አርስቶትል (384-322 ዓ.ዓ)
የግሪክ ቅኝ በነበረችው ትሬስ ውስጥ በስታጊራ ከተማ ነበር አርስቶትል የተወለደው፡፡ በ367 ዓ.ዓ የፕሌቶ ክበብ አባል ሆነ፡፡ ፕሌቶ ሲሞት የክበቡ ኃላፊ እሆናለሁ ብሎ ጠብቆ እንደነበር ይነገራል፡፡ ሆኖም የጠበቀው እውን ባለመሆኑ ተበሳጭቶ አቴንስን ለቅቆ ወጣ፡፡ በአሶስ የአትራንየስ ገዥ ከነበረው ሄርሚያስ ጋር ለእርሱ መታነጽ ጥልቅ አስተዋጽኦ የነበራቸውን ሦስት ዓመታት ካሳለፈ በኋላ፣ በ343 ዓ.ዓ ለወደፊቱ ታላቁ እስክንድር የግል አስጠኚ እንዲሆን የቀረበለትን ሹመት ተቀብሎ ወደ ንጉሥ ፍሊፕ የሜቄዶን ቤተ-ነገሥት አምርቷል፡፡ በ335 ዓ.ዓ ወደ አቴንስ ተመለሶ የራሱን “ሊሲየም” የሚል መጠሪያ ያለው የፍልስፍና ትምህርት ቤት ከፈተ፡፡ ከታላቁ እስክንድር ጋር የነበረው ግንኙነት አስክንድር በ323 ዓ.ዓ ከሞተ በኋላ በአክራሪ አቴናውያን ዘንድ ተወዳጅነት እንዳይኖረው አደረገው፤ በዚህም ምክንያት ዳግም ከአቴንስ መሰደድ ግድ አለው፡፡ አርስቶትል በመጨረሻ ህይወቱ ያሸለበው ዩቦዬ ውስጥ በቻልሲስ ከተማ ነው፡፡
አርስቶትል ካበረከታቸው አያሌ ፍልስፍናዊ፣ አመክኒዮአዊ እና ሳይንሳዊ ሥራዎቹ ውስጥ በይበልጥ የምናተኩረው “Nicomachean Ethics” እና “Politics” በተባሉት ላይ ነው፡፡ እንደ አብኛዎቹ ሁሉ እነዚህም ሥራዎቹ (“Nicomachean Ethics” ላይ የተጠቀሰው ኒኮማቸስ የአርስቶትል ልጅ ነበር) ከእርሱ ሞት በኋላ በቤተሰቦቹ እና በተማሪዎቹ አማካኝነት ተሰባስበው የተጠረዙ ናቸው፡፡ ይህም እውነታ ሥራዎቹ ጥብቅ ጥንቃቄ የሚሹ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡
የአርስቶትል የፖለቲካ እና የሞራል ፅሁፎች አስኳል ጭብጥ የፖለቲካዊ ህይወት ተፈጥሯዊነት፣ በዚህም ትክክለኛነት ነው፡፡ “ሰው በተፈጥሮው ፖለቲካዊ እንስሳ ነው። ከራስ-ገዙ ወይም ከመንግሥታዊው ከተማ ውጪ የሆነ ማንኛውም ሰው፣ ወይ ከሰብዓዊ ፍጡር የላቀ፣ አልያም ከሰብዓዊ ፍጡር ያነሰ ነው” (Politics 1:2)። እንደአርስቶትል አስተሳሰብ፣ ራስ-ገዙ ከተማ (polis) ሰብዓዊ ፍጡራን ለዝርያቸው የሚስማማ የሕይወት ዓይነት ሊኖሩ የሚችሉበት ብቸኛው ስፍራ ነው፡፡ “Politics” የተሰኘው የአርስቶትል የፍልስፍና ውጤት፣ መንግሥታት መደራጀት ስለሚችሉባቸው መንገዶች የእውቀት ማስጨበጫ ትንታኔ በማቅረብ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው። ይህን ትንታኔ የሚያስረዱ የሞራል መላምቶት “Nicomachean Ethics” ላይ በስፋት የሚገኙ ናቸው፡፡
አርስቶትል፣ ስለዓለም ያለው አጠቃላይ ምልከታ በነገሮች የመጨረሻ ግብ ላይ መሠረት የሚያደርግ ግባዊ (teleological) ተብሎ የሚታወቀው ዓይነት ነው፡፡ በጥልቁ ህዋ (universe) ውስጥ የሚገኝ እያንዳንዱ ነገር የራሱ ብቻ የሆነ ቴሎስ (ይህም የመጨረሻ “ግብ” ወይም “ዓላማ”) አለው። አርስቶትል ይህን ሲል ለማለት የፈለገው ልክ ቢላዋ ዓላማው መቁረጥ ወይም ብዕር ዓላማው መፃፍ እንደሆነው አይነት ያለ “ዓላማ” አይደለም፡፡ ሰው-ሠራሽ ያልሆኑ፣ አንድ ነገርን እንዲያደርጉ የተሠሩ ያልሆኑ ነገሮች፣ በተፈጥሯቸው ሊያሳኩት የሚገባቸው የተሟላ ወይም የመጨረሻ እድገት ላይ ከመድረስ ሁኔታ አኳያ ቴሎይ (ግቦች) አሏቸው ማለቱ ነው፡፡ የወይራ ፍሬ ቴሎስ፣ የወይራ ዛፍ መሆን ነው፡፡ እንደዚያ የሚያደርግበት ሂደት የራሱ ኤርጐን (ሥራው ወይም ተግባሩ) ነው፡፡ ይህንን ሂደት ለማከናወንና ለማጠናቀቅ ያለው የተፈጥሮ ብቃት ዳይናሚስ ነው፡፡ በመጨረሻ፣ አንድን ነገር “ጥሩ” ብለን ስንጠራው፣ ያ ነገር የራሱን ቴሎስ በስኬታማ መልኩ ቋጭቷል ወይም አጠናቋል ማለታችን ነው፡፡ ጥሩ ብዕር ግሩም አድርጐ የሚጽፍ ሲሆን፣ ጥሩ የወይራ ዛፍ ሙሉ እድገቱን የፈፀመ የወይራ ዛፎች ተምሳሌት ነው፤ ሌላውም ነገር እንዲሁ ነው፡፡
