Ankuar

Politics, culture and society in Ethiopia

COVID-19FEATUREDNews

ኮቭድ-19 በኢትዮጵያ፤ የ30 ቀናት ቁጥሮች እና ገላፃዊ ትንታኔዎች

በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ወረርሽን ኮሮናቫይረስ (ሳርስ-ኮቭ-2) የተያዘ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው መጋቢት 4 ቀን 2012 ነበር። በ30 ቀናት ውስጥ እስካሁን ቫይረሱ እንዳለባቸው በላብራቶሪ ምርመራ የተረጋገጠባቸው 69 ሰዎች ሲሆኑ፣ ከነዚህ ውስጥ 10 ሰዎች ሙሉ ለሙሉ ማገገማቸው ተገልጿል። ሆኖም 3 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉም ተነግሯል።

ሁለት ሰዎች ወደ ሀገራቸው ጃፓን በመሄዳቸው፣ በአሁን ሰዓት በለይቶ ማቆያ የሚገኙ ህሙማን ቁጥር 54 ነው። ይሁንና ወደ ሀገራቸው የተሸኙት ሁለት ህሙማን የሚገኙበት ሁኔታ እስካሁን በይፋ ባለመገለፁ፣ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 56 ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት የመጀመሪያው በቫይረሱ የተጠቃ ሰው ከታወቀ ከአስር ቀናት በኋላ፣ ከመጋቢት 14 ጀምሮ ከውጭ ሀገር ለሚገቡ ማንኛውም ተጓዦች አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ መተግበር መጀመሩ ይታወቃል።

እስከዛሬው ቀን ድረስ፣ ኢትዮጵያ 3577 የላብራቶሪ ምርመራ አድርጋለች። መያዙ የተረጋገጠው ሰው ከተደረገው ምርመራ ጋር ሲነፃፀር 2% ብቻ ነው። ሆኖም ኢትዮጵያ በቂ ምርመራ እያደረጉ ካልሆኑት ሀገራት መመደቧ ይታወቃል። በአሁን ሰዓት በተለያዩ ክልሎች እና ከተሞች የመመርመሪያ ጣቢያዎች ተቋቁመው፣ በቀን የመመርመር አቅሟም ከፍ ማለቱ ታይቷል። ዛሬ የተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ 345 መሆኑ ተገልጿል።

ጊዜው አጭር ቢሆንም፣ እስካሁን የተመዘገቡትን ቁጥሮች መሠረት በማድረግ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ፆታ፣ የጉዞ ታሪክ፣ ዜግነት፣ እና ሌሎች መስፈርቶችን መሠረት በማድረግ የሚከተሉትን ገለፃዊ ትንታኔዎች አቅርበናል።

የተያዙ ሰዎች ፆታ

በቫይረሱ ከተያዙ 69 ሰዎች ውስጥ 47 (68%) ወንድ እና 22 (32%) ሴት ናቸው።

ዜግነት

ኢትዮጵያዊያን 58 (84%)፣ የውጭ ሀገር ዜጎች ደግሞ 11 (16%) ናቸው። 4 ጃፓናዊ፣ 2 ኤርትራዊ፣ 1 ካናዳዊ፣ 1 እንግሊዛዊ፣ 1 ኦስትሪያዊ፣ 1 ሕንዳዊ፣ እና 1 ሞሪሺየሳዊ ይገኙበታል።

የጉዞ ታሪክ

ከጠቅላላው በቫይረሱ ከተያዙ 69 ሰዎች፣ 49 (71%) የሚሆኑት የጉዞ ታሪክ ያላቸው፣ ማለትም ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ በቅርብ ቀን ውስጥ የገቡ ናቸው (Repatriated Cases)። የተቀሩት 20 (29%) ሰዎች ምንም ዓይነት የጉዞ ታሪክ የሌላቸውና እዚሁ ሀገር ውስጥ የተያዙ ናቸው (Local Cases)። የተወሰኑት በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክክኪ ወይም ግንኙነት እንደነበራቸው ቢገለፅም፣ ንክኪም ሆነ ግንኙነታቸው ያልታወቀ ሰዎችም ይገኙበታል።

የተያዙት ሰዎች የተጓዙባቸው ሀገራት

የጉዞ ታሪክ ካላቸው 49 ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ የመጡት ከዱባይ ነው፤ እነዚህም 27 (55%) ናቸው። የ49 ሰዎቹ የጉዞ ታሪክ በትንሹ 14 መነሻ ሀገራትን የሚያሳይ ሲሆን፣ 3 ሰዎች ከእንግሊዝ፣ 3 ሰዎች አሜሪካ፣ እንዲሁም 3 ሰዎች ከኮንጎ ብራዛቢል መምጣታቸው ተነግሯል። ሙሉን የመነሻ ሀገራት ዝርዝር እና ድርሻ ከምስሉ ይመልከቱ።

ከአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ በኋላ

የኢትዮጵያ መንግሥት ከመጋቢት 14 ቀን 2012 ጀምሮ ማንኛውም ተጓዥ ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ እንዲሆን አስገዳጅ እርምጃ ከወሰድ በኋላ፣ 42 ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። ነገር ግን ከነዚህ ውስጥ 11 ስዎች የአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ እርምጃው ከመወሰዱ አስቀድሞ ወደ ኢትዮጵያ የገቡና በቅድመ ምርመራ ምልክቱ ያልታየባቸው ነበሩ።

ሆኖም የአስገዳጅ ለይቶ ማቆያው እርምጃው ከተወሰደ በኋላና በዚህ አማካኝነትም በለይቶ ማቆያ ከነበሩ ሰዎች መካከል፣ ከውጭ ሀገር የመጡና በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 31 ነው። ይህም የእርምጃዎን ውጤታማነት በጉልህ ሊያሳይ የሚችል ነው።

በሌላ በኩል፣ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያው ከተወሰነ ጀምሮ፣ ያለምንም የጉዞ ታሪክ (Local Cases) በሀገር ውስጥ በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከላይ በተመለከትነው ግራፍ መሠረት እየቀነሰ ቢመጣም፣ ከመጋቢት 14 ቀን 2012 በኋላ 16 ሰዎች በሀገር ውስጥ በቫይረሱ ተይዘዋል።

የ30 ቀናት ሁኔታ

የተያዙ፣ ያገገሙ፣ የሞቱ ሰዎች ምዛኔ የሌሎች ሀገራትን የስርጭት ሁኔታ በመመልከት በኢትዮጵያ የሚገኘው ሁኔታ ላይ እና በመጪዎቹ ቀናት ሊሆን ስለሚችለው መደምደምም ሆነ መገመት አዳጋች ቢሆንም፣ ከ69 ሰዎች መካከል 10 (14%) ማገገማቸው ተረጋግጧል። እንዲሁም 56 (81%) ሰዎች በቀላል ህመም (Mild Case) ላይ ሲሆኑ፣ በዛሬው እለት በጽኑ ህመም ላይ የሚገኝ ሰው የለም። 3 (4%) ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ተነግሯል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.