Ankuar

Politics, culture and society in Ethiopia

COVID-19FEATUREDNews

አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ምን ያህል ጠቃሚ ነው?!

ይህ የ3-D ሲሙሌሽን አካላዊ ርቀትን መጠበቅ በጣም አስፈላጊ ስለመሆኑ ያመላክታል::



የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች እና ባለሥልጣናት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለማቀዝቀዝ ከሁሉም የተሻለው ዘዴ ማኅበራዊ (አካላዊ) ርቀትን መጠበቅ እንደሆነ በተደጋጋሚ ትኩረት ሲሰጡት ቆይተዋል።
.
የበሽታ ቁጥጥር እና መከላከል ማዕከል (CDC) ሰዎች እቤታቸው እንዲሆኑ ይመክራል። መውጣት የግድ ከሆነ፣ ከሌሎች ሰዎች ቢያንስ በስድስት ጫማ (1.8 ሜትር) ርቀትዎን መጠበቅ አለብዎት። የዓለም ጤና ድርጀት (WHO) በትንሹ የሦስት ጫማ (0.9 ሜትር) ርቀትን ይመክራል።
.
ሳይንቲስቶች ስለ አዲሱ የኮሮናቫይረስ በየዕለቱ በመመራመር ትምህርት እየቀሰሙ ሲሆን ተመሳሳይ የመተንፈሻ አካላት ህመሞችን ያጠኑት በተሻለ ሁኔታ እስክንረዳው ድረስ የትኛውም መመሪያ ፍፁም የሆነ ደህንነትን የማስጠበቂያ መንገድ ሊጠቁመን እንደማይችል ይናገራሉ። ይልቁንም ቫይረሱ ሊተላለፍ የሚችልባቸውን ዕድሎች ማጤን፣ ርቀታችንን መጠበቅ ለምን እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ለመመልከት ይረዳናል።

.

እንደ ኢንፉሌንዛ ያሉትን የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች ስርጭት ያጠኑ ሳይንቲስቶች እንደሚሉት፤ በሽታው በዋናነት የሚተላለፈው፣ አንድ ጤነኛ ሰው በበሽታው የተያዘ ሰው ሲያስል፣ ሲያስነጥስ ወይም ሲተነፍስ ከሚወጡ ጠብታዎች ጋር ንክኪ ሲኖረው ነው።
.
የክዮቶ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ውሂብ (ዳታ) በመጠቀም የተቀናበረው ይህ ሲሙሌሽን፣ አንድ ሰው በቤት ውስጥ ቢያስል ሊከሰት የሚችለውን ሁኔታ ያመለክታል። ሳል ከመተንፈሻ አካላት የሚመነጩ የተለያየ መጠን ያላቸው ጠብታዎችን ያስወጣል። ትላልቆቹ ጠብታዎች ወደ መሬት ይወድቃሉ፣ ወይም ወደ ትናንሽ ጠብታዎች ይበታተናሉ።

.

ከባድ ሳሎች ሩብ የሻይ ማንኪያ የሚሆን ፈሳሽ የሚለቁ ሲሆን፣ ጠብታዎቹ በመላው ክፍሉ በፍጥነት ይበታተናሉ። ሲሙሌሽኑ 600 ጫማ ካሬ (182.9 ሜትር ካሬ) በሆነ ክፍል ውስጥ በአንድ ደቂቃ ውስጥ ያላቸውን ስርጭት ያሳያል። በሌላ ሁኔታዎች ውስጥ የስርጭታቸው ባህሪይ የተለየ ሊሆን ይችላል።

.

ሲ.ዲ.ሲ. ከሌሎች ሰዎች ቢያንስ የስድስት ጫማ ርቀትን መጠበቅ፣ ከጠብታዎቹ ጋር የሚኖረንን ንክኪ እንደሚያስቀርና በቫይረሱ የመያዝ ዕድልን እንደሚቀንስ ይጠቁማል። ይህ ምክር መሠረት ያደረገው በሽታው በዋናነት በቅርብ ርቀት በሚወድቁ ትላልቅ ጠብታዎች አማካኝነት ይተላለፋል በሚለው ግመት ላይ ነው።

.

ነገር ግን ይህ ሲሙሌሽን እንደሚጠቁመው እና ሳይንቲስቶችም እንደሚያቀርቡት መከራከሪያ፣ ጠብታዎች ከስድስት ጫማ (1.8 ሜትር) በላይ ሊሄዱ ይችላሉ። በተጨማሪም “ኤሮሶልስ” በመባል የሚታወቁ ትናንሽ ጠብታዎች ግዑዝ አካላት ላይ ከማረፋቸው በፊት አየር ላይ ተንጠልጥለው ሊቀሩ ወይም በአየር ውስጥ ሊጓዙ ይችላሉ። ለሚቀጥሉት 20 ደቂቃዎች ሊሰራጩ የሚችሉትም በዚህ መልኩ ነው።

.

“ ‘ኦ፣ ስድስት ጫማ ርቀት ነው፣ ሁሉም ወደመሬት ወድቀዋል፣ ምንም ነገር የለም’ የምንለው ነገር አይደለም፤ ይልቁንም ቀጣይነት ያለው ነገር ነው።” ይላሉ ዶናልድ ኬ. ሚልተን፣ በሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ የሕብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት የተላላፊ ኤሮሶልስ ሳይንቲስት።

.
በርግጥም፣ ሳሎችን እና ማስነጠሶችን የሚያጠኑ የኤም.አይ.ቲ. ተመራማሪዎች፣ ከማሳል የሚወጡ ቅንጣቶች (ፓርቲክልስ) እስከ 16 ጫማ፣ ከማስነጠስ የሚወጡት ደግሞ እስከ 26 ጫማ መጓዝ እንደሚችሉ ተመልክተዋል።

.

ይህ ሁሉ የሚጠቁመው፣ በቅርበት ከመገኘት ጋር ሲነፃፀር፣ የስድስት ጫማ ወይም ከዚያ በላይ ርቀትን መጠበቅ የበሽታ መተላለፍን ዕድል በከፍተኛ መጠን እንደሚቀንስ ነው። ዶ/ር ሚልተን ስለ ኤሮሶልስ ሲናገሩ፣ “የበለጠ በራቅን ቁጥር፣ የመቅለጥ ዕድሉም በዛው ልክ ይጨምራል።”

.

ማሳል እና ማስነጠስ ብቸኛዎቹ የስጋት ምንጮች ላይሆኑ ይችላሉ። ኢንፉሌንዛ ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ አነስተኛ ወይም ምንም ምልክቶች የማይታይባቸው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በንግግር ወይም በትንፋሽ አማካኝነትም ተላላፊ በሽታ ያዘሉ ጠብታዎችን ሊያመነጩ ይችላሉ።

.

የታመመ ሰው የአየር ዝውውር በሌለበት ክፍል ውስጥ ለአምስት ደቂቃ በሚያወራበት ጊዜ፣ አንድ ሳል ከሚያመነጨው እኩል ብዙ ቫይረስ-አዘል ጠብታዎችን ሊያመነጭ ይችላል። “10 ሰዎች በዚያ ክፍል ቢኖሩ፣ እየጨመረ ይሄዳል”፣ ይላሉ ፓራቲም ቢስዋስ፣ በሴንት ሊውስ የዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የኤሮሶልስ ባለሙያ።

.

ከቅርብ ቀናት ወዲህ የሕብረተሰብ ጤና ኃላፊዎች ከማኅበራዊ (ከአካላዊ) መራራቅ በተጨማሪ፣ ብዙ ሰዎች የፊት ጭምብል (ፌስ ማስክ) ማድረጋቸው የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ እንደሚረዳ እየጠቆሙ ይገኛሉ።

.

ጭምብሉ የሳል፣ የማስነጠስ ውይም የትንፋሽን የጉዞ ሂደት የሚገታ ሲሆን፣ ከመተንፈሻ አካላት የሚወጡ የተወሰኑ ጠብታዎችን ከመፈንጠራቸው በፊት አስቀድሞ ያስቀራቸዋል። ጭንብል ምንም እንኳን ትናንሽ ጠብታዎች ወደ ውስጥ እንዳንተነፍስ የማድረግ አነስተኛ የመከላከል አገልግሎት ቢሰጥም፣ ትላልቅ ቫይረስ-አዘል ጠብታዎች አፍንጫ እና አፍ ላይ እንዳያርፉ መከላከል ይችላል።

.

ጭምብል (ማስክ) ማጥለቅ እርስዎን እና ሌሎችን ለመጠበቅ ይረዳል። ስለዚህም ከቤትዎ መውጣት ካስፈለግዎ፣ ጭምብል ያጥልቁ፣ እንዲሁም ርቀትዎን ይጠብቁ።

——
በዩልያ ፓርስሂና-ኮታስ፣ ቤደል ሳጌት፣ ካርቲክ ፓታንጃሊ፣ ወይም ፍሌሸር እና ገብራኤል ጂያኖርዶሊ፣ በኤፕሪል 14/2020 የተሰናዳ
ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ
——

A 3-D Simulation produced by The New York Times indicated the importance of Physical distancing to slow down the spread of COVID-19. Translated to Amharic by Ankuar (@Ankuardotcom).
በአንኳር ተተርጉሞ የተሰናዳ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.