ምንድን ነው የሰው ቴሎስ፣ የሰውስ ጥሩ ምንድነው? አርስቶትል ሲመልስ፣ የዩዳይሞኒያ (eudaimonia) ደረጃን ማሳከት ነው፡፡ ዩዳይሞኒያ በመደበኛ ትርጓሜው “ደስተኛነት” ማለት ነው፤ ሆኖም “ደስተኛነት” መጠኑ አርስቶትል ዩዳይሞኒያ ከሚለው ያነሰ ነው፡፡ ለአርስቶትል ቃሉ የሚያመላክተው፣ የሰብዓዊ ፍጡር ተግባር ዓላማ ተደርጎ የሚወሰድ የዕድሜ ዘመን ንቁ የሞራል ጤናማነት ሁኔታን ነው፡፡ በዚህ ግንዛቤ “ደስተኛነት” የሰው የመጨረሻ “ግብ” መሆኑን እንዴት እናውቃለን? ደስተኛነትን የምንሻ መሆናችንን እና እንዲሁም ደስተኛነትን ለየትኛውም ሌላ ነገር ብለን የማንሻው መሆናችንን በማወቃችን ምክንያት የሰው የመጨረሻ “ግብ” ደስተኛነት መሆኑን እናውቃለንና ነው፡፡ የሆነ ሰው ለምን ገንዘብ ወይም ሥልጣን እንደምንፈልግ ቢጠይቀን፣ ምላሻችን ሁለቱንም እንፈልጋቸዋለን ምክንያቱም ደስተኛ ስለሚያደርጉን የሚል ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም አንድ ሰው ስለምን ደስተኛ መሆን እንደፈለግን ቢጠይቀን፣ ከደስተኛነት በላይ ከሆነ አንድ ዓላማ (ወይም ግብ) አኳያ ምላሽ አንሰጥም፡፡ ደስተኛነት መንስዔ የሚሆንበት ሌላ ተጨማሪ መሻት የለም በሚለው ያልተወሳሰበ ግንዛቤ አማካኝነት (ደስተኛነት) በራሱ የመጨረሻ ግብ ነው፡፡ በተጨማሪ፣ ደስተኛነት ትክክለኛ ደስተኛነት የሚሆነው በመላ የህይወት ዘመን ዘላቂ ወይም ቀጣይ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ደስተኛነት እንዲሁ ወዲያው የሚደበዝዝ ወይም አስፈላጊነቱ እዚህ ግባ የማይባል ነገር መሆን አይችልም፡፡ የአንድ ሰው ህይወት እስካላለፈ ድረስ በርግጠኝነት ህይወቱ የደስታ ነበር ማለት አይቻለንም፤ ምክንያቱም ደስታው ሙሉ በሙሉ በጥልቀት ሊመረመር የሚችለው ሰውየው ከሞተ በኋላ ነውና፡፡
እንግዲህ በምን መንገድ ነው ይህን ግብ እና ጥሩ ልንቀዳጀው የሚቻለን? እንደ አርስቶትል ከሆነ፣ ሌሎች ፍጥረታት የሌላቸው የተወሰነ የተግባር ዓይነትን በመለየት ነው የሰብዓዊ ፍጡርን የተለየ ቴሎስ ልናገኝ የምንችለው፡፡ ስለዚህም እኛ እና እኛ ብቻ ያለንን ብቃት ወይም ዳይናሚስ ማግኘት ይጠበቅብናል። ይህ ብቃት በመኖር ሂደት ውስጥ እንዲሁ የሚገኝ አይደለም፤ እፅዋትም እየኖሩ ናቸውና፤ እንዲሁም በህይወት ስላለንና ለነገሮች ስሜት ስላለንም አናገኛቸውም፤ እንደዚያ ቢሆንማ ከእንስሳት የተለየ ቴሎስ ሊኖረን አይገባም ነበር፡፡ እናም በተሰናሰለና ዓላማ ባለው መልኩ ለማውጠንጠን፣ የተቀረው ሌላው ፍጥረት የሌለው ሕሊና ወይም የማስተዋል ብቃት (reason) ሊኖረን ይገባል ሲል አርስቶትል ይደመድማል፡፡ ይህም፣ የማስተዋል ብቃት ባለቤት በመሆን ላይ ሳይሆን ጥቅም ላይ በማዋል ላይ የሚመረኮዝ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ለምሳሌ ሙዚቀኞች፣ ሙዚቀኞች የሆኑት የሕሊና ባለቤት ስለሆኑ አይደለም፤ የሙዙቃ መሣሪያዎቻቸውን ስለተጫወቱ እንጂ፡፡ በተጨማሪም የማስተዋል ብቃትን ዝም ብሎ ጥቅም ላይ ማዋሉ ላይ ብቻ ሊመረኮዝም አይችልም። አንድ ሰው ጥሩ ጊታሪስ የሆነው ጊታር ስለተጫወተ አይደለም፤ ጊታሩን ግሩም አድርጐ ስለተጫወተው እንጂ። ስለዚህም አንድ ሰው የማስተዋል ብቃቱን ግሩም አድርጎ እስካልተጠቀመ ድረስ ጥሩ ሰው ነው ማለት የለብንም፤ ሞራላዊ ልዕልናን (virtue) መሠረት በማድረግ የማስተዋል ብቃቱን ካልተጠቀመበት በስተቀር፡፡ የሰብዓዊ ፍጡር ህይወት ሚና፣ የሞራል ልዕልናን በተከተለ የማስተዋል (ምክንያታዊ) ተግባር አማካኝነት “ደስተኛነትን” ማሳካት ነው፡፡ ይህ ነው በተፈጥሯችን የተደነገገልን የእኛ የመጨረሻ “ግብ”፡፡
