COVID-19FEATUREDNews

ለይቶ የማቆየት አስገዳጅ እርምጃ ያስገኘው ፋይዳና የሀገር ውስጥ ስርጭት ሁኔታ

ኮቪድ-19 የተባለው ወረርሽኝ ዓለምን ማስጨነቅ ከጀመረ ሦስት ወራት ተቆጥረዋል። እስካሁኗ ደቂቃ ይፋ የሆነው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በዓለም ላይ ከ2.1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወረርሽኙ ተጠቂ መሆናቸው ተረጋግጧል። ከ136 ሺህ በላይ ሰዎችም ህይወታቸው አልፏል። ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ከበሽታው አገግመዋል።

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በቫይረሱ የተያዘ ሰው የታወቀው መጋቢት 4 ቀን 2012 ነበር። እስከዛሬ ድረስ 92 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ፣ ሦስት ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፣ እንዲሁም 15 ሰዎች ሙሉ ለሙሉ ማገገማቸው ተዘግቧል።

እስከ ዛሬ ሚያዚያ 8 ቀን 2012 ድረስ፣ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በቫይረሱ ከተያዙት 92 ሰዎች መካከል 64 ከውጭ ሀገር የመጡ ሲሆኑ፣ የተቀሩት 28 ሰዎች እዚሁ ሀገር የተያዙ ናቸው።

ኢትዮጵያ ወረርሽኙን ለማቀብ እየወሰደቻቸው ካሉት እርምጃዎች አንዱ ከውጭ ሀገራት የሚገቡ መንገደኞች ላይ የ14 ቀናት አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ (ኳራንታይን) ማድረግ ነው። ያም ሆኖ እርምጃው ተግባራዊ ከሆነ በኋላም በሀገር ውስጥ የጉዞ ታሪክ ሳይኖራቸው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ይገኛሉ። በተጨማሪም፣ በኢትዮጵያ ወረርሽኙ ከውጭ ከመጡ ሰዎች ከመተላለፉ ባሻገር፣ የሀገር ውስጥ ስርጭት (Local Transmission) መጀመሩን የሚያመላክት ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ ምንም ዓይነት ንክኪ የሌላቸው ኬዞች መገኘታቸው ወደ ማኅበረሰብ ስርጭትነት (Community Transmission) ከፍ እያለ ስለመሆኑ ጠቋሚ ነው።

ከአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ በፊት

ለይቶ የማቆየት አስገዳጅ እርምጃው ተግባራዊ መሆን የጀመረው መጋቢት 14 ቀን 2012 ነበር። እስከዚያ ቀን ድረስ በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 11 ሲሆን፣ ከአራቱ በስተቀር ሁሉም ከውጭ የመጡ ሰዎች ናቸው። እነዚያ በሀገር ውስጥ የተያዙት አራት ሰዎችም ቫይረሱ ከማን እንደተላለፈባቸው ወይም በሽታው እንዳለበት ከተረጋገጥ ሰው ጋር ንክኪ እንደነበራቸው ተረጋግጧል።

ከአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ በኋላ

ከእርምጃው በኋላ 81 ኬዞች ተመዝግበዋል፤ ከእነዚህም ወስጥ 57 ሰዎች ከውጭ የመጡ ወይም የጉዞ ታሪክ ያላቸው ናቸው። ነገር ግን እነዚህ 57 ሰዎች በሙሉ በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ የነበሩ አይደሉም። በጤና ሚኒስቴር በየዕለቱ የሚሰራጩትን መግለጫዎች በመመልከት፣ 14 ሰዎች ለይቶ የማቆየት አስገዳጅ እርምጃው ከመተግበሩ አስቀድሞ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ መሆናቸውን ተረድተናል።

ሆኖም በእርምጃው አማካኝነት ወደ ሕብረተሰቡ ቢቀላቀሉ ኖሮ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የበለጠ አዳጋች ሊያደርጉ ይችሉ የነበሩ 43 ሰዎችን በለይቶ ማቆያ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል። ይህ የእርምጃው ትልቅ ውጤት ነው።

በሀገር ውስጥ የተያዙ ሰዎች ሁኔታ

ሌላው ጉልህና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው፣ ምንም ዓይነት የጉዞ ታሪክ የሌላቸው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ቀላል አለመሆኑ ነው። በሀገር ውስጥ ከተያዙት 28 ሰዎች መካከል፣ አራቱ ከመጋቢት 14 በፊት መያዛቸውና ከቫይረሱ ተጠቂ ጋር ንክኪ እንዳላቸው የተረጋገጡ ናቸው።

ሆኖም 24 ሰዎች አስገዳጅ ለይቶ የማቆየት እርምጃው ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ ምንም ዓይነት የጉዞ ታሪክ ሳይኖራቸው እዚሁ ሀገር ውስጥ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 11 የሚሆኑት ከነጭራሹ ከማን እንደያዛቸው ወይም ሊይዛቸው እንደቻለ አልታወቀም።

ይህ 11 ቁጥር ቀላል ሊመስለን ይችላል። ነገር ግን በኢትዮጵያ የወረርሽኙ ስርጭት ሦስተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ስለመሆኑ ፍንጭ የሚሰጥ ነው። የመጀመሪያው ደረጃ ከውጭ የመጣ ወይም “Repatriated Case” ብንለው፣ ሁለተኛውን ደረጃ የሀገር ውስጥ ስርጭት ወይም “Local Transmission” ቢባል፣ ሦስተኛውና እጅግ አስጊው የማኅበረሰብ ስርጭት ወይም “Community Transmission” ሊባል የሚችለው ነው – ይህም የንክኪ ምንጩን ማወቅ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ሲደረስ ነው። እንዲህ ላሉት ኬዞች ጤና ሚኒስቴር ምንጫቸውን በማጣራት ላይ እንደሚገኝ ተገልፆል። ነገር ግን ምንጫቸውን ማግኘት ካልተቻለ፣ የማኅበረሰብ ተዛምቶ ጅማሬ ሊሆን ስለሚችል፣ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ሀገራት እየተገበሩት ያሉት መመርመር፣ በምርመራው የተያዘ ሰው ሲገኝ እርሱን ለይቶ ማከም (አይዞሌት)፣ ከርሱ ጋር ንክኪ ሊኖራቸው የሚችሉትን ሰዎች ማሰስና ማግኘት፣ ከዚያም የተጠረጠሩትን ሰዎች ኳራንቲን ማድረግ፣ እንዲሁም የተጠረጠሩትን መመርመር የሚለው የወረርሽኝ ማቀቢያ ስልትን ነው (Test, Isolate, Find, Quarantine, Test)። ነገር ግን ከምርመራ አኳያ ኢትዮጵያ አርኪ የሚባል ሥራ እየሰራች እንዳልሆነ ይነገራል። ከመመርመር ባሻገር፣ ንክኪን ፈልጎ የማግኘት (Tracing) ሥራ እጅግ ወሳኝ ነው።

ኢትዮጵያ እስከዛሬ 5389 የላብራቶሪ ምርመራ ብታከናውንም፣ ይህ ቁጥር አንዳንድ ሀገራት በአንድ ቀን የሚያከናውኑት ምርመራ ነው። ወረርሽኙን ለመከላከል እና ለማቀብ ሰፊ ምርመራ ማድረግን የሚጠይቅ ሲሆን፣ ምርመራውን ተከትሎም ያሉት ንክኪ የማጣራት ሥራ እና የመሳሰሉትን ሂደቶች በአግባቡ ለማከናወን ይረዳል።

Featured Coronavirus Image Source: jamanetwork.com/

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.