“ሉዓላዊ ሥልጣን የሕዝቡ ነው፤ ማንም ሊነጥቀው አይችልም”፣ ዢን-ዣክ ሩሶ (1712-78)
ከሰዓት ሠሪ ካልቪኒስት (የጆን ካልቪን የፕሮቴስታንት ሃይማኖታዊ ሥርዓት ተከታይ) አባቱ በጄኔቫ፣ ስዊዘርላንድ ነው የተወለደው። እናቱ በወሊድ ምክንያት በመሞቷ በአባት ብቻ ነው ያደገው። መጠነኛ የሆነ የመደበኛ ትምህርት ቢያገኝም፣ አባቱ ግን ታላቅ የመፅሐፍት ፍቅር ሰጥተውታል። በ15 ዓመቱ ካደገበት ቤት ወጥቶ በብቸኝነት የእውቀት ፍለጋ ህይወቱን ጀመረ። ትንሽ ነገር የሚቆጠቁጠው ትዕግስት-የለሽ ማንነትና እውቀቱን እላይ የመስቀል ባሕሪይ ነበረው። ከሌሎች ጋር ጓደኝነት የመፍጠር አቅሙ የጎላ ቢሆንም፣ ውድጅቱ ረዥም ጊዜ አይቆይም።
ስዊዘርላንድን ከለቀቀ በኋላ በወቅቱ የአውሮፓ ታላላቅ ምሁራን ማዕከል በነበረችው በፓሪስ ከመሳቡ በፊት፣ በደቡብ ምስራቅ ፈረንሳይ በምትገኘው ሳቮይ በምትባል ከተማ የኖረ ሲሆን፣ በጣሊያንም ሰርቷል። በፓሪስ የኢንላይትመንት አቀንቃኝ ከነበሩ ፈላስፎች (በ17ኛ ክፍለ ዘመን መጨረሻና በ18ኛው ክፍለ ዘመን ከልማድ ወይም ከባሕል ይልቅ በሕሊና ወይም በማስተዋል ብቃት (reason) ላይ ትኩረት የሚያደርገውን «ኢንላይትመንት» የተሰኘ የአውሮፓ ምሁራን ንቅናቄን ከሚያቀነቅኑ ፈላስፎች)፣ በተለይ ከዲድሮት ጋር ተገናኝቷል። “ኢንሳይክሎፔዲያ” ለተሰኘው ለነዚህ ፈላስፎች ግዙፍ ፕሮጀክት፣ በተለይም በሥነ-ሙዚቃ ዙሪያ መጣጥፎችን አበርክቷል፤ ነገር ግን የተወሰኑትን የእነሱን አመለካከቶች ቢቀበልም የቡድናቸው ቁርጠኛ አባል ሆኖ አያውቅም። የራሱን እሳቤዎች ያጐለበተው ከእነሱ የአመለካከት ሥርዓት እጅግ በተለየ መልኩ ነው። እንዲያውም የሩሶ በጣም አስገራሚው መገለጫ ቀዳሚ ሐሳብ አመንጪነቱ (originality) ነው።
በፖለቲካ ፅንሰ-ሐሳብ ላይ፣ በትምህርት ሥርዓት፣ በሥነ-ጽሁፍ፣ በሥነ-ምግባር፣ በራስ ማንነት እሳቤዎችና ከተፈጥሮ ጋር ባለው ዝምድና፣ እንዲሁም በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተፅዕኖ በማሳደር የአውሮፓን አስተሳሰብ ለውጧል። እነዚህ ተፅዕኖዎቹና ውስጣዊ ስሜትን እና ፈቃድን ከህሊና ወይም ከማስተዋል ብቃት (reason) የበለጠ ቦታ መስጠቱ በአንድነት ዋናው የሮማንቲክ ንቅናቄ ጠንሳሽ ያደርጉታል። (ሮማንቲሲዝም /Romanticism/ – በ18ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ የፈለቀ የሥነ-ጥበብ እና የሥነ-ጽሁፍ ንቅናቄ ሲሆን በተመስጧዊ ስሜት፣ በግላዊ አመለካከትና በግለሰብ ቀዳሚነት ላይ ያተኩራል።)
መጀመሪያ አካባቢ ያነሳቸው የነበሩ መከራከሪያዎቹ የኢንላይትመንት ፈላስፎቹን ያስቆጡ ነበሩ፤ በተመሳሳይም እጅግ የሚታወቁለት “Emile” እና “The Social Contract” (ሁለቱም በ1762 የታተሙ) ሥራዎቹ፣ በተለይም በሃይማኖታዊ ይዘታቸው ምክንያት የወቅቱን የሥልጣን ባለቤቶች አብከነከኗቸው። እናም ሁለቱም ሥራዎቹ በፓሪስም ሆነ በጄኔቫ ከያሉበት ታስሰው እንዲለቀሙና እንዲቃጠሉ ተወሰነ፤ ተቃጠሉም። ሩሶም ተይዞ ይታሰር ዘንድ ትዕዛዝ ተላለፈበት። እርሱ ግን ከፈረንሳይ ሸሽቶ በመውጣት ለዓመታት በተለያዩ ሀገራት ጥገኝነት በመጠየቅ አሳለፈ፤ ሆኖም በ1767 ስሙን ቀይሮ ወደፈረንሳይ ተመልሷል። ባለሥልጣናቱም እርሱ መፅሐፍ ፅፎ እስካላሳተመ ድረስ የት ስለመሆኑ ማወቅ የማይቻላቸው ሆኑ። የዕድሜ ዘመኑን የመጨረሻ ዓመታት በፓሪስ አቅራቢያ በአንድ አድናቂ ወዳጁ ቤት በብቸኝነት እየኖረ ነበር ያሳለፈው። በዚያም ሥነ-እፅዋትን ያጠና ሲሆን፣ በተለይ ግለ-ታሪክ የሆኑ ሥራዎችን መፃፉን ቀጥሎበታል። “Confessions” እና “Reveries of a Solitary Walker”፣ ሁለቱም የታተሙት ሩሶ በ1778 ህይወቱ ካለፈ በኋላ ነበር።