አርስቶትል “virtue” የሚለውን ቃል ሁለት የተለያዩ፣ ሆኖም ተያያዥነት ያላቸውን ነገሮች ለመጠቆም ነው። የመጀመሪያው በተለምዶ ግንዛቤ የሞራል ብቃቶች የሆኑትን የሚወክልበትና የሞራል ልዕልና በማለት የምንጠራቸውን ነው። በሌላ በኩል “virtue” የሚለው ቃል ዲያኖይቲክ (dianoetic) የተባሉትን ወይም የዕውቀት ልዕልናዎችን የሚወክል ሲሆን፣ ከእነዚህ ልዕልናዎች ውስጥም ሶፊያ (Sophia) እና ፍሮነሲስ (phronesis) የተባሉትን እንቃኛለን። ከመነሻው ሥራዎቹ ባላቸው አስቸጋሪነት ምክንያት አንዳንዴ የአርስቶትልን ትርጓሜ ግልጽ እንዳይሆን የሚያደርጉ ናቸው፤ ቢሆንም ደስተኛነት፣ በተለያዩ መንገዶች ወይም በተለያዩ ደረጃዎች ሁለቱንም ልዕልናዎች በስኬታማ መልኩ ከመጠቀም ጋር የተያያዘ ነው ብሎ ያሰበ ይመስላል፡፡ በአንድ በኩል፣ የተሟላ ደስተኛነት በሚለው ግንዛቤ መሠረት፣ ደስተኛነት ረቂቅ ሐሳቦችንና አመክኒዮአዊ ቁርኝታቸውን በጥልቀት ማውጠንጠን ላይ ይመረኮዛል፡፡ እንደዚህ ያለ ድርጊት ሶፊያ የተባለውን የእውቀት ልዕልና ይጠይቃል፡- ይህም ፅንሰ-ሐሳባዊ (theoretical) ወይም ተግባሮታዊ (demonstrative) ጥበብ ነው። ተግባሮታዊ (demonstrative) የተባለው አመክኒዮ ምንም ዓይነት ተግባራዊ ውጤት የለውም፤ ከቁሳዊው ዓለም ጋር ምንም ቁርኝት የሌለው ንፁህና ቀላል ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ እንደዚያ ያለውን ሥነ-አመክኒዮ መጠቀም ማለት ከሁሉም ለውጥ እና ጥርጣሬ የተላቀቀ በጣም ምጡቅ ዓይነት ደስተኛነትን ማጣጣም ማለት ነው፡፡
አንድ ፈላስፋ፣ ተፈላሳፊ በሆነበት ጊዜ ሁሉ፣ ልክ አማልክት ዘላለማዊ እና ለውጥ-የለሽ የሆነውን ጭው ባለ እርጋታ እና በምኞት-የለሽነት በጥልቀት እንደሚያውጠነጥኑት፣ ከፍላጐት እና ከሕመም የተነጠለ ነው፡፡ “ከአማልክቱ ተግባር ጋር በይበልጥ የሚመሳሰለው የሰብዓዊ ፍጡር ተግባር ከሁሉም በላይ የደስተኛነት ባሕሪይ ይኖረዋል” – (Nicomachean Ethics 10:8)፡፡ በሌላ በኩል፣ ከፍልስፍናዊ ማውጠንጠን የሚመጣ ደስተኛነት፣ እጅግ ምጡቅነትን ያዘለ በመሆኑ፣ የየትኛውም ሰው የተለመደ ህይወት መሆን አይችልም፡፡ ማንም ሰው የዕለት ተዕለት ተግባሮቹን አግልሎ በቋሚነት በብቸኝነት በጥልቀት የማውጠንጠን ሁነት ውስጥ መኖር አይቻለውም፡፡ ስለዚህ በጣም የተነጠለ ዓይነት ደስተኛነት ነው ብቸኛው የደስተኝነት ዓይነት እያልን ነውን? አለመሆኑ ግልፅ ነው፤ ምክንያቱም በአጠቃላይ በሰው ዘር እና በመላው ህይወት እውን ሊደረግ የሚችል ደስተኛነትን ማወቅ ነውና ፍላጎታችን፡፡ በይበልጥ መደበኛ ወይም የዕለት ተዕለት ዓይነት ደስተኛነትን መፈለግ አለብን፡፡
እዚህ ጋር ነው የሞራል ልዕልናዎችን የሚወክለው “virtue” የሚመጣው። ደስተኛነት ለአብዛኞቻችንና ብዙውን ጊዜ ረቂቅ በሆነ አመክኒዮአዊ አስተሳሰብ ሳይሆን፣ በዕለት ተዕለት ህይወታችን ውስጥ ጥሩ ወይም ክቡር ባሕሪይን በመተግበር የሚገኝ ነው፡፡ ይህ አባባል የፍልስፍና ህይወት ከሁሉም እጅግ የላቀ ነው ከሚለው አመለካከት ጋር የማይጣጣም አይደለም፡፡
“ነገር ግን በሁለተኛ ደረጃነት፣ በሌላኛው “virtue” ወይም በሞራል ልዕልናዎች መሠረት የሚመራ ህይወት የደስታ ህይወት ነው፤ ምክንያቱም ይህን መሠረት ያደረገ ተግባር ለእኛ የሰብዓዊ ሁኔታ የተመቸ ነውና፡፡” (Nicomachean Ethics 10:8)
ስለዚህም በሁለተኛ ደረጃነት የተጠቀሰው ወይም የቀን ተቀን ደስተኛነት የሚገኘው በሞራል ልዕልናዎች ትግበራ ውስጥ ነው፤ የሞራል ልዕልናዎቹም እንደ ድፍረት ወይም ወኔ፣ ቁጥብነት፣ ልግስና እና ፍትህ ያሉት ናቸው፡፡ ግን በምን ዓይነት ተለይተው በሚታወቁ ድርጊቶች ላይ ነው የእነዚህ የሞራል ልዕልናዎች ትግበራዎች የሚገኙት? ከዚህ ጋር በተያያዘ ነው አርስቶትል የአማካይ (mean) አስተምህሮውን የሚያስተዋውቀው፡፡ አርስቶትል፣ የሞራል ልዕልናን የተጎናፀፈ ድርጊትን እንዲህ ይለዋል፡-
“አንድ ተግባራዊ ጥበብ ያለው ሰው ሊወስን በሚችልበት መንገድ በምክንያታዊ መርሆ መሠረት በሁለት ጥጐች – ከበቂ በላይ በሆነ እና በአነስተኛው – መካከል የሚወሰን፣ ከራሳችን አንፃር ሲታይ አማካይ ላይ የሚወድቅ የምርጫ ተለምዶን ነው፡፡” (Nicomachean Ethics 2:6)
