“ተከታታይነት ያለው የሥልጣን ሽግግር ሊኖር ይገባል” – ጀምስ ሐሪንግተን (1611-77)
ጀምስ ሀሪንግተን የተወለደው ሊንከንሻየር፣ ኢንግላንድ ነው፡፡ ገና በወጣትነቱ ነበር የአባቱን ከፍተኛ ሀብት የወረሰው፡፡ በኦክስፎርድ ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ ታላቁን የአውሮፓ ጉብኝት አደረገ፡፡ በቬነስ ሪፐብሊክ እጅግ ተማረከ፤ እናም የቀዳማዊ ቻርልስ ታማኝ ደጋፊና ጓደኛ እንደሆነ ቢቀርም በ1635 ወደ አገሩ የተመለሰው አምኖ የተቀበለ ሪፐብሊካን ሆኖ ነበር፡፡ ንጉሡ ካበቃለት በኋላ ነው ሀሪንግተን “The Common Wealth of Oceana” ወደተሰኘው ዋነኛ ሥራው ይበልጥ ያተኮረው፤ ይህ ሥራው በ1656 ለህትመት በቅቷል፡፡ የንጉሣዊ ሥርዓቱ ወደ ቦታው ሲመለስ ሀሪንግተን የጋራ ብልፅግናውን ወደነበረበት ለመመለስ አሲሯል በሚል ተጠርጥሮ በ1661 በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡ በእስር ላይ በነበረ ጊዜም ከፍተኛ የጤና ችግር ገጠመው፤ እስከመጨረሻውም ሙሉ ለሙሉ አላገገመም፡፡ ሆኖም ህይወቱ ባለፈች ጊዜ የአእምሮ በሽተኛ ነበር የሚባለው ወሬ ተጨባጭ ማረጋገጫ አልተገኘለትም፡፡
ሀሪንግተን በእሱ ዘመን ለነበሩ የፖለቲካ ጠበብቶች እምብዛም ክብር ነበር የሚያሳየው፡፡ ቶማስ ሆብስን እንደ ፈላስፋነቱ ያደንቀዋል፤ ነገር ግን ፖለቲካውን አይወድለትም፡፡ ለእርሱ የፖለቲካ ሞዴሎቹ የፕሌቶ “Laws” የተሰኘው ሥራ፣ የአርስቶትል “Politics”፣ የፖሊቢየስ “Histories”፣ እንዲሁም በተለየ መልኩ የሚያደንቃቸው የማኪያቬሊ ፅሁፎች ናቸው፡፡ ኦሺና (Oceana)፣ ምናባዊ ተብሎ የተገለፀ የጋራ ብልፅግና መንግሥትን የሚወክል ነው፤ ሆኖም የተጠቀሱት ክስተቶች፣ ቦታዎች እና ሕዝቡ በመጠኑ ለወጥ ይደረጉ እንጂ በገሀዱ ዓለም ያሉትን ለመወከል የታሰቡ ናቸው፡- «ኢምፖሪየም» ለንደን ስትሆን፣ «ሄራ» ዌስትሚኒስትር ነው፤ «ሌቪያታን» ቶማስ ሆብስ ነው (ሌቪያታን የሆብስ መፅሐፍ ርዕስ እንደመሆኑ)፤ «ፓኑርገስ» ሐነሪ 4ኛ ነው፤ “ፓርቴኒያ” ቀዳማዊ ኤልዛቤት ናት፤ «ኦለፊየስ ሜጋሌቶር» ክሮምዌል ነው፤ ሌሎቹም እንደዚያው፡፡
