Politicsአንኳሮችፖለቲካ/ፍልስፍና

“አብዮታዊ ለውጥ አውዳሚ ውጤት አለው”፣ ኤድመንድ በርክ (1729-97)

ኤድመንድ በርክ በዱብሊን፣ አየርላንድ ተወልዶ እ.አ.አ ከ1743 እስከ 1748 ድረስ በትሪኒቲ ኮሌጅ ተምሯል። ለሕግ ባለሙያነት ብቁ የሚያደርገውን የጥብቅና ፈቃድ ፈተና ለመውሰድ ዝግጅት ለማድረግ ወደ ለንደን ቢጓዝም በሐሳቡ አልፀናም፤ ይልቁንም ልክ እንደ ዴቪድ ሂዩም በሥነ-ጽሁፍ ሙያ ላይ አተኮረ። ከዘመኑ የሥነ-ጽሁፍ አንበሶች ጋር እራሱን አቆራኘ። በ1756 “A Vindication of Natural Society” የተሰኘውን ሽሙጣዊ መጽሐፉን አሳተመ። አስከትሎም በ1757 በውበት ፍልስፍና (aesthetics) ዙሪያ “A Philosophical Enquiry into the Origin of Our Ideals of the Sublime and Beautiful” የተሰኘ ሥራውን ሲያቀርብ በጊዜው ተደንቆለት ነበር።

በ1765 የሥነ-ፅሁፍ ሙያው ለፖለቲካ ሙያው መንገድ ሊከፍትለት ችሏል። ኤድመንድ በርክ ለሕግ አውጪ ፓርላማ /ሐውስ ኦፍ ኮመንስ/ ተመራጭ ለመሆን የበቃ ሲሆን፣ የሎርድ ሮኪንግሃም የግል ፀሐፊ ሆኖ ነበር። በአንድ ወቅት ለአጭር ጊዜ ወጥቶ ቢቆይም እስከ ህይወቱ መጨረሻ የፓርላማ አባል ነበር። በሎርድ ሮኪንግሃም አቅራቢያ የቆየ እንደመሆኑ፣ በንጉሥ ጆርጅ 3ኛ ዘውዳዊ ሥርዓት ፅንሰ-ሐሳብ ላይ “Thoughts on the Causes of the Present Discontents” በሚል ርዕስ ጠንካራ ትችቱን አስፍሯል። ከ1770 ጀምሮ እስከ የአሜሪካ አብዮት ድረስ በኒው ዮርክ ግዛት የለንደን ተወካይ ሆኖ አገልግሏል። በዚህ ቆይታው ባደረጋቸው ሁለት ንግግሮቹ (በአሜሪካ የግብር አጣጣል ላይ በ1774 እና ከቅኝ ግዛቶቹ ጋር ለሚደረግ ስምምነት ውሳኔዎችን አስመልክቶ በ1777) በአሜሪካ ቅኝ ግዛቶች በብሪቲሽ አግባብ-የለሽ አስተዳደር ላይ ብጥብጥ (አመፅ) እንዲቀሰቀስ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ይኸው ተመሳሳይ አግባብ-የለሽ አስተዳደር በኢስት ኢንዲያ ካምፓኒ እንቅስቃሴዎች ላይ የተቃውሞ ቅስቀሳ እንዲያካሄድ ያደረገው ሲሆን፣ በ1788 ዋረን ሔስቲንግስ ላይ ለደረሰው ኦፊሴላዊ ውንጀላ ከፍተኛ ድርሻ ነበረው።

