ሲስሮ (106-43 ዓ.ዓ)
ማርከስ ቱሊየስ ሲስሮ ከመኳንንት ባይሆንም ከባለፀጋ ቤተሰብ በአርፒነም፣ በ106 ዓ.ዓ ነው የተወለደው፡፡ በ75 ዓ.ዓ በምዕራብ ሲሲሊ የገቢዎች ሹም ሆኖ አገልግሏል፤ በኋላም በቀድሞዋ ሮም ሪፐብሊክ በሕዝብ ዘንድ ግዙፍ ቦታ የሚሰጠውና የተናገረው ሁሉ አድማጭን ከማሳመን በቀር መሬት ጠብ የማይልበት አንደበተ-ርቱ (orator) ለመሆን በቅቷል፡፡ የሲሲሊ አገረ ገዥ የነበረውን ጃየስ ቬሬስ (በ70 ዓ.ዓ) ሕግ ፊት በማቆም ያስመዘገበው ስኬት፣ እንዲሁም (በ63 ዓ.ዓ) የሪፐብሊኩ ተሽዋሚ ዳጃ በነበረበት ወቅት የሉኪየስ ሰርጂየስ ካትሊና አሻጥርን ማቀብ የቻለበት ክስተት ከህይወቱ ወሳኝ ክፍሎች ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ የፅሁፍ ሥራዎቹ የመነጩት በስደት ወይም ከፖለቲካ እንቅስቃሴ በተገለለባቸው ወቅቶች ነበር፡፡ የወግ አጥባቂነት ሪፐብሊካዊ እሳቤዎች በብዙዎቹ ንግግሮቹና በመላምታዊ ፅሁፎቹ ላይ በግልፅ ይታያሉ፡፡ “De Republica” እና “De Legibus” በግምት ከ54-50 ዓ.ዓ ባለው ጊዜ ውስጥ የተፃፉና በቀጥታ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ሥራዎቹ ናቸው፤ ሁለቱም እጅጉን በተጐሳቆለ ሁኔታ ላይ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ከነዚህ ሥራዎቹ ባሻገር፣ “De Finibus”፣ “De Oratore” እንዲሁም፣ “De Officiis” የተሰኙትም በጉልህ የሚጠቀሱለት ናቸው፡፡
በጥንታዊቷ ሮም ሥልጣን ላይ ከነበረው የሦስት ሰዎች ቡድን ውስጥ ሲስሮ የፖምፔይ ደጋፊ ቢሆንም፣ የኦክታቪያን እና የማርክ አንቶኒ ተቃዋሚ ነበር፡፡ በተለይ የሲስሮ አስገራሚ “Philippics”የተሰኘው የጽሁፍ ጥቃት በማርክ አንቶኒ ላይ ያነጣጠረ ነበረ፡፡ ማርክ አንቶኒ ከኦክታቪያን እና ከሌፒደስ ጋር በመሆን ሁለተኛውን የሶስትዮሽ (triumvirate) መንግሥት በ43 ዓ.ዓ ሲመሠርት የሲስሮ ስም ከተወገዙ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ እንዲካተት ሆነ፡፡ ሲስሮ ለመሸሽ ቢሞክርም በቁጥጥር ስር ውሎ በታህሳስ ወር 43 ዓ.ዓ ተገደለ፤ አንገቱ እና እጆቹ ተቆርጠው በሮም አደባባይ ለእይታ ቀረቡ፡፡ የማርክ አንቶኒ ሚስት፣ ፋሊቪያ ጭንቅላቱን ይዛ ምላሱን በፀጉር ማስያዥያ መርፌ ወግታዋለች የሚባለው ታሪክ እውነት ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፤ ነገር ግን የሲስሮ አሳማኝ ንግግሮችና ጽሁፎች በተቀናቃኞቹ ዘንድ እንደከፍተኛ ስጋት መቆጠራቸው ግልጽ ነው፡፡
