የጳጉሜ ቀናት ተንገላቱ፤ ስያሜው ዘላቂ ፋይዳ ቢኖረው!
በፈረንጆቹ የ«ታንክስጊቪንግ» ቀን እንዴት እንደምቀና! የጳጉሜን ቀናት የመሰየሙ ነገር ሀሳቡ ጥሩ ነበር፤ ሀገራዊ እሴቶችን ለማጎልበትና ብሔራዊ መልካችንን ለማስቀጠል ጠቃሚ ስልት ነበር።
ሆኖም ወቅታዊ ሁኔታዎችንና የተለዋዋጩን መንግሥት ተለዋዋጭ አቋምና ትኩረት እያንፀባረቁ በየዓመቱ የሚቀያየሩ ከሆነ ተፅዕኗቸው (ኢምፓክታቸው) ዝቅተኛ ይሆናል። ተራው ዜጋ የራሱ አድርጎ ሊመለከታቸውና ሊኖራቸው ይሳነዋል።
ዘላቂነት ያላቸው፣ የጋራ ማንነት ላይ የሚያተኩሩ፣ በዜጎች ግለሰባዊ ህይወት እና አኗኗር ላይም ትርጉም የሚኖራቸው ሊሆኑ ይገባል ብዬ አስባለሁ።
ይሄ ልማድ ሦስት ዓመት የሆነው ይመስለኛል። እስኪ በየዓመቱ የሚሰጡትን ስያሜዎች እንመልከታቸው፦
2011 ፥ መሪ ቃል፡ «ጷጉሜን በመደመር»
በ2011 ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ አቅጣጫ ወርዶ የጳጉሜ ስድስት ቀናት ስያሜ ወቶላቸው አስተባባሪዎች ተመደቡላቸው።
- ጳጉሜ 1፡ የብልጽግና ቀን
- ጳጉሜ 2፡ የሰላም ቀን
- ጳጉሜ 3፡ የሀገራዊ ኩራት ቀን
- ጳጉሜ 4፡ የዴሞክራሲ ቀን
- ጳጉሜ 5፡ የፍትሕ ቀን
- ጳጉሜ 6፡ የብሔራዊ አንድነት ቀን
የዚያኔ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጽ/ቤት በሰጠው መግለጫ ጳጉሜ 5 «በየዓመቱ የፍትሕ ቀን ሆኖ እንደሚከበር» አስታውቆ ነበር። በሚቀጥለው ዓመት ቀኑ በሌላ ተሰይሟል።
ሌሎቹን ስያሜዎችንም ብንመለከት ወይ በዜጎች ህይወት ላይ ተዛማጅነት ያጡ ናቸው፣ ወይ ደግሞ በጣም «ጀነሪክ» ናቸው። ለምሳሌ የብልጽግና ቀን አዲሱን ፓርቲ ወይም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ራዕይ ለማስተዋወቅ የታለመ ነበር፣ የዴሞክራሲ ቀን ተራ ዲስኩር ነበር፣ ሀገራዊ ኩራት ደግሞ በጣም ጥቅል/ጀነሪክ ነው፣ የተቀሩት ጥቅልነት ቢኖራቸውም ከሌሎቹ ይሻሉ ነበር።
2012 ፥ መሪ ቃል፡ «አዲስ አበባን በአዲስ የተስፋ ብርሃን»
የአዲስ አበባ መስተዳደር የጳጉሜን ቀናት ከዚህ ዓመት ጀምሮ በራሱ ተነሳሽነት ይሰይማቸው ጀመር። የ2012 ስያሜዎች፦
- ጳጉሜ 1፡ የይቅርታ ቀን
- ጳጉሜ 2፡ የአብሮነት ቀን
- ጳጉሜ 3፡ የአምባሳደርነት ቀን
- ጳጉሜ 4፡ የምስጋና ቀን
- ጳጉሜ 5፡ የብሩህ ተስፋ ቀን
በዚህኛው ዓመት ጥሩ እና ከዜጎች ጋር የሚዋሃዱ ጭብጦች ተሰይመው ነበር። ለምሳሌ የይቅርታ፣ የአብሮነት እና የምስጋና ቀናት በጣም ጥሩ ነበሩ፤ ከፖለቲካ ማዕቀፍም መውጣት የሚችሉና ሕዝባችን እየሟጠጡ የመጡበትን እነዚህን ግለሰባዊ እና ማኅበራዊ እሴቶች እንዲያጤንና ወደዘላቂ ባህልነት እንዲያጠናክራቸው የሚያስችሉ ነበሩ። ከ90% በላይ የሚሆነው ሕዝብ ከመንግሥት መግለጫ ይልቅ ለጎረቤቱ ደህንነት እና ውለታ ከፍተኛ ዋጋ አለው።
