እድሉ ያመለጠን ይመስለኛል፤ ግን ሰውነታችንንም እንዳይነጥቀን እንዘጋጅ!
ከሁሉ ቀድሞ የመጀመሪያውን ጃፓናዊ በቫይረሱ መያዝ ለሕዝቡ የተናገረው ታከለ ኡማ ነው፡፡ ከዚያም በኋላ ብዙ ጥረቶችን አድርጓል፤ እጅ መታጠብ፣ ማስታጠብ፣ ሳኒታይዘር ማደል እና የመሳሰሉት
ታከለ ዛሬ ፖስት ባደረጋቸው መልዕክቶች ሰብዓዊነታችንን እንዳናጣ ማስገንዘብ ጀምሯል፤ “የመተሳሰብ የማካፈል ጊዜ ነው” ብሏል፡፡ ይህ የሚበረታታና ከዚህ በኋላም በደንብ ሊሰራበት የሚገባ ሃሳብ ነው፡፡
ትናንትና አንዲት ሴት ቤቷን ለአንድ ዓመት ለኮሮናቫይረስ ህመምተኞች ለይቶ ማቆያነት ለገሰች ያለንም እርሱ ነው፡፡ ይታያችሁ ለአንድ ዓመት! ይህ ምን ማለት ነው? ምን ቢገመት፣ ምን ቢታወቅ ነው?
ይህ እንዴት አስቀድሞ አልተገመተም? በቃ አዲስ አበባ እና አዳማ የመጀመሪያው ቀን ላይ ኳራንቲ መደረግ የነበረባቸው ይመስለኛል፡፡ እንደኔ ግምት ቫይረሱ ወደ ብዙ የሀገራችን ከተሞች ተዛምቷል፡፡ ይህን ደግሞ መንግሥታችንም ሆነ የሌሎች ሀገራት መንግሥታት በደንብ አውቀውታል፡፡
* * * *
የአውስትራሊያ አምባሳደር ዛሬ ያስተላለፉትን መልዕክት ለተመለከተ፣ የእኛ ሀገር ነገር እንዳበቃለት መገመት አያዳግተውም፡፡ እስቲ ይታያችሁ 12 ሰው የተያዘበት ሀገር ውስጥ ያሉ ዜጎቹን በጠቅላላ በተቻላችሁ መንገድ ከኢትዮጵያ ውጡና 2400 በላይ ሰው ወደተያዘበት ወደ ሀገራችሁ ወደ አውስትራሊያ ሂዱ ብለው አምባሳደሩ ሲናገሩ ምን ይሰማችኋል? አንድም የቫይረሱን በኢትዮጵያ መሰራጨት ተረድተዋል፣ አንድም በመንግሥታችን ቀውሱን ለመቆጣጠር በሚያደርገው ጥረት ወይም አቅም ፍፁም እምነት የላቸውም፡፡
ሁሉም ሀገራት ዜጎቹን ጠርቷል፤ በአፍሪካ የባሰ እንደሚሆን ቀድሞ ተረድቷል፡፡ የመንግሥት አመራር አቅም ብቻ አይደለም፤ የገንዘብ ችግርም አለብን፤ ደሃዎች ነን፡፡ ድህነት ብቻም አይደለም፤ ነገሩ ሲብስ ህዝቡም ሥርዓት አይኖረውም ተብሎ ይሰጋል፡፡
ብቻ በታከለ ኡማ መጀመሬ ነገሩ ያመለጠን ስለመሰለኝ ነው፡፡ ገና ያኔ አዲሳባን መዝጋት ነበረበት፡፡ ከአስፈላጊ ስርጭቱን መቆጣጠሪያ እና ቀለብ ከማጓጓዝ እንቅስቃሴዎች በስተቀር ወደ ከተማዋ መግባት እና መውጣት መታገድ ነበረበት የሚል ነገር ስለተሰማኝ ነው፡፡ ምናልባትም ጃፓናዊ የረገጣቸውን ከተሞች ጨምሮ፡፡
* * * *
ነበር አያኮራም፤ ግን ወደድንም ጠላንም እድሉ አምልጦናል፡፡ የድንገቴ የሚመስሉ የመንግስት እርምጃዎች ያስፎግራሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲ ቅሩ፣ ከዚያ ወደቤታችሁ ሂዱ፡፡ ቡና ቤቶች ይዘጉ፤ የትኞቹ ዓይነት? ቁርጥ ያለ ነገር አይነግሩንም፡፡ በቃ ሁሉም ሰርቪስ ቱ-ጎ ወይም ይዞ መሄድ እንጂ መጠቀም መከልከል ነበረበት፡፡ የአዲሳባ ሕዝብ ዛሬም ክብ ሰርቶ ቢራ ሲጠጣ ነው የሚያመሸው ፡፡
የተቀናጀ ነገር የለም፡፡ አሁንም ሳንዘናጋ አስከፊውን እንጠብቅ፡፡ መንግሥት በቀናት (ወይም በሰዓታት) ውስጥ የሚወስደው እርምጃ የሚሆነው ወታደራዊ ነው ፤ ሌላ ምርጫ አይኖረውም፡፡
አንዴ ፈጣሪ አምጥቶታል፤ ብቻ ሰብዓዊነታችንን እንዳይነጥቀን! እንዳንዘራረፍ፣ እንዳንገዳደል፣ እንዳንበላላ! ለራሳችን የምናስበውን ያክል ለሌሎችም እናስብ፡፡ አደራ ሰውነታችንን እንዳንረሳ፣ አደራ! ማለት የምችለው ይሄን ብቻ ነው ፤ ታኬም ሆነ አብይ፣ እንዲሁም የየክልሉ አመራሮች አንዴ አምልጦናልና ስለደግነት ስለመተሳሰብ ብቻ ስበኩ፣ አስገንዝቡ፣ በቶሎ እና በተሻለ መንገድ መቋቋም ላይ አተኩሩ፡፡ ሕዝባችሁ ከጎኑ ሰው መሞቱ ይቅርና በቫይረሱ መያዙ እየበረከተ ሲመጣ እንደማያ እንዳይለወጥባችሁ ከአሁኑ ሊከሰት የሚችለውን ችግር በግልፅ ንገሩት፤ ይዘጋጅበት፡፡ ሠራዊታችን ሲሰማራም፣ ሥርዓት አልይዝም ወይም ትዕዛዝ አልሰማም ያለን የዕለት ጉርስ ያጣ ዜጋን በጥይት መግራት ከነጭራሹ እንዳይታሰብ ከአሁኑ ይሰመርበት! አደራ!
በማኅደር አካሉ
Photo credit: Capital Ethiopia Newspaper