በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 23 ደርሷል
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ ጠዋት ባስተላለፉት መልዕክት፣ በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ኮሮናቫይረስ የተያዙት ሰዎች ቁጥር 23 መድረሱን አስታውቀዋል። በመልዕክታቸውም ይህንን ወረርሽን ለመከላከል እና ሊያስከትለው የሚችለውንም ጉዳት ለመቋቋም የሁሉን ርብርብ እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።
ይህን ተከትሎ የጤና ሚስኒቴር ባሰራጨው መረጃ፣ “ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ ባደረገው ተጨማሪ ስልሳ ስድስት (66) የላብራቶሪ ምርመራ ሁለት (2) በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች በማረጋገጡ በአጠቃላይ በሀገራችን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሃያ ሶስት (23) ደርሷል፡፡” ብሏል።
እስከዛሬ በነበሩ መረጃዎች ከኦሮሚያ ክልል አዳም ላይ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች በምርመራ የተረጋገጠ ሲሆን፣ በዛሬው መረጃ ደግሞ ሁለት አዲስ ኬዞች በአማራ ክልል ባህር ዳር እና አዲስ አዲስ ቅዳም ላይ መረጋገጡ ተጠቁሟል።
ዛሬ በጤና ሚኒስቴር የተሰራጨው መረጃ ይህን ይመስላል፦
>> በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡት ግለሰቦች በአማራ ክልል ባህር ዳር ነዋሪ የሆኑ የ37 ዓመት ሴትና በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የአዲስ ቅዳም ነዋሪ የሆኑ የ32 ዓመት ወንድ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። የአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ከመጀመሩ ዕለት አስቀድሞ አንደኛዋ ታማሚ መጋቢት 10 ከዱባይ እንዲሁም ሁለተኛው ታማሚ መጋቢት 12 ከአሜሪካ የገቡ ናቸው። ሁለቱም ታማሚዎች የበሽታው ምልክት በማሳየታቸው በላብራቶሪ ምርመራ በቫይረሱ መያዘቸው ተረጋግጧል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከታማሚዎቹ ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው ሰዎች የመለየትና ክትትል ሂደት እየተከናወነ ይገኛል። ሁለቱም ታማሚዎች በአማራ ክልል የለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል።
በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን በለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ያሉ አስራ ዘጠኝ (19) ታማሚዎች ሲኖሩ አንድ ታማሚ በጽኑ ህሙማን ህክምና ክፍል ክትትል እየተደረገላት ይገኛል። ከዚህ በፊት እንደተገለጸው ሁለት ታማሚዎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል ሲሆን ሁለት ታማሚዎች ሙሉ በሙሉ አገግመዋል። ነገር ግን ለጥንቃቄ ሲባል በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል።
ህብረተሰቡ የበሽታውን ስርጭት ግምት ውስጥ በማስገባት የመከላከያ መንገዶችን እና ከመንግስት የሚተላለፉ እርምጃዎችን ትኩረት በመስጠት እንዲተገበር እናሳስባለን።
ለተጨማሪ መረጃ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796 ወይም በኢሜል አድራሻችን [email protected] በመጠቀም ማግኘት ይቻላል። <<
#ኮቪድ19 #ኢትዮጵያ