የክልሎች ስያሜ ለብሔር ተኮር ግጭቶች ያደረገው አስተዋፅኦ
- «ኢትዮጵያ ውስጥ ድንበር የለም፤ የአስተዳደር ወሰን እንጂ» ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ
ነገሩ አዲስ ባይሆንም፣ አደባባይ ወጥቶ እንድናጣጥመው ባይደረግም፣ እንዲያውም ‘ብሔር’ በሚል ጥርናፍ ተሸብበን እንዳናጤነው ለዓመታት ቢዘመትብንም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአስተዳደር ወሰን እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ የክልል ድንበር የለም በማለት የተናገሩት፣ ለብዙ የውስጥ ችግሮቻችን መፍትሔ የሚያቀርብ ይመስለኛል፡፡
ብሔር፣ ብቸኛው ባይሆንም፣ ዋነኛው የፌዴራል አወቃቀራችን መስፈርት ስለመሆኑ እዚህ ላይ መዘርዘር ላያስፈልግ ይችላል፡፡ ሆኖም ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ኦሮሞ ብቻ እንደማይኖር እየታወቀ መጠሪያውን ‘ኦሮሚያ’ ብሎ መሰየም፤ አማራ ክልል ውስጥ የኦሮሞ፣ የአፋር፣ የአዊ፣ የአገው ብሔር ያላቸው ሕዝቦች እንደሚኖሩ እየታወቀ የክልሉ መጠሪያ ‘አማራ’ መባሉ፤ በተምሳሳይ በሌሎች ክልሎችም መጠሪያ ስሞች የአንድን ብሔር የክልል/የመሬቱን ባለቤትነት በሚያረጋግጥ መንፈስ በሕገ-መንግስታችን ላይ መስፈራቸው አስተዋፅኦው ቀላል አልመሰለኝም፡፡
በቅድሚያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘የአስተዳደር ወሰን ነው ያለው’ ሲሉ ምን ማለታቸውና ፋይዳውም ምን እንደሆነ ላብራራ፤ ከዚያም አንዳንዶችን ቱግ የሚያስብሉ ጥያቄዎችን አንስቼ፣ በማብራሪያው መሰረት እንመልሳቸዋለን፡፡
የአስተዳደር ወሰን
ለአንድ ክልል ፕሬዝዳንት፣ ወይም ካቢኔ፣ ወይም ፓርላማ የተሰጠው ሥልጣን የማስተዳደር ነው፡፡ ይህ ሥልጣን ትልቁና መሠረታዊው የፖለቲካ ሥልጣን ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ምርጫ ቢያሸንፍ፣ ኦፌኮ ቢመረጥ፣ ኢሕአዴግም ቢሆን ይህ ሥልጣን ብቻ ነው ያላቸው፡፡ አሁን የመጀመሪያው ጥያቄ ‘የት?’ የሚለው ነው፡፡ ይህ የማስተዳደር ሥልጣን የሚሰራው የት ቦታ ነው? ይሄን ጥያቄ ብዙ ሳናወሳስበው ሕገ-መንግስቱ ላይ በጥቅሉ የተቀመጡ የአስተዳደር ደረጃዎችን ወይም ንፍቀ-ክበቦችን በመጥቀስ እንመልሰው፤ በክልል ወይም በፌዴራል (በመላው ኢትዮጵያ) የሚሰራ ሥልጣን ሊሆን ይችላል – አስተዳዳሪው በሕዝቡ የያስተዳድረን ይሁንታ ባገኘባቸው ቦታዎች እንደማለት ነው፡፡
