና እርምጃዎች አንዳንዶቹ ክፍተት ቢኖራቸውም፣ እንዲያውም አንዳንድ ቦታ ላይ እንደ ‘ዘ-ኤሌፋንት ኢን ዘ-ሩም’ የተዘነጉ ወይም ሆን ተብለው የታለፉ ጉዳዮች ቢኖሩም፣ እጅግ የመሰጠኝን አንድ ነጥብ እዚህ ላይ ልገልፀው ወድጃለሁ። የተለያዩ የፖለቲካ ተቃርኖዎች እና ትርክቶች አሉ። በብሔር ፖለቲካ አቀንቃኙ ጎራ እና ‘ኢትዮጵያኒዝም’ እየተባለ በሚጠራው ጎራ መካከል ያለውን ተቃርኖ ማስታረቅ ወይም ማጥበብ እንደሚያስፈልግ በጽሁፉ ተገልጿል። በዚህ ጉዳይ እኔም ደጋግሜ ጽፌያለሁ – መፍትሔ የየጎራውን ስጋት መቀነስ እንደሆነም በተለያየ ጊዜ አንስቼ ነበር። ጀዋርም አምኖበታል። ይህን ተቃርኖ ለማጥበብም ሆነ በአጠቃላይ አምስተኛውን ‘ዲሞክራታይዜሽን’ ምዕራፍ ለማካሄድ አንድ አዲስ አይዲዮሎጂ እንደሚያስፈልግ ይጠቅሳል። ይህም “Progressive Patriotism” ይሰኛል።
7) ጀዋር ለኢትዮጵያ ይጠቅማል ብሎ የጠቆመውን “ፕሮግሬሲቭ ፓትሪዮቲዝም” አይዲዮሎጂ ሲገልጽ፣ በቅድሚያ በውስጡ ያሉትን ሁለት እሳቤዎች ያብራራል። ፕሮግሬሲቪዝም፥ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች እንዲሁም የመብቶች ጥሰቶች በፖለቲካዊ እርምጃዎች አማካኝነት ሊፈቱ ያስፈልጋል የሚል እምነትን የያዘ እሳቤ መሆኑን፤ ፓትሪዮቲዝም ደግሞ ሀገር ወዳድነትን ያዘለ፣ ለሀገር ቀጣይነት መዋደቅን ያነገበ፣ እንዲሁም ከማንኛውም ጥቃት ሀገርን መጠበቅን ያለመ እሳቤ መሆኑን ይገልፃል። ከዚያም የሁለቱ እሳቤዎች ጥምረት የሆነው “ፕሮግሬሲቭ ፓትሪዮቲዝም” ማለት ሀገርን መውደድ፣ ለአንድነቷ እና ቀጣይነቷ መቆም፣ ነገር ግን በሕዝብዎቿ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች እና መገለሎች መፈጠራቸው ሳይካድ መቀረፍ እንደሚገባቸው ማመን መሆኑን ያስረዳል። “ፕሮግሬሲቭ ፓትሪዮቲዝም” ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ ለሀገር እና ለማኅበራዊ ፍትህ በአንድነት መቆም እንደሆነም ይገልፃል።
እንግዲህ ይህን ያህል ከወሰወስኳችሁ ይበቃኛል። አንብቡት።
የጀዋር መሐመድ «Boqonnaa Qabsoo Itti Aanu» ጽሁፍ አማርኛ እና እንግሊዝኛ ቅጂዎች።