መርሆው ግልጽ ነው፡፡ የደፋርነት ባሕሪይ፣ አደጋን በግልፍት ሳይጠነቀቁ በመጋፈጥ እና በቀጥቃጣነት በመደናበር መካከል የሚገኝ ነው፡፡ እርጋታ የተላበሰ ሰው ተፈጥሯዊ መሻቶቹን ከነአካቴው አይጨቁናቸውም፣ እንዲሁም ሙሉ ለሙሉ አይዘፈቅባቸውም፤ አግባብ በሆነ መጠንና ወቅት፣ የሚያስደስተውን ይደሰትበታል፡፡ ከላይ ካየነው የአርስቶትል ትርጓሜ ውስጥ ወሳኙ ክፍል «ከራሳችን አንፃር» የሚለው ሀረግ ነው፤ ይህም «ምን ዓይነት ሰው ከመሆናችንና እረሳችንን ካገኘንበት ሁኔታ አንፃር» እንደማለት ነው፡፡ የሞራል ልዕልና ትግበራ፣ ፅንፎችን በማስወገድ ለሰው፣ ለጊዜ እና ለቦታ አመቺ የሆነውን የመፈፀም ጉዳይ ነው፡፡ ማንም ጠንካራ እና ድንገተኛ ሕግጋትን ከነገሮች አስቀድሞ መደንገግ አይችልም፡፡ የድፍረት፣ የእርጋታና የወዘተ ልዕልናዎች በተጨባጭ ሲከወኑ፣ በተለያየ ጊዜና በተለያየ ሁኔታ ላይ የተለያዩ ይሆናሉ፤ እንዲሁም በተግባሪያቸው ምዘና አንፃር የሚወሰኑ ይሆናሉ፡፡ እርግጥ ነው አንዳንዴ አጥንት ድረስ የሚዘልቅ እርካታና ጥልቅ ንዴት አግባብነት ያለው ይሆናል፡፡ የአርስቶትል አማካይ አስተምህሮ የሚደነግገው የጥልቅ ስሜት ወይም የውጥረት እርምጃ መወገድን ሳይሆን፣ ለክስተቱ የማይመቹ ከመሆናቸው አንፃር መረን የለቀቁ የሆኑ ምላሾችን መወገድ ነው፡፡
የሞራል ልዕልና ትግበራ፣ በፍልስፍና ወቅት ከምንገለገለው ሶፍያ የተለየ የሆነ የእውቀት ልዕልና ወደ ጨዋታው እንዲቀላቀል መንገድ ይከፍታል፤ ይህም ፍሮነሲስ (Phronesis) ያልነው ነው። አማካይን ለማግኘት፣ አንድ ሰው «ተግባራዊ ጥበብ ያለው» (ማለትም ፍሮኒሞስ – phronimos) መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ፍሮነሲስ፣ «ተግባራዊ አመክኒዮአዊነት» ወይም «በሳልነት»፣ በየትኛውም ዓይነት ሁኔታ ምን ማድረግ አለብን ብለን ከራሳችን ጋር ሙግት ስንገጥም ያለን የአስተሳሰብ ዓይነት ነው፡፡ ከሶፍያ የተለየ ነውና፣ ዓላማው ሐሳባዊ (ረቂቅ) እና ሁሉ-አቀፍ እውቀት አይደለም፤ ዓላማው ተግባራዊ ወይም ሞራላዊ ጠቀሜታ ያለው ዓይነት ድርጊት ነው፡፡ ፍሮነሲስ የሞራል ግቦችን በራሱ መለየት አይችልም፡፡ እነዚህ ግቦች አማካይን ለማግኘት ባለን ዝንባሌ የምናገኛቸው ናቸው፤ ይህ ዝንባሌ የሚገኘው በምክንያታዊነት ሳይሆን በልማድ ነው፡፡ ሆኖም፣ ፍሮኒሲስ የሞራል ግቦቻችንን ለማሳካት በየትኛውም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ድርጊታችን ምን መሆን እንዳለበት የሚያሳውቀን ነው፡፡ «ሞራላዊ ልዕልና ትክክለኛ ነጥብ ላይ እንድናልም የሚያደርገን ሲሆን፣ ተግባራዊ ጥበብ ደግሞ ትክክለኛውን መንገድ እንድንከተል ያደርገናል።» (Nicomachean Ethics 6:13)
ስለዚህም የእኛ የመጨረሻ ግብ ዩዳይሞኒያ ነው – «ደስተኛነት»፡፡ የምናሳካውም ህይወታችንን በሙሉ ጥሩ በሆነ መልኩ በመኖር ሲሆን፣ ጥሩ በሆነ መልኩ መኖር ደግሞ አመክኒዮአዊ ተግባርን ግሩም አድርጎ የመተግበር ጉዳይ ነው፡፡ ላዕላይ የሆነ ደስተኛነት፣ በመደበኛ ጉዳዮች በማይደናቀፉት በሶፊያ የእውቀት ልዕልናዎች አማካኝነት ረቂቅ በሆነ ማውጠንጠን የሚገኝ ነው፡፡ ነገር ግን ከአጠቃላዩ ሕይወት አንፃር በሁሉም ዘንድ ሊጨበጥ የማይችል ግብ ነው፡፡ በመደበኛነት ደስተኛነት የሚገኘው፣ ለእያንዳንዱ ድርጊታችን በፍሮነሲስ የእውቀት ልዕልና አማካኝነት በመመራት የሞራል ልዕልናዎችን በተከታታይ ስንጠቀም ነው፡፡
ከመነሻችን እንዳየነው፣ ይህ የግባዊነት (teleological) ትንታኔ ከተፈጥሮ አንፃር የተሰጠ ነው፡፡ የሰው ልጅ ያለው የመጨረሻ ግብ፣ ለተፈጥሮው ምቹ የሆነ ግብ ነው፡፡ «ሰው በተፈጥሮ ፖለቲካዊ እንስሳ ነው» የሚለውንም እንዲሁ የምናስታውሰው ነው፡፡ ስለዚህ፣ የሞራል ፍጥረታት እንደመሆናችን በእኛ የተፈጥሮ ግብ፣ እንዲሁም የፖለቲካ እንስሳ እንደመሆናችን ደግሞ በተፈጥሯዊ አኗኗራችን መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው? ልክ ፕሌቶ የፖለቲካ ማኅበር አጀማመርን አስመልክቶ እንደሰጠው ዳሰሳ፣ ለየትኛውም ዓይነት የሞራል ትግበራ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ በመሆናቸው በሥራ ክፍፍል ላይ የተመሰረቱ የቁሳዊ ሁኔታዎች መሟላት አስፈላጊ መሆኑን አርስቶትል