ሲስሮ በወጣትነቱ ሥነ-ፅሁፍ፣ ሕግ እና ፍልስፍና በሮም፣ በአቴንሰ እና በሮሆዴስ አጥንቷል፡፡ ልዩ ሀሳቦችን አመንጪ እና ጠያቂ አእምሮ ነበረው፡፡ ከእውቀት ፍልስፍና (Epistemology) አንፃር እራሱን እንደተጠራጣሪ (ስኬፕቲክ – የትክክለኛ እውቀት መኖርን የሚጠራጠር ወይም የሚክድ) ፈላስፋ አድርጐ ያስባል፡፡ በሌላ በኩል የኤቲክስ ወይም የሥነ-ምግባር የፍልስፍና ዘርፍን በተመለከተ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ2ኛው ክፍለ ዘመን የሮም የምሁራን ክበብን ወደተዋወቀው “Stoicism” (ስቶይሲዝም – ደስታን እና ሐዘንን በተለየ መልኩ የማይመለከት ፍልስፍና) ያዘምማል፡፡ ሆኖም የየትኛውም የፍልስፍና ዘርፍ ተከታይ (አቀንቃኝ) አይደለም፡፡
ለፖለቲካ ፍልስፍና ታሪክ ሲስሮ ያበረከተው አስተዋጽኦ በተለይ የግሪክ እሳቤዎችን ወደ ሮም፣ በዚህ ወደ መካከለኛው ዘመን ዓለም በማምጣት ላይ የተመሰረተ ነው። ፖለቲካዊ እሳቤዎችን በተመለከተ ፖሊቢየስ፣ የሮሆዴሱ ስቶይክ ፓኔቲየስ፣ እና ፕሌቶ ባለውለታዎቹ ናቸው፡፡ በፖለቲካ እና በሕግ ፅንሰ-ሐሳቦች ዙሪያ ያዘጋጃቸው ሁለቱ ሥራዎቹ በምልልስ (dialogue) መልክ መፃፋቸውና የፕሌቶን ምልልስ መሠረት አድረገው መሰየማቸው በአጋጣሚ የሆነ አይደለም፡፡
በአጠቃላይ ሲስሮ በ“De Republica” እና “De Legibus” ሥራዎቹ ላይ ያደረገው ትኩረት ፕሌቶ “Republic” ውስጥ ካደረገው የተለየ አልነበረም፡፡ የሮም ሪፐብሊክ በፍጥነት እየተፈረካከሰ በነበረበት ዘመን ይፅፍ የነበረው ሲስሮ፣ ቀዳሚ ዓላማው ውድቀቱ የሚቆምበትንና መረጋጋት የሚሰፍንበትን ቀመር መፈለግ ነበር፡፡ በፕሌቶ እና አርስቶትል የተጠቆመውን፣ ነገር ግን “አናክሊክሎሲስ” ተብሎ በፖሊቢየስ በይበልጥና ሙሉ በሙሉ የዳበረውን ፅንሰ-ሐሳብ ያምንበታል፡- አንድ-ወጥ (ያልተቀየጡ) የመንግሥት ሥርዓቶች – ማለትም ሞናርኪ (ንጉሳዊ ሥርዓት)፣ አሪስቶክራሲ (የላይኛው መደብ ሥርዓት) እና ዴሞክራሲ – በሞራላዊ ክስረት እና በሞራላዊ ግንባታ በሚመራ ድግግሞሽ ወይም እሽክርክሪት ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ የመንኮታኮት እና እንደገና የማንሰራራት ጠባይ ይኖራቸዋል የሚለውን ፅንሰ-ሐሳብ፡፡
ይህንን ድግግሞሽ የሚያስቆመው ወይም ሂደቱ እንዲዘገይ የሚያደርገው ምን ይሆን? ለዚህ ጥያቄ ምላሹ በቅይጥ የመንግስት ሥርዓት ላይ እንደሚመረኮዝ ሲስሮ ይጠቁማል። ይህም የሞናርኪ፣ የአሪስቶክራሲ እና የዴሞክራሲ አላባዊያን በተረጋጋ ሚዛን ለይ የሚተገበሩበት የፖለቲካ ሥርዓት ነው፡፡ ይህ ከታይበረስ ግራቸስ አብዮት (133 ዓ.ዓ) በፊት ምክር ቤቱ፣ የሪፐብሊኩ መሪዎች እና ሕዝባዊ ጉብዔው በቁጥጥራዊ (checks and balances) ሥርዓት በአንድነት ይሰሩ ዘንድ የሮም ሪፐብሊክ ተግባር ላይ ያዋለው መንግስታዊ ሥርዓት እንደነበር ሲስሮ በጠለቀ ምኞታዊ አስተሳሰብ ይገልፃል፡፡