የሀሪንግተን የፖለቲካ እሳቤ በጣም ወሳኝ እና ኦሪጅናል መርህ በኢኮኖሚያዊ (የሀብት) ክፍፍል እና በፖለቲካ ሥልጣን መካከል ያስቀመጠው የምክንያትነት ትስስር ነው፡፡ እርሱ እንደሚያስበው፣ የአንድ መንግሥት የሥርዓት ዓይነትና ትግበራ ያለጥርጥር በንብረት (በተለይም በመሬት) ክፍፍል ላይ ይመረኮዛል፡፡ የመሬት ቁጥጥር ወታደራዊ አገልግሎትን በምትኩ ለማግኘት ሲል አያሌ ተከራዮችን ባለይዞታ በሚያደርገው በንጉሡ እጅ ከገባ ውጤቱ ገደብ የለሸ ንጉሣዊ ሥርዓት (absolute monarchy) ነው፡፡ በሌላ በኩል መሬት አንፃራዊ የሆነ አነስተኛ ቁጥር ባላቸውና በሥራቸውም ሰፊ ቁጥር ያላቸውን ገባሮች ወይም ተከራዮች መያዝ በቻሉ መኳንንቶች ቁጥጥር ስር ከሆነ ውጤቱ ድብልቅ ወይም የፊውዳል ንጉሣዊ ሥርዓት ነው፡፡
የፊውዳል ባላባቶች የንጉሣዊ ሥርዓቱን ሥልጣን ወይም ጉልበት የመገደብ አቅም አላቸው፤ ነገር ግን የራሳቸው የእርስ በርስ ሽኩቻ ሥርዓቱን በአንድነት እንዳይገረስሱት ይከላከልላቸዋል፡፡ የፊውዳል ሥርዓቱ አካላቶች በሚበታተኑ ወይም በሚለያዩ ጊዜ ውጤቱ የጋራ ብልፅግና (Commonwealth) ወይም ሪፐብሊክ ነው፡፡ በአጭሩ ሲገለፅ፣ መንግሥት ንብረትን ይከተላል፡- አንድ የመንግሥት ሥርዓት ዓይነት ወደሌላ የመንግሥት ዓይነት የሚቀየረው የመሬት ክፍፍል ለውጦችን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ስለዚህም በማያስደንቅ መልኩ ሀሪንግተን የእንግሊዝን ታሪክ የሚመለከትበት ቀዳሚ መንገድ ኢኮኖሚያዊ ነው፡፡ የጥንቱ የፊውዳል ሥርዓት በንብረትና በንጉሦች እና በመኳንንቶች መካከል ባለ የሥልጣን ክፍፍል ላይ የተመረኮዘ ነበር፡፡ ይህ ክፍፍል በፅጌሬዳዎቹ ጦርነቶች (War of the Roses) እና በእነ ቲዮዶር አማካኝነት በተከሰተው የኢኮኖሚ ለውጦች ነበር ሚዛኑን ያጣው፡፡ ሔነሪ 7ኛ፣ ታላቁን የፊውዳሉን የመሬት ሀብት አንፃራዊ ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው የንግድ ባለቤቶች መልሶ አከፋፈለው፡፡ ሔነሪ 8ኛ፣ ገዳማቱን እንዲያከትሙ በማድረግ ከፍተኛውን መሬት በባለቤትነት የያዘችውን፣ የቤተ-ክርስቲያኗን ንብረት መልሶ አከፋፈለው፡፡ ውጤቱም በከፍተኛ መጠን ቁጥራቸው የበዛ የትናንሽ መሬት ባለቤቶች መደብ መፈጠር ነበር፤ እነዚህ የትናንሽ መሬት ባለቤቶች በጋራ ያላቸውን ኃይል በመገንዘባቸውም የፖለቲካ መብቶችን የመጠየቅ ጉዳይ ከእነሱ ሊመጣ ችሎ ነበር፡፡ የእርስ በርስ ጦርነቱን ተከትሎም እንደ የፖለቲካ እውነታዎች የተቀሰቀሱት ግጭቶች ወደ ኢኮኖሚያዊ እውነታዎች እራሳቸውን ለወጡ፡፡
