ውህደቱ የመንግስት ኦናነት (ቫኪዩም) አያስከትልም
- የፓርቲዎቹ መፍረስ የውህደት ውጤት እንጂ ቅድመ-ሁኔታ አይደለም!
ውህደቱ የማይቀር በሚመስል መልኩ፣ አቅጣጫዊ ፕሮፓጋንዳ እየተነዛ ነው፤ ትችቱም ጎን ለጎን ይፈሳል፡፡
ስለኢሕአዴግም ሆነ ስለፓርቲዎቹ መጨነቅ የእኛ ጉዳይ አይደለም፤ ሲሆን ሲሆን «ኤክስፓየሪ ዴት» አስቀምጠው መትነን ይገባቸዋል የሚል እምነት ቢኖረኝም፣ ውህደቱ የመንግስትን ሕጋዊነት ያሳጣል እየተባለ ከበስተሰሜን ለሚሰጠው አስተያየት መልስ ለመስጠት መሞከሬ ነው – ይህን መፃፌ፡፡
ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች አሉ፦
1) የመንግስትነት አብላጫ ወንበር የተያዘው በአራት ፓርቲዎች ግንባርነት ነው፤ ግንባርነት ሲቀር ምን ይፈጠራል?
2) ፓርቲዎች ሲዋሃዱ የቀደመው ማንነታቸው ፈርሶ ወይም ተሰርዞ ስለሆነ፣ ፓርላማ ውስጥ ያላቸው መቀመጫ እጣፈንታው ምን ይሆናል? መንግስትነታቸውስ?
2.1) ግንባር ለፈጠሩት ፓርቲዎች አብላጫ መቀመጫውን የተቀመጡበት ደግሞ ተገዢነታቸው ለሕገመንግስቱ፣ ለመረጣቸው ሕዝብ፣ እና ለኅሊናቸው የሆኑት ግለሰብ የፓርላማ አባላት ናቸው፤ እነዚህ ግለሰቦች የፓርቲ አባልነታቸውን ቀደው ቢጥሉ ምን ይፈጠራል?
እንግዲህ እነዚህን ካብራራን ብቻ የአምባሳደር ፍስሃ ስጋት ይቀረፋል ብለን እናስባልን፡፡
ግንባር ሲቀር ማን ፊት ይሆናል?
እየተባለ እንዳለው ከሆነ፣ ውህደቱ የግንባሩ አባል የሆነውን ህወሓት እንደማያካትት እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡ ህወሓትም «መጨፍለቅ» አትፈልግም፣ ሌሎቹም ዳግመኛ «ሎሌ» መባል ይፈልጋሉ ብዬ አላስብም፡፡
እርግጥ ነው፣ በግንባርነት አብላጫ መቀመጫ ተይዞ እንደሆነ፣ ግንባሩ ሲፈርስ አብላጫነት ይቀራል፡፡ ውህደቱ ህወሓትን አስወጥቶ አንድ ወይም ከዚያ በላይ አጋር ፓርቲዎች ማስገባትን የተለመ ነው፡፡ እንዲሁም በቅድሚያ የግንባሩ መፍረስ የውህደቱ ቅድመሁኔታ ነው፡፡ ሕገመንግስቱ አንቀጽ 60 (2) ላይ ስለግንባር መፍረስ እና ውጤቱ እንዲህ ይላል፦
«በጣምራ የመንግስት ሥልጣን የያዙ የፖለቲካ ድርጅቶች ጣምራነታቸው ፈርሶ በምክርቤቱ የነበራቸውን አብላጫነት ያጡ እንደሆነ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተበትኖ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሌላ ጣምራ መንግስት በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለመመስረት እንዲቻል ፕሬዝዳንቱ የፖለቲካ ድርጅቶችን ይጋብዛሉ፡፡»
ንዑስ አንቀፁ አላለቀም፣ ግን እዚህ ጋ አቁመን ሊሆን የሚችለውን ስንመለከት፣ ግንባሩ ፈርሶ ህወሓት ቢወጣ፣ የተቀሩት ሦስቱ ሌላ ግንባር ሳምንት ሳይጠብቁ ወዲያውኑ መመስረት ይችላሉ፡፡ ሌላው ቢቀር፣ የአጋር ፓርቲዎች መቀመጫ ባይቆጠር፣ እንዲሁም የደሕዴን ነገር አልለየለትም ቢባል፣ ኦዲፒ እና አዴፓ አብላጫ መቀመጫ ይኖራቸዋል፡፡ የህወሓት 38 መቀመጫ ፋይዳ ቢስ ሆኖ ይቀራል፡፡