እጅግ ታዋቂው የፖለቲካ ሥራው፣ በፈረንሳይ አብዮት ላይ ምልከታውን ያንፀባረቀበት፣ “Reflections on the Revolution in France” በ1790 ነበር የታተመው። ይህ መጽሐፉ እስካሁን ድረስ የቆመላቸውን መርሆዎች ክዷል ብለው በፈረጁት የፖለቲካ አጋሮቹ ቁጣ እንዲቀሰቀስበት አድርጓል። ሆኖም የፈረንሳይ አብዮትን የሚቃወምበትን አመለካከት የበለጠ ማዳበሩን በሌሎች ሥራዎቹም ቀጥሎበታል፡- “An Appeal from the New to the Old Whigs (1791)”፣ “Thoughts on French Affairs (1791)”፣ “Letters on a Regicide Peace (1796)” ተጠቃሾች ናቸው።

ኤድመንድ በርክን የዘመናዊው ወግ-አጥባቂነት (Modern Conservatism) መስራች አድርጎ መግለፅ የተለመደ ነው። የእርሱ እሳቤ ዋና ነጥብ ፖለቲካ ባለፈ ልምድ እና ተሞክሮ ላይ መሠረት ባላደረጉ መርሆዎች አማካኝነት ሊካሄድ ይችላል በሚለው አመለካከት አለማመኑ ነው። በዚህ እምነቱ ምክንያትም ነበር የፈረንሳይ አብዮተኞችን በዋነኝነት የተቸው። ሰብዓዊ ፍጡራን ህይወታቸውን የሚመሩባቸው አወቃቀሮች እነዚያ በረጅም ጊዜ ሙከራ እና ልምድ እንደሚሠሩ የታዩት (ውጤታማ የሆኑት) እንደሆኑ መከራከሪያውን ያስቀምጣል። የሰው ልጆች በተለዋዋጭ ሂደቶች ውስጥ ባለፉባቸው የዝግታ ሂደቶች ወቅት ነው አወቃቀሮቹ የፈለቁት። የእንግሊዝ የሕግ ሥርዓት (Common Law) ለመመስረቱ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች ለቀጣይ ጉዳዩች መወሰኛ ሕግ (Precedent) ለመሆናቸው ጠቀሜታ ምስጋና ይግባውና፣ ይህ የበርክ እሳቤ በተለይም ለብሪቲሽ ሕገ-መንግሥት እውነት ነው። ሆኖም ከእንግሊዝ ባሻገርም እንድ ጥቅላዊ ድምዳሜ ጭምር እውነትነት አለው። ከተመሠረተ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ማንኛውም ሥርዓት አሁንም ድረስ መኖር መቻሉ ብቻውን የዚያን ሥርዓት ትክክለኛነት የማረጋገጥ አዝማሚያ አለው።

ስለ ሕብረተሰብ የምናውቀው ነገር ሁሉ፣ እንዲሁም ማወቅ የሚያስፈልገን፣ ውስብስብ እና ሕብራዊ ባሕርይውን ነው። የሕብረተሰብን ምንጭ ወይም እንዴት ተመሠረተ የሚለውን ከማኅበራዊ ውል (Social Contract) ረገድ መመርመር ፋይዳ የለውም። ሕብረተሰብ አንድ የሆነ ትውልድ የፈጠረው፣ በውል (በኮንትራት) ወይም በፈቃደኝነት የተመሠረተ ማኅበር አይደለም። ይልቁንም በህይወት ባሉት፣ በሞቱት እና ገና በሚወለዱት መካከል ያለ ግዙፍ ታሪካዊ ሽርክና (ትስስር) ነው። እጅግ ውስብስብ የሆነውን ህይወት ማንኛውም ግለሰብ ወይም ቡድን ሊረዳው አይቻለውም፤ በማንኛውም በአንድ የትውልድ ጊዜ ውስጥም መረዳት አይቻልም።