በጉልህነት በሚጠቀሰው «A Discourse on Arts and Sciences» በ1750 በታተመ ሥራው፣ ሩሶ ለቀጣይ ሥራዎቹ ሁሉ ማዕከል ሊሆን የሚችል የታሪክ ንድፉን አስቀምጧል። በዚህ ሥራው ዘ-ልማዳዊ (traditional) አመለካከቶችንም ሆነ በኢንላይትመንት ፈላስፎች የተነሱትን ወቅታዊ እሳቤዎች አይደግፍም። ይልቁንም የሥልጣኔ ማበብ ተደርጎ የታሰበው ሁኔታ የማስተዋል ብቃት እና የሰብዓዊ ደስታ መጐልበትን ከመወከል በራቀ መልኩ፣ ሰብዓዊ ፍጡራንን በተግባር ሙሰኛ፣ ዋሾ እና ደስታ-አጥ እንዲሆኑ ያደረገ ነው በማለቱ ሁሉንም አስደመመ። ሩሶ የኢንላይትመንት አቀንቃኞች ያሞካሿቸው የነበሩትን – የማስተዋል ብቃት፣ ሳይንስ፣ ፍልስፍና፣ መሻሻል እና ምሁራዊ ምጥቀት – በአጠቃላይ እጅጉን ተችቷል። ሩሶ ለመደበኛው ሰው የሞራል እሴቶችን፣ ለታማኝነቱ፣ ለሀገር ወዳድነቱና ለማህበረሰባዊ ስሜቱ ክብር ይሰጣል፤ እንዲሁም በእውቀት ከምታብለጨልጨው አቴንስ ይልቅ ደብዛዛዋን፣ ወተደራዊነት የሰፈነባትንና ለእውቀት ቦታ የሌላትን ስፓርታን ያደንቃል። የኦርቶዶክስ አስተምህሮን የመጀመሪያ ኃጥያት (Original Sin) የሚቃረን እንደመሆኑ፣ ሰብዓዊ ፍጡራን በመሠረታዊነት መልካም እንደሆኑና እነርሱን የሚመርዛቸውም ሕብረተሰብ እንደሆነ ይከራከራል።
እነዚህ ጭብጦች በተከታዩ “A Discourse on the Origin of Inequality” (1755) በተሰኘ ወሳኝ ሥራው ላይም በድጋሚ ይነሳሉ። እዚህ ላይ በኢንላይትመንት ፈላስፎች ዘንድ የተለመደ የሆነውን መሣሪያ – መንግሥት አልባ ዓለም (state of nature) – ጥቅም ላይ ያውለዋል፤ ነገር ግን ሰብዓዊ ፍጡራንን የሚስላቸው በመሠረታዊ ደረጃ ምክንያታዊ (rational) እና ሕብረተሰባዊ እንደሆኑ አድርጎ ሳይሆን፣ የእርስ-በርስ ግንኙነታቸው ወቅት የጠበቀና የራስ-ፍቅር (self-love) እና ሐዘኔታ የሚቻላቸው በብቸኝነት የተዋጡ ነፃ ግለሰቦች አድርጎ ነው። በሕዝብ ቁጥር ግፊት ይህ ሰላማዊ የሆነ የተፈጥሮ ነፃነት ጠፋ፣ የግል ንብረት ተፈጠረ፣ እንዲሁም ብዝበዛን፣ አለመመጣጠንን እና ሁሉንም የሰብዓዊ ህብረተሰብ ቀውሶቹ አስከተለ። በማህበረሰብ ውስጥ የተፈጠረው አለመመጣጠን ወይም የእኩልነት እጦት የኢ-ፍትሃዊነት እና የሞራለ-ብልሹነት መሠረታዊ ምክንያት ሆነ። ይህ መፅሐፉ የሰው ልጆች መፃዒ ዕድል የባሰውኑ የጨለመ እንደሆነ ይጠቁማል። ይሁንና ሩሶ ሰብዓዊ ፍፁምነት፣ ሰብዓዊ መሻሻል መምጣት የሚችልበት ዕድልም ስለመኖሩ እምነት እንዳለው በግልፅ ያስቀምጣል። ይህም በሁለት ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ይሰጥ ዘንድ ያስገድደዋል፡- የመጀመሪያው በህብረተሰብ ያልተመረዘ ግለሰባዊ ህይወት መኖር የሚቻል ስለመሆኑ ሲሆን፣ ሁለተኛው ያልተበከለ ህብረተሰብ መፍጠር ይቻል እንደሆን ነው።
