ፖለቲካ/ፍልስፍና

የቶማስ ሙር “ዩቶጵያ” – ሰር ቶማስ ሙር (1478-1535)

ሰር ቶማስ ሙር የተወለደው በለንደን ከተማ ነው። የተሳካለት ጠበቃ ልጅ ነው። ከፊል የልጅነት ዕድሜውን በካተርቡሪ ሊቀ-ጳጳስ እና ሎርድ ቻንስለር በነበረው በጆን ሞርተን ቤተሰብ ውስጥ ነው። ሙር የተወሰኑ ዓመታትን ከካርቱሲያን መነኩሴዎች (በ1084 በቅዱስ ብሩኖ አማካኝነት የተመሠረተውን የሮማ ካቶሊክ ዘርፍ ከሚከተሉ መነኩሴዎች) ጋር አሳልፏል፤ ብዙ ጊዜም የሚስበው ሃይማኖታዊ ህይወት ይኽኛው ነበር። ለሕግ ባለሙያነት በስፋት የተማረና የሰለጠነ ሰው ነው። በሕግ ሙያ ላይ ከመሰማራቱም ባሻገር፣ በ1504 የፓርላማ አባል ለመሆን የበቃ ሲሆን፣ የንጉሡንም ትኩረት ለመሳብ ችሏል። በሔነሪ 8ኛ ዘመን የመንግሥት ኃላፊና ዲፕሎማትም ነበር፤ እንዲሁም በ1529 ከተለያዩ ሹመቶች በኋላ የኢንግላንድ ሎርድ ቻንስለር (የፍትሕ አካሉ የበላይ) መሆን ችሏል (ተራ ዜጋ ወይም መኳንንታዊ የዘር ሀረግ የሌለበት ዜጋ ይህንን ቦታ ሲይዝ ለመጀመሪይ ጊዜ ነው።) ከመንግሥታዊ የሥራ ህይወቱ ባሻገር፣ ቶማስ ሙር ዘመን አይሽሬ የሚሰኝ ልሂቅ፣ የሰሜናዊው ሬኔይሳንስ ቀዳሚ ተጠቃሽና የኤራስመስ (የሰሜን አውሮፓን ሬኔይሳንስ ዘመን የመራው) የቅርብ ጓደኛ ነበር።

ሙር ተወዳጅ እና አዋቂ ሰው የነበረ ሲሆን፣ ይህም በላቲን ቋንቋ ተፅፎ በ1516 በታተመው “Utopia” በተሰኘው እጅግ ታዋቂ መፅሐፉ ላይ ተንፀባርቋል። ይሁንና ግን በከፍተኛ መጠን ሃይማኖተኛ የነበረ ሲሆን፣ የመፅሐፉን መታተም ተከትሎ የመጣው የሃይማት ተሃድሶ እንቅስቃሴ (Reformation) ሌላ ማንነቱን እንዲገልጥ አድርጎታል፤ የሃይማኖት ተገንጣዮችን እጅግ በከባዱ አውግዟል። ዩቶፒያ (Utopia) መፅሐፉ፣ ኋላ ላይ ተቀባይነት አጥቷል (ከሌሎች ነገሮች ውጪ ለሃይማኖት መቻቻል ሞዴል የሆነ ህብረተሰብን የሳለበት መፅሐፍ ነው)፤ እርሱም ቢሆን ወደ እንግሊዝኛ እንዲገለበጥ አልፈቀደም። የሙር የሃይማኖት ምልከታዎች ወደኋላ ላይ ከንጉሡ ጋርም ችግር ውስጥ ከተውታል፤ ንጉሡ የቤተ-ክርስቲያኗ የበላይ ተጠሪ የመሆኑን ነገር ሊቀበለው ባለመቻሉ ምክንያት። በዚህ እምነቱ ሳቢያ የጽድቅ መስዕዋት (martyrdom) እንዲሆን አልመረጠምና፣ አሉ በተባሉ የሕግ መንገዶች እራሱን ለመከላከል ሞክሯል። ሆኖም በስተመጨረሻ በንጉሡ ቃል መገዛት ባለመፍቀዱ፣ በ1535 በሀገር ክህደት ተወንጅሎ አንገቱን ይቀላል። የሮማ ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያ በ1886 ህይወቱ የተቀደሰ እንደነበር፣ እንዲሁም በ1935 ከቅዱሳን አንዱ እንደሆነ አውጃለታለች፤ ጁላይ 9 የዝክር ቀኑ ሆኖ የተሰየመለት ሲሆን በቤተ-ክርስቲያኗ ዘንድም ቅዱስ ቶማስ ሙር በመባል ይጠራል።