ያስገነዝባል፡፡ ማንም ሰው ሁሉንም የህይወት መሠረታውያንን (needs) ለብቻው ሊያሟላ የማይችል መሆኑ የተፈጥሮ እውነታ ነው። ስለዚህም ሁሉም ሰብዓዊ ማኅበር አንድ የተለየ የቁሳዊ ፍላጐት ደረጃን እስካሟላ ድረስ ተፈጥሯዊ ነው፡- ቤተሰብ ተፈጥሯዊ ነው፣ መንደርም እንደዚያው፤ ራስ-ገዝ አስተዳደሩም (polis) እንዲሁ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ሆኖም፣ ይህ ፖሊስ የተባለው ራስ-ገዝ የፖለቲካ ማህበረሰብ ነው ከሁሉም በበለጠ በጣም የተሟላ፣ በዚህም ከሁሉም በላይ ሙሉ ለሙሉ ተፈጥሯዊ የሆነው ማሕበረሰብ፡፡ በይበልጥ ካልተጠናከሩ ሰብዓዊ ስብስቦች ይልቅ፣ ራስ-ገዝ የፖለቲካ ማህበረሰብ የሚያስፈልጉንን በሙሉ አንድም ሳይቀር ያሟላልናል፡፡ እዚህ ጋር አርስቶትል የሚለን ኢኮኖሚያዊ ፍላጐታችንን ብቻ ሳይሆን እንደአመክኒዮአዊ ፍጡርነታችን ያሉንን የሞራል ፍላጎቶች እስከነ ሙሉ ጠገጋቸው ድረስ ያቀርብልናል ነው፡፡፡ «የፖለቲካ ማህበረሰብ (መንግሥት) የተፈጠረው ሰዎች መኖር እንዲቻላቸው ነው፤ ጥሩ ኑሮ እንዲኖሩም ሲባል የፖለቲካ ማህበረሰብ እንደሆነ ይቀጥላል» (Politics1:2)፡፡ ይህን መርህ የሚከተሉት ነጥቦች ይበልጥ ያጎሉታል፡፡
መጀመሪያ፣ የፖለቲካ ማህበረሰቡ የሞራላዊነት ኢኮኖሚያዊ ቅድመ-ሁኔታዎችን ያቀርባል። የኢኮኖሚ እና የሞራል ፍላጐቶች እርስ በእርስ የተቆላለፉ ናቸው፡፡ ከፍልስፍናዊ ማውጠንጠን የሚመጣው የላዕላይ ደስታ ህይወትም ሆነ አርስቶትል ከመደበኛ ደስተኛነት ጋር የሚያገናኘው የተማዘነ፣ አመክኒዮአዊና ሞራላዊ ሕይወት፣ ፍላጎት በሰፈነባቸው ሁኔታዎች ውስጥ ሊኖሩ አይቻሉም፡፡ የውጫዊ ቁሶች እጅግ የተትረፈረፈ አቅርቦት ለእኛ መጥፎ ነው – ስንፍናን እንዲሁም አላዋቂነትን ያበረታታል። በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መሰማራት ያለብን ፍላጐቶቻችንን ለማሟላት እስከሚያስፈልገን ደረጃ ብቻ መሆን አለበት፡፡ ለትርፍ ብቻ የሚደረግ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ተፈጥሯዊ አይደለም፡፡ ሆኖም ጥሩ ኑሮ ለመኖር በቂ የሆነ ቁሳዊ የብልፅግና ደረጃ አስፈላጊ ነው። እንክብካቤ እጅግ ከበዛብ ወይም ጤንነታችን ከተጓደለብን ለአመዛዛኝ ፍጡር ምቹ የሆኑ ተግባሮችን መከወን ያዳግተናል። ለጋሽ ለመሆን የሚያስችለን ገቢ ካልኖረ በስተቀር ለጋሽ መሆን አይቻለንም፤ ብድራችንን መመለስ የሚያስችለን ገቢ ከሌለን ፍትሃዊ መሆን አይቻለንም፡፡ እናም፣ የራስ-ገዙ የፖለቲካ ማኅበር (የመንግሥት) የማምረትና የማከፋፈል ሂደቶች ሞራላዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ አቅጣጫዎች እውን እንዲሆኑ የሚያደርጉ ናቸው፡፡
ሁለተኛ፣ የሞራል ልዕልናን ለማጎልበትና ለማሳካት የሚፈቅዱ የትምህርት ሁኔታዎችን የራስ-ገዙ ማኅበር ነው የሚያቀርብልን፡፡ ለአርስቶትል፣ የሞራል ትምህርት ከእውቀት ልዕልና በተለየ በሥልጠናና በድግግሞሽ አማካኝነት የልማድ ወይም የተሞክሮ ስልቶችን የመቅሰም ጉዳይ ነው፡፡ ሞራላዊ ተግባሮችን በመፈፀም ነው፣ ሞራላዊነትን የተጎናጸፍን መሆን የሚቻለን፤ ልክ ሙዚቃን በድግግሞሽ በመጫወት ይህ-ቀረሽ የማንባል ሙዚቀኞች እንደምንሆነው ማለት ነው፡፡ እናም፣ ሰዎችን ጥሩ የሆኑ ለማድረግ ጥሩ ልማድ እንዲኖራቸው መጠየቅና ይህንን ማበረታታት የሕግ አስፈላጊ ግልጋሎት ነው፡፡ በዚህ መንገድ፣ ሰዎች እንዲሁ ከሕግ ጋር ተጣጥሞሽ ያላቸው እንዲሆን ከማድረግ ሚናው በዘለለ፣ ሕግ ሰዎችን ጥሩ ያደርጋል ብሎ አርስቶትል ያምናል። ይህ ቢያንስ በከፊል፣ «ሰው ሙሉነትን ሲላበስ ከሌሎች ፍጥረታት ሁሉ የላቀ፣ ከሕግ እና ከፍትህ ሲነጠል ግን ከሁሉም የባሰ መጥፎው ይሆናል» ላለበት እንደምክንያት የሚጠቀስ ነው፡፡ በተጨማሪ፣ እኛን ከሚመስሉ ሌሎች ሰዎች ጋር ህብረት በመፍጠርና በዕለት ተዕለት የኑሮ ሁነቶች ውስጥ ተሳትፎ በማድረግ ነው ፍሮነሲስን ማጎልበት፣ እንዲሁም በማስተዋል እና በመፈፀም ትግበራ ስኬታማ መሆን የምንችለው፡፡ የራስ-ገዝ ማህበረሰቡ አኗኗር፣ ይህም በሕግ እንደሚገዛ እንደ ማህበራዊ ሕብረተሰብ ሆኖ የሞራል ትምህርታችን እና ለትግበራችን አስፈላጊ የሆኑ ሁኔታዎችን ያቀርብልናል፡፡
