FEATUREDአንኳሮች

አንተ እየሸናህ ስትናፈስ፣ ትውልድ በልመና አፉን ሲፈታ

አንዳንዴ እንደቀላል የምናየው ነገር ከፍተኛ ቀውስ የማስከተል አቅም ሊኖረው ይችላል፡፡ እንደዘበት የምናልፋቸው ነገሮች ትውልድ ሊያመክኑ፣ መንግስት ላይ ሊያሳምፁ፣ አሊያም ደግሞ ሀገር ሊበታትኑ ይችላሉ፡፡

ከአዲሳባ ወደ ሀዋሳ እየሄድን ነው፡፡ እነዚህ የቻይና ባሶች ምቾት እና ፍጥነትን ለተሳፋሪው ከማቅረባቸው ባሻገር፣ የጫኝ እና አውራጅ፣ የገምት አትገምት የመናኃሪያ አተካራዎችን አስወግደውልናል፡፡ የባሶቹ ስም ብዛት ለመሸምደድ እስኪያዳግት እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ የጉዞ ላይ አገልግሎታቸውም ተመሳሳይነት አለው፡፡

ኢትዮባስ የታሸገ ውሃ ከታሸገ ኬክ ጋር ቁርስ እንድናደርግ ጋብዞን፣ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ፊልሞችን እያስኮመኮመን የሀዋሳ ጉዟችንን ቀጥለናል፡፡ (ስለውጪውስ ዓለም አቀፍ የቅጂ መብት ስምምነት ፈራሚ አይደለንም፣ የሀገራችንን ሙሉ ፊልሞች እንዲህ ማሳየታቸው ከባለፊልሞቹ ጋር ስምምነት ቢኖራቸው ነው የሚል ቀና እምነት እንዲኖረኝ መርጫለሁ፡፡)

ብዙ ከተጓዝን በኋላ፣ ቡልቡላ ልንደርስ የተወሰኑ ኪሎሜትሮች ሲቀረን፣ ባሱ ፍጥነቱን ቀንሶ መንገድ ዳር ቆመ፡፡ «እንናፈስ. . . እንናፈስ. . .» አለ ረዳቱ፤ በር ተከፍቶ ለመናፈስ ወረድን፡፡

አንተም ገጥሞህ ያውቃል፤ መናፈስ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ነገር ግን መናፈስ ማለት አየር መውሰድና እግር ማፍታታት ብቻ እንዳልሆነም ታውቀዋለህ፡፡ «ሽንት የወጠራችሁ ውረዱና ሽኑ» እያለ ነው ረዳቱ፤ ግን ይህ ጥሪው ሁሉንም ተሳፋሪ አይመለከትም፡፡

ሴቶች እንደምንም አፍኑት. . .

ወንዶች ያለምንም ሀሳብ ይናፈሳሉ – ዛፍ ተደግፈው ይሸናሉ፡፡ ሴቶች ምን ይሁኑ?!

ወንዶች በመናፈስ ላይ እያሉ (ዛፎቹ ስር በደንብ ይመልከቱ )

አጠገቤ ተቀምጠው የነበሩት እመቤት ኢትዮባስ የሰጣቸውን የታሸገ ውሃ «ሽንቴን ያስቸግረኛል» ብለው እንደታሸገ ነበር ከቦርሳቸው የሻጡት፡፡

በሕክምና ሳይንስ ሽንትን ለረጅም ጊዜ ማፈን ከወንዶች በላይ ሴቶችን ለተለያዩ ጉዳቶች ያጋልጣል፡፡ ሃምሳ በመቶ የካቢኔ አባላትን በሴቶች መሙላት ከሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን ካልተከላከለ ፋይዳው ምንድነው?

