ተጨማሪ 3 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል
የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዛሬ ባሰራጨው መግለጫ ተጨማሪ ሦስት ሰዎች በኮቪድ-19 ኮሮናቫይረስ መያዛቸውን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እስከዛሬ ድረስ በአጠቃላይ 1013 የላቦራቶሪ ምርመራ ያደረገ ሲሆን፣ የሦስቱ ሰዎች ውጤት የታወቀው ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተካሄዱ 66 የላብራቶሪ ምርመራዎች ነው። በዚህም መሰረት በአጠቃላይ በሀገራችን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሃያ አምስት (25) ደርሷል።
ትናንት በወጣ መረጃ፣ 16 ኛዋ ታማሚ 3 ጊዜ በተደረገላት ተደጋጋሚ የላቦራቶሪ ምርመራ ከቫይረሱ ነጻ መሆኗ ተመዝግቧል።
በዛሬው መረጃ፣ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡት ሁለት ግለሰቦች የ30 ዓመትና የ36 ዓመት ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ በተመሳሳይ በረራ ከዱባይ በመጋቢት 15/2012 ዓ.ም ወደ ሀገር የገቡ ሲሆን በአስገዳጅ የለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ ሲሆን የበሽታውን ምልክት ታይቶባቸው በተደረገላቸው የላብራቶሪ ምርመራ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል። ሶስተኛዋ ታማሚ የ60 ዓመት እድሜ ያላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ መጋቢት 6/2012 ዓ.ም ከፈረንሳይ የተመለሱና ክትትል ሲደረግላቸው ቆይቶ የበሽታውን ምልክት በማሳየታቸው በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆነው በተደረገላቸው የላብራቶሪ ምርመራ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ መሆናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል። ሶስቱም ታማሚዎች በለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል።
በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ በለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ያሉ ሃያ አንድ (21) ታማሚዎች ሲሆኑ፣ ሁለት ታማሚዎች በጽኑ ህሙማን ህክምና ክፍል ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል። ሌሎች ሁለት ታማሚዎች ወደ ሀገራቸው (ጃፓን) የተመለሱ ሲሆን፣ ሁለት ታማሚዎች ደግሞ ሙሉ በሙሉ አገግመዋል። ነገር ግን ለጥንቃቄ ሲባል በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡
ህብረተሰቡ የበሽታውን ስርጭት ግምት ውስጥ በማስገባት የመከላከያ መንገዶችን እና ከመንግስት የሚተላለፉ እርምጃዎችን ትኩረት በመስጠት እንዲተገበር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አሳስቧል።
ለተጨማሪ መረጃ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796 ወይም በኢሜል አድራሻችን [email protected] በመጠቀም ማግኘት ይቻላል።
——
#ኮቪድ19 #ኢትዮጵያ
——
በኢትዮጵያ ስለተያዙ ሰዎች ቁጥር ወቂታዊ እና የእለት ክትትል መረጃዎችን በዚህ ሊንክ መከታተል ይቻላል፦ https://ankuar.com/covid19-et