ስለዚህም፣ በርክ የፈረንሳይ አብዮተኞች አድርገዋል ብሎ እንደሚያስበው፣ አንድን ሕብረተሰብ ለማውደምና ሌላ ሕብረተሰብ ከሌጣው (ከዜሮ ተነስቶ) ለመገንባት መሞከር ገደብ ያጣ ቂልነት ነው። ሰብዓዊ ማኅበርን ሊያስተዳድሩ የሚገባቸው እሴቶችም ቢሆኑ ወደ “rights of man” ዓይነት ያልተረጋገጡ ጥቅል ግንዛቤዎች እንዲያንሱ ማድረግ አይቻልም። ሰብዓዊ ፍጡራን ቅንጣተ-አካላት (atoms) ወይም ለብቻቸው ተለይተው የሚታዩ አይደሉም። የረጅም እና እጅግ ውስብስብ ታሪክ ውጤቶች ነን። እኛ የተፈጠርነው በባሕል (Culture) ሲሆን፣ የዚህ ባሕል አንድ ክፍል ነን። እኛን ከዚያ ባሕል ጋር ባለማዛመድ መመልከት፣ እንዲሁም ያለዚያ ባሕል ወይም በግላችን ያሉንን ፅንሰ-ሐሳባዊ መብቶች ለእኛ ማጎናፀፍ ትርጉም አይሰጥም። ምግባሮቻችን፣ ልማዶቻችን እና ሕጎቻችን (በርክ “Prejudice” በማለት የሚጠራው ነገሮችን የመተግበሪያ ጥቅል መንገድ) የዚያ ባሕል ክፍሎች ናቸው። በግምታዊ እና ባልተሞከሩ የፖለቲካ አስተምህሮዎች ስም እነሱን ጠራርጎ ማስወገድ፣ ሰብዓዊ ማኅበር ምንድነው የሚለውን ሐሳብ እራሱን ሰብዓዊ ማኅበርን እውን ካደረጉት ነገሮች ውጪ መገንዘብ ነው።

ስለዚህም አብዮታዊ ለውጥ ለተፈጥሮ አውዳሚ የሆነ ድርጊት ነው፡- ከሚታወቀው አደጋ ወደተንጣለለበት የማይታወቅ ሁኔታ የሚደረግ ዝላይ። ሽግግር ወይም ለውጥ መካሄድ አለበት የተባለ እንደሆነ፣ ቀስ በቀስና ሂደቱን በተከተለ አኳኋን ሊመጣ ይገባዋል። ግልፅ ላልሆነ አስተምህሮት ሳይሆን የለውጥ ፍላጎቶች እና ሁኔታዎች ለመቀስቀሳቸው ምላሽ ሆኖ መከሰት አለበት። በአንድ ተለይቶ በሚታወቅ ችግር ላይ ያነጣጠረ መሆን አለበት። ለዚያ ችግር መፍትሔ ከመሆን የዘለለ ጥቅል ዓላማ ሊኖረው አይገባም። ቀድሞውኑ የነበሩ ሕብራዊ (harmonious) ግንኙነቶችን መጠበቅ አለበት፤ ሁሌም ቢሆን ነገሮችን እንደነበሩ የመተው ቅድመ-ግምት ሊኖር ይገባል። በዚህም የተነሳ፣ ምንም እንኳን የኃይማኖት መቻቻልን የሚደግፍ ቢሆንም፣ በርክ ቋሚ መሠረት ያላት ቤተ-ክርስቲያን መኖርን ይደግፋል። በተጨማሪም እርሱ የላይኛው መደብ የሕብረተሰብ ክፍል አባል ባይሆንም፣ በእርሱ ግንዛቤ የሕብረተሰብን ውስብስብ አወቃቀር እንደነበረ ለማቆየት መሬት ላይ መሠረት ያደረገ አሪስቶክራሲ፣ ማለትም ሐብት ያለው፣ ጊዜ የሞላለት፣ እንዲሁም ውስብስብ ነገሮችን ተመልክቶ ምለሽ የመስጠት አቅም ያለው አሪስቶክራሲ አስፈላጊ እንደሆነ ያምናል።