ሁለተኛው እና መሠረታዊው ጥያቄ ግን ‘ማንን?’ የሚለው ነው፡፡ ማንን ነው የሚያስተዳድረው? የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት የማስተዳደር ሥልጣናቸው በሁሉም ኢትዮጵያዊ ኦሮሞዎች ላይ አይደለም፤ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚኖሩ ኦሮሞዎች ብቻ ላይም አይደለም፡፡ ይልቁንስ ሥልጣናቸው፣ ወይም በትክክለኛ አባባሉ ኃላፊነታቸው (ኃላፊነት ያለባቸው) ኦሮሚያ ተብሎ በሚጠራው ክልል ውስጥ በቋሚነት ለሚኖሩ ማንኛውም ብሔር ላላቸው ሕዝቦች፣ በክልሉ የመኖሪያ ፍቃድ ላላቸው የውጭ ዜጎች፣ ኢንቨስተሮች፣ እንዲሁም የኃላፊነታቸው መጠን ይለያይ እንጂ ክልሉን ለመጎብኝት ለሚመጡ ቱሪስቶች ሁሉ ነው፡፡ (በርግጥ አቶ ለማም ከዚህ በተሻለ ሲግልፁት ሰምቻለሁ፡፡) ለማንኛውም፣ ይህ ማለት የአስተዳደር ወሰን ነው፡፡
በሌላ አገላለፅ፣ አማራ ክልል ከሚሴ ላይ የሚገኝ ኦሮሞ የመጠጥ ውሃ ችግር ቢገጥመው፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አይመለክተውም፡፡ አቶ ለማ ከኦሮሞነት በላይ፣ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የከሚሴ ችግር እንደሚቆረቁራቸው አምናለሁ፡፡ ሰውዬው ምርጥ ስብዕና አላቸው፡፡ ሆኖም እንደ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንትነታቸው ለከሚሴው ኦሮሞ በጀት የማዘጋጀት ሥልጣን የላቸውም፤ የሥልጣን ወሰናቸው አይደለምና፡፡ ባይሆን ለአቻቸው አቶ ገዱ ጉዳዩን ሊጠቁሙ ይችላሉ፤ ምክንያቱም ከሚሴ አማራ ተብሎ በሚጠራው ክልል ውስጥ ናትና፡፡ ይህ ነው የአስተዳደር ወሰን፡፡
የአስተዳደር ወሰን ብሔርን መሠረት አያደርግም፤ በነዋሪ ወይም በቦታው በመገኝት ላይ ያተኩራል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው፣ በዚያ ተለይቶ በተቀመጠ የአስተዳደር ወሰን ውስጥ የሚኖር ግለሰብም ሆነ ብሔር ሁል-አቀፍ መብቱን የማስከብር ሥልጣን፣ እንዲያውም ኃላፊነት የክልሉ አስተዳደር ነው፡፡ ግዴታ ነው፡፡ ዓመታዊ በጀቱም ለክልሉ ነዋሪ የታለመ ነው፡፡ አብላጫ ቁጥር ላለው የኦሮሚያ ብሔር ተወላጅ የባህል ማዕከል ማስገንባት ተገቢ ነው፤ ቁጥሩ ትንሽ ቢሆንም በኦሮሚያ ክልል ለሚኖር አማርኛ ተናጋሪ እና የአማራ ብሔር ተወላጅም በቋንቋው የሚማርበት ትምህርት ቤት ማሰናዳትም የክልሉ ፕሬዝዳንት ኃላፊነት ነው፡፡
እዚህ ላይ ለማለት የተፈልገው፣ የአንድ ክልል አስተዳደር በሌላ ክልል ስለሚኖር ኢትዮጵያዊ አይመለከተውም አይደለም፡፡ ይመለከተዋል፤ እንደ ኢትዮጵያዊነቱ፡፡ ቀዳሚ ኃላፊነቱ ግን ለሚያስተዳድረው ሕዝብ ነው፤ በጀት ለሚቆርጥለት እና ኦዲት ለሚደረግበት፡፡ አቶ ገዱን ቤንሻንጉል ለሚኖሩ አማራዎች ለምን ጥርጊያ መንገድ አልሰራህም ብሎ የሚጠይቃቸው አይኖርም፤ የአስተዳደር ሥልጣናቸው አይደለምና፡፡