እንዲህ ያለው አወቃቀር በቀስ በቀስ የዝግመተ-ለውጥ ሂደት የመጣ ነበር፡፡ ለስኬታማነቱም የፍልስፍና ልሂቃን፣ እንዲሁም የጋራ ጥቅምን መሠረት ያደረገ አገልግሎት የመጨረሻ ትልቁ ግብ መሆኑንና ፍልስፍናም ተግባራዊ ሊሆንበት እንደሚችል የተረዱ ሁሉ ባለውለታው ናቸው፡፡
ልክ እንደ ፕሌቶ ሁሉ፣ ለሲስሮም ጥበብ ተግባራዊ ተሞክሮ (ልምድ) ታክሎበት ባለቤቱ (ባለጥበቡ) በአግባቡ ያስተዳድርበት ዘንድ በቀዳሚነት ግብዓቶችን የሚያቀብለው ከፍተኛ እሴት (virtue) ነው፡፡ በሁለቱም “De Republica” እና “De Legibus” ሥራዎቹ ውስጥ የምልልሶቹ ተዋናዮች ትርፍ ጊዜያቸውን በሕዝባዊ ጥቅም ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ምርምር እያደረጉ ከማሳለፍ የሚሻል አንዳችም ነገር እንደሌለ በተደጋጋሚ ይገልፃሉ፡፡ “Deofficiis” በተሰኘው የሲስሮ ሥራ ላይ የሞራል ልዕልናን የተካነው (virtuous) ሰው ለሚኖሩበት ሕዝባዊ ኃላፊነቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ “Deoratore” ላይ ደግሞ ፍፁም የሚሰኝ ተናጋሪ ወይም አንደበተ-ርቱ በሕግ እና በፍልስፍና የበቃ እንደሆነ ተደርጐ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ምርጥ ተናጋሪ ምርጥ የሰው ፍጡርም ነው፡፡ እንዴት በአግባቡ መኖር እንዳለበት ይገነዘባል፣ በንግግሮቹ እና በራሱ የህይወት ተሞክሮ አማካኝነት፣ እንዲሁም መልካም ሕጐች እንዲወጡ አስተዋጽኦውን በማበርከት ሌሎችም እንዴት መኖር እንዳለባቸው ትምህርት ይሰጣል፡፡
ለወቅቱ ችግሮች እንደመፍትሔ የቀረበ ሐሳብ ተደረጐ ሲቆጠር፣ የሲስሮ ቅይጥ የመንግሥት ሥርዓት የህልም ዓለም ነው፡፡ የሮምን ጥንታዊ ሥርዓት የገለፀበት መንገድ በአብዛኛው ፖለቲካዊ ንግርት (myth) መፍጠር ላይ ያነጣጠረ ነው፤ እንዲሁም በእርሱ ዘመን ሪፐብሊካዊዋ ሮም በየትኛውም መንገድ ልትድን ከምትችልበት መስመር ተሻግራ ነበር፤ ጥንታዊው ሥርዓት ተመልሶ ሊመጣ የሚችልበትን ማንኛውንም ዘዴም አልጠቆመም፡፡ ይሁንና ግን መከራከሪያውን በማጠናከር፣ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊኖራቸው ይችሉ የነበሩ የተለያዩ ጭብጦችን አስቀምጧል፡፡ ከነዚህም ጉልህ ቦታ የሚሰጠው የስቶይክ አስተምህሮ የሆነውን ምክንያታዊ እና ሁል-አቀፍ የተፈጥሮ ሕግ አስመልክቶ የተናገረው ነው፡፡ “De Republica” ውስጥ የሚከተሉት ቃላት በምልልሱ መሪ፣ በጃየስ ሌልየስ አንደበት የተገለፁ ናቸው፡-