በሌላ በኩል ፓርላማውም የተለያየ ፍላጎቶችን የሚያራምዱ ቡድኖችን ከማቀፍ እና ከመከፋፈል፣ እንዲሁም ከተለዋዋጭ አስተያየት እራሱን ማላቀቅ ይኖርበታል። “Address to the Electors of Brisitol” ተብሎ በሚታወቀው፣ በብሪስቶል ከተማ ለሚገኙ መራጮች ባደረገው ንግግሩ፣ የፓርላማ አባላት ሥራቸው ለመጡበት አካባቢ ጥቅም ብቻ ቅስቀሳ /ውትወታ/ ማድረግ እንዳልሆነ አስረድቷል። ይልቁንም የማኅበረሰቡን አጠቃላይና የረጅም ጊዜ መልካም ግብ ለማረጋገጥ ወደፓርላማ የመጡ ተወካዮች ናቸው። የፖለቲካ ፓርቲዎችን መኖር ያበረታታል፤ ነገር ግን እነዚህ ፓርቲዎች ትክክለኛ ከሆነ አዕምሮ በሚፈልቁ አስተያየቶች ላይ ለመስማማትና አስተያየቶቹን ለማፅደቅ የሚውሉ መሣሪያዎች እስከሆኑ ድረስ ብቻ ነው።

በርክ ከአብዛኛዎቹ ወግ-አጥባቂዎች በተቃራኒው፣ የፖለቲካ ትንታኔውን በንግርታዊ (mythical) የመንግሥት ሥርዓት ተምሳሌት ላይ ወይም የፖለቲካ ዓላማ እርሱን ማወደስ ወይም መልሶ ማምጣት መሆን አለበት በሚባለው የወርቃማው ዘመን (Golden Age) ንግርት ላይ መሠረት ማድረግ አይፈልግም። የነገሮች ታሪካዊ ምንጭ /መነሻ/ ተመልሶ የማይገኝ እንደሆነ ይረዳል። በመሠረታዊ ደረጃ፣ የእርሱ ወግ-አጥባቂነት ጥቂት ጥቅላዊነቶችን ያካትታል፡- የነገሮች አሁን ያሉበት ሁኔታ የሁሉም ያለፉ ጉልብትናዎች ጠቅላላ ድምር መሆኑ፤ ይህንንም ለመረዳት እጅግ ውስብስብ መሆኑ፤ ስለዚህም በዚህ ሁኔታ ላይ ጣልቃ መግባት አደገኛ እንደሆነ፤ እንዲሁም በጥሩ ሁኔታ እየሰሩ የሚገኙ አወቃቀሮችን እንዳሉ መተዉ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ያምናል።

በርክ፣ የ1688 የእንግሊዝን አብዮት /ግሎሪየስ ሪቮሊዩሽን/ በጭብጨባ መደገፉና በአሜሪካ ቅኝ ግዛቶቹ በንጉሥ ጆርጅ 3ኛ ላይ የነበራቸውን ተቃውሞ መደገፉ፣ እንደገና ደግሞ በ1790 የፈረንሳይ አብዮተኞችን በመኮነኑ ተግባር ላይ በስፋት መሳተፉ ግራ የሚያጋባ ይመስላል፤ ሆኖም ይህ በግልፅ የሚታየው ወጥነት ማጣት የእርሱን ወግ-አጥባቂነት ባሕሪይ ያብራራዋል። የእንግሊዝ አብዮት ንጉሥን በማስወገድ ሂደት ውስጥ እንኳን የመንግሥትን ዘ-ልማዳዊ /traditional/ ተቋማት ሳይነካ ትቷቸዋል። አሜሪካኖቹም የደገፉት የእንግሊዞቹን ሳይወከሉ ግብር ያለመክፈል ዘ-ልማዳዊ መብት ነበር። በአንፃሩ ፈረንሳዮቹ ግን ታሪካዊነት ለሌለውና አግባብ የለሽ ለሆነው “rights of man” ለተሰኘ መርሆ ሲሉ ዘመናት ያስቆጠረውን ሥርዓት ነበር እያስወገዱ የነበሩት።

