FEATUREDፖለቲካ/ፍልስፍና

“ፈላስፎች መሪ መሆን አለባቸው፤ ወይም መሪዎች ፈላስፋ ይሁኑ”፦ፕሌቶ (427-347 ዓ.ዓ)

የፕሌቶ ፍልስፍና፣ ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል፣ በሌላ ሰው አንደበት የቀረበ ሆኖ ለየት ያለ መልክ አለው። ከጥቂቶቹ በስተቀር፣ ሁሉም ሥራዎቹ ምልልሶች (ውይይቶች) ናቸው፤ በሚገናኛቸው ሰዎች መካከል የሚደረጉ በፅሁፍ መልክ የቀረቡ እውነተኛ ወይም ሐሳበዊ ውይይቶች። ከተነጋጋሪዎቹ ውስጥ፣ መምህሩ ሶቅራጠስ የአምበሳውን ድርሻ ይይዛል። በምልልሶቹ ውስጥ ፕሌቶ መጠቆም የፈለጋቸው አስተምህሮዎች የሚገለፁት በሶቅራጠስ ነው። በመርህ ደረጃ፣ የሶቅራጠስን አመለካከቶች ፕሌቶ በእርሱ ስም ካስቀመጣቸው አመለካከቶች ውስጥ መለየት ይቻላል፤ ነገር ግን መለያያ ነጥቡ አስቸጋሪ ነው። እኛም ይህንን ለማድረግ አንሞክርም።

ሶቅራጠስን በተመለከተ የምናውቀው ከፕሌቶ ምልልሶች፣ ከዜኖፎን ፅሑፎች፣ እንዲሁም በአሪስቶፋነስ ኮሜዲ (Clouds) ላይ ከተገለፀበት እውነታ ሊነቀስ የሚችለውን ብቻ ነው። በሙያው ድንጋይ ጠራቢ ሲሆን፣ ጊዜውን ከጓደኞቹ ጋር ፍልስፍና በመወያየት ማሳለፍን ይመርጣል። ምንም ነገር አልፃፈም። አመክኒዮአዊ የውይይት ዘዴው “ኢሌንቾስ” ተብሎ የሚጠራውን፣ እሳቤዎችን በጥያቄና መልስ ይበልጥ ግልፅ የማድረግ ሂደትን ያካተተ ነው። እራሱን የሚመለከተው አንድ የሆነ አዲስ ነገርን እንደሚያስተምር ሳይሆን፣ ሰዎች ቀድሞውኑ የሚያውቁትን እንዲረዱት እንደሚያበረታታ አድርጎ ነው። እንዲሁም ሰዎች እናውቃለን ብለው የሚያስቡት በጭራሽ እውቀት እንዳልሆነ እንዲገነዘቡ የመጨቅጨቅ ተልዕኮ ያነገበ «አዋኪ» ወይም «ጨቅጫቂ» (gadfly) ሲል እራሱን በራሱ የሰየመ ነው።

ፕሌቶ ከ409 ዓመተ ዓለም (ከክርስቶስ ልደት በፊት) ጀምሮ ሶቅራጠስ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ የሶቅራጠስ ጓደኛ እና ተማሪው (ደቀ መዝሙሩ) ነበር። ፕሌቶ የሦስት የገዛዘፉ የፖለቲካ ሥራዎች ደራሲ ነው፡- “Republic”፣ “Politicus” ወይም “Statesman”፣ እንዲሁም “Laws” በተሰኙ ርዕሶች። ሌሎቹ ብዙ ቁጥር ያላቸው ምልልሶቹም – በተለይም “Crito” – ወሳኝ የፖለቲካ አስተምህሮዎችን የያዙ ወይም የሚጠቁሙ ናቸው፤ ነገር ግን የእርሱ የፖለቲካ ፍልስፍና ተፅዕኖ ባሳደረ መልኩ በዝርዝር የተገለፀውና እይታንም ያገኘው “Republic” በተሰኘው ሥራው ነው። በይበልጥ የምናተኩረውም እዚሁ ላይ ይሆናል።

የፕሌቶ የጉልምስና ዘመን ከ431-404 ዓ.ዓ ጊዜ ውስጥ በተካሄደው፣ በፔሎፖኔሲያን ጦርነት የአቴንስ መሸነፍን ተከትሎ ከነበረው የፖለቲካ ሽግግር ዘመን ጋር የተገናኘ ነበር። የፔሪክለስ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገርሰስ እና ሰላሳ አባላት ያሉት የኦሊጋርኪ (የመንግሥት ሥልጣን በተወሰኑ ሰዎች የሚያዝበት ሥርዓት) ምክር ቤት አገዛዝ መመስረት፣ የጦርነቱ ሽንፈት ቀጥተኛ ውጤት ነበሩ። ፕሌቶ ይህ ኦሊጋርኪ የተሳካ የድህረ-ጦርነት መልሶ ግንባታን ያካሂዳል (ይመራል) የሚል ትልቅ ተስፋ ነበረው፤ ሆኖም እንዲህ ያለው ተስፈኝነቱ ብዙም ሳይቆይ መና ሆኗል።