ሩሶ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሰጠው ምላሸ የዳበረ የህበረተሰብ እና የፖለቲካ ፍልስፍናውን የሚያንፀባርቅ ነው፤ እናም በ1762 በታተሙት ሁለት መፅሐፍቱ አስፍሯቸዋል። የመጀመሪያው “Emile” የተሰኘው ነው፤ በዚህ መፅሐፍ ሩሶ የትምህርት አሰጣጥ እሳቤዎችን አስፍሯል፤ በዚህም የሕፃናት አስተዳደግንና ሕፃናት እንዴት መጠበቅ እና መማር እንዳለባቸው በተመለከተ የአውሮፓን ግንዛቤ ለውጧል። አንድ ግለሰብ ከበራዡ የህብረተሰብ ተፅዕኖ ርቆ «ተፈጥሮን መሠረት በማድረግ» እንዴት መማር እንደሚችል የሚያመላክት አስተማሪ ልብ-ወለድ መፅሐፍ ነው። ይሁንና ግን የመፅሐፉ ዋና ገፀ-ባሕሪይ፣ ኤሚል ጉልምስና ዕድሜ ላይ የሚደርስበትና ትምህርቱ የሚጠናቀቅበት ጊዜ ይመጣል። በኋላም ከተበከለው ህብረተሰብ ጋር እራሱን ለማጣጣም ሲል ተፈጥሯዊ ማንነቱን መጨቆን ግዴታ የሚሆንበት ይመስላል፤ በዚህም እንደዚያ የተዋቀረ ትምህርት የመማሩ ፋይዳ ምን ስለመሆኑ አንባቢው እንዲያሰላስል ያደርገዋል።
ያልተበከለ ህብረተሰብ የመፍጠሪያ አማራጭ መንገድ “The Social Contract” በተሰኘው ሁለተኛ መፅሐፉ ላይ ተጠቅሷል። የመጀመሪያው ምዕራፍ በእነዚህ ታዋቂ ቃላቶች ይጀምራል፡- “Man is born free, and every where he is in chains”፤ “የሰው ልጅ ነፃ ሆኖ ነው የተወለደው፤ በየቦታው ግን በሰንሰለት እንደታሰረ ነው”። ይህ በርግጥም ሙስና፣ ብዝበዛና ጭቆና ከህብረተሰብ እና ከአለመመጣጠኖቹ ጋር መከሰታቸውን፣ እንዲሁም በተፈጥሯዊው ሰው ላይ ተፈፃሚ መሆናቸውን ተከትሎ የሚመጣ ነው። ነገር ግን ከታዋቂው አባባሉ በስተጀርባ የሩሶን የሰው ልጅ ተፈጥሮ ግንዛቤ መሠረታዊ ነጥብ በተመለከተ ጥልቅ የሆነ ፍልስፍናዊ ቁምነገር አለ። ሰብዓዊ ፍጡራንን በትክክሉ ሰብዓዊ የሚያደርጋቸው፣ ከእርሱ ቀደም የነበሩት ፈላስፎች እንዳስቀመጡት የሕሊና ወይም የማስተዋል አቅም ሳይሆን፣ ይልቁንም የሞራላዊ ምርጫ አቅም እንደሆነ ያምናል። ከዚህም በመነሳት፣ ሰብዓዊ ፍጡራን እንዲያ ያሉ ምርጫዎችን የማድረግ ነፃነት እስከሌላቸው ድረስ ሙሉ የሆነ ሰብዓዊ ህይወት ለመኖር አይቻላቸውም፤ ሰብዓዊነታቸው ተነፍጓል። በተጋነነው የሩሶ አገላለፅ መሠረት፣ ባሪያዎች ናቸው።
ይህም አሻሚ ሁኔታን ያስነሳል። ሰብዓዊ ፍጡራን በተፈጥሯቸው ነፃ ከሆኑ፣ እንዲሁም በተግባርም በመንግሥት-አልባው ዓለም (State of Nature) ነፃ ከሆኑ፣ (ከማህበራዊ ህይወት ጋር ተያይዞ በሚመጣው ጭቆናና ብዝበዛ ሳቢያ፣ ወይም በሌሎች ሰዎች አማካኝነት በሚጫኑባቸው ሕጐች መሠረት እንዲኖሩ በመሆኑ ምክንያት) ነፃነት-የለሽነትን በሚያስከትለው በህብረተሰብ ውስጥ እንዴት ነፃ ሊሆኑ ይችላሉ? ለሰዎች በህብረተሰብ ውስጥ መኖር፣ ብሎም ሙሉና ነፃ ሰብዓዊ ኑሮ መምራት እንዴት ይቻላቸዋል? ሩሶ ማህበራዊ ውልን በሚያወሳው “The Social Contract» መፅሐፉ ሊቀርፈው የሚሞክረው ችግር ይህ ነው።
