Ankuar

Politics, culture and society in Ethiopia

COVID-19FEATUREDNews

«የኮሮናቫይረስ በሽታ ወረርሽኝ በቁጥር ከሚገለፀው በላይ ነው።» ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ የጤና ሚኒስትር

› › ዛሬ የሦስት ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነግሯል፤ 22 ሰዎች አገግመዋል።

/ሰኔ 3 ቀን 2012/

መጋቢት 4 ቀን 2012 የመጀመሪያ የኮቪድ-19 ተጠቂ በኢትዮጵያ ከተመዘገበ ድፍን ሦስት ወራት ተቆጥረዋል። በአጠቃላይ 158,521 የላብራቶሪ ምርመራዎች የተደረጉ ሲሆን፣ 2,506 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ የተደረገው ምርመራ ቁጥር እስከዛሬ ከተደረጉ ዕለታዊ ምርመራዎች ከፍተኛው ነው። ከ6,187 የናሙና ምርመራዎች ውስጥ 170 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው መረጋገጡን የዛሬው ሪፖርት ያሳያል። ኢትዮጵያ በሦስት ወር ውስጥ ከዜሮ ተነስታ በቀን ውስጥ 8 ሺህ ገደማ ናሙናዎች የመመርመር አቅም እንዳዳበረች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሰሞኑን ጠቁመው ነበር።

ዛሬ ሪፖርት የተደረገውን ጨምሮ፣ 35 ሰዎች ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል። በሌላ በኩል፣ እስከዛሬ ድረስ 401 ሰዎች ሙሉ ለሙሉ አገግመዋል።

እስካሁን ባለው መረጃ ምርመራ ከሚደረግባቸው ናሙናዎች ውስጥ የፖዘቲቭ ውጤት (positive rate) 1.58 በመቶ ነው። ይህም ማለት ከ200 ምርመራዎች 3 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው ሊረጋገጥ እንደሚችል ይጠቁማል።

በተጨማሪም የሞት ስሌትን (death rate) ስንመለከት፣ አሁን በተመዘገበው መረጃ መሠረት 1 በመቶ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ይህም ማለት ቫይረሱ ከተገኘባቸው 100 ሰዎች ውስጥ 1 ሰው ሊሞት ይችላል የሚለውን ግምት ሊሰጠን ይችላል።

ሆኖም እነዚህ ሁለቱም ስሌቶች በምንመረምረው መጠን እና በየእለቱ በሚፈጠሩ ሁኔታዎች ሊለዋወጡ የሚችሉ ናቸው። እንዲሁም አጠቃላይ የቫይረሱን ስርጭትም ሆነ በሕብረተሰቡ ላይ እያስከተለ የሚገኘውን ጉዳት በትክክል ለመገመት አያስችሉም።

የጤና ሚኒስትሯ፣ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በዛሬው ዕለታዊ መግለጫቸው ላይ እንዳሰፈሩት፣ «የኮሮናቫይረስ በሽታ ወረርሽኝ በቁጥር ከሚገለፀው በላይ ነው።» በተጨማሪም፣ «ከእያንዳንዱ በየዕለቱ ከምንገልፃቸው በቫይረሱ ከተያዙ ቁጥሮች ጀርባ የብዙ ቤተሰቦች እና ጓደኞቻቸው ጭንቀት እና ስጋት አለ» ብለዋል።

የጽኑ ህሙማን ቁጥርም በመጨመር ላይ ሲሆን፣ ዛሬ 33 ሰዎች በጠና ታመው ይገኛሉ።

እስከ ሰኔ 3 ቀን 2012 ድረስ 35 ሰዎች በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ሳቢያ ህይወታቸው አልፏል። 16 ሰዎች ቫይረሱ እንደነበረባቸው የታወቀው ህይወታቸው ካለፈ በኋላ በአስክሬን ምርመራ ነበር።

እድሜያቸው ከ26 እስከ 115 ዓመት ሲሆን፣ 19 ወንድ እና 16 ሴት ኢትዮጵያዊያን ናቸው። 11 ሰዎች (31%) 35 ዓመት እና ከዚያ በታች፣ 17 ሰዎች (49%) ከ36 እስከ 70 ዓመት፣ እንዲሁም 7 ሰዎች (20%) ከ70 ዓመት በላይ መሆናቸውን መረጃዎቹ ያሳያሉ።

የቴሌግራም ቻናል ከፍተናል፣ መረጃዎች በስልኮ እንዲደርስዎ ከፈለጉ ይከታተሉ፦ https://t.me/ankuardotcom

እስካዛሬ ለነበሩ እና ለእለታዊ ቁጥሮች ዝርዝር፣ እንዲሁም ግራፎች ድረ-ገፃችንን ይጎብኙ፦ https://ankuar.com/covid19-et/

#ኮቪድ19 #ኢትዮጵያ #COVID19 #Ethiopia

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.