በተለይም የኦሊጋርኪው እጅግ ታዋቂ አባልና የፕሌቶ አጎት በነበረው፣ በክሪሺያ ባሕሪይ አማካኝነት ኦሊጋርኪው መደበኛ የሞራላዊነት መመዘኛዎችን በከፍተኛ መጠን ወደጎን በመተው ይታወቃል። ክሪሺያ በሁሉም መመዘኛዎች ጨካኝ እና ራስ ወዳድነት የተጠናወተው ፖለቲከኛ ነበር። «ሰላሳዎቹ ጨቋኞች»፣ የአገዛዛቸው መልካምነት መጀመሪያ ሰሞን ታይቷቸው የነበሩ የአቴንስ ባለፀጎችን ባዶ እጅ እስከማስቀረት የደረሱ መራር የመንግሥት ዘዴዎችን ወይም ስልቶችን ይጠቀማሉ። በትራሲቡለስ መሪነት፣ በ403 ዓ.ዓ የተደረገው በአብዮት ላይ አብዮት ጠራርጎ ካወረደው በኋላ፣ የቀድሞውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በቦታው አስቀመጠው። በዚህ በአዲሱ ሥርዓት ነበር ሶቅራጠስ የሞተው፤ በአስገራሚውና ምናልባትም በተሳሳተው «ከተማው እውቅና ለሰጣቸው አማልክት እውቅና አልሰጠህም… አዲስ አማልክት አስተዋውቀኻል [እና] ወጣቶችን አጭበርብረኻል [መርዘኻል]» ክስ የተወገዘው። ሶቅራጠስ የፖለቲካ ሰለባ ነበር ማለት ይቻላል። ምንም እንኳን ከሁሉም ከሰላሳዎቹ ጋር የግል ግንኙነት ባይኖረውም የተሻላ ከነበረው ክሪሺያ ጋር ግን የጠበቀ ግንኙነት ነበረው። እንዲሁም ኦሊጋርኩ ቻርሚደስ የእርሱ ክብ ጠረጴዛ አባል ሲሆን፣ የፀረ-ዴሞክራሲነት አዝማሚያ ከነበረው አልቺባይደስ ጋርም ጓደኛ ናቸው። አንደበተ-ርቱው ኤስቺነስ፣ በ345 ዓ.ዓ እንደነገረን ከሆነ፣ ሶቅራጠስ ከክሪሺያ ጋር በነበረው ግንኙነት ምክንያት የተወገዘ ነበር።

የሶቅራጠስ ውግዘት ለፕሌቶ የመጨረሻ ማንነት ወሳኝ ክስተት ነበር። የክቡር መምህሩን ህይወት መዘከር ተልዕኮው ሆነ። በ399 ዓ.ዓ ፕሌቶ አቴንስን ለቅቆ በፈቃደኝነት የተሰደደ ሲሆን፣ እስከ 386 ዓ.ዓ አልተመለሰም ነበር። ይሰማው የነበረውን ስሜት ለመገመት የሚያዳግት አይደለም። ሰዎችን ከመጥፎ የህይወት መንገድ መልካም ወደሆነው ይመልሳል የሚል ተስፋ የጣለበት የሰላሳዎቹ ኦሊጋርኪ ወደ አሳፋሪ ደም አፋሳሽነት ሲቀየር ተመልክቷል። ጓደኛው እና መምህሩ ዴሞክራሲ በመጣ ማግስት ሲወገዝ ተመልክቷል። ሁሉም የታዩት እና እየታዩ ያሉት የመንግሥት ዓይነቶች መጥፎ ናቸው የሚል ድምዳሜ በህሊናው ተቀረፀ። ገና ወጣት ሳለ ይህንን እምነት እንዲይዝ ሆነ፡-

«ትክክለኛ እና ሐቀኛ ፈላስፎች የፖለቲካ ሥልጣንን እስካልያዙ ድረስ፣ ወይም የመንግሥታት መሪዎች በሆነ ተዓምር ሐቀኛ ፈላስፎች እስካልሆኑ ድረስ የሰው ልጅ ችግሮች መቼም ቢሆን አይወገዱም።»

ፕሌቶ በወጣትነት ዘመኑ የተመለከተውን የፖለቲካ ስንክሳር በይበልጥ ከሶፊስቶች ጋር ወደማያያዙ ያመዝናል። ሶፊስት ከክርስቶስ ልደት በፊት በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአቴንስ የነበሩ የመምህራን እና የአንደበተ-ርቱዎች ቡድን ስያሜ ነው። “Republic” የተሰናዳው፣ «አክራሪ» ሶፊስት የነበረው ትራሲማከስ፣ ሶቅራጠስን በሚፈትንበት መንገድ መሆኑ በአጋጣሚ የሆነ አይደለም። የምልልሱ አካሄድ የፍትህን ምንነት የመጠየቅ (የማፈላለግ) ነው። ለጥቂት ገጾች ያክል ውይይቱ በተረጋጋ መልኩ ከቀጠለ በኋላ መድረኩ በትራሲማከስ ይያዛል።

በውይይቱ መሪ (በሶቅራጠስ)፣ የፍትህ ምንነት ላይ ለመድረስ የሚደረጉ እርጋታ የተሞላባቸው ሙከራዎችን በትዕግስት የለሽነት ሲያዳምጥ ቆይቷል – ትራሲማከስ። ከዚያም የራሱን ትርጓሜ ያቀርባል፡- «ፍትህ ማለት የጠንካራው (የጉልበታሙ) ፍላጎት እንጂ ሌላ አይደለም።» ይህ ትርጓሜ ፕሌቶ ከወጣቱ የሶፊስቶች ትውልድ (ከነዚህ መካከል በፕሌቶ ምልልስ ውስጥ ‘ጆርጂያስ’ ተብሎ የሚጠቀሰው ካሊክለስ ይገኝበታል) ጋር የሚያዛምደውን የፖለቲካ ሞራል-አልባነት ለመጠቆም በግልፅ የታሰበ ነው። የተቀረውን የመጀመሪያ መፅሐፍ ክፍል በሚያካልለው ረዥም ውይይት ላይ፣ ትራሲማከስ አቋሙን ለብዙ ጊዜ እንዲቀያይር ተደርጓል። በኋላ ሲታይ በሕሊናው የነበረው የፍትህ ትርጓሜ የጉልበታሙ ፍላጎት ሳይሆን፣ የሌሎች ፍትሃዊ (Just) መሆን እና የእርሱ ኢ-ፍትሃዊ መሆን የጉልበታሙ ፍላጎት ነው። የትራሲማከስ አቋም እንዲህ በአራት ነጥቦች ሊቀመጥ ይችላል፡-