በርክ፣ በከፍተኛ መጠን ለነገሮች ስሜታዊ (Sentimental) ነው። እናም ይህ ስሜታዊነቱ ጣሪያ በነካ ጊዜ እጅግ አድሃሪ ወይም የፖለቲካ ለውጥን በፅኑ የሚቃወም (Reactionary) ነው። የፈረንሳይ አብዮተኞች እርምጃቸው በኢ-ፍትሃዊነት ላይ ስለመሆኑ ያለቸው እምነት እስከማይዋጥለት ድረስ የፈረንሳይ አብዮት ባደረሰው ውድመት እጅግ ይበሳጫል። ቶማስ ፔይን “The Rights of Man” በተሰኘ ሥራው ይህንን ስለ በርክ ፅፏል፡-

“በእውን ያለ ልቡን የሚነካ ሐዘን አያስገርመውም፣ በምናቡ የሚቀረፀው አንጸባራቂ ተመሳሳዩ እንጂ። በላባው እጣፈንታ ያዝናል፣ እየሞተች ያለችውን እርግብ ግን አይመለከትም።”

በእርሱ ዘመን የነበሩ የተወሰኑ ፀሐፊዎች ወጥ እንዳልሆነ ወይም የሚጋጩ ሐሳቦች እንዳሉትና የሚታመን እንዳልሆነ አድርገው ያስቡታል። በርግጥም በእንግሊዝ ፓርላመንታዊ ያልሆነ፣ ብቁነት የጎደለውና ግትር የሆነ መንግሥት እንዲመሠረት አይፈልግም፤ ይሁንና በፈረንሳይ ልክ እንደዚህ ዓይነቱ መንግሥት መወገዱን አስመልክቶ ተቃውሞውን ያንፀባርቃል። በዚህ አቋሙ ሜሪ ዎልስቶንክራፍት /1759-97/፣ ፈረንሳይያዊ ቢሆን ኖሮ በርክ እራሱ አብዮተኛ በሆነ ነበር ብላ ለማመን ተገዳለች። የሆነ ሆኖ ካልተሞከረ ፅንሰ-ሐሳብ ይልቅ መሠረት የተጣለበት አሰራርን ወይም ተሞክሮን የመምረጡ ውሳኔው፣ ለአካባቢያዊ እና ለብሔራዊ ባሕሎች የሚያስቀምጠው መከራከሪያው፣ እንዲሁም ጥንቃቄ ስለተሞላባቸው እና ስለ ለዘብተኛ ለውጦች ወይም ሽግግሮች የሚከራከርበት ነጥብ እርሱ ከሞተ ከሁለት ክፍለ ዘመን በላይ በኋላም ወሳኝ የወግ-አጥባቂነት አላባዊያን እንደሆኑ ቆይተዋል። በ20ኛው ክፍለ ዘመን የፖለቲካ እሳቤ ላይ ተፅዕኖ ያሳደሩ፣ እንደ ካርል ፖፐር፣ ማይክል ኦውክሾት እና ፍሬድሪክ ሃይክ ያሉት ሁሉ በተወሰነ መጠን በኤድመንድ በርክ ተፅዕኖ ስር ናቸው።

ለበለጠ ንባብ

ቀዳሚ ምንጮች

Reflections on the Revolution in France, ed. C.C. O’Brien (Harmondsworth: Penguin, 1968).

Edmund Burke on Government, Politics and Society, ed. B.W. Hill (London: Fontana, 1975).

The Political Philosophy of Edmund Burke, ed. I. Hampsher-Monk (London: Longman, 1987).

ተቀፅላ ምንጮች

Dreyer, F.A.: Burke’s Politics: A Study in Whig Orthodoxy (Waterloo, Ont.: Laurier University Press, 1982).

Freeman, M.: Burke and the Critique of Political Radicalism (Oxford: Blackwell, 1980). Macpherson, C.B.: Burke (Oxford: Oxford University Press, 1982).

O’Gorman, F.: Edmund Burke: His Political Philosophy (London: Allen & Unwin, 1983).

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.