FEATUREDየመጽሐፍት ዳሰሳ

ያላረፉ ነፍሶች – በቆንጂት ብርሃን

ደራሲ- ቆንጂት ብርሃን
ርዕስ – ያላረፉ ነፍሶች
የገፅ ብዛት  – 398
ዋጋ – 182.50
ኅትመት – ፋር ኢስት ትሬዲንግ ኃላ. የተ. የግ. ማኅበር
ዠነር/ዘውግ – በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ
መቼ – ከ1965 መጨረሻ – 1983 ዓ.ም
የት –  ፍቼ፣ አዲስ አባባ፣ ሻሸመኔ፣ ባሌ ሮቤ፣ ዱብቲ፣ አዲስ አበባ
መታሰቢያነቱ – በዚያን ዘመን መስዋዕትነት ለከፈሉ ሰዎች፣ በአካልና በአእምሮ ከባድ ዋጋ ለከፈሉ ወላጆች፣ በተለይም እናቶች

በማኅደር አካሉ

ያለረፉ ነፍሶችን የመረጥኩበት ዋናው ምክንያት ኢሕአፓን እና በወቅቱ የነበሩ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ከአመራሮቹ አንፃር ሳይሆን ከተራ አባላቶቹና ከነዋሪዎቹ አንፃር በግልፅ እንድናይ የሚያደርገን መፅሐፍ ሆኖ ስላገኘሁት ነው፡፡

ያላረፉ ነፍሶች፤ 1966 ሊገባ አንድ ወር ሲቀረው፤ ንጹህ ተሻገር ምትባል በትምህርቷ ጎበዝ የሆነች፣ ከቤተሰቧ በተለይም ከወንድሟ ጋር የተለየ ቅርበት ያላት፣ በአስተማሪዎቿና በመንደሩ ሰዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆነች፣ የ15 ዓመት ልጅ፣ ያለፍቃዷ፣ በታላቅ እህቷ ተፅዕኖ ፣ ከእናት አባቷ ርቃ፣ አዲስ አበባ ከታላቅ እህቷ ጋር ሆና እንድትማር ከፍቼ ወደ አዲስ አበባ ስትጓዝ ትረካውን ይጀምራል፡፡ የመጽሐፉ ዋና ገፀ-ባህሪይ የሆነችው ንጹህ፤ ትምህርቷን እየተከታተለች በግሩፕ ጥናት ሰበብ በተዋወቀቻቸው ወጣቶች አማካኝነት ወደ ኢሕአፓ (የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ) … ትቀላቀላለች፡፡

ከዛስ የሚለውን ከመጽሐፉ ታገኙታላችሁ፤ ለአሁኑ ግን መፅሐፉን በአጭሩ በራሴ መነፅር ላስቃኛችሁ፡፡

መፅሐፉ በዘመኑ የነበረውን ትውልድ ምን ያህል ጎበዝ፣ ታታሪ፣ ከእድሜያቸው ቀድመው የበሰሉ፣ ድንበር አልባ ሀገራዊ ፍቅር የነበራቸው፣ ጠንካራ ቤተሰባዊ ትስስርና ጓደኝነት እስከ መስዋዕትነት የሚደርስ ጥልቅ ምስጢራዊነት፣ ሁለመናቸውን ለሀገራቸው የሰጡ፣ ለጭቁኑ ህዝብ የቆሙ እንደነበሩ ይነግረናል፡፡

የኢሕአፓ የበላይ አመራር የነበሩት ብርሃነ መስቀል ረዳና ጌታቸው ማሩ የፈጠሩት የሃሳብ ልዩነት ከታች ያሉትን አባላት ምን ያህል እንደጎዳቸው እና እርስ በራሳቸው የነበራቸውን መተማመን እንደሸረሸረባቸው በግልፅ ይነግረናል፡፡

. . .

የአተራረክ ዘዴው በሶስተኛ መደብ/ሁሉን አወቅ መንገድ ነው፡፡ የታሪኩ ፍሰት፣ ቋንቋው፣ አገላለፁ … ለመቼቶቹ ቅርብ እንድሆንና በወቅቱ የነበርኩ ያህል እንዲሰማኝ አድርጎኛል፤ የገፀ-ባህሪያቱ ህመም፣ ስቃይ፣ ደስታ… እንዲጋባብኝ ሆኗል፡፡

ገፀ-ባህሪያቶቹ በስብዕናቸው ተገለፁ እንጂ በአካላዊ ቁመናቸው አልተሳሉም፡፡ መፅሐፉን አንብቤ እስክጨርስ  ስለዋና ገፀ-ባህሪይዋ ንጹህ ፤ ለነገሮች ያላትን አመለካከት፣ ለማወቅ ያላትን ጥረት፣ ጥንካሬዋን እና አጠቃላይ ማንነቷን እንጂ ስለተክለ-ሰውነቷ ምንም አይነት ምስል የለኝም፡፡ ለሌሎቹ ገፀ-ባህሪያትም እንዲሁ ስለአጠቃላይ ስብዕናቸው እንጂ አካላዊ ቁመናቸው ምን እንደሚመስል በመፅሐፉ አልተገለፀም፡፡ በእኔ እይታ ገፀ-ባህርያቶቹ በስብዕናቸው መገለፃቸውን እጅግ አግባብ ነው እላለሁ፤ አንባቢው ትኩረቱን ሙሉ ለሙሉ መቼቱ ላይ እንዲያደርግ ይረዳዋል ብዬም አስባለሁ፡፡

