«የሚፈልገው ፖለቲካዊ ጥያቄ ካለ መደራደር እንዳለበት እንመክራለን» – ጀነራል ብርሃኑ ጁላ (ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም)
የጀነራል ብርሃኑ ጁላን ንግግር ለመመልከት ፈልጌ ኢቲቪ ላይ ብፈልግ የለም፣ ፋናንም አየሁ – የለም። የማታ ሁለት ሰዓት የኢቲቪ ዜና ላይ በመሃል የአምስት ደቂቃ ገደማ ዜና ተደርጎ መቅረቡን ተመለከትኩኝ። በኋላ ግን ኢዜአ ላይ ሙሉውን አየሁት።
በርግጥ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ይህን መግለጫ የሰጡበት ዋነኛ ምክንያት የህዳሴ ግድቡ “ሁለተኛ ዙር ሙሌት” ይመስላል። ለግብጽም፣ ለአባይ ፖለቲካም የጀነራሉ መግለጫ ጠቃሚ ነው። ኢቲቪም ስለሀገሪቱ ሁኔታና ስለትግራይ ጦርነት በዜናው በመጠኑ ቢያነሳም፣ የጀነራሉን መግለጫ ዋና ነጥብ አድርጎ የዘገበው የእንኳን ደሳለን መልክቱን ነበር።
ሆኖም የመከላከያ ቲቪ እና ኢዜአ ብቻ በተገኙበት በዚህ መግለጫ ላይ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ የተናገሩት ለ20 ደቂቃ ነው። ስለግድቡ ያወሩት ለ4 ደቂቃ ብቻ ነበር። መጨረሻ ላይም፣ «ወዳጆቻችን በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ። ዛሬ የድል ቀን ነው፤ በዚህ የድል ቀን ለመተንፈስ ፈልጌ ነው እዚህ የተገኘሁት።» በማለት አመስግነው ተሰናብተዋል።
የሆነ ሆነና ጀነራሉ ሠራዊቱ ያለበትን ቁመና እና ዝግጁነት፣ ለመንግሥት የፖለቲካ ውሳኔ ታዛዥ መሆኑን፣ አሁንም ትዕዛዝ እየጠበቀ መሆኑን አስረግጠው የተናገሩ ሲሆን፣ ምክረ ሀሳቦችንም አቅርበዋል። የፖለቲካ ድርድር ጠቃሚ እንደሚሆን ግን ደግሞ ቅድመ-ሁኔታዎችን መደርደር እንደማያዋጣ የተነናገሩበትን እነሆ ልጋብዛቹ፦
«ጁንታው ለሦስተኛ ዙር ቆሞ ቢያስብ የተሻለነው። ማዕከሉ የትግራይ ሕዝብ ከሆነ፣ የትግራይን ሕዝብ እስከዛሬ ያሰቃየው ስለሚበቃ፣ ቆም ብሎ አስቦ መንግሥት ያመቻቸውን የተናጠል ተኩስ አቁም [ተቀብሎ] እሱም ተኩስ አቁሞ፣ የሚፈልገው ፖለቲካዊ ጥያቄ ካለ መደራደር እንዳለበት እንመክራለን። በቅድመ ሁኔታ የተሽቆጠቆጠ ሰላም አይመጣም፤ ማንም ቅድመ-ሁኔታ፣ እዚህ ውስጥ ግባና ነው የምንደራደረው የሚል ካለ ማንም እሺ አይልም። አንድ ነገር ስታደርግ ሌላው ምን ያደርጋል የምለውንም ነገር ማሰብ ጥሩ ነው።»
ጀነራል ብርሃኑ ጁላ አክለውም «የጥሞና ጊዜ ለትግራይ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለራሱ ለጁንታውም የሚያስፈልገው ይመስለኛል» ብለዋል።
እኔን የሚያሰጋኝ መንግሥት ህወሓት የዘረዘራቸውን ቅድመ-ሁኔታዎች ለመቀበል እና ላለመቀበል እየዋለለ ያለበት ሁኔታ ላይ የምንገኝ ስለሚመስል ነው። የሰሞኑ የአማራ ክልል የክተት አዋጅ፤ የፌደራል መንግሥቱ በሀገር እና በዜጎች ደህነነት ጉዳይ (አከራካሪዎቹን ቦታዎ ተቆጣጥሮ ለማስተዳደር) የመሪነት ሚና ለመጫወት የሚያሳየው ማቅማማት፣ ብሎም አብያችን እሁድ እለት፣ «በግብ አንድ ሆነን የአካሄድ ክርክር ይፈጠር ይሆናል።» በማለት የፃፈው ነገር ከፍተኛ መተራመስ እንዳለ የሚጠቁም ነው። ትናንት እንዳልኩት፣ የውጭ ጫናን ለመቋቋም የውስጥ አንድነት መሠረታዊ ነው፤ ይህንን የውስጥ አንድነት መፍጠር እና ማፅናት የሚቻለው ደግሞ በፌደራል መንግሥቱ ይመስለኛል፤ የፌደራል መንግሥቱን ጥንካሬ ከመቼውም በበለጠ ማረጋገጥ የሚያስፈልግበት ጊዜ ይመስለኛል። በተጨማሪም በፖለቲካዊ መፍትሔ እስከመጨረሻው ተስፋ አለመቁረጥ ብዙ ህይወትን ይታደጋል።
በግዛው ለገሠ