እዚህ ላይ ለሴቶች መቆርቆሬ ተፈጥሮን መውቀሴ ወይም አደባባይ ያለመሽናት ጨዋነታቸውን ማወደሴም አይደለም፡፡ ወንዶች አደባባይ ላይ መሽናታቸው አጠቃላይ ስብዕናቸውን ላይገልፅም ይችላል፡፡ እነሱም ሰው እርሻ ላይ እንዳይሸኑ፣ ሴቶችም በአግባቡና በምቾት የሚናፈሱበትን መንገድ መፍጠር እንዴት ያቅተናል? ይሄ ሁሉ የግልም የመንግስትም የባስ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች እያሉ ሁለት መፀዳጃ ቤት ከለል አድርገን መስራት እንዴት ያቅተናል? «እኔ ምናገባኝ»፣ «ሁሉም እንዲሁ ነው የሚያደርገው»፣ «የመንግስት ኃላፊነት ነው»፣ «የሚያስተባብር ጠፋ» የሚሉት ምክንያቶች በየዘርፉ ስንሰማቸው የኖርናቸው ናቸው፡፡ ውሃ አያነሱም፡፡

ልመና፣ የአፍ መፍቻ ቋንቋችን. . .

«ብዙ እንዳትቆዩ፣ ቶሎ ተናፍሳችሁ ተመለሱ!» የሚለውን የረዳቱን ማስታወቂያ ተከትሎ፣ ገና በሩ ከመከፈቱ የታዳጊ ሕፃናት ድምፅ ከውጭ ይሰማሃል፡፡ «አባባ ዳቦ፣ አባባ ብስኩቱን» ይሉሃል፣ አንድ ፍሬ የገበሬ ልጆች በር ላይ ቆመው፡፡

ታዳጊ ሕፃናት በልመና ላይ

አዲሳባ ላይ የትምህርት ፍኖተ-ካርታ በከፍተኛ ምሁራን እየተረቀቀ፣ በአንጋፋ ፖለቲከኞች ሲነቀፍና ሂስ ሲወርድበት፣ ልጆቻችን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር አለባቸው እየተባለ ሲነገር፣ እኚህ ትናንሽ የገበሬ ልጆች ግን አፋቸውን በልመና ስለመፍታታቸው የተረዳ የለም፡፡

አማርኛን ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ቢማሩ በመላው ሀገሪቱ ተዟዙረው እንዲሰሩ ያስችላቸዋል እያልን ስንተነትን፣ ሕፃናቱ ግን ቀድመው ለምደውትና የትም መዟዟር ሳያስፈልጋቸው እዚሁ ቀዬያቸው ላይ የገቢ ምንጭ አድርገውታል – አማርኛን እየተኮላተፉም ቢሆን ይለምኑበታል፡፡

በእርግጥ የዛሬ ቁምነገሬ ቋንቋ አይደለም፤ ልመና ነው፡፡ እነዚህ ልጆች በዚሁ ከቀጠሉ ትምህርትስ እንዴት ያምራቸዋል? (ሌላው ቢቀር፣ ያንተን ኬክ ለምደው የእናታቸው ቂጣ እንዴት ይገመጥላቸዋል?) ልጁን በአግባቡ ማሳደግ የወላጅ ፋንታ ነው ካልከኝ፣ «በሰው ቁስል…» ይሆናልና እንዳታስበው፡፡ ይልቁንስ ሁሉም ባሶች ለ10 ደቂቃ የሚቆሙባቸው፣ መፀዳጃ ቤት ለመጠቀም 1 ብር ብቻ የሚያስከፍሉ፣ እንዲሁም በቀላሉ በእጅ የሚንጠለጠሉ የአካባቢው ምርቶች የሚሸጡባቸው ኪዮስኮች ቢሰሩና ገበሬውም መጠነኛ ገቢ አግኝቶ ልጁን ትምህርት ቤት መላክ ቢችል . . . እያልን ብናስብ ሳይሻል አይቀርም፡፡

ከተማ እየፀዳ – ገጠር እየቆሸሸ

ሳንታክት ወርሃዊ የከተማ ፅዳት መጀመራችን መልካም ነው፡፡ ሆኖም ገጠር መጥተን እየተፀዳዳን፣ ‘ሪሳይክል’ የሚለው ቃል ግዕዝ ይሁን አረብ በማያውቀው የገጠሩ ሕዝባችን ላይ የውሃ ላስቲካችንን ጥለን ማለፉ ጉዳቱ የረጅም ጊዜ ነው፡፡