ሀሪንግተን ይቀጥላል፡፡ የቅርቡ የእንግሊዝ ታሪክ ለሕዝቡ የሚያደላ የንብረት መልሶ ክፍፍልን እንደመታዘቡ፣ በዚያች አገር በማያሻማ መልኩ ተስማሚ የሚሆነው የመንግሥት ሥርዓት ዓይነት የሪፐብሊክ ሥርዓት መሆኑን ያመለክታል፡፡ የሀሪንግተን ፕሮጀክት «እኩል» የጋራ ብልፅግና የሚለውን የሚፈጥር ሕገ-መንግስት ለ«ኦሺና» መንደፍ ነው፡- በተጠቃሽም በውስጡ በራስ ጥቅም እና በሕዝባዊ ጥቅም መካከል ጉልህ ግጭቶች የማይኖሩበት፣ ሚዛኑን የጠበቀ እና የተረጋጋ የጋራ ብልፅግና፡፡ በዚህም አማካኝነት የጋራ ብልፅግናውን የመቀልበስ ፍላጐት የሚያድርበት አይኖርም፡፡ እንደሱ ሐሳብ፣ እንዲህ ያለው የጋራ ብልፅግና ወጥነት በሌለውና ወገንተኛ በሆነው የሰው ፈቃድ ሳይሆን ሁሉንም በእኩል ዓይን በሚመለከት የሕግ የበላይነት ሊመሠረት ይገባል፡፡ የሚመራበትም መሠረታዊ መንገድ የንብረትን በጥቂቶች እጅ የመከማቸት ተፈጥሯዊ አዝማሚያ በተቃረነ መልኩ ሕዝባዊ የመሬት ባለቤትነትን የሚያስጠብቅ የመሬት አጠቃቀም ሕግ ይሆናል፡፡ ይህ የመሬት አጠቃቀም ሕግ ዓመታዊ ዋጋቸው ከ2000 ፓውንድ ለማይበልጡ ይዞታዎች በተቻለ መጠን የመሬት ባለቤትነትን ሊገድብ ይችላል፡፡ ይሁንና ግን የሀሪንግተን የሕዝባዊ ባለቤትነት ሐሳብ ይዘት እኛ በዛሬ ዘመን ሕዝባዊ ብለን ከምንጠራው ጋር የተለየ ነው፡፡ ቢያንስ 5000 የሚያህሉ የመሬት ባለቤቶች የጋራ ብልፅግናውን የተረጋጋ ለማድረግ በቂ እንደሆኑ ያስባል፡፡
መንግሥት የሕዝባዊ ወይም የአብላጫው ፈቀድ (popular will) መስፈንን የሚያረጋግጡ ሦስት መገለጫዎች ወይም ጠባዮችን ማካተት እንዳለበት ሀሪንግተን ያስባል፡፡ የመጀመሪያው፣ ሁሉም የማህበረሰቡ አባላት በመንግሥት ውስጥ የበኩላቸውን ሚና የመጫወት እድል እንዲኖራቸው ለማረጋገጥ ተከታታይነት ያለው የሥልጣን ሽግግር ሊኖር ይገባል፡፡ ማጂስትሬት ወይም የመንግሥት ኃላፊዎች ብዙውን ጊዜ ከአንድ ዓመት ለማይበልጥ ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚመረጡ ሲሆን ጊዜያቸውን ከጨረሱ በኋላ ወድያውኑ በድጋሚ ለመመረጥ አይፈቀድላቸውም፡፡ ሁለተኛው፣ ፍርሃት እና ውለታ በውጤቱ ላይ ተፅዕኖ እንዳይኖራቸው ሲባል ምርጫዎች በምስጢራዊ ድምፅ አሰጣጥ ሊከናወኑ ይገባል፡፡ ሦስት፣ የሕግ አውጪው አካል በሁለት ምክር ቤቶች የተዋቀረ (bicameral legislature) ይሆናል፡፡ የመወያየት ወይም ፖሊሲ የመቅረጽ ተግባር ጥቂት የጥበብ እና የተሞክሮ ግለሰቦችን ባካተተው በሴኔቱ ይተገበራል፡፡ ሴኔቱ ያቀረበውን ሕግ የማፅደቅና የመጣል ሥራ ደግሞ ከፍ ያለ እርከን ባለውና «ፕሪሮጋቲቭ ትራይብ» ተብሎ በሚጠራው አካል ላይ ይወድቀል፤ ሆኖም ይህ አካል የራሱ የሆነ የመወያየት ሥልጣን የለውም፡፡ ሁለቱም የሕግ አውጪ አካላት አባላት የመንግሥትን ከታች ወደላይ እርከን እና የንብረት መመዘኛዎችን ባካተተ መልኩ ቀጥተኛ ባልሆነ የምርጫ ሥርዓት ይመረጣሉ፡፡