ሩሶ፣ ሰዎች በመንግሥት-አልባው ዓለም ወደነበረው ነፃነት መመለሳቸው ሊሆን የማይችል ስለመሆኑ ግልፅ ነው፤ ነገር ግን ያንን ነፃነት ለዜጎች በሚሰጥ ነፃነት መመንዘር ወይም መለወጥ የሚቻል መሆኑን ያመለክታል። ይህም የሚደረገው ማህበራዊውን አካል በሚፈጥርና ሁሉም ሰዎች መብቶቻቸውን ገድበው ተገዥዎች በሚሆኑበት፣ በተመሳሳይ ሰዓትም እንደ ዘጎችና እንደ የሉዓላዊው አካል አባላት መብቶችን በሚቀበሉበት የመደራጀት ወይም ሕብረት የመፍጠር ተግባር ነው። ይህ “ማህበራዊ ውል” ነው፤ ምንም እንኳን ሉዓላዊው በሕጎች እና በመንግሥት አማካኝነት እራሱን የሚገልጥበት መንገድ ለተለየ የሕገመንግሥት ቀረፃ ሂደት የተተወ ቢሆንም። እያንዳንዱ ግለሰብ በተመሳሳይ ሰዓት ተገዥም፣ ተሳታፊ ዜጋም እስከሆነ ድረስ ነፃነት እውን ሊሆን ይችላል።
ሰዎች እራሳቸው ባወጧቸው ሕግጋቶች መሠረት ከኖሩ በነፃነት መኖር ይቻላቸዋል። ይህም የራሳቸውን ሕጎች የሚያወጡበት ሀገር ዜጎች መሆን ይገባቸዋል ማለት ነው – ዴሞክራሲ። ሆኖም ሩሶ ይህንን በጣም በጠባቡ ይተረጉመዋል። በአንተ ቦታ ሆኖ ሕግ የሚያወጣ ሰውን መምረጥ ማለት አይደለም። በሌላ አገላለፅ፣ የውክልና ዴሞክራሲ ከነጭራሹ ዴሞክራሲ አይደለም። እንደ ሩሶ ከሆነ፣ አንድ ሰው የሌላን ሰው ፈቃድ ወይም ምርጫ ሊወክል አይቻለውም። ስለዚህም አንድ ሰው በውክልና ዴሞክራሲ (Representative Democracy) ውስጥ በሌላ ሰው ሕግ መሠረት እየኖረ ሲሆን፣ አሁንም ባሪያ እንደሆነ ነው ያለው። የሩሶ የዴሞክራሲ ፅንሰ-ሐሳብ አጠቃላዩ የዜጎች ስብስብ በአንድ ላይ ሆኖ ሕጎችን የሚያወጣበት ቀጥተኛ ዴሞክራሲ (Direct Democracy) ነው። እዚህ ላይ የእርሱ ሞዴል ይህ በተግባር ይቻል የነበረበት የጥንታዊቷ ግሪክ ትናንሽ ራስ-ገዦች ናቸው። ታዲያ በእርሱ ዘመን እንደነበረችው ፈረንሳይ ዓይነት ባሉ ትላልቅ ዘመናዊ ሀገራት ይህ ተፈፃሚ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ሩሶ ግልፅ አያደርገውም። ይልቁንም ግልፅ የሆነው ነገር ትላልቆቹ ዘመናዊ ሀገራት ተቀባይነት ሊኖራቸው እንደማይችል ማመላከቱ ነው (ቀጥተኛ ዴሞክራሲን አልተገበሩምና)።
ይሁንና ግን፣ አብላጫ ድምፅ ማለት አናሳዎቹ በራሳቸው ሕጎች መሠረት መኖር አይችሉም ማለት በመሆኑ ቀጥተኛ ዴሞክራሲም ቢሆን የሩሶን ችግር የሚፈታ አይደለም። ይህ የተሳካ እንዲሆን ሁሉም ሕጎች በሙሉ ድምፅ መፅደቅ ይኖርባቸዋል። ነገር ግን የትኛውንም ዓይነት የዴሞክራሲ ፖለቲካ አስመልክቶ ከምናውቀው በመነሳት፣ ይህ ሁኔታ መቼም ሊሆን የማይችል ይመስላል። ይህንን ችግር ለመፍታት በሚል ነው፣ ሩሶ በይበልጥ የሚታወቅበትን “General Will” ወይም “ጥቅል ፈቃድ” የሰኘውን ያስተዋወቀው። መሠረታዊው ሐሳብ፣ እያንዳንዳችን የተለያዩ ነገሮችን እንፈቅዳለን ወይም እንሻለን፣ ሆኖም እያንዳንዳችን ከምንሻቸው ነገሮች መካከል ነው ለምንኖርበት ማህበረሰብ መልካሙ ወይም ጠቃሚው የሚገኘው። የዚህ ለጋራ ጥቅም ሲባል የሚደረግ መሻት ድምርን ነው ሩሶ “General will” ወይም “ጥቅል ፈቃድ” ሲል የሚጠራው። እናም አንድ ሕግ ጥቅል ፈቀድን መሠረት አድርጎ ከፀደቀና እኛም ለዚህ ሕግ ተገዢ ስንሆን በተመሳሳይም ለራሳችን ተገዢ እየሆንን ነው።
በሌላ በኩል ለጥቅሉ ፈቃድ ተገዢ በመሆናችን ለራሳችንም ተገዢ በመሆን ነፃነትን እንደምናገኝ ሁሉ፤ ለጥቅሉ ፈቀድ አለመገዛት ማለት ደግሞ የራሳችንን ነፃነት እራሳችን ነፈግን ማለት ነው። ይህም ለሕጉ አልገዛም ስለሚሉ ሰዎች «ነፃ እንዲሆኑ እየተገደዱ» ስለመሆናቸው ሩሶ የሚያቀርበውን መከራከሪያ ያብራራል። እዚህ ላይ ሩሶ በተለምዶ የፈለግነውን የማድረግ ተደርጎ የሚወሰደውን የነፃነት እሳቤ አይደለም የተጠቀመው፤ ይልቁንም እውነተኛ በሆነ መልኩ ነፃ የምንሆነው ለሞራል-የለሽ የራስ ወዳድነት ደመ-ነፍሳችን (ማለትም ለሚገነፍሉ ስሜቶቻችን ባሪያ ስንሆን) ስንገዛ ሳይሆን ለላዕላይ ማንነታችን (ማለትም ለጋራ ጥቅም ሲባል ለሚያድርብን ፍላጎት) ተገዢዎች በምንሆን ጊዜ ብቻ እንደሆነ የሚያስቀምጠውን የነፃነት እሳቤ ነው።