ሦስተኛ፣ የሞራላዊ ጥሩነታችን ማህበራዊ ቅድመ-ሁኔታዎችን ከራስ-ገዙ ማኅበር እናገኛለን። ያም የሆነበት ምክንያት በብቸኝነት መኖር በተፈጥሯችን የሌለ፤ እንዲሁም እርካታን ወይም ደስተኛነትን በራሳችን አማካኝነት ብቻና በራሳችን ፍላጎት ብቻ ማግኘት በተፈጥሯችን የሌለ በመሆኑ ነው፡፡ በየዕለቱ ልናገኝ የምንችለው ደስተኛነት በተወሰነ መጠን በሌሎች ደስተኛነት ላይ የሚጫወተው ሚና ከሌለ የተሟላ አይሆንም፡፡ እዚህ ጋር አርስቶትል ሰብዓዊ ፍጡር ከራሱ አስቀድሞ የሌሎችን ጥቅም ማስበለጥ ተፈጥሮው ነው ለማለት ፈልጎ አይደለም። እንዲሁም፣ ለሌሎች ሰዎች ደህንነት ያለን የተቆርቋሪነት ስሜት ገደብ-የለሽ ሊሆን ይችላል ወይም አለበት ብሎም አያስብም፡፡ እያለ ያለው፣ የሌሎች ጥሩ መሆን ወይም መጠቀም ለራሳችንም ጥሩነት አስፈላጊ አስተዋፅኦ ሊኖረው ይችላል ነው፡፡ ስለጓደኞቻችን ከሚኖረን ስሜትና ጓደኝነታችን ከወለዳቸው ሁኔታዎች ደስታንና እርካታን እናገኛለን፡፡ ጓደኝነት የተለያዩ ገፅታዎች አሉት፤ እናም ሁሉም በግላዊ ጥቅሞች የማይጠቁ አይደሉም። ሆኖም፣ ለእነሱ ስንል ጓደኞቻችንን ማፍቀር ከህይወት ከምናገኛቸው ከፍተኛ ደስታዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በሌላ በኩል፣ በሌሎች ደህንነት እና ደስተኛነት አንዳች ፍላጎት ካላሳደርን በማህበራዊ ፍጡርነታችን ያሉንን ተፈጥሯዊ ብቃቶች ለማሟላት አስፈላጊ ከሆኑት የመተሳሰብ እና የመተማመን ግንኙነቶች እራሳችንን ነጥለን አውጥተናል። በተጨማሪም፣ የሞራል ልዕልናዎች በቀዳሚነት ማህበራዊ ልዕልናዎች ናቸውና፣ ከሌሎች ተነጥለን ልንተገብራቸው አይቻለንም፤ አንድ ሰው ለጋሽ ወይም ፍትሃዊ ለመሆን እንደዚያ የሚሆንላቸው ሰዎች ያስፈልጉታል፣ ከሌሉ መሆን አይቻለውምና፡፡
እናም፣ አርስቶትል እንደሚያስቀምጠው፣ ራስ-ገዙ ማህበረሰብ ካቀፋቸው ነዋሪዎች ተፈጥሮ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሁለቱንም ሞራላዊ እና ቁሳዊ ፍላጐቶች በሙሉ የሚያሟላ ተፈጥሯዊ ማህበረሰብ ነው። ሰብዓዊ ፍጡራን ከዚህ ማህበረሰብ ከተነጠሉ ማንነታቸውን ያጣሉ – ልክ የተቆረጠ እጅ ከሌላው የሰውነት አካል የተነጠለ እንደሚሆነው፡፡ በእኛ እና አባል በሆንበት (ማሕበረሰብ) መካከል ባሉ ተጨባጭ መስተጋብሮች አማካኝነት ነው እኛነታችን የሚገለጸው። በተመሳሳይም፣ ከዚህ ግንዛቤ አንፃር ይህ የፖለቲካ ማኅበር ሁሉም የተሟላበት ማህበረሰብ ነውና፣ የፖለቲካ ጥናት ከሰብዓዊ ፍጡር ደስተኛነት ጋር ቁርኝት ካላቸው ሌሎች ጥናቶች ሁሉ የሚበልጥ ወይም የበላያቸው የሆነ ሳይንስ መሆኑ ጥርጥር እንደሌለው አርስቶትል ያምናል፡፡ የፖለቲካ ሳይንስ፣ የጋራ የሆነውን መልካም ወይም ጥሩ ነገር የሚያጠና ሳይንስ ነው፡- «የመጨረሻው ግቡ ለሰው ልጅ ጥሩ የሆነውን ማግኘት ሊሆን ይገባል» (Nicomachean Ethics 1:2)።
ይህ ፖለቲካን እንደ ሳይንሳዊ እና ትግበራዊ ምርመር አድርጎ የሚመለከተው ሐሳብ፣ አርስቶትል የተለያዩ የመንግሥት ሥርዓት ዓይነቶችን ለማነፃፀር እና ለመከፋፈል የሚጠቀምበት ነው፡፡ አርስቶትል መንግሥታዊ ሥርዓትን የሚተረጉመው፣ «በጥቅሉ ከተቋማቱ አንፃር፣ ግን ደግሞ በተለይ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ሉዓላዊ ከሆነ ተቋሙ አንፃር» ነው (Politics 3:6)፡፡ አርስቶትል፣ ፕሌቶ እንዳደረገው፣ ሌሎች ነገሮች ሁሉ የሚመዘዙበት ወይም የሚመነጩበት ሐሳባዊ ወይም አምሳል (ideal) የሆነ የመንግሥት ዓይነትን መሠረት ያደረገ መከራከሪያ ለማቅረድ አልፈለገም፡፡ በገሃዱ ዓለም ያሉ መንግሥታት ራሳቸውን የሚያደራጁበት በርካታ መንገዶች መቅረፃቸውን ያውቃል፤ እናም በተግባር ያለውን እንጂ ሊኖር ይገባል የምንለውን ማጤን የለብንም የሚለውን ሐሳብ ይቀበላል፡፡ ሌላው ቀርቶ ብልሹ የተባሉ አደረጃጀቶች