“በትክክልም ከአጥናፍ እስከ አጥናፋ የሚሠራ፣ የማይለዋወጥ እና ዘላለማዊ የሆነ ሕግ – ተፈጥሮን መሠረት ያደረገ ትክክለኛ ምክንያት – አለ፡፡ በትዛዛቱ ግዴታዎችን ያስተላልፋል፤ በክልከላዎቹም የጥፋት ሥራዎችን ያቅባል… መቼም ቢሆን ይህንን ሕግ በሰው (በጽሁፍ) በሚደነገጉ ሕጐች መቃረንም ሆነ ትግበራውን መገደብ ትክክል አይደለም፤ እንዲሁም ይህንን ሕግ ሙሉ ለሙሉ (ከነጭራሹ) ማስወገድ የሚቻል አይደለም፡፡ ምክር ቤቱም ሆነ ሕዝቡ የዚህን ሕግ ግዴታዎች ሊያነሱልን አይቻላቸውም፤ ይህንን ሕግ ለማስረዳት ወይም ለመተርጐም ከእኛ ባሻገር መመልከት አያስፈልገንም፡፡ ለሮም አንድ ሕግ፣ ለአቴንስ ደግሞ ሌላ ሕግ አይኖርም፤ ለአሁን አንድ ሕግ፣ ለወደፊት ደግሞ ሌላ ሕግ የለም፡፡ ይልቁንም ለሁሉም ሀገራት (ሕዝቦች) እና ለሁሉም ጊዜያት የሚስማማ (የሚሠራ)፣ ዘላለማዊ እና የማይለዋወጥ አንድ ሕግ ይኖራል፡፡”
የተፈጥሮ ሕግ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ስለሚሠራ ሁሉም ሰው ተገዢው ነው፤ ሁሉም ለእርሱ ተገዢ በመሆኑ በሆነ መንገድ ሁሉም ሰው በዜግነት አንድ መሆኑ ግድ ነው፤ ሁሉም ሰው በዜግነት አንድ ስለሆነ ሁለም ሰው እኩል ነው፡፡ ሲስሮ “De Legibus” ላይ እንዲህ ይናገራል፡-
“እወቀት ያላቸው ከሚያደርጓቸው ማንኛውም ውይይቶች ውስጥ ከሚፈልቁት ሁሉ፣ የተወለድነው ለፍትህ መሆኑንና ይህም መብት የመጣው በአመለካከት (በአስተያየት) ሳይሆን በተፈጥሮ መሆኑን ከሚጠቁም ግልፅ ግንዛቤ የበለጠ ጠቃሚ የሚሆን የለም፡፡ ሰዎች፣ አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር ያላቸውን ማኅበር እና ሕብረት ከግምት ባስገባችሁ ሰዓት ይህ ግልፅ ይሆናል፡፡ እኛ እራሳችን እርስ በራሳችን እንቅጩን እንደምንመሳሰለው ያህል፣ ምንም ነገር ማንኛውንም ነገር አይመስልም፡፡ በርግጥም መጥፎ ልማዶች እና ሀሰተኛ እምነቶች ደካማ አእምሮዎችን ካላጭበረበሯቸውና በራሳቸው የዝመት መንገዶች ካልመሯቸው በቀር፣ ሁሉም ሰው ልክ እንደሌላ ሰው፣ እያንዳንዱ ሰውም እንደራሱ ነው፡፡ … ምክንያትን ከተፈጥሮ በስጦታ መልክ የተቀበሉ ፍጥረታት ትክክለኛ ምክንያትንም ጭምር ተቀብለዋልና፡፡ ስለዚህም ለማዘዝ እና ለመከልከል ተግባር ላይ የሚውል ትክክለኛ ምክንያት የሆነውን የሕግ ስጦታ ተቀብለዋል፡፡”
እዚህ ላይ ሲስሮ ኢኮኖሚያዊ እኩልነትን እየጠቀሰ አለመሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፤ እንዲሁም ከመማር ወይም ከችሎታ አንፃር ሁሉም ሰው እኩል ነው እያለም አይደለም፡፡ ‹እኩልነት› እና ‹ፍትህ› ማለቱ የግሪክ ስቶይኮች ከሚሉት አንፃር ነው፡፡ ሰዎች ይለያያሉ፣ ሆኖም ተመሳሳይ መሆናቸውን የሚያመለክት ወሳኝ ነጥብ አለ፡፡ ምክንያትን የያዙ በመሆናቸው ሁሉም አንዳቸው ከሌላው ይመሳሰላሉ፤ ይህ የምክንያት ይዞታ አንዳቸው ሌላኛቸውን የአንድ የሰው ልጅ ቤተሰብ አባላት አድርገው የሚቆጥሩበትን ግዴታ በእያንዳንዳቸው ውስጥ ያሰርፃል፡፡ ግዴታ ያለብን ስለመሆኑ “በመጥፎ ልማዶች እና በሀሰተኛ እምነቶች” አማካኝነት ሊዛባብን የሚችል ቢሆንም፣ እንደምክንያታዊ ፍጡራን ሁላችንም ለምንሳተፍበት መሠረታዊ ህልውና እውቅና በመስጠት ወገኖቻችንን በክብርና ከውጫዊ ልዩነቶች ባሻገር እንመለከታቸው ዘንድ የተፈጥሮ ፍትህ ይጠይቀናል፡፡