1). መልካም ህይወት ሁሉንም ገደቦች ወደጎን የጣለና በገደብ-የለሽ እርካታ የተሞላ ህይወትን ማጣጣም ነው። ሰዎች የራሳቸውን እንጂ የሌላ የማንኛውንም ሰው ጥቅም (ፍላጎት) ከግምት እስካላስገቡ ድረስ ደስተኞች ናቸው። /ተመሳሳይ ጥቅል አመለካከት “Gorgias” ውስጥ በካሊከስ ተገልጿል።/

2). ‘ፍትህ’ ማለት ‘ሕግን አለመተላለፍ’ ነው። ስለዚህም በበላይ ካለው የተቀመጡለትን ገደቦች ወይም ቁጥጥሮች መቀበልን ያካትታል።

3). ሕጎች በጠንካሮቹ ተዘጋጅተው በደካሞቹ ላይ የሚጫኑ ድንጋጌዎች ናቸው። ጠንካሮቹ ለራሳቸው ጥቅም (ወይም የራሳቸው ጥቅም እንደሆነ ባሰቡበት በማንኛውም መጠን) ደካሞቹን የሚቆጣጠሩባቸው መሣሪያዎች ናቸው።

4). ስለዚህም የገዢው (የመሪው) ጥቅም፣ በደንብ (በአግባቡ) የሚጠበቀው ተገዢዎቹ ፍትሃዊ በሚሆኑበት (ማለትም የእርሱን ሕጎች በማይተላለፉ) ጊዜና እሱም ከእርሱ ፈቃድ በሚቃረን በማንኛውም ፈቃድ በማይገደብበት መንፈስ ‘ኢ-ፍትሃዊ’ መሆን በሚችልበት ጊዜ ነው። ከዚህ አንፃር የፍትህ አለመኖር ወይም ኢ-ፍትሃዊነት ከፍትህ የተሻለና ጠንካራ ነው ሲል ትራሲማንከስ ያስባል።

በማያስገርም መልኩ፣ ትራሲማከስ የጨቋኝ ሥርዓት (tyranny) ግልፅ አድናቂ ነው። ጥሩ ገዥ የሚባለው የተገዢዎቹን ጥቅም በተቻለ መጠን ሙሉ ለሙሉና በተሳካ መልኩ የሚወስድ ነው። በአንፃሩም ተገዢዎቹ አሰልቺ እና አስጨናቂ ህይወት የሚመሩ ሕዝቦች ናቸው። ይህም ፕሌቶ በወጣትነት ዘመኑ የታዘበውን ያልተረጋጋ እና የብጥብጥ ፖለቲካ የመደበበትና ሶቅራጠስን በወኪልነት አስቀምጦ በመላው “Republic” መፅሐፉ ገጾች ውስጥ የሚሞግተው የአመለካከት ዓይነት ነው።

ትራሲማከስ፣ ፍትህ ገደቦችን የመቀበል ሐሳብን ያካተተ በመሆኑ ምክንያት፣ ከፍትህ ይልቅ የፍትህ አለመኖር ተመራጭ እንደሆነ ያምናል። ፍትሃዊ ሰው አንገቱን የደፋ ጅል (ቂል) ዓይነት ነው። በተፈጥሮው የበላይ የሆነ ሰው፣ መልካም ህይወት ሁሉንም ገደቦች አለመቀበል (መጣስ) መሆኑን ያውቃል።

ሆኖም ሶቅራጠስ፣ ለመልካም ህይወት ይህ መልክ መሰጠቱ በማያሻማ ሁኔታ የተሳሳተ መሆኑን ይገልጻል። ሁሉም ገደቦች የተዘነጉበት ህይወት ላይ የምናነጣጥር ከሆነ የፈለግነውን በቀላሉ ማግኘት አይቻለንም። መሣሪያውን እየቃኘ ያለ ሙዚቀኛ ክሮቹን በተገቢው መጠን ማጥበቅ አለበት፤ ሳይበዛ ወይም ሳያንስ። በሽተኛን የሚያክም ሐኪም ትክክለኛውን የመድኃኒት መጠን መስጠት አለበት፤ ሳይጨምር ወይም ሳይቀንስ።

ሐሳቡ ተቃርኖ ቢኖርበትም፣ ዘራፊዎች እንኳን የ«ፍትህ» ዓይነት መንገድ መከተል አለባቸው። ወንበዴዎቹ በመካከላቸው የሥራ ከፍፍልን በሚያስቀምጡ ሕጎች መሠረት መንቀሳቀስ ይገባቸዋል። ይህን ካላደረጉ ቀድሞውኑ የወንበዴ ቡድኑ የተሰባሰበበትን ዓላማዎች ማሳካት አይቻላቸውም። ማንኛውም የሰው ልጅ እንቅስቃሴ ስኬታማነት፣ የዚያ እንቅስቃሴ መሆኛ (መተግበሪያ) የሆኑትን ገደቦች በማክበር ላይ ይመረኮዛል። በገደቦቹ ውስጥ መሆን ወይም ገደቦቹን አለማለፍ ማለታችን ፍትህ ማለት ከሆነ፣ ፍትህ ታዲያ ደካማውን ለመቆጣጠር በጠንካራው የተፈበረከ መሣሪያ አይደለም ማለት ነው።