ዜጎች በጉባኤ ተሰብስበው በራሳቸው የራስ ወዳድነት ፍላጎቶች ላይ ተመስርተው ሳይሆን በጥቅል ፈቃዱ መሠረት ድምፃቸውን ስለመስጠታቸው እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል የሚለው ችግር እንደለ ነው። ሩሶ በማንኛውም አንድ ክስተት ላይ በጉባኤው ውስጥ ለአጠቃላዩ መልካም የሆነን ነገር አንድ ዜጋ ብቻ ሊያስብ የሚችልበትን ወይም ማንም ላያስብ የሚችልበትን እውነታ መጀመሪያ ላይ አምኖ ይቀበላል። ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ ጥቅሉ ፈቃድ የሁሉም ሰዎች ፈቃድ (the Will of All) ከሆነው ጋር ተመሳሳይ አለመሆኑን ያስቀምጣል። ይሁንና ግን ለሕዝባዊ ጥቅም የሚያስበው እና የማያስበው ማን እንደሆነ የምናውቅበትን መንገድ አይነግረንም። ይህም ጥያቄ የሚያስነሳ ይሆናል፤ ሆኖም በመፅሐፉ ወደኋላ ላይ (ክፍል 4፣ ምዕራፍ 2) የአብላጫው ሕዝብ ፈቃድ ጥቅሉ ፈቃድ እንደሆነ አድርጎ ይጠቅሰዋል፤ ይህም ከቀደመው ምልከታው (አብላጫ ድምፅ ማለት አናሳዎቹ በራሳቸው ሕጎች መሠረት መኖር አይችሉም ማለት ከመሆኑ) ጋር የማይጣጣም ይሆናል። እንዲሁም የሁሉም ሰው ፈቃድ ጥቅሉ ፈቃድ ማለት ካልሆነ፣ የአብላጫው ፈቃድም እንዲሁ ጥቅል ፈቃድ ሊሆን አይችልም።
ይሁንና ግን ሩሶ የተዋሃደ የቡድን አመለካከት በሁለት ምክንያቶች እንደሚመጣ ያምናል። በመጀመሪያ በአንፃራዊ መልኩ ውስብስብነት የሌለው፣ ሀብታም ሆነ ደሃ የሌለበት የገበሬዎች እና የዕደ-ጥበብ ባለሙያዎች ሕብረተሰብን ያስባል። ሁሉም እኩል ናቸው፤ ይህንንም ተከትሎ ግጭቶች ጥቂት ይሆኑና ለሕብረተሰቡ መልካም ነው የሚባላው ነገር አንፃራዊ ቀላልነት ይኖረዋል፤ ይህም ለማህበረሰቡ ፍቅር እንዲኖራቸው ለማስተማር ቀላል የሆነ ሁኔታ ነው። ሁለተኛ፣ ሩሶ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ግፊት ፈጣሪ ቡድኖች የማይኖሩበትና ዜጎች ያለምንም ቅድመ ዝግጅት እና ያለ ክርክር በሕጎች ላይ ድምፅ የሚሰጡበትን የፖለቲካ ሥርዓት ያስባል።
ይህ አካሄድ ያልተለመደ ወይም ወጣ ያለ ሊመስል ይችላል፣ ሆኖም ሩሶ ዴሞክራሲን በውይይት ረገድ ወይም አለመግባባቶችን እንደመፍቻ መሣሪያ አድርጎ አላሰበውም። ለእሱ ጥሩ የሚባለው ሕብረተሰብ ሰዎች የራሳቸውን ህይወት የሚመሩበትንና ተያይዞም የማይጣጣሙ ወይም የሚጋጩ ፍላጎቶች የሚኖራቸው ግለሰቦች ስብስብን አልነበረም። ሀገርን በጥንታዊቷ ግሪክ መሠረት ነው የተመለከተው፤ በሞራል እንደታነፀ ሕብረተሰብና አንድ ነጠላ ፈቃድ (ምርጫ) ይዞ እንደተቧደነ ሰው። ፓርቲዎች እና ቡድኖች ገነጣጣዮች ነበሩ። እጅጉን እንደሚያደንቀው ፕሌቶ ሁሉ፣ የአንድነት እሳቤን ይቀበላል። እንደ ጥንታዊቷ ስፓርታ እና እንደመጀመሪያው የሮም ሪፐብሊክ /እርሱ በተመለከታቸው መንገድ/ በሀገር ወዳድነት እና በሕዝባዊ የሞራል ልዕልና የሚያምንና አንድነትን የመሠረተ የዜጎች ስብስብን ይፈልጋል።