ይህ ዕድሜ ጠገብ አስተምህሮ ስለፖለቲካ የሚሰጠው ጥቆማ፣ አንድ ለጋራ ጥቅም የቆመ ማህበረሰብ (“commonwealth” ወይም “res publica”) ከግልፅ እና ከትክክለኛ ዓላማ አንፃር መገለፅ ይገባዋል የሚለው ነው፡፡ የሰው ፍጡራን በአንድ ላይ የተሰባሰቡት በተፈጥሯዊ መቀራረብ (መወዳጀት) አማካኝነት ነው፤ ሆኖም የሰው ፍጡራን ስብስብ ሁሉ የጋራ (ጥቅም) ማህበረሰብ (commonwealth) አይደለም፡፡ ፍትህ በውስጡ ከሌለ በቀር፣ የጋራ ማህበረሰብ በቃል እንደሚባለው ሊኖር አይችልም፤ ለሁሉም ዜጐቹ የሞራል ማንነት፣ ብሎም የሞራል ጥያቄዎች እውቅና በመስጠት ለጋራ ጥቅም ካልቆመ በቀር፡፡ በርግጥ የጋራ ጥቅሙ ለሁሉም በተመሳሳይ መንገድ የሚገለጥ ወይም የሚቀርብ አይደለም፡፡ ሲስሮ ከኢጋሊታሪያን (Egalitarian – ሁሉም ሰው እኩል ነው፤ እኩል መብቶች እና እድሎች ይገባዋል ከሚሉት) ዘንድ ወይም ከዴሞክራቶች ዘንድ አይደለም፤ እናም የሰው ፍጡራን በማህበረሰባዊ ደረጃ፣ በጥበብ እና በሞራል ልዕልና ልኬት እንደሚለያዩ ይገነዘባል፡፡ ከእርሱ በፊት እንደነበሩት የግሪክ እና የሮም ስቶይኮች ሁሉ፣ በሰብዓዊ እኩልነት እና በባሪያ ሥርዓትና በግለሰብ ንብረት መካከል ምንም ዓይነት አለመጣጣም አይታየውም፡፡ ነገር ግን በእውነተኛው የስቶይክ አካሄድ፣ ማንም ሰው ባሪያም ሆነ ነፃ፣ ሀብታምም ሆነ ደሃ በተፈጥሮው እንደሁኔታው ከፍትህ እና በእኩል ዓይን ከመታየት መብት አልተገለለም፡፡ ስለ የጋራ ማህበረሰብ “Derepublica”ላይ እንዲህ ይላል፡-
“የጋራ ማህበረሰብ የሕዝብ የሆነ ነገር ነው፤ እንዲሁም «ሕዝብ» በማንኛውም መንገድ የተሰባሰበ የሰዎች ስብስብ ሁሉ ሳይሆን፣ ትክክል ማለት ምን እንደሆነ የጋራ ስምምነት ላይ የደረሰና ለጋራ ጥቅም ያበረ የብዙሃን አንድነት ነው፡፡”
በሌላ አገላለጽ፣ የጋራ ማህበረሰብ የተገዢዎች ሳይሆን የዜጐች ማህበር ነው፡፡ በአንድ ወይም በጥቂቶች ፍላጎት ብቻ የሚመራ ወይም በኃይል የሚገዛ መንግስት (Tyrannical Government) አንድ የመንግሥት ዓይነት ነው፤ ሆኖም በዚህ መንገድ የሚመራው የግለሰቦች ስብስብ ግን የጋራ ማህበረሰብ (res publica) አይደለም፡፡ እውነተኛ የጋራ ማህበረሰብ፣ ለሁሉም ጥቅም ሲባል ሁሉም በሚጋራው የፍትህ እና የሥርዓት ግንዛቤ አማካኝነት አንድነት ያለው ሞራላዊ ማህበረሰብ ነው፡፡ እንዲህ ያለ የጋራ ማህበረሰብ የተፈጥሮን ሕግ በሚገነዘቡ፣ ጥበባቸውን እና ሞራላዊ ልዕልናቸውን ባረጋገጡ ግለሰቦች የሚመራና ዜጐቹም ምክንያታዊ ይሁንታን የሚሰጡ ሊሆኑ ይገባል፡፡