ጉዳዩን ከግብር አኳያ ከተመለከትነው ይበልጥ ያስገርመናል፡፡ ከቤንሻንጉል የተፈናቀሉት አማራዎች ግብር ሲከፍሉ የኖሩት ለቤንሻንጉል ክልል ነው፤ የአማራ ክልል አስተዳደር ሳንቲማቸውን አግኝቶ አያውቅም፡፡ የትኛውም አስተዳዳሪ ደግሞ የማስተዳደሪያ ፈሰሱን የሚቀምረው በዋናነት ከሚያስተዳድረው ሕዝብ ከሚሰበስበው ግብር ነው፡፡ ከሱማሌ የተፈናቀለው ኦሮሞም እንዲሁ ነው፤ ከሱቅም ሆነ ከደሞዝ ከሚያገኘው ገቢ ለሱማሌ ክልል ሲገብር ነበር – ለሚያስተዳድረው፡፡
በዚህ መልኩ የአስተዳደር ወሰንን ከተገነዘብነው፤ በፌዴራል አወቃቀራችን ውስጥ የብሔር ሚና የማያጣላን እንዲሆን ማድረግ ከባድ እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡ ከዚህም አልፈን ካየነው፣ በአንድ ክልል ውስጥ ሰፊ ቁጥር ያላቸውን ሕዝቦች ብቻ ለማስደሰት የቆመን የፖለቲካ ፓርቲ መምረጥ ነገ ከደህና ጎረቤት፣ ክጥንት የትምህርት ቤት ጉዋደኛ መቀያየምን የሚያስከትል መሆኑን አስቀድመን እንነቃበታለን፡፡
ይህን ሁሉ መዘርዘሬ፣ በየቦታው ለምንታዘበው የብሔር ግጭት 27 ዓመት በሥልጣን የቆየው መንግስት በተናጠል ሊወቀስ አይገባም ስለምል ነው፡፡ እኛም ሳናመነታ እራሳችንን የሸጥንበት፣ እገሌ የኛ ነው ያልንበት፣ እኛ-እነሱ ብለን የተመዳደብንበት ዘመን ነበር፡፡ ያ ሁሉ ሲሆን የፌዴራል ሥርዓቱን ተጠያቂ የሚያደርግ ቁጥሩ ቀላል አይደለም፡፡ ‘እንዴት ይዋቀር?’ ብለህ ብትጠይቀው፣ አሁን ያለውን አወቃቀር ገልብጦ ይነግርሃል፡፡
አሁን ቱግ የሚያስብሉ ጥያቄዎች እንጠይቅ፤
የአማራ ክልል አስተዳደር ከቤንሻንጉል – ወልደው ከብደው ከኖሩበት ቀዬአቸው – ተፈናቅለው ባህር ዳር ለፈሰሱት ሕዝቦች ምን ዕዳ አለበት? ምን ኃላፊነት አለበት? አማራ ስለሆኑ? ቢሆኑስ፣ ግብር ከፍለውት ያቃሉ? ለነሱ ብሎ የያዘው በጀት አለ? የአማራ ክልል መንግስት በመሠረቱ አይመለከተውም፡፡ የበለጠ ግልፅ ለማድረግ፣ የአማራ ክልል መንግስት ‘በተለየ’ አይመለከተውም፡፡ እንደማንኛውም በውስጥ ግጭት ለተፈናቀሉ ኢትዮጵያዊያን ያገባዋል፡፡ ያ ግን ከኦሮሚያ፣ ከሃረሪ፣ ከሱማሌ ክልል መንግስት የተለየ መቆርቆር ሊያሳይ አይጠበቅበትም፡፡ ይልቁኑ ዋናው ኃላፊነት የቤንሻንጉል-ጉምዝ ክልላዊ መንግሥት ነው፤ ከዚያ ሲያልፍ ደግሞ የፌዴራል መንግሥት አጥብቆ ይመለከተዋል፡፡
‘በአማራነታቸው ነው የተፈናቀሉት’ ሊባል ይችላል፡፡ ይሄ ጭራሽ ጉዳዩን አንድ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል፤ የፌዴራል ጉዳይ ይሆናል፡፡ እንጂ አማራ የተባለ ክልል ብቻውን ለዚህ ዓይነት ጉዳዮች ብሎ የሚይዘው በጀት የለም፡፡ በሱማሌ ክልል እንዳየነው በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ነቅለው ሲወጡና ወደሌላ ክልል ሲገቡ በተቀባዩ ክልል ላይ የሚያመጣው የኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ አይጣል ነው፡፡ ነዋሪዎቹን የማስተዳደር ኃላፊነት ያለበት ሱማሌ ክልል ለዓመታት