«ፍትህ»፣ ከማንኛውም ምክንያታዊ ድርጊት ጋር የማይነጣጠል ከመሆኑ አንፃር፣ ተፈጥሯዊ ነው፤ እንዲሁም ኢ-ፍትሃዊነት የተፈለገውን ግብ ያለመምታትን ያህል ስህተት አይደለም። የሰው ልጅ ህይወት ዓላማ ያለው እንቅስቃሴ እንደመሆኑ መጠን፣ ለስኬታማ ሂደቱ ፍትህ አስፈላጊ ነው። ስለዚህም ለእያንዳንዱ የሰብዓዊ ፍጡር (ወይም ሶቅራጠስ እንዳስቀመጠው፣ ለእያንዳንዱ ነፍስ) ፍትህ ማለት፣ ለቢላዋ ስለት ወይም ለዓይን ትኩረት እንደማለት ነው። ነፍስ ተግባሯን በአግባቡ እንድትወጣ የሚያስችላት መሠረታዊ ነገር ነው። እናም የአንድ ነፍስ ፍትህ በትክክል ምን እንደሆነ፣ ወይም በነፍስ ውስጥ የት እንደሚገኝ መረዳት አስፈላጊ ነው። ለዚህም ሶቅራጠስ በቅድሚያ ፍትህን ከፖለቲካ ማህበረሰብ (polis) አንፃር ማየት እንደሚገባን ይናገራል። ፍትህን በሰፊው መጠን መመርመር፣ በአነስተኛ ወይም በግለሰብ መልኩ ለመረዳት የተሻለ ይሆንልናል።

ታዲያ የአንድን የፖለቲካ ማህበረሰብ ፍትህ የሚገልጸው (የሚወስነው) ምንድነው? ሶቅራጠስ፣ በጊዜው የነበረ ማንኛውንም የመንግሥት ሥርዓት በመመርመር ሳይሆን፣ ይልቁንም «ካሊፖሊስ» (ውብ ከተማ) በማለት የሚጠራውን “ሐሳባዊ” የፖለቲካ ማህበረሰብ የመገንባትን ሂደት በመግለጽ ይህንን ጥያቄ ይመልሳል። እንዲህ ዓይነቱ ማህበረሰብ፣ የሰው ልጆች ቁሳዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ተባብረው መሥራታቸው ከማስፈለጉ እውነታ ሊመነጭ የሚችል ነው። ነገር ግን የመሠረታዊ ፍላጎቶች መሟላት ያለጥርጥር ተጨማሪ ፍላጎቶችን ይፈጥራል፤ እናም እነሱን ለማቅረብ ይበልጥ ውስብስብ መዋቅሮች መዘርጋታቸው ግድ ይላል። ሶቅራጠስ እንደሚጠቁመው፣ ማህበረሰቡ በሂደቱ መጨረሻ የሞራል ልዕልናዎቹን (virtues) የሚጋሩ ሦስት ቡድኖችን ያቀፈ ማህበረሰብ ይሆናል። እነዚህ ቡድኖች፡- ጠባቂዎች (Guardians)፣ ደጋፊ ኃይሎች (Auxiliaries)፣ እንዲሁም አምራቾች (Producers) ይባላሉ።

ጠባቂዎቹ የመንግሥትን ጥበብ ይጨብጣሉ፤ ደጋፊው ኃይል ወይም ወታደራዊ መደቡ ወኔውን ይይዛል፤ አምራቾቹ የግለ-ቁጥብነትን (self-restraint) ባሕሪይ ይኖራቸዋል፣ በዚህም ጠባቂዎቹ ለሚያወጡት ሕግ ተገዢ የመሆን አስፈላጊነትን ይገነዘባሉ።

እንደሶቅራጠስ መከራከሪያ፣ ፍትህ ከወኔ፣ ከጥበብ እና ከግለ-ቁጥብነት ተጨማሪ የሆነ ራሱን የቻለ ሌላ የሞራል ልዕልና አይሆንም። ፍትሕ፣ ደጋፊ ኃይሎቹ እና አምራቾቹ በጠባቂዎቹ አማካኝነት በተቀመጡ ገደቦች ውስጥ ሲሆኑ፣ በመካከላቸው የሚገኝ ተዛምዶ (ግንኙነት) ነው። በሌላ አገላለፅ ጠባቂዎቹ፣ ደጋፊዎቹ እና አምራቾቹ ለመላው ማህበረሰብ መልካም ሁኔታን ለማምጣት በአንድነት በሚሰሩ (በሚንቀሳቀሱ) ጊዜ ፍትህ ይረጋገጣል። ፍትህ ሁሉም ሰው ይበልጥ የሚስማማውን ሥራ የሚሰራበትና በሌላ ሰው ላይ ጣልቃ የማይገባበት ሁኔታ ነው።

አሁን ይህንን ሐሳብ እንደ ሰርዶ በመምዘዝ የእያንዳንዱን ነፍስ ፍትህ በተመለከት የተወሰነ ነገር መናገር እንችላለን። ሶቅራጠስ እንደሚጠቁመው፣ ነፍስ ሦስት ክፍሎች ወይም ትግበራዎች አሉት፡- ምክንያት ወይም አስተውሎት (reason)፣ አምሮት (appetite) እና መንፈስ ወይም ስሜት (spirit/emotion)። የነፍስ ክፍሎች ሦስት እንደሆኑ ወይም ሦስት ብቻ ስለመሆናቸው ያመነበትን ምክንያት አያስረዳም፤ ሆኖም ይህ በመከራከሪያ ነጥቡ ላይ ለውጥ አያመጣም። በዚህ መከራከሪያ ነጥብ ላይ አስፈላጊው ነገር ነፍስ ክፍሎች እንዳሉት መቀበላችን ነው፤ ቢያንስ በተወሰነ መልኩ ከላይ ከተገለፁት የፖለቲካ ማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ተነጻጻሪ የሆኑ ክፍሎች።