እንኳን መሻሻል እንደሚችሉና ለአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ የተመቸ የሆነው ለሌላው ላይመች እንደሚችል ያውቃል፡፡ እነዚህ ድምዳሜዎች በይበልጥ የንፅፅሮሽ አካሄድ ውጤቶች ናቸው። አርስቶትል ለ158 የግሪክ ራስ-ገዝ መንግሥታት ለእያንዳንዳቸው ማህበረሰባቸውን መሠረት ያደረገ የመንግሥት ሥርዓት ጥናት እንደፃፈ (ወይም ጥናቱን በበላይነት ሲከታተል እንደነበር) ይነገራል፤ ሆኖም እስከዛሬው ዘመን ዘልቆ የሚገኘው ስለ አቴንስ ራስ-ገዝ የመንግሥት ሥርዓት የፃፈው “The Constitution of Athens” የተሰኘው ሥራው ብቻ ነው።
የአርስቶትል ንፅፅሮሽ ጠቅለል ባለ ድምዳሜ፣ የመንግሥት ሥርዓት ዓይነቶች በሦስት ሰፋፊ ምድቦች የሚከፋፈሉ መሆናቸውን ያስቀምጣል፡- የአንድ ሰው አገዛዝ፣ የጥቂቶች አገዛዝ እና የብዙዎች አገዛዝ፡፡ በእነዚህ ሦስት የመንግሥት ሥርዓት ዓይነቶች ዝርዝር ማብራሪያና በሂደት ሊለወጡ ስለሚችሉበት ይዘታቸው ላይ አተኩሯል። በይበልጥ የተረጋጋ ስለመሆንና ስለለውጥ ትግበራዊ ጥያቄዎችን በማንሳት ላይ አፅንዖት ይሰጣል። ጉልህ የሆነ ገለልተኛነት ባለው ምልከታ፣ በጣም መጥፎው ወይም የተሰናከለውም የመንግሥት ሥርዓት ቢሆን ይበልጥ የተረጋጋ ሊሆን የሚችልበትን መንገድ ይጠቁማል። እንደአርስቶትል፣ አንድ የመንግሥት ሥርዓት ዘላቂነቱ እና የተረጋጋነቱ የሚረጋገጠው ከአገዛዙ የሚገለሉት ሰዎች ቁጥር በተቻለ መጠን አነስተኛ በሚሆንበት መንገድ የአገዛዙን ባሕሪይ የ«ጥቂትነት» እና የ«ብዙነት» ንጥረ ነገር ሚዛናዊ በማድረግ ነው፡፡
በአጠቃላይ፣ የመንግሥት ሥርዓቱ ይበልጥ ለዘብ ያለ እና መሠረተ-ሰፊ በሆነ ቁጥር የተረጋጋ የመሆኑ ዕድል እየሰፋ ይሄዳል፡፡ በተመሳሳይ፣ አንድ ወጥ (pure) የሥርዓት ዓይነቶች አለመረጋጋት የሰረፀባቸው ናቸው፤ ምክንያቱም ሁሌም በውስጣቸው ቂም ያረገዙ ቡደኖችን የያዙ ናቸውና፡፡ የጥቂቶች መንግሥት (ኦልጋሪኪ) በቁጥር አብላጫውን በሚያዘው ደሃ ሕዝብ ላይ ጥላቻን ያሰርፃል፤ ዴሞክራሲዎች ደግሞ ጥቂት ቢሆኑም ተፅዕኖ አሳዳሪ የሆኑትን ሀብታሞች ያስቀይማሉ፡፡ እናም፣ ኦሊጋሪኪዎች የተወሰነ የፖለቲካ ሥልጣንን ለማጋራት የተቻላቸውን ያህል ብዙ ሰው ወደራሳቸው በማምጣት እራሳቸውን ሊጠብቁ ይችላሉ፤ ዴሞክራሲዎች ደግሞ የሀብት ክፍፍልን አስመልክቶ ለዘብተኝነትን በመከተልና ሀብታሙን ወገን የተከበረና ከፍ ያለ ሥልጣን ላይ በማስቀመጠ እራሳቸውን ይበልጥ የተረጋጉ ማድረግ ይችላሉ፡፡
ከሁሉም በላይ ዘላቂነት ያለውና የተረጋጋ የመንግሥት ሥርዓት የፖለቲካ ሥልጣን በሰፊው የመካከለኛ መደብ (መካከለኛ ገቢ ባለው የህብረተሰቡ ክፍል) እጅ ስር የሆነበት ነው፡- ይህም፣ የጥቂት ሀብታሞችም ሆነ የብዙሃኑ ንብረት-የለሾች ያልሆነ፣ ነገር ግን በተወሰነ መልኩ መካከል ላይ ያለ ነው። የመሀከለኛው መደብ አባላት በመንግሥት እርምጃዎች ላይ እንዲያማርሩ የሚያደርጋቸው ያን ያህል ሀብት የላቸውም፤ በሌላ በኩል ደግሞ በቂ የሆነ ሀብት ስላላቸው የላይኛውን መደብ ወይም ሀብታሙን የመንጠቅ ፍላጎት አያሳድሩም። ይህ ነው እንግዲህ የአርስቶትል አማካይ (mean) የተባለው አስተምህሮ መገለጫ፡፡
ሆኖም በፖለቲካ እና በሞራል መካከል የሚያስቀምጠውን የቅርብ ቁርኝት ተመልክተን ልንገምት እንደምንችለው፣ የአርስቶትል በመንግሥት ሥርዓት ላይ ያሳደረው ፍላጎት ነጣጥሎ የመመልከት ዓይነት አይደለም። የመንግሥት ሥርዓትን የሚመለከተው እንዲሁ እንደ አደረጃጀት ሳይሆን እንደ የሞራል ክስተት ነው። ከመረጋጋት እና ከዘላቂነት በተናጠል፣ የአንድ የመንግሥት ሥርዓት ሞራላዊ ብቃት የመዋቅር ጉዳይ ሳይሆን የዓላማ መገለጫነት ጉዳይ ነው፡፡ ገዥው ወይም የገዢዎች ቡድን የሚያነጣጥርበት ጥሩ ወይም መልካም የተባለውን የማመልከት ጉዳይ ነው፡፡ አሪስቶክራሲ (የላይኛው መደብ አገዛዝ) እና ዘውዳዊ ሥርዓት ጥሩ የመንግሥት ሥርዓት ዓይነቶች ሲሆኑ፣ ኦሊጋሪኪ እና የጨቋኝ ሥርዓት (tyranny) መጥፎ ወይም ቅጥ-የለሽ ናቸው፤ ያም ሆኖ አሪስቶክራሲ እና ኦሊጋሪኪ፣ ሁለቱም