ግብር ሲቀበላቸው የኖረው ቢያንስ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶቻቸውን ለማስከበር አያንስም፡፡ ኃላፊነት ነበረበት፡፡ ታዲያ ኦሮሚያ ክልል ምን ዕዳ አለበት? ምን ሕግስ ያስገድደዋል ያን ሁላ ሕዝብ ለማስፈር ወጪ የሚያወጣው? የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በሱማሌ ከሚኖሩ ኦሮሞዎች በበለጠ፣ ኦሮሚያ ውስጥ ለሚኖሩ አማራዎች ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ የአስተዳደር ወሰን ይህ ይመስላል፡፡
ይህ ሀሳብ በየክልሉ እያስተዳደሩ የሚገኙ ፓርቲዎች ከተነሱለት እና ከቆሙለት ዓላማ ጋር ለማስታረቅም የሚቸግር አይመስለኝም፡፡ አራቱም የኢሕአዴግ ፓርቲዎች፣ ከመጠሪያቸው አንስቶ የተወሰነ ብሔርን ለመታደግ የታገሉ ወይም የሚታገሉ ያስምስላቸዋል፡፡ ሆኖም መሠረታዊ ዓላማቸው በብሔሮች መካከል እኩልነትን ማስፈን እንጂ በልጦ መገኘትን አይደለም፡፡ ነገሩን በዚህ መልኩ ደግሞ እናጢነው፤ ክልሉን የሚያስተዳድረው ሕብረ-ብሔራዊ ፓርቲ ቢሆንስ? አንድ ወዳጄ፣ በለማ መገርሳ ክስተትነት ተማርኮ፣ ‘እባክዎን፣ በገዛ እጆህ ትግራይንም አስተዳድሩልን ብሎ መፃፉን አስታውሳለሁ፡፡ ዋናው ነጥብ፣ ‘የአማራ…’ የሚል ቃል መጠሪያው ላይ የሌለ፣ እንደ መኢአድ ዓይነት ፓርቲ አማራ ክልልን ለማስተዳደር ሕጋዊ ብቃት አለው – ከተመረጠ፡፡ ታዲያ የመኢአድ የአስተዳደር ወሰን በአማራ ክልል ከሚኖረው ሕዝብ ባሻገር ቤንሻጉል ለሚኖረው አማራ ከሌሎች ክልሎች በተለየ ቢቆረቆር ሰው ምን ይለዋል? እንደ ኢትዮጵያዊ ድርጊቱን ቢያወግዝ መልካም፤ አማራ ስለሆኑ ብሎ እምቡር ቢል መሳቂያ ልናደርገው ይገባል፡፡ ቤንሻንጉል ይኖሩ ከነበሩት አማራዎች በላይ፣ የጣና ደሴቶችን ለመጎብኘት ለሄደ ሌላ ኢትዮጵያዊ ከፍተኝ ኃላፊነት አለበት፡፡
ታዲያ ይሄ አመክኒዮ ለብአዴን የማይሰራበት ምክንያት ምንድን ነው? ያኔ እራሱን ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ብሎ (ኢሕዴን የሚለው ቀርቶ) ሲሰየም ለአማራ ብሔር በመጨነቅ መታገሉን ሊያመላክተን ይችላል፡፡ ሕገ-መንግሥቱ ፀድቆ እኝያ ሰውዬ በታላቅ ፍንደቃ ከጨፈሩ በኋላ ግን የብሔር እኩልነት ሰፍኗል፣ ብአዴንም የአስተዳደር ወሰኑን አማራ ክልል ላይ መትሯል፡፡ መጠሪያው ግን ቀጥሏል፡፡ ስለዚህም ብአዴን በመላው ኢትዮጵያ ያሉ አማራዎችን የሚያስተዳድር፣ የልደት ሰርተፍኬት የሚሰጣቸው፣ እገሌ እገሌ ብሎ በስም የሚያውቃቸው፣ ግዴታውም ያለበት፣ ግብር የሚሰበስብባቸው ይመስለናል፡፡ ሆኖም ተሳስተናል፤ አይመለከተውም፡፡ በክልሉ ባሉ አማራዎች ላይ ነው ሥልጣኑ፤ ለዚያውም በክልሉ ከሚኖረው ሌላ ብሔር ላይ ካለው የአስተዳደር ሥልጣን እኩል፡፡
