Ankuar

Politics, culture and society in Ethiopia

COVID-19FEATURED

የሰሞኑ የኮቪድ-19 ቁጥሮች ምን ትርጉም አላቸው?

(ግንቦት 3 ቀን 2012 – Ankuardotcom)

ጤና ሚኒስቴር እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ በየቀኑ ከሚያወጡት የምርመራ ውጤቶች መግለጫ በዘለለ፣ ቁጥሮቹ ምን ማለት እንደሆኑ ለሕብረተሰቡ ቢያብራሩ መልካም ነበር።

ባላፈው ሳምንት ሐሙስ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር ተመዝግቧል። ይኸውም 29 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡ ሲሆን፣ አስደንጋጩ እውነታ 19 ሰዎች የጉዞ ታሪክ የሌላቸውና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያለነበራቸው መሆኑ ነበር። እነዚህ 19 ሰዎች ሁሉም ማለት ይቻላል ከአዲስ አበባ ናቸው።

ይህን ተከትሎ የሕበረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከእነዚህ ሰዎች ጋር ንክኪ ሊኖራቸው ይችላሉ የተባሉ ሰዎችን በሙሉ ወደ ለይቶ ማቆያ ለማስገባት ፈጣን እርምጃ ወስዷል። በለይቶ ማቆያ የገቡት ሰዎች የምርመራ ውጤት ደርሶ ይፋ ሊደረግ የሚችለው ከአንድ ቀን በኋላ መሆኑ ይታወቃል፤ ስለሆነም በነጋታው ዓርብ ዕለት የተነገርው የሦስት ሰዎች በቫይረሱ መያዝ እነሱን ሊጨምር አይችልም።

ቅዳሜ 16 ሰዎች መያዛቸው ተነገረ። ሁለቱ በአማራ እና በደቡብ ክልል በለይቶ ማቆያ የነበሩ የጉዞ ታሪክ ያላቸው ናቸው። አንድ ሰው ከደቡብ ክልል ያለጉዞ ታሪክ እና ንክኪ የተያዘ ነው፤ እንዲህ ዓይነቱ ውጤት ወረርሽኙን እየታገሉ ለሚገኙት የሀገራችን ተቋማት ራስ-ምታት ነው። በሌላ በኩል 13 ሰዎች ከአዲስ አበባ በሽታው ካለበት ሰው ጋር ንክኪ እንደነበራቸው ተገልጿል፤ ከላይ በለይቶ ማቆያ ተደረጉ ያልናቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች ይመለከታል። ይህም በተወሰነ መልኩ ወረርሽኙን “ኮንቴይን” ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ውጤት የሚያሳይ ነው።

» ትላንት እና ዛሬ

የሁለቱን ቀናት ቁጥር ተመሳሳይ የሚያደርገው፣ በሁለቱም የጉዞ ታሪክም ሆነ ንክኪ የሌለው ሰው አልተገኘም። ትላንት ከ2171 ምርመራ ውስጥ 29 ሰው በቫይረሱ መያዙ ሲታወቅ፣ 8 የጉዞ ታሪክ ያላቸው ናቸው፤ የተቀሩት 21 ሰዎች ንክኪያቸው ይታወቃል።

ዛሬ ይፋ የተደረገው የ1764 ምርመራ ውጤት 11 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ሲያሳይ፣ 5 የጉዞ ታሪክ አላቸው፣ የተቀሩት 6 ንክኪያቸው ይታወቃል።

የዚህ ቀጥተኛ ትርጉም፣ ከላይ እንደተባለው፣ ወረርሽኙን በቁጥጥር ስር ለማዋል አንድ ሰው መያዙ ሲታወቅ በአካባቢው የሚገኙ ንክኪ ሊኖራቸው የሚችል ሰዎችን በአፋጣኝ የመለየት እና የመመርመር ሥራ መከናወኑን ነው።

