«ከነጋዴ እና ከምሁር» የሚል የአራተኛ ክፍል ክርክር ላይ የለሁበትም!
በአንድ ወቅት የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት አማረ አረጋዊ፣ አንዳንድ ጋዜጠኞች ለባለሃብቶች እያሽቋለጡና የጋዜጠኝነትን ሙያ ሲያረክሱ ሲመለከት፣ ሥራቸውን «ሸሌ ጆርናሊዝም» ብሎ ስም እንዳወጣለት አስታውሳለሁ፡፡ (አማረ ይሄን ሊል አይችልም የሚል ቢኖር እንኳን በስያሜው መስማማቱ አይቀርም፡፡)
እናም በቀደም ጠቅላይ ሚኒስትራችን አብይ አህመድ ምሁርነትን አረከሰ እየተባለ ከፍተኛ ውርጅብኝ እየወረደበት ነው፡፡ ይህ ሰው በሌሎች መድረኮች ላይ ስለእውቀት አስፈላጊነት ሳይናገር ቀርቶ አይመስለኝም፡፡ ኧረ እንዲያውም ስለ ‘አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ’ ምናምን የሆነ ውስዋስ ወስጥ ሁሉ ከቶን ነበር፡፡
ግን ደግሞ አብይ በቀደም ከነጋዴ ጋር ነበር፤ በምን ያመስግናቸው፣ ያሞካሻቸው? ያው አብይ አንድ አባዜ አለበት፣ ጆሮ ይወዳል፤ የሚሰማው ካለ፣ የሚያጨበጭብማ ካለ፣ በቃ ነን-ስቶፕ ይመስለኛል፡፡ ምንም ዓይነት ሱስ እንደሌለበት አምናለሁ፤ ግን ጆሮ እና ጭብጨባ ያጦዘዋል፡፡ እናም መስመር ይስታል፡፡ የአብያችን አባዜ ይህ ብቻም አይደለም፤ ‘ኦዲየንስ’ ይንቃል፡፡ ሰዉ ሁሉ ጆሮ እና መዳፍ እንጂ ጭንቅላት ያለው አይመስለውም፡፡
ምን ለማለት ነው፣ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የምሁራን ሀገራዊ ጥቅም ጠፍቶት አይደለም፤ የባለሃብቱን አንጀት ለማራስ ብሎ እንጂ፡፡ በቃ እኔ ከዚህ በላይ ምንም አልልም፤ አንተ ግን «እያሽቋለጠ ነው» ወይም «ከሸሌ ጆርናሊዝም አይለይም» ማለት ትችላለህ፡፡
እኔ ግን ምንም አልልም፡፡ ምክንያቱም አንድ ሂደት በግልፅ እየታየኝ ነው፡፡ ከላይ ካየናቸው አባዜዎች ባሻገር፣ አብይ ሌላ ብቃትም አለው፡፡ ያሰበውን በየትኛውም መንገድ ከማስፈፀም ወደኋላ አይልም፡፡ በተጨማሪ ደግሞ የመደመር አማኞች እና የብልፅግና ካድሬዎች ቁጥር ከኮሮና በላይ እየተንሰራፋ ይገኛል፡፡
እናም በግልፅ እየታየኝ የመጣው ሂደት፣ መንግሥታችን፣ አብያችን ምናልባትም በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ፍፁም ወደሆነ አምባገነንነት መቀየሩ የማይቀር መሆኑ ነው፡፡ (ይበልጥ የሚያሳስበኝ፣ አብይን እንደግለሰብ ጥሩነቱ እያየ «አምባገነን ቢሆንም ለበጎ ነው» የሚለው ሕዝብ ቁጥሩ አያሌነት ነው፡፡)
እናም እኔ ምንም አልልም፡፡ ምክንያቱም፦ አንደኛ አብይን ደረት ነፍቶ መተቸትም ሆነ ግልፅ ስድብ መሳደብ፣ የአምባገነንነት ‘ትራንስፎርሜሽን’ ሂደቱን ያብሰው እንደሆን እንጂ አያስቀረውም የሚል ፍራቻ አድሮብኛል፡፡ ላሰበው ነገር የሚገድበው የለም ወይም ያለ አይመስለውም ብዬ አልነበር፤ ራዕይ እና እልኸኝነቱንም አክሎ መመልከት ይበጃል፡፡ ሁለተኛ፣ ከፍ ብሎ እንዳልኩት አማኙና ካድሬው እየጨመረ ነው፡፡ የአንተን ትችት ወይም ስድብ አብይ ላይሰማ፣ ላያይ ይችላል፡፡ ይሄ አማኝና ካድሬ መቀጣጫ ያደርግሃል፣ መሞካሻ ያደርግሃል፣ እድሜ ማራዘሚያው ያደርግሃል፡፡
እናም እኔ ምንም አልልም፡፡ ልጆቼን ላሳድግበት!
___________
በግዛው ለገሠ