እጅ ከመታጠብ ባሻገር. . . (ሀገራችን ደሃ ነች፤ የታመመውን ሁሉ ተቀብሎ የሚያስታምም መንግሥትም ሆነ የጤና ባለሙያ የላትም)
አዲሳባ ላይ እየተተገበሩ እና እየተመከሩ ይሉት ኮሮናቫይረስን (ኮቪድ-19) የመከላከያ መንገዱች ትክክለኛ ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ ግን ለመከላከል ነው፡፡ አንተ ወይም ከቤተሰብህ አንዱ በበሽታው ቢያዝ ምንድነው የምታደርገው?
መንግሥት ቁጥሩን ደብቋል፣ አልነገረንም ምናምን የሚለው ጉዳይ ጉንጭ አልፋ ነው፡፡ (ቢነግርህ ምን ልታመጣ ነው? ያኔ ገና መጠንቀቅ ልትጀምር ነው?)
ቁምነገሩ ግን፣ ዛሬ መንግሥት የገለጣቸው ኬዞች የቫይረሱን በክፍለ ሀገር ከተሞችም መዛመቱን፣ እንዲሁም ዋናው ጉዳይ ደግሞ በሀገር ውስጥ በእርስበርስ ንክኪ መዛመት (ደረጃ ሁለት) መጀመሩን ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ በጥቂት ቀናት ብዙ ቁጥር ሲነገርህ ደግሞ፣ መንግሥት ለምን ነገረን እንደማትል አምናለሁ፡፡ (መንግሥት የሚጠበቅበትን ሰርቷል ወይም አልሰራም የሚለውንም ብናወራው ከአሁን በኋላ ጥቅም አይኖረውም፡፡)
ስለዚህ በሚቀጥሉት ቀናት ወይም ሳምንታት የሚሆነውን እንገምትና ምን ማድረግ እንደሚጠበቅብን እናውራ፦
– አዲሳባን ጨምሮ ቢያንስ በአምስት ከተሞች በቫይረሱ የሚያዘው ሰው ቁጥር ሽቅብ ይጨምራል፤
– ሚሊኒየም አዳራሽ፣ የኮተቤው ሆስፒታል፣ በችሮታ የተዋስናቸው የግል ቤቶ፣ እንዲሁም በሌሎች ከተሞች የተዘጋጁት ለይቶ ማቆያዎች ቶሎ መሙላታቸው አይቀርም፤
– የመሙላታቸው ስጋት ስለሚኖር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ይበልጥ የሕክምና እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ይሆናል፤
– አብዛኛው ሰው እንደኃይለኛ ጉንፋን ትንሽ ቀናት አድክሞት ስለሚያገግም፣ ቤትህ ሆነህ እራስህን ተንከባከብ መባሉ አይቀርም፤
– ትልቁ ችግራችን፣ ድህነታችን እንደሀገር ስለሆነ፣ ትርፍ መኝታቤት ይቅርና፣ በአንድ ቤተሰብ 5-6-7 እና ከዚያ በላይ ሆነን ነው የምንኖረው፤
– 1ኛ) ስለዚህ የቤት ውስጥ አይዞሌሽን ግድ በሚሆን ሰዓት አንተ እና ቤተሰብህ ምን እንደምታደርጉ ከአሁኑ አስብበት፤ አንድ መኝታቤት ለቅቆ ማዘጋጀት ይሻላል ወይስ ሳሎኑን፣ እያልክ ተማከርበት፡፡
– ህመሞቹ የጉንፋን አይነት ቢመስሉም ቀላል አይደሉም፤ ከፍተኛ እንክብካቤ ይፈልጋሉ፤
– 2ኛ) ስለዚህ ከቤተሰብ አንዱ ቢያዝ ማስታገሻ መድሃኒት፣ በተለይም ፓራሲታሞል እንደሚያግዝ ሲነገር ነበር፤ በተጨማሪም ፈሳሽ እና ትኩስ ነገሮች፣ ቫይታሚኖች እና የመሳሰሉት እንደሚያስፈልጉህ አትዘንጋ፤ እንዲሁም ህመሙ እህል አያስበላምና አቅም የምናጎለብትበትን አጥሚትም ሆነ ሌላ ዘዴ ካሁኑ ተዘጋጅበት፤
– የቫይረሱ ስርጭት አስደንጋጭ መሆኑን ታዝበሃል፣ ፈረንጅ ሀገር ዶክተሮች እና ባላሥልጣናት፣ ሀብታሞች እና ታዋቂ ሰዎች፣ እንዲሁም ንጉሳዊ ቤተሰቦች እየተያዙ ነው፤
– ግንዛቤም ገንዘብም ያላቸው ናቸው፤ ጽዳትም ሆነ ከቤት የማያስወጣ የዓመታት ቀለብ ያላቸው ሰዎች ናቸው፤
– የእኔን እና የአንተን ሁኔታ እዚህ አደባባይ ላይ ማውጣት አያስፈልግም፤ ነገር ግን ከላይ ያልናቸውን ለማካካስ እጥፍ ድርብ ጥንቃቄ እና ዝግጅት ያስፈልገናል፤
– 3ኛ) ስለዚህ በቤትህ ውስጥ አንተ ወይም ከቤተሰብህ አንዱ ኳራንቲን መደረግ እንዳለባቸው ስታውቅ ማንኛውንም ንክኪ ማስወገድ እንዳለብህ፣ እንዲሁም እንዴት የሚለውን አስብበት፤ ለምሳሌ የታመመውን ሰው የቤት ውስጥ እንቅስቃሴ መገደብ፣ መፀዳጃ ቤት ያው የጋራ ስለሆነ ያ ሰው ገብቶ ከመቀመጥ በቀር ምንም እቃ እንዳይነካ ማድረግ፣ ድንገት የበር እጀታም ሆነ ሌላ ነገር ቢነካ ጓንት እንዳይለየው ከወዲሁ ማዘጋጀት፣ ንክኪ ሊኖራቸው የሚችሉ ማንኛውንም ቁሳቁሶች በአልኮል ወይም በተመሳሳይ ዘዴ ወዲያው ወዲያው ማፅዳት፣ የመተንፈሻ ጭንብል (ማስክ) እንዲጠቀም ማድረግ፤
ወዳጄ፣ ይህ አይመጣም ብለህ አትዘናጋ፡፡ ሀገራችን ደሃ ነች፤ የታመመውን ሁሉ ተቀብሎ የሚያስታምም መንግሥትም ሆነ የጤና ባለሙያ የላትም፡፡ እናም ከወዲሁ በቤት ውስጥ ስለሚደረግ አይዞሌሽን እና እንክብካቤ አስብበት፡፡ ይህ የወዳጅ ምክር ነው! ላንተ ስመክር የእኔም እየታሰበኝ ነው፤ መንታ ልጆቼን ጨምሮ አምስት የቤተሰብ አባላት ነን፤ ምን አድርጌ ምን እንደማደርግ እያውጠነጠንኩኝ ነው ይህን መፃፌ፡፡ እናም ለወዳጄ ማጋራቴ፡፡ ያጎደልኩት ካለ አንተም ጨምርልኝና አብረን እንበርታ!
በግዛው ለገሠ
Picture source: www.standardmedia.co.ke