ሆኖም የአምባሳደርነት እና የብሩህ ተስፋ ቀን የተባሉት፣ አገላለፃቸው ራሱ ችግር አለበት። ለምሳሌ ብሩህ ያልሆነ ተስፋ የለም።
2013 ፥ መሪ ቃል፡ «አዲስ – የኢትዮጵያ የድል ነፀብራቅ»
እንደገና ዘንድሮ የአዲስ አበባ መስተዳደር አዳዲስ ስያሜዎችን ይዞ መቷል።
- ጳጉሜ 1፡ የኢትዮጵያዊነት ቀን
- ጳጉሜ 2፡ የአገልጋይነት ቀን
- ጳጉሜ 3፡ የመልካምነት ቀን
- ጳጉሜ 4፡ የጀግንነት ቀን
- ጳጉሜ 5፡ የድል ቃልኪዳን ብስራት ቀን

እንግዲህ ላለፈው አንድ ዓመትና ከዚያም በላይ ሀገሪቱ የነበረችበት ሁኔታ ከማንም የተደበቀ አይደለም። ካቻምና የነበሩት የሰላም ቀን እና የብሔራዊ አንድነት ቀን ምን እያደረግን ስለዋልንባቸው ነው ዛሬ እዚህ ላይ የደረስነው? አምና የነበረው የይቅርታ ቀንስ ፋይዳው ከምን ደርሶ ነው በዚህ ጊዜ ላይ ከጥቅም ውጪ እንዲሆን የተፈለገው?
ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያዊነት ቀን ብሎ መሰየም ስህተቱ ሁሉም ስያሜዎች በእርሱ ላይ የሚያውጠነጥኑ ስለመሆናቸው መዘንጋቱ ብቻ ሳይሆን፣ በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ እንደተለመደው አውርደው እንደሚጥሉት አለማስተዋላቸው ነው። አገልጋይነት እና መልካምነት እርስበርስ ተቃቃፊ (ኮምፕልመንተሪ) ናቸው።
የጀግንነት ቀን የቃሉ ትርጉም አንድምታው ብዙ ከመሆኑ የተነሳ አከራካሪነት የሚኖረው ሲሆን፣ ስለጦርነት ከሆነ ደግሞ በዓመቱ ውስጥ ከአንድም ሁለት እና ሦስት ቀናት እንዳሉን በመዘንጋት ቋሚነት ላይ ሳይሆን ወቅታዊ አጀንዳ ላይ ማተኮሩን ይጠቁማል። በሌላ በኩል የመጨረሻው የድል ቃልኪዳን ብስራት ቀን የምር ግራ አጋቢ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ድል ለማድረግ ቃልኪዳን የሚገባበት ነው ወይስ ድል የሚበሰርበት? ያም ሆነ ይህ የጀግንነት ቀን ከተባለው ጋር የተጋመደ ተደርጎ ሊያምታታ የሚችል ስያሜ ነው።
በመጨረሻም ለማለት የተፈለገው፦
- የራሳችን የቀን አቆጣጠር ያለን እንደመሆናችን እነዚህ የጳጉሜ ቀናት ሀገራዊ መንፈስን በሚያነቃቁና ለእያንዳንዱ ዜጋ ትርጉም በሚሰጡ ሰዋዊ ጭብጦች ላይ በማተኮር ብንሰይማቸው፤
- በየዓመቱ የወቅቱን የፖለቲካ ንፋስ እየተከተሉ ቀናቱን ከመሰየም ይልቅ ሰው መሆናችንን እና የጋራ ማንነታችንን የሚያስታውሱ እና የሚያጠናክሩ ስድስት መሠረታዊ ጭብጦች በዘላቂነት ሰይመን አምስቱን በየዓመቱ ብናከብራቸው፣ ስድስተኛውን ደግሞ በየአራት ዓመቱ በልዩ ሁኔታ ብናከብረው፤
- የአዲስ አበባ መስተዳደር ሲያውጀውና አከባበሩን ሲያቅድ በሀገር-አቀፍ ደረጃ ለማክበርና ልማድ ለማድረግ ስለሚያዳግት በአንዱ የፌዴራል ተቋም አማካኝነት ቢታቀድና ክልላዊ ትስስርም ቢኖረው፤
ምን ይመስላችኋል?
በግዛው ለገሠ