ለፖለቲካ ፅንሰ-ሐሳብ የሙር አስተዋፅኦ ሙሉ ለሙሉ በአጭር መፅሐፉ ላይ የተመረኮዘ ነው። “Concerning the Best State of a Commonwealth and the New Island of Utopia” የሚለው የመፅሐፉ ርዕስ ይሁን እንጂ፣ ይበልጥ የሚታወቀው “Utopia” በመባል ነው። አስደናቂ ሥራ ቢሆንም በጣም ውስብስብ እና ግልፅ ያልሆነ ነበር፤ እንዲሁም የደራሲውን ማንነት የሚያንፀባርቅ ነው። ዓላማው ምን ነበር የሚለው እስካሁንም ድረስ ምሁራን የሚከራከሩበት ጉዳይ ነው። የዩቶፒያ (Utopia) አሻሚነት ከርዕሱ ይጀምራል። ቃሉ በሁለት የግሪክ ቃላት አማካኝነት የትርጉም ጨዋታ የሚጫወት ነው፤ “u-topia” ማለት ስፍራ-የለሽ (no place) ሲሆን፣ “eu-topia” ደግሞ የሐሴት ስፍራ (happy place) ማለት ነው። አሻሚነቱ በመፅሐፉ ውስጥ ማዕከላዊ በሆነው ገፀ-ባሕሪይ ራፌል ሂትሎዳይ ስም ላይም ይቀጥላል፤ ራፌል (ሩፋኤል) ትርጓሜው የእግዚአብሔር መልዕክተኛ ሲሆን፣ ሂትሎዳይ ደግሞ የሚናገረው ፍሬ-ፈርሲኪ የሆነ ማለት ነው። ከዚህም በላይ ይህ ገፀ-ባሕሪይ ታሪኩን የሚነግራቸው ሁለቱ ገፀ-ባሕሪያት እራሱ ሙር እና በህይወት ያለ ሌላ ጓደኛው ናቸው፤ እንዲሁም ይህን የሚነግራቸው በትክክልም በተደረገ (ወደ ምዕራብ አውሮፓ ሀገራት በሄዱበት የዲፕሎማቲክ ተልዕኮ) ጉዞ ላይ ነው። እነዚህ እና አያሌ ሌሎች እንቆቅልሾች፣ ቀልዶች እና አሳዛኝ ሁኔታዎች መፅሐፉን በቁም ነገር ለመውሰድም ሆነ ደራሲው ምን ለማለት እንደሞከረ ለማወቅ ግራ የሚያጋቡ ይሆናሉ።

ዋናዎቹ ገፀ-ባሕሪያት ከተዋወቁ በኋላ ስለ የፖለቲካ ህይወት ጥሩና መጥፎ ጎኖች፣ እንዲሁም የሔነሪ 8ኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ሊገጥሟቸው ስለሚችሉ ማህበራዊ ችግሮች፣ በተለይም ስለ ድህነት፣ ስለ አደገኛ ቦዘኔነት እና ስለ ወንጀል ውይይቶች ተደርገውበታል። በተከታይም ዩቶፒያ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ የሚያቀርብ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፤ ሆኖም ይህ ከግልፅነት የራቀ ነው።