አምሮትም ሆነ ስሜት፣ ያለ አስተውሎት ምሪት አግባብ በሆነ መንገድ እንደማይሰሩ ግልፅ ነው። ያልተመራ አምሮት ወይም የድንገተኛና የቁጥጥር-የለሽ ስሜት ህይወት ፍሬ-ቢስ እና ግብ-የለሽ ነው። ከመንግሥት ጋር በንፅፅሮሽ ስንመለከተው፤ ፍትህ በነፍስ ውስጥ የሚኖረው፣ አምሮት እና ስሜት ለሁሉም መልካም የሆነውን በሚያመጣ መንገድ በምክንያት ወይም በአስተውሎት በሚመሩ ጊዜ ነው። ስለዚህም የህይወት ስኬታማነት፣ ማለትም ሁሉም ሰው ያሻውን ደስታ የሚያገኝበት ስኬታማነት የሚመረኮዘው በአግባቡ የተገራ ነፍስ አለን ወይ በሚለው ላይ ነው፤ ወይም በአሁኑ ዘመን እንደሚባለው፣ ምሉዕ የሆነ ስብዕና (well-integrated personality) መጨበጣችን ላይ ይመረኮዛል።

ግለሰባዊ ደስታን በማረጋገጥ ላይ ይበልጥ የሚያተኩር የፍትህ ዓይነት፣ የሶፊስቶች እራስን ማስደሰት ወይም ማርካት (self-gratification) የሁሉም ሰው የማያሻማ ግብ ነው የሚለው አስተምህሮ መጠነኛ መሻሻል ተደርጎበት የቀረበ ነውን? ይህ ምልከታ በፕሌቶ “Republic” ላይ በወንድማማቾቹ ግላውኮን እና አዲዬማንተስ አማካኝነት የተነሳ ነው። መከራከሪያዎቹ እንዲህ ይከተላሉ፡- ስለምን ዝም ብዬ በሌላ ሰው መስዕዋትነት የምፈልገውን ለማግኘት ስል አምሮቶቼን እና ስሜቶቼን ለመምራት አስተውሎቴን አልጠቀምበትም? ስለምን ለእኔ የሚመቸኝ ከሆነ ፍትሃዊ እንደሆንኩ በማስመሰል ሳይታወቅብኝ ማድረግ በምችልበት ጊዜ የቻልኩትን ያህል ለራሴ አልሰበስብም (አላግበሰብስም)? በፈለኩት ጊዜና ቦታ አለመታየት ወይም እንዳይታወቅብኝ ማድረግ ከቻልኩኝ፣ ፍትሃዊ መሆን የሚኖረው ፋይዳ ይኖር ይሆን?

ለእንዲህ ያሉ ጥያቄዎች ሶቅራጠስ የሰጠው ምላሽ በጥቅሉ ሲቀመጥ፣ ምሉዕ ስብዕና ያላቸው ሰዎች፣ ማለትም ፍላጎታቸው እና ስሜታቸው የተመጣጠነና ምክንያት-የለሽ እና ቅጥ-አልባ ያልሆኑ ሰዎች፣ ከስር መሠረቱ የተቻላቸውን ያህል ለራሳቸው ማግበስበስ አይፈልጉም። ፍትሃዊ ሰው፣ መሻቶቹ (ምኞቶቹ) ከሚያስፈልጉት ነገሮች በልጠው የማይገኙበት ደስተኛ፣ ውስጠ-ሰላም፣ በደንብ የተዋቀረ ግለሰብ ነው። የሌሎችን የሞራል ጥያቄዎች በቀጥታ የማይቀበልበትና ለሌሎችም ሆነ ለራሱ ደስታና መልካምነት ፈቃደኛ የማይሆንበት ምንም ምክንያት ሊኖረው አይችልም። የነፍስ የብቃት ደረጃ ተደርጎ የሚታየው ፍትህ፣ በእርግጠኝነት የፍትሃዊውን ሰው ጥቅሞች ያስጠብቃል፤ ነገር ግን ሌሎችንም ከግምት ያስገባል።

ይሁንና ግን በገሃዱ ዓለም ከዚህ አንፃር ፍትሃዊ የሆኑ ጥቂት ግለሰቦችን ብቻ እናገኛለን። ሶቅራጠስ እንደሚያስበው፣ ይህ የሆነው ብዙ ሰዎች እውቀት ስለሚያጥራቸው ነው። የፍትህ፣ የትክክል፣ የመልካምነትና የመሳሰሉትን ነገሮችን ምንነት አያውቁም። ስለዚህም ጥብቅ እና የማያወላውሉ የምክንያት መርሆዎችን ተከትለው ህይወታቸውን መምራት አይቻላቸውም።

ተሞክሮዎች እንደሚጠቁሙት፣ አብዛኛው ሰው የሚኖረው በሶፊስቶቹ ፕሮታጎረስ እና ጆርጂያስ አማካኝነት በተገለፀው ዓለም ዓይነት ውስጥ ነው፡- ይህም እርግጥ የሆነ ዕውቀት የሌለበት፣ ነገር ግን አመለካከት ወይም እምነት ብቻ ያለበት ዓለም። እንዲህ ዓይነቱ ዓለም የተረጋጋ አይደለም፤ ምክንያቱም አመለካከቶች ወይም እምነቶች በቀላሉ ሊለዋወጡ ይችላሉና። በተለይም በምክንያት ላይ መሠረት በማያደርጉና የማሳመን አቅም ባላቸው አፈ-ቀላጤዎች (demagogues)፣ በአሳማኝ አንደበተ-ርቱዎች ተፅዕኖ ሊለወጡ ይችላሉ። ይህም በዴሞክራሲዎች ዘንድ የተለየ አደጋ ስለመሆኑ ሶቅራጠስ ይጠቁማል፤ ምክንያቱም ዴሞክራሲዎች የሚያሰፍኗቸው የኑሮ ሁኔታዎች ብቁ ውሳኔዎች ማሳለፍ የሚሳናቸውን ወይም ቆራጥ ያልሆኑ ሰዎችን የሚያፈሩ ወደመሆን ያዘምማሉና።