የሩሶ ያልተለመደ ዓይነት የፖለቲካ ሥርዓት ለጥቅሉ ፈቃድ መተግበር ምቹ ዕድል ይሰጥ ዘንድ የተነደፈ ነው። ሰዎች በመንግሥት-አልባው ዓለም (State of Nature) ማግስት እንዲያ ያለውን መንግሥት ያቋቁማሉ፣ ይህንን እሳቤያዊ ሥርዓተ-መንግሥት ለማሰብ ጥበቡ እና ግንዛቤው ይኖራቸዋል ተብሎ አይጠበቅም። (ሩሶ እዚህ ላይ ሰዎች ማለቱ ወንዶችን ነው፤ ለእርሱ ሴቶች መቼም ቢሆን የፖለቲካ ሚና አይኖራቸውም፤ ለሚስትነት እና ለእናትነት ብቻ ነው የሚበቁት ብሎ ያስባል።) ይልቁንም ሩሶ ሕገ-መንግሥትን የሚያቀርብ ሕግ ሰጪ (law giver) መኖር እንዳለበት ያስባል። አንዳንድ ትችቶች ይህንን ምልከታ ጥቅሉን ፈቃድ በራሱ ማንነት ስር እወክላለሁ እንደሚል አምባገነን፣ ብሎም እንደጨቋኝ ሥርዓት (totalitarian) ሲመለከቱት ቆይተዋል። ሆኖም የሩሶ ዓላማ ግን ይህ አልነበረም። በተደጋጋሚ እንደታየው፣ የእርሱ ሞዴል የሆኑት ብዙዎቹ ሕገ-መንግሥታቸው በሕግ ሰጪዎች (law givers) የሚሰጣቸው የጥንታዊቷ ግሪክ ራስ-ገዞች (city states) ናቸው፤ ለምሳሌ በስፓርታ ሕገ-መንግሥቱን የነደፈው ሊካርገስ ነበር።
ሁልጊዜም ቢሆን ሉዓላዊነት የሕዝቡ ነው (ይህን እሳቤ ሩሶ ነው ያመነጨው)፤ እናም ይህ ሥልጣን ሊነጠቅ ወይም በሌላ ሊያዝ አይችልም። ሆኖም የሉዓላዊው ተግባር ሕጎችን ማውጣት ሲሆን፣ የአስፈፃሚው ተግባር ደግሞ እነዚህን ሕጎች ማስተግበር ነው። ነገር ግን ይህ ዴሞክራሲያዊ አይደለም፤ እንዲያውም ሩሶ ግራ በሚያጋባ መልኩ ዴሞክራሲ የሚሰራው ለአማልክት እንጂ ለሰዎች እንዳልሆነ ይናገራል። እዚህ ላይ ለማለት የፈለገው፣ ዴሞክራሲያዊ (የሕግ) አፈፃፀም በተግባር የማይታሰብ ነው፤ ምክንያቱም በእርሱ የዴሞክራሲ እሳቤ መሠረት አጠቃላዩ የዜጎች ስብስብ በእኩል መልኩ መሳተፍ ይኖርበታልና። በተጓዳኝም ሕጉን የሚያወጡት እና ሕጉን የሚያስተገብሩት ተመሳሳይ ሰዎች ሊሆኑ አይገባቸውም። መንግሥት የሉዓላዊው ሕዝብ ወኪል እስከሆነ ድረስ፣ ሕጎች ጥቅሉን ፈቃድ እስካንፀባረቁ ድረስ፣ እንዲሁም መተዳደሪያ ሕግጋቶች ልክ እንደ ጥንታዊት ሮም ተመሳሳይ የዜግነት ኃላፊነትን እስከያዙ ድረስ ሕግ አስፈፃሚው ምንም ዓይነት ቅርፅ ቢኖረው ለውጥ አያመጣም ወይም ችግር የለውም። የሩሶ ምርጫ የውክልና ዴሞክራሲ ወይም በእርሱ አጠራር በምርጫ የመጣ አሪስቶክራሲ /elective aristocracy/ ቢመስልም፣ በንጉሥ የሚመራ አስፈፃሚ ቢሆንም እንኳን ተቀባይነት አለው።
ሩሶ በመንግሥት-አልባው ዓለም ወደነበረው ነፃነት በቀላሉ መመለስ እንደማይቻል ያውቃል። ነገር ግን ያ ነፃነት፣ ግለሰቦች ጥብቅ በሆነ ሕዝባዊ ምግባር ወደታነጸና አንድነት ወዳለው የሞራል ማህበረሰብ ሲጣመሩ የላቀ በሆነው የዜጎች ነፃነት መቀየር እንደሚችል ያምናል። ይህም በአንድ ሕዝባዊ ሃይማኖት መደገፍ ወይም መጠንከር እንዳለበት ሩሶ ያስቀምጣል። እንደርሱ አባባል፣ ክርስትና እውነትነት ሊኖረው ይችላል፤ ነገር ግን የጥንታዊ ግሪክ እና ሮም ሃይማኖቶችን ያህል ሕዝባዊ ሞራላዊነትን ማበረታታት ባለመቻሉ ምክንያት፣ እንደ ሕዝባዊ ሃይማኖት ማገልገል አይችልም። ከኢ-አማኞች (atheists) በስተቀር ሌላው የግሉ እምነት እንዲኖረው የሚፈቀድበት፣ በተመሳሳይ ደግሞ በውጪ ከሕዝባዊ ሃይማኖቱ ጋር መጣረስ የማይፈጠርበት የሚለው የሮማዊያን መሰል መፍትሔው እንዲያው አጥጋቢ አይደለም።
በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ሩሶ ያነሳቸው ምልከታዎች በዚያን ወቅት ከፍተኛ ውዝግቦችን ያስነሱ ሲሆን፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ጥብቅ ክርክሮች ሲደረግባቸው ቆይተዋል። ጥቅል ፈቃድ (General Will) ባለው እሳቤው ላይም አያሌ ትችቶች ተሰንዝረዋል። እንዲህ ያለ ነገር አለ ቢባል እንኳን እርምጃዎቹ ምን እንደሆኑ የምናውቅበትን እርግጠኛ መንገድ ሩሶ እንዳልሰጠን ተመልክተናል። ይሁንና ዜጎች ሊያከብሯቸው የሚያስፈልጓቸው ትክክለኛዎቹ ሕጎች ጥቅል ፈቃድን መሠረት ያደረጉት ሕጎች ብቻ ናቸው እንደማለቱ፣ ለሩሶ የፖለቲካ ሥርዓት ይህንን ጥቅል ፈቃድ ነጥሎ ማወቅ ወሳኝ ነው። በሌላ በኩል ሕግ ጥሰሃል የሚባል ማንኛውም ሰው ሕጉ ጥቅል ፈቃድን አይገልፅም፣ ስለዚህ አግባብ ያለው ሕግ አልነበረም ቢል ትክክል አለመሆኑን የማሳመኛ እርግጠኛ መንገድ አልተቀመጠም። ሆኖም እንዲህ ዓይነት ሕጎችን በማክበር ብቻ ነው ነፃነት የሚረጋገጠው።
ያለ እነዚህ ችግሮችም ቢሆን የጥቅል ፈቃድ እሳቤ ለጥያቄ ክፍት የሆነ ነው። ሁሉም ሕዝብ ንፁህ በሆነ መንገድ ለማህበረሰቡ የተሻለ የሚለውን በሚያስብበት ጊዜ እንኳን፣ ሕዝቡ ስምምነት ላይ የደረሰበት ነገር ለማህበረሰቡ የተሻለ ጥቅም የሚያስገኝ ስለመሆኑ ምንም ዋስትና የለም። ሩሶ ግን ዜጎች ያለምንም ቅድመ ዝግጅትና ያለክርክር ለጋራ ጥቅም ሲሉ ድምፃቸውን ከሰጡና በዚህም ጥቅል ፈቃድ ከተገለፀ ሁሉም ለተመሳሳይ ፖሊሲ ድምፃቸውን ይሰጣሉ ብሎ ያምናል። በዚህም ምክንያት ይህ ፖሊሲ የማህበረሰቡን ጥቅሞችና ፍላጎቶች በተሻለ መልኩ የሚያስጠብቅ ይሆናል፤ ሩሶ ጥቅል ፈቃድ ሁልጊዜም ትክክል ነው ብሏልና። ነገር ግን ይህ ሳይጐረብጥ የሚዋጥ አይደለም። ለማህበረሰቡ መልካም የሆነው ነገር ትክክለኛውን ሂደት በመከተል ሊታወቅ የሚችል ፍፁም እና አሻሚነት የሌለው ነገር አይደለም። የተሻለው ምንድነው በሚለው ላይ ተቀባይነት ያለው አለመስማማት ሊኖር ይችላል፤ ይህ ግን ሩሶ በር ሊከፍትለት የማይፈቅደው አጋጣሚ ነው።
ከእነዚህ አመክኒዮአዊ ችግሮች ባሻገር፣ የሩሶ እሳቤዎች ለዘመናዊው ፖለቲካ ከሚያሳድሩት አስተዋጽኦዎች ጋር በተያያዘ ጠንከር ያሉ የተግባር ችግሮችም አሉ። እነዚህ እሳቤዎች በእርሱ ዘመን ላሉት እንደ ፈረንሳይ ዓይነት ዘመናዊ ሀገራት እንዴት ተፈፃሚ ሊሆኑ ይችላሉ? እንዲሁ ሳይገልፅልን ያልፈዋል። በርግጥ ተቀባይነት ያለው ቀጥተኛ ዴሞክራሲ (መላው ሕዝብ በአንድነት በሕግ ማውጣቱ ላይ የሚሳተፍበት) ብቻ ስለሆነ በዘመናዊው ዓለም ተቀባይነት ያለው መንግሥት የማይታሰብ ነው።
ይህ ጉዳይ ጨቋኝ ሥርዓትን /totalitarianism/ በተመለከተ ከሌላ ዋና ትችት ጋርም በቅርበት የተያያዘ ነው። ሩሶ የመጀመሪያው ዘመናዊ የዴሞክራሲ ፈላስፋ የመሆኑ ዝና ቢኖርም፣ በእውነታው ግን የዘመናዊ ጨቋኝ ሥርዓት አባት ነበር በማለት ጄ. ኤል. ታልሞን “The Origins of Totalitarian Democracy” (1952) በተሰኘ መፅሐፉ መከራከሪያውን ያስቀምጣል። ይህን ያለበት ምክንያትም፣ አንድ ግለሰብም ሆነ ፓርቲ ሁሉም ሊገዛበት የሚገባውን ጥቅል ፈቃድ እንወክላለን እንዲሉና የራሳቸውን የበላይ ማንነት ሌሎች እንዲያከብሩ የሚደረግበት ዕድል ሁልጊዜ በመኖሩ ነው። በርግጥም ሩሶን መነሻ ያደረጉት የፈረንሳይ አብዮተኞች (ሩሶ ለአብዮት አቀንቅኖ ባያውቅም) እንዲህ ያለውን አቋም ተከትለዋል። ሮቤስፒር የፈረንሳይን ፈቃድ እንደሚወክል ይናገር ነበር፤ እናም ከዚያ ፈቃድ ጋር የማይስማሙትን ሁሉ ሊወገዱ የሚገባቸው «የሕዝብ ጠላቶች» ናቸው ሲል አውጇል። ሆኖም ሩሶ ዘመናዊ ጨቋኝ ሥርዓትን አስቦ እንዳልነበር ግልፅ ነው።