የመፅሐፉ ማዕከላዊ ገፀ-ባሕሪይ ስለጎበኛት አስደናቂ ስፍራ የሚተርክ መንገደኛ ነው፤ በደሴት ላይ ስለሚኖሩ ሕዝቦች፣ ዩቶፒያ ስለተባለ ህብረተሰብ ይተርካል፤ ከክርስቶስ ልደት በፊት በሦስተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ዩቶፐስ በተባለ ንጉሥ አማካኝነት ስለተመሠረተ ማህበረሰብ። አንድ ሀገር አይደለም፤ ይልቁንም አምሳ-አራት እራሳቸውን የቻሉ፣ ግን ደግሞ በሚያስገርም መልኩ አንድ ወጥ የሆኑ ራስ-ገዝ ከተማዊ መንግሥታት (city-states) ያሉበት ፌዴሬሽን ነው። ተወካዮቻቸው የጋራ ችግሮቻቸውን ለመወያየት በዓመት አንድ ጊዜ ይሰበሰባሉ፤ ሆኖም መላ ደሴቷን የሚያካልል አስፈፃሚ አካል የለም። በእያንዳንዱ ከተማ ሁሉም ሕዝቡ፣ ወይም ቢያንስ በቤተሰብ ደረጃ፣ ነገሮችን የሚያስተባብሩና 200 አባላት ያሉት ጉባኤ የሚመሠርቱ ኃላፊዎችን ይመርጣሉ፤ ይህ ጉባኤም በተራው ሃያ አባላት ያሉት ሴኔትን የሚመሠርቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ይሾማሉ። በሕዝቡ ከታጨ በኋላ መልካም ፀባዩን መሠረት በማድረግ በምክር ቤቶቹ አማካኝነት የተመረጠ አንድ ልዑል አለ፤ የሥልጣን ዘመኑም ዕድሜ ልክ ነው።

ዩቶፒያ፣ ምንም ዓይነት የግል ንብረት የሚባል ነገር ባይኖርም፣ እጅግ የሞላና የተትረፈረፈላት ደሴት ናት። የከበሩ ማዕድናት እንደመኩራሪያነት ይታዩ እንጂ፣ ሁሉም ሰው የሚያስፈልገው ይሟላለታል፤ ምግብ፣ መጠለያና ሌሎች መሠረታዊያን የጋራ ከሆነው ምንጭ ወይም ሀብት የሚሟላላቸው ሲሆን፣ በጋራ የመመገብ ሥርዓት አለ፤ እንዲሁም ሁሉም የመሥራት ግዴታ አለበት። በዩቶፒያ በዘር ሀረግ ላይ መሠረት ያደረገ የመደብ ክፍፍል የለም፤ የእኩልነት መርሆ እጅግ አድርጎ የሰፈነበትና በብቃት ወይም በችሎታ የሚያምን ህብረተሰብ ነው። ሆኖም ሁሉም የመንግሥት ኃላፊዎችና የሃይማኖት መሪዎች ተመርጠው የሚወጡበት የምሁራን መደብ አለ። አብዛኛው የህብረተሰቡ አባላት በትርፍ ጊዜያቸው እውቀታቸውን የሚያዳብሩ ቢሆንም፣ የምሁርነት ተስፋ የተጣለባቸው ሕፃናት በልጅነታቸው ተለይተው ይመረጣሉ። ምሁራን የጉልበት ሥራ እንዲሠሩ አይገደዱም፤ ነገር ግን የተቀረው ሰው ከግብርና እና ከሌሎች ከተማ-ነክ የዕደ-ጥበብ ሥራዎች መካከል አንዱን መርጦ በቀን እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ መሥራት ይገባዋል።

በተመሳሳይ ሰዓት ደግሞ፣ ዩቶፒያ እጅግ ግዞት ጠያቂ (authoritarian) ህብረተሰብ ነው፤ ጥብቅ የሆነ ማህበራዊ ሥነ-ሥርዓት አለ። ከተለመደው የቀን ተቀን ተግባር ውጪ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ የአካባቢ ሽማግሌዎችን ወይም የመንግሥት ኃላፊዎችን ፈቃድ ማግኘት የግድ ነው። የሞት ቅጣት አልፎ አልፎ ቢሆንም፣ የዩቶፒያ ሕግ እጅግ ጥብቅ ነው። ከፍተኛ ወንጀሎች ለባርነት ይዳርጋሉ፤ ባርያዎች የሌላውን ሕዝብ ሥራ ደግፈው ይሠራሉ።