ሶቅራጠስ እንደሚያስበው፣ ብቸኛዎቹ እውነተኛ ፍትሃዊ ሰዎች ከአመለካከት ወይም ከአስተያየት (opinion) ይልቅ፣ እውቀት ያላቸው ናቸው፤ ‘እይታ እና ጭብጨባ ወዳድ’ ከሆኑት የተለዩ ‘ጥበብ አፍቃሪዎች’ (philosophoi – ‘wisdom lovers’) ናቸው። ስለዚህም፣ በሐሳብ ደረጃ፣ ሀገርን የማስተዳደር ኃላፊነት ሊሰጥ የሚገባው ለፈላስፎች ነው።

ታዲያ ከአመለካከት የሚለይ ከሆነ፣ እውቀት ምንድነው? ሶፊስቶች እውቀትን በተመለከተ የጥርጣሬ ምልከታ አላቸው፤ እውቀት የሚባል ማንኛውም ነገር የመኖሩን ሁኔታ አይቀበሉም። በእነሱ ሐሳብ ከሆነ፣ የትኛውም አንድ አመለካከት (አስተያየት) ከተቃራኒው የተሻለ እውነትነት እንዳለው ማሳየት ስለማይቻል የምንኖረው እርግጠኛ መሆን በማይቻልባት ዓለም ውስጥ ነው።

ሶቅራጠስ፣ በመደበኛ የስሜት ተሞክሮ የምንኖርበት ዓለም እርግጠኛ አለመሆን የሰፈነበት ስለመሆኑ ይስማማል፤ ነገር ግን ትክክለኛው የትምህርት ዓይነት (ማለትም ፍልስፍናዊ ትምህርት) አእምሮን ከሚጨበጠው የእይታ ዓለም «እውነተኛ» (real) ወደሆነው ‘የሐሳቦች’ ወይም ‘የቅርፆች’ ዓለም ይመራዋል። (ፕሌቶ የማይታየውን ዓለም «world of ‘ideas’ ወይም ‘forms’» በማለት ይጠራዋል።) ይህ የድብቁ ዓለም ፅንሰ-ሐሳብ (theory of forms)፣ ፕሌቶ ብዙውን ጊዜ ይጥቀሰው እንጂ በየትኛዎቹም ምልልሶቹ ሙሉ ለሙሉ ያልተብራራ ከመሆኑም በላይ ግር የሚያሰኝ እና አስቸጋሪ አስተምህሮ ነው። (እኛም እዚህ ላይ እንዲሁ በቀላሉ እንደገለጽነው ሊታወስ ይገባል።)

እሱ እንደሚያስበው፣ ሁሉም ፍትሃዊ ድርጊት፣ ሁሉም ውብ የሆነ ነገር በአንድ እና በአንድ ምክንያት ብቻ ፍትሃዊ እና ውብ ነው። ይህም ከፍትህ እና ከውበት ንፁህ እሳቤዎች ጋር ተሳትፎ (participate) በማድረጉ ወይም የሚጋራው ነገር በመኖሩ ምክንያት ነው፤ እነዚህም በሰለጠነ አዕምሮ ብቻ ሊቀሰሙ የሚችሉ ሐሳቦች ናቸው። እነዚህ ሐሳቦች፣ ሶቅራጠስ እንደሚያስቀምጣቸው፣ እነርሱ ሐሳቦቻቸው ስለሆኑት ነገሮች እውነተኛ ተፈጥሮ በተመለከተ ለአዕምሮ መገለጥን የመፍጠር አቅም አላቸው። «የእይታ ዓለም» ውስጥ ባሉ አያሌ ነገሮች ላይ የአሻሚነት ሁኔታ የሚታይበት ምክንያት፣ የሚሳተፏቸው ሐሳቦች ወልጋዳ ቅጂዎች ብቻ በመሆናቸው ነው። አብዛኛው ሕዝብ እየተመለከተ ያለው ቅጂዎቹን ብቻ ሲሆን፣ ቅጂዎች መሆናቸውንም አይገነዘብም። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ፊትለፊት የሚታየውን ነገር፣ እውነታ (reality) እንደሆነ አድርገው ይወስዱታል። ነገር ግን በትርጉም ደረጃ፣ ፈላስፋ እራሳቸው ሐሳቦቹን የቀሰመ፣ በዚህም ምክንያት እንቅስቃሴው ሁሉ በሚወላውል አመለካከት ሳይሆን፣ በትክክለኛ እውቀት የሚመራ ሰው ነው። ፈላስፋ፣ ወዳጆቹ በጨለማ ውስጥ ቀርተው እርሱ ከዋሻ ውስጥ አምልጦ ወደ ፀሐይ እንደወጣ እስረኛ ነው። ጭለማውን የእምነት (የአመለካከት) መጋረጃ ተሻግሮ በማለፍ የነገሮችን እውነተኛ ምንነት ተገንዝቧል። በዚህ ምክንያትም በተለየ መልኩ ሌሎችን ለመምራት ችሎታው አለው።

ስለዚህም ለሶቅራጠስ፣ ከሁለም የሚሻል መንግሥት አብዛኛዎቻችን ያለንበትን በዓይን የሚታየውን ዓለም ተሻግረው ባለፉ፣ በዚህም መልካም ማለት ምን እንደሆነ በማወቃቸው መልካሙን በሚያደርጉ ሰዎች የሚመራ አሪስቶክራሲ ይሆናል። ሕጎችን አያወጡም፤ በራሳቸው ግለሰባዊ የመወሰን ነፃነት ያስተዳድራሉ። ከሶፈስቶች ግምት በተቃራኒው፣ የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ የሚያስተዳድሩትን ሕዝብ አይበዘብዙም። ድርጊቶቻቸው በእውቀት የሚመሩ የበራላቸው ፍጡራን ከመሆናቸው ባሻገር፣ የግላዊ ጥቅም እና ዝና ማንኛውንም ሐሳብ ከአዕምሮአቸው አሽቀንጥረው በማውጣት እንዲኖሩ የሐሳባዊው ከተማ ትምህርታዊ እና ማህበራዊ ሥርዓት ይጠይቃቸዋል። ምንም ዓይነት ቤተሰብ ወይም ንብረት አይኖራቸውም። ፍለጋቸው ሁሉ የጋራ ጥቅምን ለማምጣት ብቻ ይሆናል፤ እንዲሁም ድረጊታቸው ሁሉ ሁሉም ሰው እንደተሰማራበትና እንደችሎታው የሞራል ልዕልና እና ደስታ የሚያገኝበትን መንገድ የተከተለ ይሆናል።