በሌላ በኩል በትላንት ውጤት 21 ሰዎች ከአዲስ አበባ ሲሆኑ፣ (ምናልባት ከአንዱ በስተቀር የተቀሩት) የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ግን የታወቀ ንክኪ ያላቸው ናቸው። በተጨማሪም ዛሬ ይፋ በተደረገው ውጤት፣ የጉዞ ታሪክ ባይኖራቸውም የታወቀ ንክኪ እንዳላቸው ከተገለፁት 6 ሰዎች አምስቱ ከአዲስ አበባ ናቸው። ምን ያህሉ እንደሆን ባይገለፅም፣ አሁንም ከሐሙስ ዕለት የምርመራ ውጤት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ይገመታል።

ሆኖም ሁለት ነገሮች ጥያቄ ያጭራሉ። በትላንትናው ውጤት፣ አንድ ሰው ከኦሮሚያ ክልል አዳማ ላይ «በቤት ለቤት አሰሳ እና ቅኝት» ተለይቶ ምርመራ ከተደረገለት በኋላ የተረጋገጠበት ነው። መግለጫው ግልፅ ባይሆንም፣ ንክኪያቸው ያልታወቀ ኬዞች በዕለቱ ባለመመዝገባቸው፣ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግለሰቡ ንክኪው የሚታወቅ ወይም የጉዞ ታሪክ ያለው መሆኑን ነው። ይህ ሰው ንክኪው ከታወቀ፣ እንዴት በወቅቱ ተገኝቶ ሊለይ አልቻለም? በሌላ በኩል ይህ ሰው የጉዞ ታሪክ ካለው፣ መቼ ወደ ኢትዮጵያ የገባ ነው? እንዲሁም እንዴት ወደ ሕብረተሰቡ ሊቀላቀል ቻለ?

በዛሬው ውጤት ላይም ተጨማሪ ጥያቄ የሚያጭር ነገር አለ። የጉዞ ታሪክ አላቸው የተባሉት 5 ሰዎች አፋር እና ትግራይ ለይቶ ማቆያ እንደሚገኙ ተገልጿል። ነገር ግን በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ አላቸው ከተባሉት 6 ሰዎች ውስጥ አንድ ግለሰብ ኦሮሚያ ክልል አዳማ “ለይቶ መከታተያ” እንደሚገኝ ተገልጿል። “ለይቶ መከታተያ” የሚለው ሀረግ በመግለጫው የእንግሊዝኛ አቻ ላይ “Isolation” የሚለውን የሚወክል ሲሆን፣ ይህም በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ተለይተው ሕክምና የሚከታተሉበት ቦታ ነው። በለይቶ መከታተያ ተገኝቶ በቫይረሱ ሊያዝ የቻለበት ሁኔታ ተጋላጭነትን በአግባቡ ካለመቀነሰ የመጣ ከሆነ ለወደፊቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያሻ ያመላክታል።

ጤና ሚኒስቴር ከላይ የተነሱትን ብዥታዎች የሚያብራሩ በቂ ምላሾችን እንደሚሰጥ ተስፋ እናደርጋለን።

» የተያያዘው ምስል እስከዛሬ በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሁኔታን የሚያሳይ ነው። በዚህም፦

– አጠቃላይ የተያዙ፡ 250
– ያገገሙ፡ 105
– ህይወታቸው ያለፈ፡ 5
– ተይዘው የሚገኙ፡ 140 (ሁለቱ በሀገር የሉም)
– ጽኑ ህሙማን፡ 0
– ወንዶች፡ 187 ፤ ሴቶች፡ 63
– ኢትዮጵያዊያን፡ 225 ፤ የውጭ ዜጎች፡ 25
– ከውጭ የመጡ ኬዞች፡ 129
– አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ከኅብረተሰቡ እንዳይቀላቀሉ ያደረጋቸው፡ 104
– ሀገር ውስጥ የተያዙ፡ 121
– ሀገር ውስጥ ሲያዙ ንክኪያቸው የታወቀ፡ 77
– ሀገር ውስጥ ሲያዙ ከማን እንደተላለፈባቸው በወቅቱ ያልታወቀ፡ 44

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.