ሀሪንግተን ዜጋነትን የራሳቸው የሆነ የገቢ ምንጭ ላላቸው ግለሰቦች ብቻ ይገድበዋል፡፡ የጉልበት ሠራተኞች ወይም አገልጋዮች – የዕለት ተዕለት ኑሯቸው በሌላ ሰው ላይ ተመረኮዘ ሰዎች – በግል ጥቅም የማይታለል የፖለቲካ ፈቃድ ሊኖራቸው እንደማይችል ያስባል፡፡ ዜጐቹ እድሜያቸው ከሰላሳ በታች በሆኑት መደበኛ የወታደራዊ መደብ እና ተጠባባቂ ወታደራዊ ኃይልና ዋናው የፖለቲካ ጥበብ ማጠራቀሚያ በሆኑት አዛውንቶች መካከል ይከፈላሉ፡፡ የዓመት ገቢያቸው 100 ፓውንድ እና ከዚያ በላይ የሆነ ዜጐች አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ፈረሰኛ ወታደር ሆነው ያገለግላሉ፤ የዓመት ገቢያቸው ከ100 ፓውንድ በታች የሆኑት ደግሞ የእግረኛ ጦሩን ይቀላቀላሉ፡፡ ማንም ቢሆን በውትድርና አገልግሎት ይሳተፋል፤ እንዲያውም አስፈላጊ ከሆነ ግዳጅ አለ፡፡ አዛውንቶችን እና አቅመ ደካሞችን ለመንከባከብ ምቹ የሆነ አወቃቀርም ይዘረጋል፡፡
ትምህርት የጋራ ብልፅግናው ወሳኝ ገጽታ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ትምህርት ቤቶች የሚተዳደሩት በመንግሥት ወጪ ይሆናል፡፡ እድሜያቸው ከዘጠኝ እስከ 15 የሆኑ ተማሪዎች በትምህርት ክፍለ ጊዜ መገኘታቸው ግዴታ ነው፤ መቅረት የተከለከለ ነው። የመንግሥት ህልውና (ጥንካሬ) በሚያስተዳድራቸው ሕዝቦች አስተሳሰብና ግንዛቤ ላይ በይበልጥ እንደሚመረኮዝ ሀሪንግተን ተረድቷል፡፡ ስለዚህም ትምህርት ሕገ-መንግስቱን ለማብራራትና የፖለቲካ ግንዛቤን ለማጠናከር ዓላማ ሳምንታዊ የትምህርት ክፍለ ጊዜዎችን ያካተተ ይሆናል፡፡ የጋራ ብልጽግናው ሃይማኖታዊ ህይወት እንዴት መዋቀር እንዳለበትም ሀሪንግተን የበለጠ አፅንኦት ሰጥቶታል፡፡ በሴኔቱ አማካኝነት የተመረጠ የሃማኖት ምክር ቤት ክትትል የሚያደርግለትና አስገዳጅነት የሌለው ሀገር አቀፍ ሃይማኖት ይኖራል፡፡ እያንዳንዱ በቡድን፣ በቡድን የሚገኝ ምዕመን የራሱን ሃይማኖታዊ መሪ የመምረጥ ነፃነት አለው፡፡
ሀሪንግተን የሚያነሳው አብዛኛው ሐሳብ “ancient prudence” ብሎ ከሚጠራው የተወሰደ ስለመሆኑ እሱም በደስታ የሚይምነው ነው፡፡ (ancient prudence – በጥንቱ ዓለም የሕጐች መንግሥት የሰፈነበት የፖለቲካ አወቃቀር ነው፤ modern prudence – ደግሞ በመፅሐፉ ሁለተኛ ክፍል ውስጥ የሚጠቅሰው ከሮም ስርወ-መንግስ መውደቅ በኋላ የታየው የአውሮፓ የፖለቲካ መዋቅር ሲሆን፣ ለሀሪንግተን የሕጐች ሳይሆን የሰዎች መንግሥት የሰፈነበት ነው፡፡) ሆኖም ሀሪንግተን የፖለቲካ ፅንሰ-ሐሰብን የመተንተን አስደናቂ ብቃት የተላበሰ ነው፡፡ በሕገ-መንግሥቶች ነዳፊነቱ በ18ኛው ክፍለ ዘመን በነበረችው አሜሪካ አድናቆት ተችሮትል፡፡ የካሮላይና እና የፔንሲልቫኒያ ሕገ-መንግሥቶች በተረቀቁ ጊዜ የሀሪንግተን ተፅዕኖ እንዳረፈባቸው ይጠቆማል፡፡ ማርክሲስት የታሪክ ተማራማሪዎች የእንግሊዝ እርስ በርስ ጦርነት የከበርቴው መነሳት (rise of the gentry) በሚባለው አማካኝነት የተቀሰቀሰ የብርዥዋዚ አብዮት ነበር ለሚለው ፅንሰ-ሐሳብ ድጋፍ የሚሆናቸውን ከእርሱ ጽሁፎች ውስጥ አግኝተዋል፡፡
ሀሪንግተን የጠቆማቸው አብዛኛዎቹ መርሆዎች የሊበራል መንግሥት መገለጫዎች መመዘኛ ለመሆን በቅተዋል፡- የተፃፈ ሕገ-መንግሥት፤ ምርጫና የመንግሥት ኃላፊዎች በአጭር ጊዜ የሥልጣን ዘመን መለዋወጥ፤ የሃይማኖት ነፃነት ዋስትናዎች፤ በመንግሥት ወጪ የሚሸፈን ለሁሉም የሚሰጥ ትምህርት፡፡
ብዙውን ጊዜ የፖለቲካ ችግሮችን ሁሉንም ነገሮች ባማከለ መልኩ የሚመለከት በመሆኑ ይወደሳል፡፡ እሱም ቢሆን የፖለቲካ እሳቤን ከተዋቂው የሕክምና ባለሙያ፣ ከዊሊያም ሀርቬይ (1578-1657) ሥራ ጋር ሊዛመድ የሚችል ሳይንስ ስለመሆኑ ያስቀምጣል፡፡ (ዊልያም ሀርቬይ በሰውነታችን ወስጥ ደም ከልብ ተረጭቶ እንዴት እንደሚዘዋወር ትክክለኛና ዝርዝር በሆነ መልኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ያብራራ እንግሊዛዊ ሳይንቲስት ነው፡፡) እርሱ የኖረበት ዘመን የፖለቲካ ቀውስ የተስተዋለበት ሆኖ ሳለ፣ ሥራዎቹ አመክኒዮአዊ በሆነ ገለልተኛነት መቅረባቸው የበለጠ ነጥብ እንዲመዘገብለት አድርገዋል፡፡
ለበለጠ ንባብ
ቀዳሚ ምጮች፡-
The Political Works of James Harrington, ed. J.G.A. Pocock (Cambridge: Cambridge University Press, 1977).
ተቀፅላ ምንጮች፡-
Blitzer, C.: An Immortal Commonwealth: The Political Thought of James Harrington (New Haven, CT: Yale University Press, 1960).
Macpherson, C.B.: The Political Theory of Possessive Individualism (Oxford: Oxford University Press, 1962).
Raab, F.: The English Face of Machiavelli (London: Routledge & Kegan Paul, 1964).
Tawney, R.H.: Harrington’s Interpretation of His Age (Oxford: Oxford University Press, 1942).