የቅርብ ዘመን ፀሐፊዎች ፕሌቶ በዴሞክራሲ ላይ ያለውን ጥርጣሬ ለመተቸት ይሞክራሉ። እነዚህ ሐያሲዎች፣ ሰብዓዊ ፍጡራን የጣልቃ-ገብነት ቁጥጥር ሳይኖርባቸው ህይወታቸውን የማደራጀት አቅም ያላቸው ስለመሆናቸው ፕሌቶ እምነት እንደሚጎድለው ይተቻሉ። የፕሌቶ ‘ፈላስፋ-ገዢዎች’ የሚመሩበት ሥርዓት የጨቋኝ ሥርዓት (totalitarian) ዓይነት እንደሆነ፤ ፈላስፋ አመራሮቹም፣ ፕሌቶ ሶፊስቶችን ከሚነቅፍባቸው ባልተናነሱ አስከፊ ስልቶች አማካኝነት፣ አለን የሚሉትን እውቀት በመጠቀም የተገዢዎቻቸውን እያንዳንዱን የህይወት አቅጣጫ የሚቆጣጠሩ አምባገነኖች እንደሆኑ ይጠቁማሉ። ፕሌቶ ቦታ የሚሰጠው የእውቀት ዓይነት ሕዝብን ነፃ ለማድረግ ሳይሆን፣ እርሱ ምቾታማ ነው ብሎ የሚቆጥረውን ነፃነት-የለሽነት ለመፍጠር ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ነው።

እንዲህ ያለው ትችት ከቁም ነገር መቆጠር ይገባዋል ለማለት ያዳግታል። በቅድሚያ ፕሌቶን ዘመንኛ ሊበራሎች የሚያወድሷቸው እሴቶች እና አመለካከቶች ስለሌሉት መንቀፍ ፋይዳቢስነት ነው። እንዲሁም ትችቱ በትክክል የፕሌቶ ዓላማዎች ምን እንደሆኑ ትኩረት የሰጠ አይደለም። በሌላ በኩል፣ የእርሱ ምልከታ መሪ የመሆን ተሰጥኦ የሚኖራቸው ጥቂት ሰዎች ብቻ መሆናቸውና እውቀት-የለሹም የጠቢቡን አመራር መከተል ያለበት መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም።

በርግጥ ፕሌቶ እንደሚያስበው ከሆነ፣ ጠባቂዎቹ (Guardians) የጋራ ብልፅግና ማህበረሰቡን ለማስተዳደር፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ አፈ-ታሪክን፣ ተፅዕኖን፣ እንዲሁም ማታለልን እንደመሳሪያ መጠቀማቸውም እውነት ነው። መዋሸት አስፈላጊ ሲሆንባቸው ይዋሻሉ፤ በተመራጮች ዘንድ የተሻለ ጥምረትን ለማምጣት የምርጫ ኮሮጆዎችን በሚስጥር ይበርዛሉ፤ አማልክት ሰዎችን ከወርቅ፣ ከብር እና ከነሐስ ሠርተዋልና እያንዳንዱ ሰው ቦታውን (ደረጃውን) ማወቅ አለበት የሚለውን ተቀባይነት ያገኘ ውሸት ያስፈፅማሉ።

ነገር ግን፣ በሌላ በኩል፣ እነዚህ ነገሮች የሚደረጉት ለራሳቸው ለገዢዎቹ ጥቅም ሲባል ሳይሆን የጋራ የሆነና ረጅም ጊዜ የሚዘልቅ መልካምን ለማስፈን ነው በሚለው እምነቱ ላይ ፕሌቶ የማያንገራግር መሆኑ እጅግ ግልፅ ነው። ጠባቂዎቹ ይህን የማድረጋቸው ምክንያት፣ በአንድ ጊዜ ሞራላዊ ለመሆን አቅሙ የሌላቸውን ሞራላዊ ልዕልናን እንዲላበሱ አድርገው መቅረፅ ስላለባቸው ነው። እነሱም ከፍተኛ መልካምነትን ያዘለ ዓላማ ያላቸው ሰዎች ይሆናሉ። ቁጥብ እና ፍላጎት-የለሽ ህይወት ይኖራቸዋል፤ ለሚመሩት ማህበረሰብ ደህንነት ከፍተኛ የእውቀት ሀብታቸውን ያፈሳሉ፤ ተገዢዎቻቸው በሚችሉት መጠን በደስታ የተሞላና የተሟላ ህይወት እንዲኖራቸው ሌት ከቀን ይተጋሉ።

ፕሌቶ ወደኋላ ባፈለቃቸው፣ “Politicus” እና “Laws” በተሰኙት የፖለቲካ ሥራዎቹ ላይ እንደተቀመጠው፣ የጠቢብ ሉዓላዊ አገዛዝን እምነት መቼም ቢሆን ሙሉ ለሙሉ ባያስወግደውም በተወሰነ መልኩ አሻሽሎታል። ይህ ወደኋላ የታየው መሻሻል ከሁለት ነገሮች ጋር የተያያዘ ተደርጐ ይታሰባል። የመጀመሪያው፣ የእውቀት አስተምህሮዎቹ ላይ የነበሩት ጥርጣሬዎች ከዚህ ቀደም በረቂቅ እውቀት እና በፖለቲካ ትግበራ መካከል የሚገኝ ቀጥተኛ ማያያዣ ስለመሆኑ በተናገረው ላይ ጥያቄ እንዲያጭርበት ሳያደርጉት አልቀሩም። ከጊዜ በኋላ “የቅርፆች” ወይም “የሐሳቦች” ፅንሰ-ሐሳባን በተመለከተ መወላወል መጀመሩ ግልፅ ነው። ይህን ፅንሰ-ሐሳብ እንደገና መመርመሩ “Parmenides” በተሰኘው የኋለኛ ምልልስ ላይ ተስተውሏል፤ ይህ ፕሌቶ የአርስቶትልን ድምፅ በመጠቀም የተለያዩ የሚቃወሙ ሐሳቦችን ያሰፈረበት አስገራሚ የግለ-ሂስ ፅሁፍ ነው።