አንድ ትውልድ ልክ እንደ ተወርዋሪ ኮከብ ለቅጽበት ያህል ታይቶ እንዴት ይጠፋል — ገፅ 332

በእኔ እይታ ግን ታይቶ የጠፋው አንድ ትውልድ ብቻ አልነበረም፤ የዛን ትውልድ ወላጆች በተለይም እናቶች አጉል ሞት ሞተዋል! … ለአንዲት እናት የልጇን ሬሳ በሯ ላይ ጥሎ፤ እንዳትነካው እንደመከልከል ምን ሞት አለ? … ከሟች መሃል በስቃይ የልጇን እሬሳ እንደመፈለግ ምን ሞት አለ? … ፈልጋ አግኝታ ልትወስደው ስትል ከፍለሽ ውሰጅ እንደመባል ምን ሞት አለ? … የመክፈል አቅም ስለሌላት የልጇን እሬሳ መውሰድ አለመቻልስ? … ልጆቻቸው ይሙቱ ይኑሩ የማያውቁትስ? … ከዛሬ ነገ ይመጣሉ እያሉ በር በሩን የሚያዩትስ? … ያማል! ያጣነው ብዙ ነው!

መጽሐፉ በፖለቲካ ሰበብ የግል ፍላጎታቸውን የሚያረኩ ባለስልጣኖችን … በተለይ የአብዮት ጥበቃዎቹ ኢንፊሪየሪቲ ኮንፕሌክስ ያለባቸው ስለነበሩ መሳሪያ ሲታጠቁ የቂም በቀል መወጫ እንዳደረጉት በግልፅ ያሳየናል፡፡

ይህን መጽሐፍ እንደኔ ያሉ፤ በኢሕአፓ ጊዜ ላልነበሩ፣ ስለ ኢሕአፓ እና በወቅቱ ስለነበረው አጠቃላይ ሁኔታ ከአባላቱ አንፃር ማወቅ ለሚሹ፣ እስከዛሬ ስለኢሕአፓ ከበላይ አመራሮች አንፃር ብቻ የሚያትቱ መፅሐፍትን ሲያነቡ ለነበሩቱ፣ እንዲሁም ያንን ዘመን ዛሬ ላይ ሆኖ ለመዳኘት ሳይሆን ለማወቅና ለመማር ለሚሹ ሰዎች ያነቡት ዘንድ እመክራለሁ፡፡

በመጠኑም ቢሆን የመፅሐፉን መልዕክት ይገልፃል ብዬ ባሰብኩትና ከመፅሐፉ በተወሰደው አንቀፅ ተሰናበትኩ፡፡

“… ኢትዮጵያ ሆይ ወዴት እየተጓዝሽ ነው? የንፁሕ ትውልድ ያለመው፤ መስዋዕትነትንም የከፈለው ለህዝብ የተሻለ ሕይወት እንደሚመጣ በማሰብ ነበር፡፡ መስዋዕትነቱ ግን ድልን ሳያፈራ ቀረ፡፡ ኢትዮጵያም አሽቆልቁላ ከድጡ ወደ ማጡ ገባች፡፡ ህዝብን ረሀብና ቸነፈር እየቆላው መሆኑን እያወቁ በውስኪ የሚራጩ መሪዎች፤ ስለ ሴት እኩልነት እደሰኮሩ፤ ሴት ልጅን ከጊዜያዊ ፍላጎት ማርኪያነት ውጪ የማይመለከቱ … ባለሥልጣኖች የሚሰሩትን እያወቀ እንዳላወቀ፣ የሰማውንም እንዳልሰማ ዝም የሚል፣ እንዲያውም የሆዱን በሆዱ ይዞ ዳንኪራውን የሚያሞቅ ህዝብ አገር ሆነች – ኢትዮጵያ፡፡ ግን መፍረድስ እንዴት ይቻላል? በእያንዳንዱ ቤት የወረደው ሰቆቃ የፈጠረው ቁስል በምን መንገድ ይድናል? ይህን ህዝብ ፍርሃት ቢሸብበው ምን ይደንቃል? ህዝቡ በውስጡ የቀደመውን መንግስት ቢናፍቅ ምን ይቆጠርበታል? ሁል ጊዜ “ትሻልን ትቼ ትብስን አገባሁ” እያለ እንዲተርት የተፈረደበት ህዝብ፡፡“

One thought on “ያላረፉ ነፍሶች – በቆንጂት ብርሃን

  • Gizaw Legesse

    Nice review, and you have shown us a glimpse on how this particular book is different from other numerous books narrating that period.

    Reply

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.