ሲስሮ ከዚህ ቀደም ያልተነሳ ወይም ኢሪጂናል ሊባል የሚችል ሥራ የቀረበ አለመሆኑ ሊታመን ይገባል፤ እርሱም ቢሆን አቀርብኩ አላለም፡፡ ይሁንና አንድን ሀሳብ በተለያየ መንገድ በመግለጽና በጥልቅ ትንታኔ ነገሮችን በአሳማኝ መልኩ በማቅረብ የበቃ ነው፡፡ የእርሱ የተፈጥሮ ሕግ አስተምህሮ በቤተ-ክርስቲያን አባቶች ሥነ-ምግባራዊ እና ፖለቲካዊ እሳቤዎች ላይ፣ ለሮም የሕግ ፍልስፍና መጐልበት፣ ብሎም ከመካከለኛው ዘመን እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ድረስ በነበረው የፖለቲካ ፍልስፍና ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ካሳደሩት መካከል አንዱ ነው ቢባል እንደማጋነን አይታይም፡፡ ሳቢን እና ቶርሰን “A History of Political Theory” በተሰኘ መፅሐፋቸው እንደገለፁት፣ “በጣም ወሳኞቹ ምንባቦች በመላው የመካከለኛው ዘመን ጊዜያት ተደጋግመው (በሌሎች) ሲጠቀሱ ቆይተዋል፡፡… ስለተከታይ ክፍለዘመናት የፖለቲካ ፍልስፍና ማንበብ የሚሻ ማንኛውም ሰው ጥቂት የሲስሮ ታላላቅ ምንባቦች በህሊናው ተቀርፀው ሊቀሩ ግድ ይለዋል፡፡” እናም በዚህ ምክንያት ነው ማርከስ ቱሊየስ ሲስሮ በፖለቲካ እሳቤ (ፍልስፍና) ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና እንዳለው ሊቆጠር የሚገባው፡፡
ለበለጠ ንባብ
ቀዳሚ ምንጮች፡-
De oratore (London: William Heinemann; Loeb Classical Library, vols 3 and 4).
Philippics (Loeb Classical Library, vol. 15).
De republica and De legibus (Loeb Classical Library, vol. 16).
De finibus (Loeb Classical Library, vol. 17).
De officiis (Loeb Classical Library, vol. 21).
ተቀፅላ ምንጮች፡-
Dyson, R.W.: Natural Law and Political Realism in the History of Political Thought (New York: Peter Lang, 2005), ch. 4.
Lacey, W.K.: Cicero and the End of the Roman Republic (New York: Barnes and Noble, 1978).
Sabine, G.H. and Thorson, T.L.: A History of Political Theory (4th edn; Hinsdale, IL: Dryden Press, 1973), ch. 10.
Smith, R.E.: Cicero the Statesman (Cambridge: Cambridge University Press, 1966).
Wood N.: Cicero’s Social and Political Thought (Berkeley, CA: University of California Press, 1988).