ሁለተኛው፣ ምናልባትም ይበልጥ ወሳኙ፣ ፕሌቶ በ367 ዓ.ዓ የሲራከስ ወጣት አምባገነን ገዥ ለነበረው ዲዮናይሲየስ 2ኛ የፖለቲካ አማካሪ ሆኖ ነበር። ይህ ሁኔታ በገሃዱ ዓለም በፍልስፍና አማካኝነት የበራለት የፖለቲካ መሪ ለመቅረጽ ጥሩ ዕድል እንደሚሆን አስቦ ነበር። ሆኖም ቤተ-ሙከራው የተሳካ ወጤትን አላረጋገጠም። በዚህ ጊዜ ፕሌቶ እራሱን የፈላስፋ መሪ እሳቤው የተነነበት ተከታታይ የፖለቲካ ውስስቦሽ ውስጥ ሆኖ አገኘው።

“Politicus” ላይም በምቹ የፖለቲካ መሪ እሳቤው ላይ በመርህ ደረጃም ቢሆን ቁርጠኛ ነው፤ ሆኖም አሁን ያነገበው ጭብጥ እንዲያ ያለ የፖለቲካ መሪ የመገኘቱ ነገር የማይሆን ነው የሚል ሲሆን፣ በእርሱ ምትክ ሁለተኛው የተሻለ የመንግሥት ዓይነት ድርጊታቸው በሕግ ገደብ የተበጀለትና ትክክለኛውን የሚያደርጉ መሪዎች የሚይዙት ይሆናል። እንዲህ ያሉ መሪዎች እውቀት የላቸውም። የፖለቲካ ሳይንስም ሆነ ጥበብ ምን እንደሆነ በራሳቸው ግንዛቤው የላቸውም። ነገር ግን የመጠቁ ሕጐች ቢያንስ እውነተኛውን አመለካከት ይሰጧቸዋል፤ የእውነተኛ አመለካከት (አስተያየት) አገዛዝ ደግሞ ከአግባብ-የለሽ እና ወደ አንድ ወገን ከሚያመዝን አገዛዝ የተሻለ ነው። ይሁንና ግን እነዚህ ምጡቅ ሕጎች ከየት እንደሚመጡ በጥቅሉ ግልጽ አይደለም።

ፕሌቶ፣ ምናልባትም ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ያዘጋጀው “Laws” የተሰኘው የመጨረሻ ምልልስ፣ የሕግን የመጨረሻ ጫፍ ያስቀምጣል። በዚህ ምልልስ ላይ «ማግኔዢያ» በመባል የተገለፀው ሐሳባዊ የፖለቲካ ማህበረሰብ፣ በእያንዳንዱ ዝርዝር እንቅስቃሴው የሚተዳደረው «ኖክቸርናል» የተባለው ምክር ቤት በሚያወጣቸውና በሚቆጣጠራቸው ሕጎች ነው። የምክር ቤቱ አባላት “Republic” ላይ ከተገለፁት «ጠባቂች (ጋርዲያንስ)» ጋር ተመሣሣይ ናቸው፤ ነገር ግን አሁን የእነሱ ጥበብ በግላዊ የመወሰን ነፃነታቸው ብቻ ሀገሪቱን እንዲመሩ አያስችላቸውም። ተግባራዊ ሊሆን የሚችልና ከሁሉም የተሻለ የመንግሥት ዓይነት፣ እንከን-የለሽ ባይሆንም፣ የጥበብ ስብስብ እና ጥርቅም በሰረፀባቸው ሕጎች የሚመራው ነው የሚለው የፕሌቶ የመጨረሻ አቋም ነው። እንዲህ ባለ አወቃቀር የዜጎች የሞራል ልዕልና በጣም ቁርጥራጭ (አናሳ) የሆኑትን ጨምሮ እያንዳንዱን የህይወት ዝርዝር ክፍሎች ለሚቆጣጠሩ ሕጎች መገዛት ይሆናል።

==/==

(ይህ ጽሁፍ “Fifty Major Political Thinkers” ከተሰኘው Ian Adams ena R.W. Dyson ካዘጋጁት መጽሐፍ በግዛው ለገሠ ተተርጉሞ የቀረበ ሲሆን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀድሞ አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ታትሟል።)

ለበለጠ ንባብ

ቀዳሚ ምንጮች

Republic, ed. F.M. Cornford (Oxford: Oxford University Press, 1941).

Statesman, ed. J.B. Skemp (New York: Liberal Arts Press, 1957).

Laws, ed. T.J. Saunders (Harmondsworth: Penguin, 1970).

ተቀፅላ ምንጮች

Annas, J.: An Introduction to Plato’s Republic (Oxford: Clarendon Press, 1981).

Coleman, J.: A History of Political Thought, vol. 1 (Oxford: Blackwell, 2000).

Cross, R.C. and Woozley, A.D.: Plato’s Republic: A Philosophical Commentary (London: Macmillan, 1964).

Klosko, G.: The Development of Plato’s Political Theory (London and New York: Methuen, 1986).

Sayers, S.: Plato’s Republic: An Introduction (Edinburgh: Edinburgh University Press, 1999).

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.