ያቋረጥነው ንዑስ አንቀፅ አዲስ ጣምራ መመስረት ካልተቻለ በስድስት ወር ውስጥ ሀገር አቀፍ ምርጫ ይካሄዳል የሚል ነው፡፡ ሆኖም ይህ «አንላይክሊ» የሚባለው አጋጣሚ ነው፣ ከጣምራነት አልፈን ስለውህደት እያወራን ስለሆነ ማለት ነው፡፡
መፍረስ፣ የውህደት ውጤት
እስካሁን ስለግንባር መፍረስ ነው ያወራነው፡፡ ስለውህደት ስንቀጥል፣ ፓርቲዎች ሲዋሃዱ የቀደመ የተናጠል ፓርቲነታቸው አክትሞ ሌላ አዲስ ፓርቲ ይፈጠራል፡፡ ነገር ግን የፓርቲዎቹ መፍረስ ወይም የድሮው ምዝገባቸው መሰረዝ የውህደት ውጤት እንጂ ቅድመ-ሁኔታ አይደለም፡፡
ይህ መሰረታዊ ነጥብ ነው፣ «ሲዋሃዱ ፓርቲነታቸው ስለሚሰረዝ በፓርላማ ያላቸውን መቀመጫ፣ ይህን ተከትሎም በመቀመጫቸው ያገኙትን መንግስትነት ያጣሉ» የሚለውን መከራከሪያ ውድቅ የሚያደርግ ነው፡፡
በአዲሱ የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ አንቀጽ 91 (4)(ሀ) እና አንቀጽ 92 መሰረት፣ የፓርቲዎቹ መሰረዝ የውህደት ውጤት እንጂ ቅድመ-ሁኔታ አይደለም፡፡ በሌላ አገላለጽ ከተዋሃዱ በኋላ ነው የሚሰረዙት እንደማለት ነው፡፡
እነዚህ የተዋሃዱ ፓርቲዎች በፓርላማ ያላቸው (አብላጫ) መቀመጫ በ«ዲፎልት» ወይም ያለምንም «ፕሮሲጀር» ወደ አዲሱ ፓርቲ የሚዘዋወር መሆኑን ይበልጥ የሚያስረዳልን ደግሞ ስለፓርላማ አባላት ግለሰቦች የሚያትተው የዚሁ አዋጅ አንቀስ 92 (3) ነው፡፡ እንዲህ ይላል፦
«ውህደት የፈጠሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባል የነበረና በማናቸውም ደረጃ ያሉ ምክር ቤቶች ተመራጭ ሆኖ በማገልገል ላይ የነበር ሰው በውህደቱ የተፈጠረው የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኖ መቀጠል የማይፈልግ ከሆነ የግል ተመራጭ እንደሆነ ተቆጥሮ የቀረውን የምርጫ ዘመን ያጠናቅቃል፡፡»
‘አኮንትራሪዮ ሪዲንግ’፣ ሲዋሃዱ በቀጥታ የአዲሱ ፓርቲ አባል ይሆናል፣ እንዲሁም ፓርላማ ውስጥ የተቀመጠበት መቀመጫ ያንን ፓርቲ የሚወክልበት ነው፡፡ ስለሆነም ያ አዲሱ ውህድ ፓርቲ «የተደመረ» አብላጫ መቀመጫውን ይዞ ስለሚቀጥል የመንግስትነት ክፍተት አይፈጠርም፤ ፓርላማ ያሉት የኦዲፒ ወይም የአዴፓ ወይም የሌላ ተዋሃጅ ፓርቲ አባላት በጠቅላላ ወይም በጉልህ መጠን አባልነታቸውን ካልተዉ በስተቀር፣ ያ ደግሞ በይበልጥ «አንላይክሊ» ነው፡፡ ያም ቢሆን፣ አይሆንም እንጂ፣ ቢሆን እንኳን፣ አሁን ያለው የሚኒስትሮች ምክርቤት እና ፓርላማ መሠረታዊ የሕግ እና የፖሊሲ ለውጥ ሳያደርግ ለስድስት ወር ይቀጥላል፣ እስከምርጫ፡፡
እናም ውድ አንባቢ፣ በቅድሚያ የኢሕአዴግ ፓርቲዎች አባል ወይም ደጋፊ ካልሆንክ በስተቀር ስለውህደቱ አትጨነቅ፤ የራሳቸው ጉዳይ፡፡ ግን ደግሞ በውህደቱ ሂደት የመንግሥት ኦናነት (ቫኪዩም) ይፈጠራል ብለህ ከሰጋህ፣ ከላይ እንዳነበብከው ስጋት አይግባህ፡፡ መንግስትም፣ ሀገርም ይቀጥላል፡፡
በግዛው ለገሠ
(ህዳር 6/2012፣ አዲሳባ)