Ankuar

Politics, culture and society in Ethiopia

COVID-19FEATURED

ኮቪድ-19 በስፋት እየተሰራጨ መሆኑን የዛሬው ውጤት ያረጋግጣል! (አሁንም አንዘናጋ!)

ዛሬ 1843 የላብራቶሪ ምርመራዎች ተደርገው 25 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። ይህ ቁጥር ትላንት ከተመዘገበው (17) ጋር ሲነፃፀር ብዙም ልዩነት ያለው ላይመስል ይችላል። ሆኖም ትላንት 13 ሰዎች በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ የነበሩ ናቸው። ነገር ግን የዛሬው ውጤት ኮቪድ-19 በኅብረተሰቡ ውስጥ በስፋት የተሰራጨ ወይም እየተሰራጨ መሆኑን በግልፅ ያመላክታል።

የሀገር ውስጥ ሥርጭት

ዛሬ ከተገለፀው ቁጥር 22 ኬዞች የሀገር ውስጥ ሥርጭቶች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ግን 19 ኬዞች በሽታው ካለበት ሰው ጋር የነበራቸው ንክኪ አልታወቀም። ማለትም ከማን እንደተላለፈባቸው አይታወቅም። ይህም በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 የኅብረተሰብ ሥርጭት ከፍተኛ ቁጥር ላይ መድረሱን ያመላክታል።

በየዕለቱ የሚሰጡ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ፣ እስከዛሬ በሀገር ውስጥ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 77 ነው። ከእነዚህ ውስጥ፣ የዛሬዎቹን 19 ሰዎች ጨምሮ፣ 42 ሰዎች (55%) ንክኪያቸው እንዳልታወቀ የተገለፀ ነው። ይህም ከፍተኛ ስጋት ሲሆን፣ ከመቼውም በላይ ኅብረተሰቡ መዘናጋት እንደሌለበትና ጥንቃቄውን መጨመር እንዳለበት ይጠቁማል።

ከውጭ የገቡ ኬዞች

በዛሬው መግለጫ 3 ሰዎች የጉዞ ታሪክ እንዳላቸው ቢገለፅም፣ በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ እንደነበረ የተገለፀው ግን አንድ ሰው ብቻ ነው – በቦረና ለይቶ ማቆያ።

ሁለቱ ሰዎች የጉዞ ታሪክ ከነበራቸው እና በለይቶ ማቆያ ካልነበሩ፣ በምን ሁኔታ ላይ እንደነበሩ ግልፅ አይደለም። አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ እርምጃው ተግባራዊ መሆን የጀመረው መጋቢት 14 ቀን 2012 እንደመሆኑ፣ እነዚህ ሰዎች ከእርምጃው በፊት የገቡ ናቸው ብሎ ለመደምደም ያዳግታል። ጤና ሚኒስቴርም እስካሁን የገለፀው ነገር የለም። ይህን መሠረት በማድረግ አንኳር የራሱን ማጣራት አድርጓል።

ሆኖም ባደረግነው ማጣራት በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ቆይተው በሚደረግላቸው ምርመራ “ኔጋቲቭ” መሆናቸው በመረጋገጡ ኅብረተሰቡን እንዲቀላቀል ቢደረግም፣ ከጊዜ በኋላ በሚገጥም የህመም ስሜት ምክንያት በድጋሚ ሲመረመሩ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች እንዳሉ ለማወቅ ችለናል። እንዲህ ዓይነት “ፎልስ ኔጋቲቭ” በሌሎች ሀገራት የሚያጋጥም ቢሆንም፣ ግለሰቡ በቫይረሱ የተያዘው ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት ይሁን ወይም እዚሁ ሀገር ውስጥ ለማወቅ አይቻልም። በዚህ ጉዳይ ጤና ሚኒስቴር ማብራሪያ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

እስከዛሬ ከውጭ የገቡ ኬዞች ቁጥር 110 ነው።

ኢትዮጵያ በአጠቃላይ 28,360 የላብራቶሪ ምርመራ ያከናወነች ሲሆን፣ 187 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። አራት ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል። 93 ሰዎች ሙሉ ለሙሉ ያገገሙ ሲሆን፣ ከሚያዚያ 12 ቀን 2012 በኋላ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ሰው በጽኑ ህሙማን ሕክምና ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

——

አሁንም አንዘናጋ፤ ለራሳችን እና ለምንወዳቸው ስንል እንጠንቀቅ!

#ኮቪድ19 #ኢትዮጵያ #COVID19 #Ethiopia

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.