ለመከለስ ያህል፣ ስለ የአስተዳደር ወሰን እያወራን ነው – ስለአጠቃላይ መርሆው፡፡ አሁን ስለ ክልሎች ስያሜ እናንሳና ጉዳያችንን እንቅጭ፡፡
የክልሎች ስያሜ
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ስንል ባለቤትነትን የሚጠቁም ይምስላል፡፡ የክልሉ፣ በተለይም የሌጣው መሬት ባለቤት የኦሮሞ ሕዝብ እንደሆነ ለመጠቆም ስለሚሞክር፣ በክልሉ የሚኖር ሌላው ሕዝብ ባይተዋርነት እንዲሰማው ያደርጋል፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ በክልሉ የሚኖር ኦሮሞ የልብ ልብ እንዲሰማው ያደርጋል፤ ክልሉ ‘የኔ ነው’ ቢልና አማራዎችን ወይም ሌላውን ብሔር ቢያፈናቅል የሚገርመው ሰው ብዙ ላይሆን ይችላል፡፡ የመሬት ባለቤትነት/ይዞታ የሚረጋገጠው ለዓመታት በከፈልከው ግብር እንጂ በአባት ወይም በአያት ስም እንዳልሆነ እየታወቀ፣ ሕገ-መንግስቱም መሬት የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ነው እያለ፣ መፈነቃቀልን ምን አመጣው? ኦሮሚያን ማንሳቴ ምሳሌ ነው፡፡
ሌላውም ክልል እንዲሁ ነው፡፡ አማራዎች ከቤንሻንጉል ሲፈናቀሉ ክልላችሁ አይደለም ተብለው ነው፤ ክልሉ የማን ነው – መጠሪያውን ማየት ነዋ፡፡ እነ ቤንሻንጉል እና ጉምዝ የኛ ነው አሉ፤ ለዓመታት የአማራ ብሔር ያለው የክልሉ ነዋሪ ሲያርሰው የነበረን የሕዝብ መሬት የኛ ነው አሉ፡፡ በሌላ በኩል እነዚህ ተፈናቃዮች ጣና መጥተው አንድ እንቦጭ ቆርጠው ላያውቁ ይችላሉ፤ ቀጥ ብለው ሄደው አቤት ያሉት ግን የአማራ ክልል መንግስት ላይ ነው፡፡ ምን አገባው? የክልሉ መጠሪያ (የአስተዳዳሪው ፓርቲ ጭምር) የአማራ ቅጽል አለዋ!
እንደ ሀሳብ እንየው እስኪ፣ የክልሎች ስያሜ ‘ክልል ሀ፣ ለ፣ ሐ…’ ቢሆን ኖሮ ለውጥ ይኖረው ይሆን? በክልሎች ረዥም መጠሪያ ላይ ‘መንግስት’ የሚለው ቀርቶ ‘አስተዳደር’ በሚለው ቢተካ፣ ለጀመርነው የመደመር ሂደት አቀላጣፊ መረዳትን ይሰጠን ይሆን? የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፤ መንግስትነትን ምን አመጣው? መልካም ጎኑ እንዳለ ሆኖ፣ ብሔር በፌዴራል ሥርዓታችን ላይ የፈጠረብንን አይነጥላ ለመግፈፍ፣ የአስተዳደር ወሰን ሁሉንም ብሔር በእኩል ማስተዳደርን የሚጠይቅ መሆኑን ለመገንዘብ፣ የክልሎች መጠሪያ ማሻሻያ የሚያስፈልገው ይመስለኛል፡፡ አይሻሻልም ቢባል እንኳን፣ የአንድ ብሔር ስም መያዙ ከመጠሪያነት በዘለለ የባለቤትነት መብትን እንደማያመለክት ደጋግምን ልናስተምር ይገባል፡፡
ይሄ እንግዲህ የእኔ አንድ ሀሳብ ነው፤ ጠባብም ሰፊም አይደለም፣ ግን ቀላል ሀሳብ ነው፡፡ ምናልባትም የፌዴራል ሥርዓቱ አወቃቀ በደፈናው ‘ችግር አለበት’ ለሚሉ ወገኖች፣ የችግሩን መፍቻ ቁልፍ በአግባቡ እንዲያስቀርፁ ይረዳቸው ይሆናል፡፡ ለጊዜው አበቃሁ።
በግዛው፡ለገሠ
(ሰኔ 14/2010፣ አዲሳባ)