ባሶቹ (ለወንዶች ብቻ ቢሆንም) የመናፈስ እድልን ለተሳፋሪያቸው መስጠታቸው ጥሩ ቢሆንም፣ ለከፍተኛ የአካባቢ ብክለት አስተዋፅዖ እያበረከቱ መሆናቸው ልብ ሊባል ይገባል፡፡ በብዙ ሚሊዮኖች የውጭ ምንዛሪ (እንዲሁም የገዛ ሕዝቡ ገንዘብ – በብድር መልክ)ፈስሶባቸው የተቋቋሙት የትራንስፖርት ድርጅቶች ማኅበረሰባዊ ኃላፊነታቸውን ቢወጡ ይመሰገናሉ፡፡ ተባብረው ትምህርት ቤቶች ቢገነቡ፣ መፀዳጃ ቤቶችን እና ኪዮስኮችን ሰርተው ለአካባቢው ገበሬ ተጨማሪ ገቢ ቢያስገኙ ይወደሳሉ፡፡ አካባቢ እንዲበከል ማድረጋቸው ግን ሊያስቀጣቸው ይገባል፡፡ ይህን ለመከላከልም ከመንግስት አቅጣጫ እስኪወርድ የሚጠብቁ ከሆነ ደግሞ እንደ ሀገር ቁሞ-ቀርነታችን ይቀጥላል ማለት ነው፡፡

ማጠቃለያ. . .

እንግዲህ የእንናፈስ ጉዳይን በሦስት ማዕዘን ለማስመልከት ሞክርያለሁ፡፡ ሌሎች ማዕዘኖች ካሏችሁ ጨምሩባቸው፡፡ «ልጆቻችንን ለልመና ዳረጋችሁብን፣ አካባቢያችንን እየበከላችሁ ነው» ብሎ የሰፈሩ ወጣት ነገ ጠዋት መንገድ ቢዘጋ ለችግሩ ባለቤት ፍለጋ እና ስም ልጠፋ ላይ መዳከራችን የማይቀር መሆኑን ሳስብ ስጋት ይሰማኛል፡፡ ይህ ችግር ያለው በዚህ የጉዞ መስመር ላይ ብቻ እንዳልሆነም ልብ ይሏል፡፡ መላ ሊበጅለት ይገባል፡፡

መልካም ተሞክሮዎች . . .

ይህን ጉዳይ ለሰዎች አንስቼ ስናወራበት፣ ወደ ስልጤ በሚወስድ መንገድ ላይ መልካም ተሞክሮ እንዳለ ሰማሁኝ፡፡ በየተወሰነ ርቀት ላይ የሕዝብ ሽንት ቤቶች መኖራቸውን አንዱ ነገረኝ፡፡ በእርግጥ ይህ ከሆነ፣ ልናባዛው የሚገባ ተሞክሮ ነው፡፡ ሌሎች ተሞክሮዎች ካሉም እንኮርጅ – ሀገርዊ መፍትሄ እናድርጋቸው፡፡

. . . ሾፌሩን እናመሰግናለን፤ ሀዋሳ በሰላም ደርሰናል፡፡ ሳውዝ ስታር ሆቴል በፌደራል ፖሊስ እና በደቡብ ክልል ልዩ ኃይል በአግባቡ እየተጠበቀ ነው – ሀገር ነጋ ቢሆን ነው!

(በግዛው ለገሠ)

2 thoughts on “አንተ እየሸናህ ስትናፈስ፣ ትውልድ በልመና አፉን ሲፈታ

  • ሀሳበወርቅ

    ግዝሽ ልዩ ነዉ
    አቦ እድሜህ ይርዘም

    Reply
    • Gizaw

      Thank you, Hasabework.

      Reply

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.