ከጨቋኝ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ትቶት ያለፈው ትሩፋት ለጥያቄዎች በር የሚከፍት ሆኖ ቢገኝም፣ ሩሶ ለዴሞክራሲ እሳቤ መጎልበት በዋናነት የሚጠቀስ ነው። ከፕሌቶ አንስቶ ከእርሱ ቀደም የነበሩ ጉልህ ፈላስፎች ዴሞክራሲን በጥርጣሬ ዓይን ነበር የሚመለከቱት፤ ብዙውን ጊዜ ከግፊተ-ሕዝብ (mob) አገዛዝ ጋር ሲመዛዘን የነበረ ሲሆን፣ ግፋ ቢል በሰፊ ሥርዓት ውስጥ የተወሰነ መጠን የፖለቲካ ተሳትፎን እንደሚፈጥር አንድ አላባ ወይም እንደ ንጥረ-ነገር ብቻ ሊወሰድ የሚችል ነበር።
የሕዝቦች ሉዓላዊነት እሳቤን ያጎለበተው ሩሶ ነው፤ እንዲሁም የመደበኛ ሕዝቦችን በፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ እንደ ሙሉ ዜጎች የመሳተፍ ብቃት እና መብት በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ ትኩረት ሰጥቶ የጐተጐተው እርሱ ነው። እነዚህ በእርሱ ዘመን አንገብጋቢ የነበሩ ጉዳዮች ናቸው፤ ሆኖም በዘመናዊው የፖለቲካ እሳቤና ትግበራ ውስጥ ቀስ-በቀስ ዘልቀው ሊገቡ ችለዋል። እጅግ በጥቅሉ ስንመለከተው፣ እኛን የሕሊና ወይም የማስተዋል (reason) ብቻ ሳይሆን የስሜት ፍጥረታት አድርጎ በመውሰድ፣ ሩሶ እንደሰብዓዊ ፍጡራን እራሳችንን የምናስብበትን መንገድ በከፍተኛ ሁኔታ ለውጧል። የእርሱ እሳቤ ውስብስብ፣ ጠንካራ እና ቀዳሚ (Original) ነው፤ እናም እርሱ ከዘመናዊው ዓለም እጅግ ተፅዕኖ አድራጊ ፈላስፎች መካከል ነው።
ለበለጠ ንባብ
ቀዳሚ ምንጮች፡
The Discourses and Other Early Political Writings, ed. V. Gourevitch (Cambridge: Cambridge University Press, 1997).
The Social Contract and Other Later Political Writings, ed. V. Gourevitch (Cambridge: Cambridge University Press, 1997).
ተቀፅላ ምንጮች፡
Cooper, L.D.: Rousseau, Nature, and the Problem of the Good Life (University Park, PA: Pennsylvania State University Press, 1999).
Hall, J.C.: Rousseau: An Introduction to his Political Philosophy (Basingstoke: Macmillan, 1972).
Hendel, W.: Jean-Jacques Rousseau: Moralist (New York: Library of the Liberal Arts, 1962).
Talmon, J.L.: The Origins of Totalitarian Democracy (London: Sphere Books, 1970).
Wokler, R.: Rousseau (Oxford: Oxford University Press, 2001).