ዩቶፒያኖች ሞራልን እና ሃይማኖታዊ እምነቶችን በተመለከተ አስደናቂ የሆነ መቻቻል አላቸው፤ የተለያዩ ዓይነት የአምልኮ ሥርዓቶች ይገኛሉ። ሆኖም ሁሉን ፈጣሪ የሆነ አንድ አምላክ ስለመኖሩ አጠቀላይ መግባባት ያለ ሲሆን፣ ሁሉም ሰው የሚቀበላቸው የተወሰኑ የሞራል መርሆዎችም አሉ። ዩቶፒያኖች ክርስትናን ለመቀበል ዝግጁነት ያላቸው ይመስላሉ፤ ምክንያቱም ለሞራላዊ እሳቤዎቻቸው የቀረበ ነውና። እዚህ ጋር የሚንፀባረቀው ነጥብ፣ ከቅዱስ ቶማስ አኩዊናስ በተመዘዘ መልኩ፣ ሃይማኖት እና ሞራላዊነት በመሠረታዊ ሁኔታ ምክንያታዊ መሆናቸውና ከፍፃሜም ለመድረስ ራዕይ አስፈላጊ መሆኑን ነው። ዩቶፒያኖች በከፍተኛ ደረጃ ምክንያታዊ ሕዝቦች በመሆናቸው፣ እነዚህን ነገሮች ልክ እንደ ጥንታዊት ግሪክ ሕዝቦች በራሳቸው አግኝተዋቸዋል።

እያንዳንዱን ጥያቄ ምክንያታዊ እና አስተውሎ በተሞላበት መንገድ የመመለስ ተሞክሮ ያላቸው ዩቶፒያኖች፣ ፍፁም የሆነ ሕብራዊነት እና ደስተኛነት የሰፈነበት ዓለም ፈጥረዋል። ይሁንና ግን የክርስቲያን ህብረተሰብ ባለመሆኑ ምክንያት ብቻ፣ ይህ የቶማስ ሙር ፍፁም የሆነ ህብረተሰብ የግል ራዕዩ ሊሆን አይችልም። ይህም፣ መፅሐፉ ስለምን ምክንያት ሲባል ተፃፈ ወደሚለው ጥያቄ ይመልሰናል።

የቶማስ ሙር ዩቶፒያ መፅሐፍ በይበልጥ የሬኔይሳን ሂዩማኒዝም ሥራ ነው፤ ሂዩማኒዝም የሬኔይሳንስ ዘመንን በቀዳሚነት የመራና ለሰው ልጅ ብቃት ወይም ችሎታ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጥ አስተምህሮ ነው። በመካከለኛው ዘመን ከነገሰው አስተሳሰብ ይልቅ፣ ሰብዓዊ ፍጡራን የማስተዋል ብቃታቸውን በመጠቀም ሊያሳኩ ስለሚችሉት ውጤት ከፍተኛ ምልከታን ያንፀባርቃል። የዩቶፒያ ህብረተሰብ አባላት፣ ከሂዩማኒዝም ተከታዮች ምልከታ አንፃር ከጥንታዊቷ ግሪክ ሕዝቦች ጋር ከፍተኛ መመሳሰል አላቸው። መፅሐፉ፣ ቶማስ ሙር ለግሪክ እሳቤዎች እና ሥነ-ፅሁፎች የነበረውን ጥልቅ አድናቆት ያሳያል፤ በተለይም እጅግ የሆነ መነቃቃትን ላሰረፀበት፣ “Republic” ለተሰኘው የፕሌቶ ሥራ። እዚህ ጋር በሁሉም ዘንድ የሚተገበር ሆነ እንጂ፣ የማህበረሰቡ የጋራ ህይወት አኗኗር ከፕሌቶ ጋርዲያንስ ወይም “ጠባቂዎቹ” ከተባሉ የሪፐብሊኩ ማህበረሰብ ክፍሎች ምግባር ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ አለው። ከፕሌቶ ከተገለለው የጋርዲያንስ አዋቂነት ይልቅ፣ በዩቶፒያ በመላው ህብረተሰብ ዘንድ የተንሰራፋ የምሁራዊነት ጥማት እና አድናቆት አለ። ዩቶፒያ የሬኔይሳንስ ሂዩማኒስቶች ገነት ናት።