የጥቂቶች አገዛዝ ናቸው፡፡ ከውጭ በሚታየው የሥልጣን ክፍፍል አንፃር ተመሳሳይ ይመስላሉ፡፡ ሆኖም አሪስቶክራሲ ለብዙሃኑ ጥቅም የቆመ የምርጥ ጥቂቶች አገዛዝ ሲሆን፣ ኦሊጋሪኪ የሀብታሞች የራሳቸውን ጥቅም የማስጠበቂያ አገዛዝ ነው፡፡ በተመሳሳይ፣ ዘውዳዊ ሥርዓት እና ጨቋኝ ወይም አምባገነናዊ ሥርዓት የአንድ ሰው አገዛዞች ቢሆኑም፣ ዘውዳዊ ሥርዓት ለአብላጫው ጥቅም የቆመ ሲሆን፣ በተቃራኒው አምባገነናዊው ደግሞ ለራሱ ጥቅም ብቻ የሚገዛ ነው። አርስቶትል ፖሊቲ (polity) ብሎ የሚጠራው ለአብዛኛው ጥቅም የቆመ የብዙዎች አገዛዝ ነው፡፡ የእርሱ ተፃራሪና መጥፎ አቻው ዴሞክራሲ ደግሞ ውጤቱ የግልፍተ-ሕዝብ (mob) አገዛዝ ነው፡- ለብዙሃን ጥቅም የብዙሃን አገዛዝ። ጥሩ የመንግሥት ሥርዓቶች ለሁሉም አባላቶቻቸው ጥሩ የሆነውን በማረጋገጥ ለእውነተኛው የመንግሥት ሥርዓት ተፈጥሮ ምላሽ ይሰጣሉ፤ መጥፎ ወይም ቅጥ-የለሽ የሆኑ ሥርዓቶች ለከፊሉ አባላታቸው ጥቅም ብቻ በመቆማቸው ምክንያት ይህን ማድረግ ይሳናቸዋል።
አርስቶትል፣ ለሁሉም ዜጎቹ ጥቅም የቆመ ማንኛውንም የመንግሥት ሥርዓት ለመቀበል ዝግጁ ቢሆንም፣ በአጠቃላይ ከሁሉም በተሻለ መልኩ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል የፖለቲካ ማኅበር በመንግሥታዊ ትግበራዎች ላይ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎችን (ወይም በተቻለ መጠን ብዙ ነፃ የሆኑ፣ ባርያ ያልሆኑ የዚያው ዜጋ ሰዎችን) የሚያሳትፈው እንደሆነ ያስባል። በተመሳሳይም ከሁሉም የተሻለው ራስ-ገዝ የፖለቲካ ማህበረሰብ (polis) እራሱን ለማስተዳደር ብቁ በሆነ መልኩ ሰፊ የሆነው፣ ነገር ግን ሁሉም ሰው በአኗኗሩ ላይ ተሳታፊ ይሆን ዘንድ መጠኑ አነስ ያለው ነው። ዜጎች በጥሩ የመንግሥት ሥርዓት ስር አንድ በሚሆኑበት፣ ፍትሃዊ እና ለሁሉም በእኩል በሚሠሩ ሕጎች በሚተዳደሩበት፣ እንዲሁም ለአጠቃላዩ ሕዝብ ጥቅም ሁሉም የድርሻቸውን ሚና በሚጫወቱበት የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ የሰው ልጅ የሞራል ልዕልና እና የጥሩ ዜጋ የሞራል ልዕልና ተመሳሳይ ይሆናል። የጋራ ብልፅግናው (commonwealth) ሞራላዊ ዓላማ እጅግ ሙሉ በሆነ መልኩ እውን ይሆናል።
ፕሌቶ እና አርስቶትል፣ ከእነሱ በኋላ የተነሳ የፖለቲካ ፍልስፍና ሁሉ ክላሲካል ወይም ዘመን አይሽሬ አድርጎ የሚቆጥረውን የመንግሥት ሥርዓት አስተምህሮ አፍልቀዋል። ከእነሱ በኋላ ለነበረው ለሁሉም የምዕራቡ የፖለቲካ ፅንሰ-ሐሳብ፣ እውቅና ለሰጠውም ሆነ ላልሰጠው፣ ባለውለታዎች መሆናቸው አያሻማም። መንግሥት የአባላቱን ህይወት ለማነፅ በተፈጥሮ የመጣ ነው የሚለው ሰፊው ድምዳሜያቸው፣ ብቸኛው ባይሆንም እንኳን በዋነኝነት ለአሥራ-አምስተኛው ክፍለ ዘመን ለአዲሱ እና ለክርስቲያናዊው የፖለቲካ ዓይነት መመስረት ጉልህ ሚና የነበረው የፖለቲካ ማኅበር ፅንሰ-ሐሳብ ነው። ይህ በራሱ የስኬታቸው መለኪያ ነው።
ለበለጠ ንባብ
ቀዳሚ ምንጮች፡
Nicomachean Ethics, ed. W.D. Ross (Oxford: Oxford University Press, 1980).
Politics, ed. C. Lord (Chicago, IL, and London: University of Chicago Press,
1984).
ተቀፅላ ምንጮች፡
Coleman, J.: A History of Political Thought, vol. 1 (Oxford: Blackwell, 2000).
Davis, M.: The Politics of Philosophy (Lanham, MD: Rowman & Littlefield, 1996).
Hardie, W.F.R.: Aristotle’s Ethical Theory (Oxford: Oxford University Press, 1968).
Kraut, R.: Aristotle (Oxford: Oxford University Press, 1995).
Mulgan, R.G.: Aristotle’s Political Theory (Oxford: Clarendon Press, 1977).