ሃይማኖት እና አስተሳሰብን በተመለከተ፣ ልክ እንደ ሬኔይሳንስ ሁሉ መፅሐፉም መቻቻልን የሚሰብክና ሃይማኖታዊ ብዝሃነትን የሚፈቅድ ነው። የሞራል ፍልስፍናንም ቢሆን ነገሮችን ቀለል ባለና ሥነ-ፅሁፋዊ በሆነ፣ ግን ደግሞ ጉልህ ቦታ በሚሰጥ መንገድ የሚያወያይ ሲሆን፣ በይበልጥ የሬኔይሳንስ ሂዩማኒስቶች አተገባበር ነው። ሆኖም ከወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታዎች ጋር ምን ያህል ተዛምዶ እንዳለው፣ ወይም የተፃፈውም ተዛምዶ እንዲኖረው ተደርጎ ስለመሆኑ በትክክል ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። በዚያ ዘመን ስለነበረ ህብረተሰብ መደበኛ ችግሮች በጥልቀት የሚያወያይ እና የሚያብራራ ነው። ግን ደግሞ በከፊል ሽሙጣዊ መፅሐፍ ነው። በርግጥ በመፅሐፉ ላይ የተገለፀው የቶማስ ሙር የህብረተሰብ አምሳል (ideal) አለመሆኑ ግልፅ ነው፤ ሆኖም በተወሰነ መንገድ፣ የሰው ልጆች ምክንያታዊ መሆን ቢቻላቸው ሊሳካ የሚችለውን ውጤት የሚያንፀባርቅ የህብረተሰብ አምሳል ወይም ተምሳሌት ስለመሆኑ አያጠራጥም። ከዚህ አኳያም፣ ከመንፈሳዊ መዝሙር አንስቶ እስከ የጦርነት ስልት በደረሱ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ለቶማስ ሙር ምልከታዎች መንሸራሸሪያቸው ነበር።

ዩቶፒያ የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን ያካተተ ነው። ነገር ግን፣ የሙር ዓላማ ምንም ይሁን ምን፣ “ዩቶፒያ” የሚለውን ቃል መሠረት ያደረጉ የሥነ-ፅሁፍ ሥራዎች ለእነዚህ እና ለሌሎች ብዙ ዓላማዎችም ሲባል እስከዛሬ ድረስ ጥቅም ላይ ሲውሉ ቆይተዋል። አምሳል (ideal) የሆነ ህብረተሰብን በመቅረፅ ረገድ የቶማስ ሙር “ዩቶፒያ” መፅሐፍ የመጀመሪያው ባይሆንም (በተለይ በጥንቱ ዓለም የሥነ-ፅሁፍ እና የፍልስፍና ሥራዎች ላይ የሚገኝ ቢሆንም)፣ በርግጥም “ዩቶፒያ” የሚለውን ቃል የቀመረው እርሱ ነው፤ ይህንንም ተከትሎ ነው ራስ-አወቅ የሆነ የዩቶፒያ አፃፃፍ ባሕል የጀመረውና እስካሁንም የዘለቀው። ይሁንና ግን የዩቶፒያ ሥነ-ፅሁፍ ባሕል ምንነት እና ዓላማው እስካሁን ድረስ ለጥያቄዎች ክፍት የሆነና ምሁራን መከራከራቸውን የቀጠሉበት ጉዳይ ነው።

Fifty Major Political Thinkers, Ian Adams and R. W. Dyson

ለበለጠ ንባብ

ቀዳሚ ምጮች

Utopia (Cambridge: Cambridge University Press, 1989).

ተቀፅላ ምንጮች

Cousins, A.D. and Grace, D. (eds): More’s Utopia and the Utopian Inheritance (Lanham, MD: University Press of America, 1995).

Guy, J.A.: Thomas More (Oxford: Oxford University Press, 2001).

Hexter, J.H.: More’s Utopia: The Biography of an Idea (Harper, 1965).

Kenny, A.J.P.: Thomas More (Oxford: Oxford University Press, 1983).

Logan, G.M.: The Meaning of More’s Utopia (Princeton, NJ: Princeton University Press, 1983).

Olin, J.C. (ed.): Interpreting Thomas More’s Utopia (New York: Fordham University Press, 1989).

Surtz, E.: The Praise of Wisdom (Chicago, IL: Chicago University Press, 1957).

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.